ወንዶች የማይወዱኝ ለምንድን ነው?
የወጣቶች ጥያቄ
ወንዶች የማይወዱኝ ለምንድን ነው?
ብዙ ወንዶች እንደሚወዱኝ ስለነገርኩት ምን ያህል ተፈላጊ እንደሆንኩ ያውቃል። አንዳንዶቹ ጓደኞቼ በጣም ሞኞች እንደሆኑ ስነግረው ይስቅ ነበር። ደግሞም ነቃ ያልኩ መሆኔን ያውቃል፤ ምክንያቱም አንዳንድ ጊዜ ሲሳሳት አርሜዋለሁ። መቼም የሴት ጓደኛው እንድሆን ቶሎ ይጠይቀኛል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።
ስትታይ ታምራለች፤ ሆኖም ምንም ቁም ነገር ያላት አትመስልም! በዚያ ላይ ለመናገር ምንም ፋታ አትሰጥም። ትንሽ ፋታ አግኝቼ መናገር ብጀምር እንኳ ታርመኛለች! ባገኘኋት ቁጥር ከአጠገቤ ዞር የምትልበት ጊዜ ይናፍቀኛል።
ወንዶች አይወዱኝም ብለሽ ትጨነቂያለሽ? ብዙ ወጣቶች ሌላው ቀርቶ በዚህ ረገድ ምንም ችግር እንደሌለባቸው የሚሰሙሽ ሴቶች እንኳ ይህ ጉዳይ ያስጨንቃቸዋል! ጆአን የተባለችውን ወጣት እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ጆአን ፈጣን አእምሮ ያላት እንዲሁም ሐሳቧን በደንብ መግለጽ የምትችል የደስ ደስ ያላት ሴት ናት። ሆኖም እንዲህ ትላለች፦ “ወንዶች እንደማይወዱኝ ብዙ ጊዜ ይሰማኛል። የወደድኳቸው አንዳንድ ወንዶች ለእኔ የፍቅር ስሜት እንዳላቸው ያሳዩኝና ከጥቂት ጊዜ በኋላ ይዘጉኛል!”
ወንዶች በአንዲት ወጣት እንዲማረኩ የሚያደርጋቸው ነገር ምንድን ነው? የማይወዱት ነገርስ ምንድን ነው? ለራስሽ ያለሽን ግምት ሳታጪ ጨዋ የሆነ አንድ ወንድ እንዲወድሽ ምን ማድረግ ትችያለሽ?
ማድረግ ያለብሽ ነገር
● ራስሽን እወቂ። የጉርምስና ዕድሜ ላይ ስትደርሺ ለወንዶች የፍቅር ስሜት እያደረብሽ መምጣቱ ይታወቅሽ ይሆናል። ምናልባትም ልብሽ በተለያዩ ወንዶች ተማርኮ ሊሆን ይችላል። ይህ ተፈጥሯዊ ነው። ይሁን እንጂ ዓይንሽ ውስጥ ለገባው ለመጀመሪያው ወንድ ቶሎ ልብሽን ሰጥተሽ ቢሆን ኖሮ በስሜት እንዳትበስይና በመንፈሳዊ እንዳታድጊ ራስሽን አደጋ ላይ ትጥይ ነበር። ጥሩ ባሕርያትን በማዳበር መልካም ስብዕና እንዲኖርሽ ለማድረግ፣ ይበልጥ አስፈላጊ በሆኑ ነገሮች በማተኮር ‘አእምሮሽን ለማደስ’ እንዲሁም አንዳንዶቹ ግቦችሽ ላይ ለመድረስ ጊዜ ያስፈልግሻል።—ሮም 12:2፤ 1 ቆሮንቶስ 7:36፤ ቆላስይስ 3:9, 10
እውነት ነው፣ ብዙ ወንዶች ትኩረት የሚያደርጉት ጠንካራ አቋም በሌላት ወይም ምንም የማታውቅ በምትመስላቸው ሴት ላይ ነው። ይሁን እንጂ እንዲህ ያሉት ወንዶች ማቴዎስ 19:6
በዋነኝነት ልጅቷን የሚቀርቧት በማንነቷ ተማርከው ሳይሆን ሥጋዊ ፍላጎታቸውን ለማርካት ሲሉ ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ሚዛናዊ የሆነ ወንድ መቅረብ የሚፈልገው ጥሩ የትዳር አጋር የምትሆነውን ሴት ነው።—ወንዶች ምን ይላሉ? “የራሷ አመለካከትና አቋም ያላት እንዲሁም በራሷ የምትተማመን ሴት ትማርከኛለች።”—ጄምስ
“አክብሮት በተሞላበት መንገድ ስሜቷን በግልጽ የምትናገርና ያልኩትን ሁሉ ዝም ብላ የማትቀበል ሴት ደስ ትለኛለች። ምንም ያህል ቆንጆ ብትሆን እኔ መስማት የምፈልገውን ብቻ የምትናገር ሴት አትመቸኝም። እንዲህ ካለ ሰው ጋር ማውራት ይጨንቀኛል!”—ዳረን
