በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሁሉም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች አሁንም ይጠቅማሉ?

ሁሉም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች አሁንም ይጠቅማሉ?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ሁሉም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች አሁንም ይጠቅማሉ?

“መጽሐፍ ቅዱስ፣ ለጨዋታ የተዘጋጁ ሰንጠረዦችን ለመሙላት ወይም በጥያቄና መልስ ውድድር ላይ የሚቀርቡ ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚያስችሉ አንዳንድ አጠቃላይ እውቀቶችን ከመያዝ በቀር በዘመናችን ያሉ ሰዎች በሕይወታቸው ሊጠቀሙበት የሚችሉት ተግባራዊ ሐሳብ የለውም።”

“ስለ ትውልድ ሐረግ፣ ስለ ድንግልና እንዲሁም ፈሪሃ አምላክ ስለማዳበር የሚናገሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳቦች በተጻፉበት ዘመን ለነበረው ባሕል ጠቃሚ እሴት ሆነው ቢያገለግሉም በ21ኛው መቶ ዘመን ያላቸው ጠቀሜታ በጣም አነስተኛ ነው።”

“መጽሐፍ ቅዱስ ለመጀመሪያ ጊዜ ለኅትመት ከመብቃቱ በፊትም እንኳን ጊዜ አልፎበት ነበር።”

ነዚህ አስተያየቶች፣ “መጽሐፍ ቅዱስ ጊዜ ያለፈበትና ጥቅም የሌለው ነው?” የሚል ርዕስ ይዞ ከወጣ አንድ የኢንተርኔት ድረ ገጽ ላይ በቅርብ የተወሰዱ ናቸው። ስለ እነዚህ አስተያየቶች ምን ይሰማሃል? ትስማማባቸዋለህ?

የመጽሐፍ ቅዱስን ዋጋማነት ከልክ በላይ በሚያጥላሉ እንደነዚህ በመሰሉ አስተያየቶች ባትስማማም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለው እያንዳንዱ ነገር ጠቃሚ የመሆኑ ጉዳይ ግን ያጠራጥርህ ይሆናል። ደግሞም አብዛኞቹ አብያተ ክርስቲያናት የሚጠቀሙባቸው መጽሐፍ ቅዱሶች በተለምዶ ብሉይ (ወይም አሮጌ) ኪዳን እና አዲስ ኪዳን በመባል ስለሚከፈሉ ከ75 በመቶ በላይ የሚሆነው የመጽሐፉ ክፍል አሮጌና ዘመን ያለፈበት ነው የሚል ስሜት ያስተላልፋል።

በዛሬው ጊዜ በሙሴ ሕግ ውስጥ የታዘዙትን የእንስሳት መሥዋዕቶች የሚያቀርብ ማንም የለም። ታዲያ በዘሌዋውያን መጽሐፍ ውስጥ መሥዋዕቶችን አስመልክቶ የተሰጡትን እነዚያን ሁሉ ዝርዝር መመሪያዎች ጠብቆ ማቆየት ጥቅሙ ምንድን ነው? (ዘሌዋውያን 1:1 እስከ 7:38) እንዲሁም በአብዛኛው የዘር ሐረግ ዝርዝሮችን ስለያዙት የ1ኛ ዜና መዋዕል መጽሐፍ የመጀመሪያ ምዕራፎችስ ምን ሊባል ይችላል? (1 ዜና መዋዕል 1:1 እስከ 9:44) በዛሬው ጊዜ የሚኖር ማንኛውም ሰው የራሱን የዘር ሐረግ ከእነዚያ ምዕራፎች ውስጥ ፈልጎ ማግኘት የማይችል ከሆነ እንደነዚህ ያሉት ዝርዝሮች ጥቅማቸው ምንድን ነው?

ከፖም ዛፍ ላይ አንድ ፍሬ ቀነጠስክ እንበል። ፍሬውን አንዴ ካገኘህ በኋላ ዛፉ ምንም ጥቅም የለውም ማለት ነው? ሌላ ፍሬ ለማግኘት የምትፈልግ ከሆነ እንደዚህ አይሰማህም! በአንዳንድ መንገዶች መጽሐፍ ቅዱስ ከዚህ የፖም ዛፍ ጋር ይመሳሰላል። እንደ መዝሙር መጽሐፍ ወይም የተራራውን ስብከት እንደሚዘግቡት ያሉትን አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በቀላሉ ልታገኛቸው ብሎም ስታነባቸው “ጣፋጭ” ሊሆኑልህ ይችላሉ። ታዲያ ልክ እንደምንወደው ፍሬ እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ከፍ አድርገን እየተመለከትን ሌሎቹን ማጣጣል ይኖርብናል? መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይላል?

