በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትዳር ለመመሥረት በማሰብ የፍቅር ጓደኛ መያዝ

ትዳር ለመመሥረት በማሰብ የፍቅር ጓደኛ መያዝ

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ትዳር ለመመሥረት በማሰብ የፍቅር ጓደኛ መያዝ

ጁሊ እና ሊ በሚጠናኑበት ጊዜ ሁሉ ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናቸውን ጠብቀው ለመቆየት ቁርጥ ውሳኔ አድርገው ነበር። * ይሁንና አንድ ምሽት ብቻቸውን እያሉ የፆታ ስሜታቸው መቀስቀስ ጀመረ። ደግነቱ አልፈው በመሄድ ከባድ ኃጢአት ከመፈጸማቸው በፊት ወደ ልቦናቸው ተመለሱ።

እውነተኛ አምልኮ በየሳምንቱ በሚደረግ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት ላይ ከመገኘት ያለፈ ነገርን ይጨምራል። እውነተኛ አምልኮ በአንድ ሰው መላ ሕይወት ውስጥ የሚንጸባረቅ ነገር ነው፤ በአኗኗሩና በሥነ ምግባር መሥፈርቶቹ ላይ ለውጥ ያመጣል። የአምላክን ሞገስ የሚያገኙት ‘ፈቃዱን የሚያደርጉ’ ሰዎች ብቻ እንደሆኑ ኢየሱስ ክርስቶስ ተናግሯል። (ማቴዎስ 7:21) አምላክን ለማስደሰት ከፈለግን ከተቃራኒ ፆታ ጋር ያለን ግንኙነት ክብር ያለው እንዲሆን ልናደርግ እንዲሁም የፍቅር ጓደኝነት የምንመሠርተው ለማግባት በማሰብ ሊሆን ይገባል።

በተለይ ጥንዶች የሥነ ምግባር አቋማቸውን እንዲያላሉ ከሚደረግባቸው ከፍተኛ ግፊት አንፃር ግንኙነታችሁ በአምላክ ፊት ንጹሕ ሆኖ እንዲቀጥል ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ፣ የአምላክ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ለራሳችን ጥቅም የታሰቡ መሆናቸውን መገንዘብ ይኖርባችኋል። ሁለተኛ፣ ፍጽምና ስለጎደላቸው ሰዎች ባሕርይ እውነታውን መቀበል ያስፈልጋችኋል። ሦስተኛ፣ ትክክለኛውን የሥነ ምግባር አቋም በተመለከተ ለራሳችሁ ቁርጥ ያሉ ገደቦችን አብጁ። አራተኛ፣ በግንኙነታችሁ መሃል አምላክ እንዲኖር አድርጉ። እስቲ እነዚህን ነጥቦች አንድ በአንድ እንመልከታቸው።

ለእኛ ጥቅም ታስበው የተቀመጡ መሥፈርቶች

ኢሳይያስ 48:17, 18 እንደሚከተለው ይላል፦ “እኔ እግዚአብሔር አምላክህ፣ የሚበጅህ ምን እንደ ሆነ የማስተምርህ፣ መሄድ በሚገባህ መንገድ የምመራህ ነኝ። ትእዛዜን ሰምተህ ብቻ ቢሆን ኖሮ፣ ሰላምህ እንደ ወንዝ፣ ጽድቅህም እንደ ባሕር ሞገድ በሆነ ነበር።”

አዎን፣ አምላክ በመንፈሱ መሪነት ባጻፈው በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈሩት ትእዛዛትና መሠረታዊ ሥርዓቶች ለራሳችን ጥቅም ሲባል የተሰጡን ናቸው። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) እነዚህ ትእዛዛትና መሠረታዊ ሥርዓቶች ፈጣሪያችን በእርግጥ እንደሚያስብልንና በሁሉም የሕይወታችን ዘርፎች ደስተኞችና ስኬታማ እንድንሆን እንደሚፈልግ የሚያሳዩ ማስረጃዎች ናቸው። (መዝሙር 19:7-10) እናንተስ በእርግጥ እንደዚህ ይሰማችኋል? ከሆነ እውነተኛ ጥበብ አላችሁ ማለት ነው።

