በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በሥራ ብዛት ተወጥረሃል?

በሥራ ብዛት ተወጥረሃል?

በሥራ ብዛት ተወጥረሃል?

በሁሉም የዓለም ክፍሎች በሥራና በቤተሰብ ሕይወት መካከል የሚፈጠረው ግጭት አሳሳቢ ጉዳይ ሆኗል። አንድ ምንጭ እንደጠቆመው ‘ግሎባላይዜሽንና አዳዲስ ቴክኖሎጂ እንዲሁም ከሰኞ እስከ ሰኞ የ24 ሰዓት ልፋት የሚጠይቀው የኢኮኖሚ ሥርዓት ያስከተለው ከፍተኛ ውጥረት ለዘመናት የቆየውን በቤተሰብ ሕይወትና በሥራ መካከል ያለውን ድንበር በእጅጉ አጥብበውታል።’ እነዚህ ለውጦች ከአሁን በፊት ታይቶ የማይታወቅ ብልጽግና አስገኝተዋል። ይሁን እንጂ ይህ ስኬት የተገኘው ከፍተኛ ዋጋ ተከፍሎበት ነው። አንድ ደራሲ እንዲህ ብለዋል፦ “በሚሊዮን የምንቆጠር ሰዎች አለመጠን እንሠራለን፣ ፕሮግራማችን ከሚገባው በላይ ተጣብቧል፣ ሥራችን ከአቅማችን በላይ ሆኖብናል። በአጭሩ በሥራ ብዛት ተወጥረናል።”

በዚህ ላይ ደግሞ በቅርቡ የተከሰተው የኢኮኖሚ ድቀት ያስከተለውን ቅስም የሚሰብር ሁኔታ እናስብ። በመላው ዓለም ያሉ የቢሮም ሆኑ የጉልበት ሠራተኞች ከሥራቸውና ከመኖሪያ ቤታቸው ተፈናቅለዋል። እነዚህ ሰዎች ‘ምነው ሥራው በተገኘና በደከምኩ’ ብለው ይመኙ ይሆናል።

እስቲ የችግሩን ስፋት እንመልከት፦

በአውሮፓ ከሚገኙ ሠራተኞች መካከል ከአሥሩ ስድስቱ ሥራቸው ከፍተኛ ውጥረት ያስከትልባቸዋል።

በዩናይትድ ስቴትስ ከሚኖሩ ሠራተኞች መካከል ከሦስቱ አንዱ ከሚገባው በላይ ሥራ እንደሚበዛበት ይሰማዋል።

ከ66 በመቶ በላይ የሚሆኑት ካናዳውያን፣ የቤተሰብ ሕይወታቸውንና ሥራቸውን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ መምራት ይቸግራቸዋል።

በመላው ዓለም ከ600 ሚሊዮን የሚበልጡ ሠራተኞች ወይም በዓለም ላይ ካሉት ሠራተኞች መካከል 22 በመቶ የሚሆኑት በሳምንት ከ48 ሰዓት በላይ ይሠራሉ።

እነዚህ አኃዛዊ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የሰው ልጅ አሳዛኝ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ይገኛል። ረጅምና መደበኛ ያልሆነ የሥራ ሰዓት ያላቸው ሰዎች የጤና መታወክ ሊያጋጥማቸው፣ ከሌሎች ጋር ያላቸው ግንኙነት ሊሻክር፣ ልጆችን ጥሩ አድርጎ ማሳደግ ሊያስቸግራቸው እንዲሁም መለያየትና ፍቺ ሊያጋጥማቸው እንደሚችል አንዳንድ ጥናቶች ያመለክታሉ።

አንተስ? ከአቅምህ በላይ እየሠራህ ነው? ወይስ በአሁኑ ጊዜ ሥራ አጥ ከሆኑት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መካከል አንዱ ነህ? ሥራህንና የቤተሰብ ሕይወትህን ይበልጥ ሚዛናዊ በሆነ መንገድ መምራት የምትችልበትን ጊዜ ትናፍቃለህ? ታዲያ እንዲህ ያለውን ሁኔታ ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው?

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

“የምሽት ፈረቃ”

“ቤት እንደገባሁ ራት መሥራት፣ ቤቱን ማጽዳት፣ ልብስ ማጠብ፣ ልጆቹን ከዋሉበት ማምጣት፣ የቤት ሥራቸውን ማሠራት እንዲሁም እነሱን አጣጥቤ ማስተኛት አለብኝ” በማለት አንዲት ተቀጥራ የምትሠራ ሴት ተናግራለች። አክላም “ይህን ሁሉ ሥራ ስጨርስ ሰውነቴ በድካም ውልቅልቅ ይላል” ብላለች። በዓለም ላይ ካሉት 1.2 ቢሊዮን እንደሚደርሱ የሚገመቱ ሴት ሠራተኞች መካከል በሚሊዮኖች የሚቆጠሩት እንዲህ ዓይነቱን አድካሚ “የምሽት ፈረቃ” ይሠራሉ። ተመሳሳይ ዕጣ የሚደርሳቸው በርካታ ወንዶች ቢኖሩም አብዛኛውን ጊዜ ወንዶች የቤት ውስጥ ሥራ ለመሥራት ፈቃደኛ እንደማይሆኑ ጥናቶች ያመለክታሉ። ሴቶች ግን በሥራ ቦታ የሚውሉ ሆኑም አልሆኑ በቤት ውስጥ የሚከናወነውን አብዛኛውን ሥራ የሚሠሩት እነሱ ናቸው።