“ብዙ ጊዜ ከሴቶች መጀመሪያ ላይ የሚማርከኝ ውበታቸው እንደሆነ አልክድም። ይሁን እንጂ ልጅቷ ፍላጎቷ ምን እንደሆነ በትክክል የማታውቅ ከሆነችና የማያስቆጭ ግብ ከሌላት ለእሷ የነበረኝ ስሜት ወዲያውኑ ሊጠፋ ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ በሕይወቷ ምን ማድረግ እንደምትፈልግ የምታውቅና እንዲያውም አንዳንዶቹ ግቦቿ ላይ መድረስ የቻለች ሴት በሌሎች ዘንድ ተወዳጅነት ታተርፋለች።”—ዴሚየን
● ለሌሎች አክብሮት ይኑርሽ። አንቺ መወደድ እንደምትፈልጊ ሁሉ ማንኛውም ወንድ የመከበር ከፍተኛ ፍላጎት አለው። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ባል ሚስቱን መውደድ እንዳለበት ሚስት ደግሞ ባሏን “በጥልቅ ልታከብር” እንደሚገባ የተናገረው ያለ ምክንያት አይደለም። (ኤፌሶን 5:33) በመቶዎች በሚቆጠሩ ወጣት ወንዶች ላይ የተደረገ አንድ ጥናትም የዚህን ጥልቅ ማስተዋል እውነተኝነት ያረጋግጣል፤ ጥናቱ ከተካሄደባቸው ወንዶች መካከል ከ60 በመቶ በላይ የሚሆኑት ከፍቅር የበለጠ ትልቅ ቦታ የሚሰጡት ለአክብሮት እንደሆነ ጥናቱ ገልጿል። በጎልማሳ ወንዶች ላይ በተካሄደ ጥናት መሠረት ደግሞ ከ70 በመቶ የሚበልጡት ተመሳሳይ ምርጫ እንዳላቸው ታውቋል።
አክብሮት ማሳየት ሲባል እሱ ያለሽን ሁሉ መቀበል ማለት አይደለም፤ በሌላ አባባል የተለየ አመለካከት የመያዝም ሆነ ስሜትሽን የመግለጽ መብት እንደሌለሽ ሊሰማሽ አይገባም። (ዘፍጥረት 21:10-12) ይሁን እንጂ አመለካከትሽን የምትገልጪበት መንገድ አንድን ወንድ ሊያሸሸው ወይም ሊያቀርበው ይችላል። አንድ ነገር በተናገረ ቁጥር ሐሳቡን የምትቃረኚ ወይም የምታርሚው ከሆነ ለእሱ አክብሮት እንደጎደለሽ ሊሰማው ይችላል። ሆኖም አመለካከቱን የምታከብሪለት እንዲሁም ደስ የሚል አስተያየት ሲሰነዝር አድናቆትሽን የምትገልጪለት ከሆነ የአንቺን አመለካከት ለመቀበልም ሆነ ለማክበር ቀላል ይሆንለታል። በተጨማሪም አስተዋይ የሆነ ወንድ ቤተሰብሽንም ሆነ ሌሎችን በአክብሮት የምትይዢ መሆን አለመሆንሽን ልብ ማለቱ አይቀርም። *
ወንዶች ምን ይላሉ? “ወንዶች በሰዎች ዘንድ በተለይ ደግሞ በሚወዷት ሴት ዘንድ አመለካከታቸው ተቀባይነት እንዳገኘ ሲሰማቸው ደስ ይላቸዋል።”—አንቶኒ
“አንድ ወንድና አንዲት ሴት በግንኙነታቸው መጀመሪያ ላይ ይበልጥ የሚያስፈልጋቸው ነገር መከባበር እንደሆነ ይሰማኛል። ፍቅር እያደር ሊዳብር ይችላል።”—አድሪያን
“አንዲት ሴት አክብሮት ልታሳየኝ ከቻለች በእርግጠኝነት ልትወደኝ እንደምትችል ይሰማኛል።”—ማርክ
● ልከኛ አለባበስ ይኑርሽ፤ ንጽሕናሽንም ጠብቂ። አለባበስሽና አጋጌጥሽ የልብሽን ሐሳብና ዝንባሌ ልክ እንደ ድምፅ ማጉያ ያስተጋባል። ከአንድ ወንድ ጋር ገና ማውራት እንኳ ሳትጀምሪ አለባበስሽ ስለ አንቺ ብዙ ነገር ይነግረዋል። ልብስሽ ሥርዓታማና ልከኛ ከሆነ ስለ አንቺ ጥሩ መልእክት ያስተላልፋል። (1 ጢሞቴዎስ 2:9) አለባበስሽ የፆታ ስሜት የሚቀሰቅስ ወይም ቅጥ ያጣ ከሆነ ደግሞ የሚያስተላልፈው መልእክት ግልጽ ነው፤ ስለ አንቺ ጥሩ አይናገርም!
