በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አንድን የአፍሪካ ገበያ ጎብኙ

አንድን የአፍሪካ ገበያ ጎብኙ

አንድን የአፍሪካ ገበያ ጎብኙ

አንድን አገር ባሕል፣ ልማድና የምግብ አዘገጃጀት ዘዴ ለማወቅ ከሁሉ የተሻለው መንገድ የአገሩን ገበያ መጎብኘት ነው። ገበያውን ስትጎበኙ የአካባቢውን ሕዝብ ልትመለከቱ፣ ምግባቸውን ልትቀምሱና ዕቃዎቻቸውን ልትገዙ ትችላላችሁ። በተጨማሪም ቋንቋችሁ ምንም ይሁን ምን፣ ከእናንተ ጋር ለመግባባት የሚፍጨረጨሩ የሚገርሙ ቸርቻሪ ነጋዴዎችን ታገኛላችሁ።

በአፍሪካ እንዳሉት ያሉ የሚያስደንቁ ገበያዎችን ማግኘት በጣም አስቸጋሪ ነው። እነዚህ ገበያዎች በሰው የተጨናነቁ ከመሆናቸው በላይ በውስጣቸው የማይገኝ የዕቃ ዓይነት የለም። አፍሪካን ከሌላው ዓለም ለየት ከሚያደርጓት ነገሮች መካከል አንዱ ገበያ ነው። እስቲ ካሜሩን ውስጥ ዱዋላ በምትባል ከተማ የሚገኘውን አንድ ገበያ ላስጎብኛችሁ።

አፍሪካ ውስጥ ገበያተኞች የሚጠቀሙባቸው መጓጓዣዎች

በበርካታ ትላልቅ የአፍሪካ ከተሞች ወደ ገበያ ለመሄድ ርካሹና ፈጣኑ የመጓጓዣ ዘዴ ሞተር ብስክሌት ነው። የሞተር ብስክሌት ሾፌሮች በየመንገዱ ላይ ማለት ይቻላል ቆመው ለገበያተኞች አገልግሎት ይሰጣሉ። የማትፈሩ ከሆነ ከእነዚህ ሞተር ብስክሌቶች በአንዱ ላይ ተሳፍራችሁ መሄድ ትችላላችሁ። በካሜሩን ይህ ተወዳጅ የመጓጓዣ ዘዴ ከዋጋም ሆነ ከፍጥነቱ አንጻር ተወዳዳሪ የለውም።

በሞተር ብስክሌት መሳፈር የሚፈሩ ሰዎች ደግሞ በርካታ ታክሲዎች ስላሉ በእነዚያ መሄድ ይችላሉ። በርካታ ተሳፋሪዎች ሂሳቡ እንዲቀንስላቸው ሲሉ በአንድ ታክሲ ውስጥ ታጭቀው ይሄዳሉ።

በመቶዎች የሚቆጠሩ መደቦች

ገበያውን ለመጀመሪያ ጊዜ የሚጎበኝ ሰው እዚያ በሚያየው ሕዝብ ብዛትና በገበያው ውስጥ በመደዳ በተሠሩት መደቦች ብዛት ሊገረም ይችላል። ልጆችን ጨምሮ ብዛት ያላቸው ሰዎች የሚሸጡትን ነገር በራሳቸው ላይ ተሸክመው ይታያሉ። እነዚህ ሰዎች በቅርጫቶቻቸው ውስጥ ዶሮ፣ የተላጠ ብርቱካን፣ የተለያዩ መድኃኒቶች ወይም ሌሎች ሸቀጦችን ይይዛሉ።