ስለ ተፈጥሯችሁ እውነታውን ተቀበሉ

ይሖዋ ልክ እንደ አንድ እውነተኛ ወዳጅ ሐቀኛ ስለሆነ ስለ ራሳችን እውነቱን ይነግረናል። ለምሳሌ ያህል፣ ቃሉ “የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ ነው፤ ፈውስም የለውም፤ ማንስ ሊረዳው ይችላል?” በማለት ያስጠነቅቀናል። (ኤርምያስ 17:9) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ “በራሱ የሚታመን ተላላ ነው፤ በጥበብ የሚመላለስ ግን ክፉ አያገኘውም” በማለት ይናገራል።—ምሳሌ 28:26

የፍቅር ጓደኝነት የጀመሩ አንድ ወንድና አንዲት ሴት በራሳቸው እንደሚታመኑ የሚያሳዩት እንዴት ሊሆን ይችላል? አንዱ መንገድ፣ በመግቢያው ላይ ከተጠቀሱት ጥንዶች ጋር በሚመሳሰል መልኩ ገደባቸውን አልፈው እንዲሄዱ ሊጋብዟቸው የሚችሉ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ በመፍቀድ ነው። ሌላው መንገድ ደግሞ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ወላጆቻቸው የሚሰጧቸውን ጥበብ ያዘሉ ምክሮች ችላ በማለት ነው። ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ወላጆች የፆታ ስሜት በተለይ በወጣትነት ዕድሜ ላይ ልክ እንደ ኃይለኛ ሞተር ቁጥጥር ሊደረግበት እንደሚገባ ያውቃሉ።

በመሆኑም ‘በአምላካዊ ጥበብ የሚመላለሱ’ ወጣቶች ወላጆቻቸው የሚሰጧቸውን አመራር በቁም ነገር ይመለከቱታል። ወላጆች፣ ልጆቻቸው ሊሰሟቸው ባይፈልጉ እንኳ ለእነሱ ባላቸው ፍቅር በመገፋፋት ለልጆቻቸው ምክር ይሰጧቸዋል፤ ጥበበኛ የሆኑ ወጣቶች ደግሞ ወላጆቻቸው የሚሰጧቸውን ምክር ልብ ይላሉ። እርግጥ ነው፣ ከማንም በላይ አብልጦ የሚወዳችሁ የሰማዩ አባታችሁ ይሖዋ አምላክ ሲሆን እሱም “ጭንቀትን ከልብህ አርቅ፤ ክፉ ነገርንም ከሰውነትህ አስወግድ” በማለት መክሯችኋል። (መክብብ 11:9, 10) ይህን ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው? ተገቢ ላልሆኑ ፍላጎቶች ባለመሸነፍ ነው።

በሥነ ምግባር ረገድ ግልጽ የሆኑ ገደቦችን አብጁ

“ጥበብ . . . ምክርን በሚቀበሉ ዘንድ ትገኛለች።” (ምሳሌ 13:10) አስተዋይ የሆኑ ጥንዶች ይህንን ምክር ተግባራዊ በማድረግ ገና ግንኙነታቸውን ሲጀምሩ በቅዱሳን መጻሕፍት መሠረት ተገቢ የፍቅር መግለጫዎች የትኞቹ እንደሆኑ አስቀድመው ይነጋገራሉ፤ እንዲሁም እነዚህን ገደቦች ላለማለፍ ቁርጥ ውሳኔ ያደርጋሉ። ተገቢ ባልሆኑ የፍቅር መግለጫዎች መጠቀም ወይም ከልክ በላይ በራስ መተማመን ለአደጋ በሚያጋልጥ ሁኔታ መኪና ከማሽከርከር ጋር ይመሳሰላል። አደጋ አጋጥሞህ ከመኪናው ውስጥ ተጎትተህ ከወጣህ በኋላ የትራፊክ ደኅንነት ደንቦችን ለመከተል ቁርጥ ውሳኔ ብታደርግ ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ ይሆንብሃል!