ወንዶች ምን ይላሉ? “የአንዲት ሴት አለባበስ ለሕይወት ስላላት አመለካከት ብዙ ይናገራል። ሰውነትን የሚያሳዩ ወይም ቅጥ ያጡ ልብሶችን የምትለብስ ከሆነ የሰውን ትኩረት መሳብ በጣም እንደፈለገች ይሰማኛል።”—አድሪያን
“ፀጉሯን የምትንከባከብ፣ ጥሩ መዓዛ ያላትና አነጋገሯ ረጋ ያለ ሴት ትስበኛለች። በሌላ በኩል ደግሞ በአንድ ወቅት በአንዲት ቆንጆ ሴት ተማርኬ የነበረ ቢሆንም ንጽሕናዋን በደንብ እንደማትጠብቅ ስገነዘብ ግን ራቅኳት።”—ሪያን
“የሌሎችን ትኩረት ለመሳብ ስትል ብዙ መኳኳል እንዲሁም ገላ ላይ የሚጣበቅ ወይም ሰውነትን የሚያሳይ ልብስ መልበስ እንደማያስፈልጋት የሚሰማት ሴት በጣም ደስ ትለኛለች።”—ኤታን
“አንዲት ሴት አለባበሷ የፆታ ስሜት የሚቀሰቅስ ከሆነ መጀመሪያ ላይ የወንዶችን ዓይን ቶሎ እንደምትስብ ግልጽ ነው። እኔ ግን የፍቅር ግንኙነት መጀመር የምፈልገው ከእንዲህ ዓይነት ሴት ጋር አይደለም።”—ኒኮላስ
ማድረግ የሌለብሽ ነገር
● ከማሽኮርመም ተቆጠቢ። ሴቶች በወንዶች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ የማሳደር ችሎታ አላቸው። እንዲህ ያለው ወንዶችን የመማረክ ችሎታ ለጥሩ ብቻ ሳይሆን ለመጥፎ ዓላማም ሊውል ይችላል። (ዘፍጥረት 29:17, 18፤ ምሳሌ 7:6-23) በዚህ ችሎታሽ ተጠቅመሽ ያገኘሽውን ወንድ ሁሉ ለመማረክ የምትሞክሪ ከሆነ የማሽኮርመም ልማድ እንደተጠናወተሽ ተደርገሽ ልትታዪ ትችያለሽ።
ወንዶች ምን ይላሉ? “ከአንዲት ቆንጆ ልጅ ጎን በጣም ተቀራርቦ መቀመጥ በራሱ አንድን ወንድ ልቡ በደስታ እንዲሞላና አልፎ ተርፎም የተለየ ዓይነት ስሜት እንዲሰማው ሊያደርግ ይችላል። አንዲት ሴት ስታወራህ አሁንም አሁንም የምትነካካህ ከሆነ እያሽኮረመመችህ ነው ብዬ አስባለሁ።”—ኒኮላስ
“አንዲት ሴት ከወንድ ጋር በምትሆንበት ጊዜ ሁሉ ሰበብ አስባብ እየፈለገች እጁን የምትይዝ ከሆነ ወይም አላፊ አግዳሚውን ወንድ ሁሉ ለመማረክ ዓይኗን የምታስለመልም ከሆነ የማሽኮርመም አባዜ እንዳለባት ይሰማኛል፤ ይህ ደግሞ በጣም ይደብራል።”—ሆሴ
“አንዲት ሴት ያገኘችውን ወንድ ሁሉ ለመነካካት የምትሞክር ከሆነና የበለጠ ትኩረት የሚሰጣት ወንድ ስታገኝ ደግሞ ቶሎ ብላ ወደ እሱ ዞር የምትል ከሆነ የማሽኮርመም ልማድ እንዳላት አድርጌ እቆጥራታለሁ።”—ኤታን
● መፈናፈኛ የምታሳጪ አትሁኚ። አንድ ወንድና አንዲት ሴት ሲጋቡ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው “አንድ ሥጋ” ይሆናሉ። (ዘፍጥረት 2:24) በዚህ ወቅት ባልና ሚስቱ በነጠላነት ጊዜያቸው የነበራቸውን አብዛኛውን ነፃነታቸውን ይተዋሉ፤ በእርግጥም አንዳቸው ለሌላው ለመኖር ቃል ይገባሉ። (1 ቆሮንቶስ 7:32-34) ይሁን እንጂ ከአንድ ወንድ ጋር ገና መተዋወቅሽ ከሆነ እንደ ባል እንዲሆንልሽ መጠበቅ የለብሽም፤ እሱም ቢሆን እንደ ሚስት እንድትሆኚለት መጠበቅ የለበትም። ገና ምኑንም ሳትይዙት ሙሉ ትኩረቱን እንዲሰጥሽ የምትጠብቂ ከሆነ ጓደኝነታችሁን ልታፈርሽው ትችያለሽ። *