በመቶ በሚቆጠሩ የእንጨት ጠረጴዛዎች ላይ እንደ ጎመን፣ ካሮት፣ ኪያር፣ ደበርጃን፣ ዱባ፣ ፎሶልያ፣ ስኳር ድንች፣ ቲማቲም፣ የተለያዩ የሰላጣ ዓይነቶችና እነዚህን የመሳሰሉት አትክልቶች ተደርድረዋል። አንዳንዶቹ ነገሮች በአፍሪካ ብቻ ያሉና በዚያ የሚገኙ ሰዎች የሚጠቀሙባቸው በመሆናቸው ከሌሎች አሕጉሮች የመጡ ጎብኚዎች ላያውቋቸው ይችላሉ። ምናልባትም ከሁሉም መደቦች በቀለማት አሸብርቀው የሚታዩት፣ የማለዳው የፀሐይ ብርሃን ሲያበራባቸው የሚያንጸባርቁትና ከእርሻ ከተለቀሙ ብዙ ያልቆዩት ትናንሽ ቀይና ቢጫ ቃሪያ የሚሸጥባቸው መደቦች ሳይሆኑ አይቀሩም። በበርካታ መደቦች ላይ ደግሞ አቮካዶ፣ ሙዝ፣ ባሕረ ሎሚ፣ ሐብሐብ፣ አናናስ፣ ብርቱካንና ሎሚ ይሸጣል። እነዚህ ፍራፍሬዎች ሲታዩ ለመብላት የሚያጓጉ ከመሆናቸውም በላይ ዋጋቸውም ቢሆን ርካሽ ነው! የአካባቢው ዋና ምርቶች የሆኑት ስኳር ድንች፣ ካሳቫና ሩዝ ከውጭ ከሚገቡት ቀይና ነጭ ሽንኩርቶች ጋር በጥሩ ሁኔታ ተደርድረው ይታያሉ።

በዱዋላ ከሚገኙት ገበያዎች መካከል በአንዱ ውስጥ ያሉት አብዛኞቹ ነጋዴዎች የሃውሳና የፉላ ጎሳ አባላት ናቸው። እነዚህ ነጋዴዎች ጋንዱራ ወይም ቡቡ ተብሎ በሚጠራ ሰማያዊ፣ ነጭ ወይም ቢጫ ቀለም ባለው ረጅም ልብሳቸው እንዲሁም በፉልፉልዴ ቋንቋ በሚያቀርቡት ሰላምታ ተለይተው ይታወቃሉ። በዚያ አካባቢ የሚታየው ዘና ያለ መንፈስ የገበያው አንዱ ገጽታ ነው። በጉብኝት ላይ እያለሁ ኢብራሂም የሚባል አንድ ነጋዴ ሦስት ትላልቅ ሽንኩርቶችን መርጦ በነጻ ሰጠኝ። ከዚያም “ለባለቤትህ በእነዚህ ሽንኩርቶች ውስጥ በቅመም የተሠራ ሩዝ ሞልታ ለሰስ ባለ እሳት እንድታበስላቸው ንገራት” አለኝ።

ትንሽ አለፍ ብሎ ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ የበሬ ወይም የፍየል ትኩስ ሥጋ የሚሸጥበት ቦታ አለ። ፈርጠም ፈርጠም ያሉ ወንዶች ያልተቆራረጡ ትልልቅ የከብት ብልቶችን ተሸክመው በማምጣት በጠረጴዛዎቹ ላይ ያስቀምጧቸዋል። ሥጋ ሻጮቹ ረጃጅም ቢላዎቻቸውን በቅልጥፍና በመሰንዘር ደንበኞቻቸውን የት ጋር እንዲቆረጥላቸው እንደሚፈልጉ ይጠይቋቸዋል። ራሳቸው አርደው መብላት የሚፈልጉ ደንበኞች ደግሞ ፍየል፣ ዶሮ ወይም አሳማ ገዝተው መሄድ ይችላሉ።

ወደ ቾፕሃውስ ጎራ በሉ

ምንጊዜም ቢሆን በገበያዎቹ ውስጥ ምግብ ቤቶች አይጠፋም። በካሜሩን ገበያዎች ውስጥ ምግብ የሚሸጥባቸው መደቦች ቾፕሃውስ በመባል ይታወቃሉ። አንዳንዶቹ ደንበኛ ለመሳብ ሲሉ ሙዚቃ ከፍ አድርገው ይከፍታሉ፤ ይሁን እንጂ የአፍሪካ ባሕላዊ ምግቦች የሚሸጡባቸውና የአካባቢውን ሰው ማግኘት የሚቻልባቸው ጸጥ ያሉ ቦታዎችም አሉ። አብዛኛውን ጊዜ የምግብ ዝርዝሩ በጥቁር ሰሌዳ ላይ ይጻፋል፤ ሆኖም አንድ ሰው የተጻፈውን የባሕል ምግብ ካላወቀው የሚያስረዳ ሰው ሊያስፈልገው ይችላል።