መጽሐፍ ቅዱስ “አስተዋይ ሰው አደጋ ሲያይ መጠጊያ ይሻል፤ ብስለት የጐደለው ግን በዚያው ይቀጥላል፤ መከራም ያገኘዋል” ይላል። (ምሳሌ 22:3) አንድ ወንድና አንዲት ሴት በሚጠናኑበት ጊዜ ለአምላክ ሕግ አክብሮት ካላቸው ሰዎች ጋር በመሆን ወይም አንድ ሰው አብሯቸው እንዲሆን በማድረግ ችግሮች እንዳይፈጠሩ ራሳቸውን መጠበቅ ይችላሉ። የሚጠናኑ ሰዎች ተገቢ ያልሆነ ድርጊት መፈጸማቸው ከሚያስከትላቸው መከራዎች መካከል የሕሊና መቆሸሽ፣ ለራስም ሆነ ለሌላው ወገን አክብሮት ማጣትና የቤተሰብ አባሎችን ጨምሮ ጉዳዩ በሚመለከታቸው ሁሉ ላይ የሚደርሰው ኃፍረት ይገኙበታል። ስለዚህ አስተዋዮች ሁኑ፤ የመጽሐፍ ቅዱስን መሥፈርቶች ተግባራዊ ለማድረግ ፈቃደኞች ሁኑ፤ እንዲሁም በዚህ አቋማችሁ ጽኑ!

‘ሦስተኛው ገመድ’ ይሖዋ እንዲሆን አድርጉ

ጋብቻ በሦስት እንደተገመደ ገመድ ሲሆን ዋነኛው ገመድ አምላክ ነው። መክብብ 4:12 “በሦስት የተገመደ ገመድም ቶሎ አይበጠስም” በማለት ይናገራል። በሚጠናኑ ወንድና ሴት ላይም ይኸው መሠረታዊ ሥርዓት ይሠራል። ጥንዶቹ፣ አምላክ ግንኙነታቸውን እንዲባርክላቸው የሚፈልጉ ከሆነ በግለሰብ ደረጃ ከእሱ ጋር የቅርብ ዝምድና ሊኖራቸው ይገባል። መዝሙር 1:1-3 እንዲህ ይላል፦ “በክፉዎች ምክር የማይሄድ፣ . . . ሰው ብፁዕ ነው። ነገር ግን ደስ የሚሰኘው በእግዚአብሔር ሕግ ነው፤ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያሰላስለዋል። . . . የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል።”

አዎን፣ መጠናናትንና ጋብቻን ጨምሮ በሕይወታችን ውስጥ እውነተኛ ስኬት የምናገኘው ከይሖዋ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ ስንመላለስ ነው። ደግሞም ይሖዋ ፈጣሪያችን መሆኑን ልንዘነጋ አይገባም፤ የፍቅር ስሜትም ሆነ ጋብቻ ከእሱ ያገኘናቸው ውድ ስጦታዎች ናቸው። ይህም በመሆኑ ለእነዚህ ስጦታዎች ከፍተኛ አክብሮት ሊኖረን ይገባል።—ያዕቆብ 1:17

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.3 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

ይህን አስተውለኸዋል?

አምላክ ከሁሉ የተሻለውን እንድናገኝ የሚፈልግ መሆኑን እንዴት እናውቃለን?ኢሳይያስ 48:17, 18

ስለ ተፈጥሯችን መቀበል የሚኖርብን ሐቅ ምንድን ነው?ኤርምያስ 17:9

አንድ ወንድና አንዲት ሴት ሲጠናኑም ሆነ ከተጋቡ በኋላ ስኬታማ እንዲሆኑ የሚረዳቸው ቁልፍ ምንድን ነው?መዝሙር 1:1-3

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አስተዋይ የሆኑ ጥንዶች ገና ግንኙነታቸውን ሲጀምሩ በቅዱሳን መጻሕፍት መሠረት ተገቢ የፍቅር መግለጫዎች የትኞቹ እንደሆኑ አስቀድመው ይነጋገራሉ፤ እንዲሁም እነዚህን ገደቦች ላለማለፍ ቁርጥ ውሳኔ ያደርጋሉ