ትዳራችሁ ከመፍረስ መዳን ይችል ይሆን?
የቤቱ ባለቤቶች ቤቱ በጣም እንደተጎሳቆለ ተገንዝበዋል፤ ቢሆንም ሊያድሱት ወሰኑ።
እናንተስ ከትዳራችሁ ጋር በተያያዘ ተመሳሳይ እርምጃ ለመውሰድ ትፈልጋላችሁ? ከሆነ ከየት መጀመር ትችላላችሁ? የሚከተሉትን ሐሳቦች ተግባራዊ ለማድረግ ሞክሩ።
1 ቁርጠኛ ሁኑ።
በትዳራችሁ ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር የጋራ ጥረት ለማድረግ ተስማሙ። ውሳኔያችሁን በወረቀት ላይ አስፍሩ። ሁለታችሁም ትዳራችሁን ከመፍረስ ለማዳን ቆርጣችሁ ከተነሳችሁ ግባችሁ ላይ ለመድረስ በምታደርጉት ጥረት ትተጋገዛላችሁ።—መክብብ 4:9, 10
2 ችግሩን ለይታችሁ እወቁት።
ትዳራችሁን የበጠበጠው ችግር ምንድን ነው? በትዳራችሁ ውስጥ እንደጎደለ የሚሰማችሁን ወይም እንዲለወጥ የምትፈልጉትን ነገር በአንድ ዓረፍተ ነገር ለማስፈር ሞክሩ። (ኤፌሶን 4:22-24) እናንተ የምትጠቅሱትና የትዳር ጓደኛችሁ የሚጠቅሰው ችግር የተለያየ ቢሆን ሊገርማችሁ አይገባም።
3 ግብ አውጡ።
ትዳራችሁ ከስድስት ወር በኋላ ምን ደረጃ ላይ እንዲደርስ ትፈልጋላችሁ? ምን ነገሮች ተስተካክለው ለማየት ትመኛላችሁ? ግባችሁን ወረቀት ላይ ጻፉ። በትዳራችሁ ውስጥ እንዲኖር የምትፈልጉት ምን እንደሆነ በግልጽ ካወቃችሁ ግባችሁ ላይ መድረስ ቀላል ይሆንላችኋል።—1 ቆሮንቶስ 9:26
4 የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር ሥራ ላይ አውሉ።
ችግሩ ምን እንደሆነ ለይታችሁ ካወቃችሁና ልታደርጓቸው የምትፈልጓቸውን ማስተካከያዎች ከተነጋገራችሁ በኋላ ምክር ለማግኘት መጽሐፍ ቅዱስን መርምሩ። የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጊዜ የማይሽራቸው ሲሆኑ በእርግጥም ይሠራሉ። (ኢሳይያስ 48:17፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:17) ለምሳሌ፣ ቅዱሳን መጻሕፍት ሁለታችሁም ይቅር ባዮች እንድትሆኑ ያበረታታሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ‘በደልን ንቆ መተው መከበሪያ ነው’ ይላል።—ምሳሌ 19:11፤ ኤፌሶን 4:32
የምታደርጉት ጥረት በሙሉ መጀመሪያ ላይ ፋይዳ የሌለው መስሎ ቢታይም ተስፋ አትቁረጡ! ዘ ኬዝ ፎር ሜሬጅ የተባለው መጽሐፍ በአንድ ጥናት ላይ የተገኘውን አበረታች ውጤት እንዲህ በማለት ዘግቧል፦ “ሐቁ በጣም አስገራሚ ነው፦ ጋብቻቸው ደስታ የራቀው ቢሆንም ጥርሳቸውን ነክሰው በትዳራቸው ከዘለቁት ሰዎች መካከል 86 በመቶ የሚሆኑት ከአምስት ዓመት በኋላ ትዳራቸውን ይበልጥ አስደሳች ሆኖ አግኝተውታል።” ፈጽሞ ደስተኛ እንዳልሆኑ ይናገሩ የነበሩ ባልና ሚስቶች እንኳን በትዳራቸው ከፍተኛ ለውጥ ማየት ችለዋል።
እናንተም በትዳራችሁ እንዲህ ዓይነት ለውጥ ማየት ትችሉ ይሆናል። የዚህ መጽሔት አዘጋጆች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች፣ መጽሐፍ ቅዱስ ለባለትዳሮች የሚጠቅሙ መሠረታዊ ሥርዓቶች እንደያዘ ተገንዝበዋል። ለምሳሌ፣ ባለትዳሮች አንዳቸው ለሌላው ደጎችና ከአንጀት የሚራሩ ከሆኑ እንዲሁም በነፃ ይቅር ከተባባሉ ብዙ ትዳሮች ይስተካከላሉ። ሚስቶች “ጭምትና ገር መንፈስ” ማሳየት ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ ተገንዝበዋል፤ ባሎች ደግሞ በሚስቶች ላይ መራራ አለመሆንና አለመቆጣት ብዙ ጥቅም እንዳለው ተምረዋል።—1 ጴጥሮስ 3:4፤ ቆላስይስ 3:19
እነዚህ ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች ውጤታማ የሆኑት መጽሐፍ ቅዱስን ያጻፈው የጋብቻ ዝግጅት መሥራች የሆነው ይሖዋ አምላክ በመሆኑ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ትዳራችሁ የተሻለ እንዲሆን የሚረዳችሁ እንዴት እንደሆነ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ለምን የይሖዋ ምሥክሮችን አትጠይቁም? *
^ አን.14 የይሖዋ ምሥክሮች ቤተሰቦችን ለመርዳት ሲሉ ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው? የተባለ ባለ 192 ገጽ መጽሐፍ አዘጋጅተዋል። ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በዚህ መጽሔት ገጽ 5 ላይ ከሚገኙት አድራሻዎች አመቺ ወደሆነው መጻፍ ትችላላችሁ።