በእነዚህ ምግብ ቤቶች ውስጥ የሚሸጡት ሁለት ዋና ዋና ምግቦች ሩዝና ከተፈጨ ካሳቫ፣ ሙዝ፣ ወይም ስኳር ድንች የሚዘጋጀው ፉፉ ናቸው። እንዲሁም ከባሚያ፣ ከኦቾሎኒ ቅቤ ወይም ከቲማቲም ስጎ ጋር የሚበላ የዓሣ፣ የበሬ ወይም የዶሮ አሮስቶ ሊቀርብላችሁ ይችላል። ቾፕሃውስ የሚገቡ ሰዎች ብዙም ስለማይጣደፉ ለመጨዋወት የሚያስችል ሰፊ ጊዜ ይኖራል።

ሁለት ሴት አስተናጋጆች ሊያስተናግዱን መጡ። አንደኛዋ በትልቅ ትሪ ላይ ትኩስ ሩዝ፣ ባቄላና ፉፉ የያዙ ጎድጓዳ ሣህኖችን ይዛ መጣች። በእነዚህ ምግቦች ውስጥ በባሚያ የተሠራ ስጎ የገባ ሲሆን ከሥጋና ከዓሣ በተዘጋጀ ሽሽ ክበብ አጊጠዋል። በተጨማሪም ምግባቸው ላይ ቅመም መጨመር ለሚፈልጉ ሰዎች በጣም የሚያቃጥል ትንንሽ ቀይ ቃሪያዎች ያሉበት ዕቃ አብሮ ይቀርባል። ሁለተኛዋ ሴት ደግሞ እጃችንን ለማስታጠብ ፎጣና የእጅ መታጠቢያ ሣህን ከውኃ ጋር ይዛ መጣች። በባሕሉ መሠረት የአካባቢው ምግብ በእጅ ስለሚበላ እጃችንን መታጠባችን አስፈላጊ ነበር። ተስተናጋጁ ከመብላቱ በፊት መጸለዩም ሆነ በአጠገቡ ባሉት ጠረጴዛዎች ዙሪያ የተቀመጡት ሰዎች ጸሎቱን ሰምተው አብረው “አሜን” ማለታቸው የተለመደ ነገር ነው።

ገበያ ውስጥ ምሥራቹን መስበክ

ከጥንት ጀምሮ የገበያ ስፍራዎች በብዙ ማኅበረሰቦች ዘንድ አስፈላጊ ማኅበራዊ ሚና ሲጫወቱ ኖረዋል። ለመግዛትና ለመሸጥ ብቻ ሳይሆን ምሥራች ለማካፈል፣ ከወዳጆች ጋር ለመገናኘት አልፎ ተርፎም ሥራ ለማግኘት ተስማሚ ቦታዎች ሆነው አገልግለዋል። ኢየሱስ ወደ ገበያ ስፍራዎች በመሄድ ሰዎችን ስለ አምላክ ያስተምር እንዲሁም ከሕመማቸው ይፈውስ እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ሐዋርያው ጳውሎስም “በገበያ ስፍራ ከሚያገኛቸው ሰዎች ጋር ይወያይ” ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 17:16, 17፤ ማርቆስ 6:56) ዛሬም በተመሳሳይ በካሜሩን የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች፣ የገበያ ስፍራ የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለመስበክ ጥሩ ቦታ እንደሆነ ይሰማቸዋል።—ተጽፎ የተላከልን

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የተለያየ ቀለም ያላቸው ትናንሽ ቃሪያዎች