ወንዶች ምን ይላሉ? “አንዲት ወጣት እያንዳንዱን እንቅስቃሴዬን ለማወቅ የምትፈልግ ከሆነ እንዲሁም ከእኔ ጋር ካልሆነች በቀር ማኅበራዊም ሆነ ሌሎች እንቅስቃሴዎቿን መፈጸም ያቃታት ይመስል ‘ከአንተ ጋር ካልሆንኩ’ የምትለኝ ከሆነ መፈናፈኛ እንዳሳጣችኝ ይሰማኛል።”—ዳረን
“በቅርብ የተዋወቅኋት አንዲት ወጣት ነጋ ጠባ በሞባይል መልእክት እየላከች ከማን ጋር እንዳለሁ በተለይ ደግሞ ሴቶች አብረውኝ ካሉ ስማቸው ማን እንደሆነ የምትጠይቀኝ ከሆነ ይህ ለእኔ የማስጠንቀቂያ ምልክት ነው ብዬ አስባለሁ።”—ሪያን
“አንዲት ሴት ከወንድ ጓደኞችህ ጋር ጊዜ እንድታሳልፍ የማትፈቅድልህ ከሆነና ሁልጊዜ አብራህ እንድትሆን ካላደረግህ የምትበሳጭ ከሆነ መፈናፈኛ አትሰጥም ማለት ነው፤ ይህ ደግሞ ይደብራል።”—አድሪያን
ለራስሽ ከፍ ያለ ግምት ይኑርሽ
የወንዶችን ትኩረትና አድናቆት ለማግኘት ሲሉ ምንም ነገር ከማድረግ ወደኋላ የማይሉ ሴቶች እንዳሉ ታውቂ ይሆናል። ሌሎች ደግሞ አንድ ወንድ ጓደኛቸው አልፎ ተርፎም የትዳር አጋራቸው እንዲሆን ለማድረግ ሲሉ የአቋም ደረጃቸውን ዝቅ ሊያደርጉ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ‘የዘራችሁትን ታጭዳላችሁ’ የሚለው መሠረታዊ ሥርዓት በዚህ ጉዳይ ላይም ይሠራል። (ገላትያ 6:7-9) ለራስሽም ሆነ ሕይወትሽን ለምትመሪባቸው የአቋም ደረጃዎች ከፍ ያለ ግምት የማትሰጪ ከሆነ በአንቺ የሚማረኩት ወንዶችም ቢሆኑ ለአንቺም ሆነ ለምትመሪባቸው የአቋም ደረጃዎች ከፍ ያለ ግምት የማይሰጡ እንደሚሆኑ መገመት ይቻላል።
እንግዲያው የሚወዱሽ ሁሉም ወንዶች አለመሆናቸውን አትዘንጊ፤ ይህ ደግሞ እሰየው ነው! ለውጪያዊና ለውስጣዊ ውበትሽ ትኩረት የምትሰጪ ከሆነ “በአምላክ ዓይን ከፍተኛ ዋጋ” ይኖርሻል፤ እንዲሁም በአንቺነትሽ የሚማረክ ብሎም የሚሆንሽን ወንድ ማግኘት ትችያለሽ።—1 ጴጥሮስ 3:4
www.watchtower.org/ype በሚለው ድረ ገጽ ላይ “Young People Ask” በሚል አምድ ሥር ተጨማሪ ርዕሶችን ማግኘት ይቻላል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.14 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች—ጥራዝ 2 (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 3ን ተመልከቺ።
^ አን.28 አንድ ወንድና አንዲት ሴት ሲተጫጩ አንዳቸው ለሌላው ተጨማሪ ኃላፊነት እንደሚኖርባቸው የተረጋገጠ ነው።
ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች
● የአንድን ወንድ ሐሳብ እንደምታከብሪና ስሜቱን እንደምትረጂ ማሳየት የምትችይው እንዴት ነው?
● ለራስሽ ከፍ ያለ ግምት እንደምትሰጪ ማሳየት የምትችይው እንዴት ነው?
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ፍቅርና አክብሮት በአንድ ብስክሌት ላይ እንዳሉ ሁለት ጎማዎች ናቸው ማለት ይቻላል፤ ሁለቱም በጣም አስፈላጊ ናቸው