ሐዋርያው ጳውሎስ በ65 ዓ.ም. ገደማ ለጢሞቴዎስ ሁለተኛውን ደብዳቤ በጻፈለት ጊዜ “በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን ለመዳን የሚያበቃ ጥበብ እንድታገኝ የሚያስችሉህን ቅዱሳን መጻሕፍት ከጨቅላነትህ ጀምሮ አውቀሃል” ብሎት ነበር። አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “ቅዱስ መጽሐፉ ሁሉ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ ነው፤ እንዲሁም ለማስተማር፣ ለመገሠጽ፣ ነገሮችን ለማቅናትና በጽድቅ ለመምከር ይጠቅማል።” (2 ጢሞቴዎስ 3:15, 16) ጳውሎስ ‘ቅዱስ መጽሐፉ ሁሉ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈና ጠቃሚ’ ነው ብሎ ሲጽፍ እየተናገረ የነበረው ስለ አዲስ ኪዳን ብቻ ነበር?

ጳውሎስ፣ ጢሞቴዎስ ‘ከጨቅላነቱ’ ጀምሮ ‘ቅዱሳን መጻሕፍትን’ እንዳወቀ የተናገረውን ሐሳብ ልብ በል። በአንዳንዶች ዘንድ እንደሚታመነው ጢሞቴዎስ ይህ ደብዳቤ በተጻፈለት ጊዜ ዕድሜው በ30ዎቹ ውስጥ ከሆነ ኢየሱስ በሞተበት ወቅት ጨቅላ ሕፃን ነበር ማለት ነው። ኢየሱስ የሞተው ደግሞ ከአዲስ ኪዳን ወይም ከግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ አንዱም ክፍል ከመጻፉ በፊት ነበር። የጢሞቴዎስ እናት አይሁዳዊት ስለነበረች ጢሞቴዎስን ከልጅነቱ ጀምሮ ያስተማረችው ቅዱሳን መጻሕፍት፣ ብሉይ ኪዳን ወይም የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት መሆን ይኖርባቸዋል። (የሐዋርያት ሥራ 16:1) በመሆኑም ጳውሎስ “ቅዱስ መጽሐፉ ሁሉ” ብሎ ሲጠቅስ መሥዋዕት ስለማቅረብ የሚናገረውን ሕግና የዘር ሐረጎችን የያዘውን መላውን ብሉይ ኪዳን በአእምሮው ይዞ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም።

ሐዋርያው ጳውሎስ ከላይ ያለውን ከተናገረ 1,900 ዓመታት ቢያልፉም እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች አሁንም በብዙ መንገዶች ይጠቅሙናል። በመጀመሪያ፣ መጽሐፍ ቅዱስ እጃችን ውስጥ ሊገባ የቻለው አምላክ፣ በመረጣቸው ሰዎች አማካኝነት እንዲጻፍና ተጠብቆ እንዲቆይ ስላደረገው ነው። (ሮም 3:1, 2) የሙሴ ሕግ፣ በጥንቷ እስራኤል ለመጪው ትውልድ የሚተላለፍ ቅርስ ብቻ ሳይሆን የብሔሩ ሕገ መንግሥት ጭምር ሆኖ ያገለግል ነበር። በሕጉ ውስጥ የሰፈሩት ዝርዝር ሐሳቦች በዛሬው ጊዜ የማያስፈልጉ ቢመስሉም የጥንቷ እስራኤል ሕዝብ ሕልውናው እንዲቀጥልና በሥርዓት እንዲኖር በእጅጉ ያስፈልጉ ነበር። ከዚህም በላይ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰፍረው የሚገኙት የዘር ሐረግ ዝርዝሮች፣ ከንጉሥ ዳዊት ዘር እንደሚመጣ በትንቢት የተነገረለትን መሲሕ ለይቶ ለማወቅ ያስፈልጉ ነበር።—2 ሳሙኤል 7:12, 13፤ ሉቃስ 1:32፤ 3:23-31

ክርስቲያኖች በሙሴ ሕግ ሥር ባይሆኑም እንኳን በትንቢት አስቀድሞ በተነገረለት መሲሕ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እምነት እንዳላቸው በተግባር ማሳየት ያስፈልጋቸዋል። እስከ ዘመናችን ተጠብቀው የቆዩት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት የዘር ሐረግ ዝርዝሮች ኢየሱስ በእርግጥ ተስፋ የተሰጠበት “የዳዊት ልጅ” እንደሆነ ያረጋግጣሉ። እንዲሁም መሥዋዕቶችን በተመለከተ የተሰጡት ዝርዝር መመሪያዎች፣ የላቀ ጠቀሜታ ላለው የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ያለንን አድናቆት ከፍ በማድረግ መሥዋዕቱ ባለው ዋጋ ላይ ያለንን እምነት ያሳድጉልናል።—ዕብራውያን 9:11, 12

ጳውሎስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በሮም ለነበረው የክርስቲያን ጉባኤ ሲጽፍ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “በምናሳየው ጽናትና ከቅዱሳን መጻሕፍት በምናገኘው መጽናኛ ተስፋ ይኖረን ዘንድ ቀደም ብሎ የተጻፈው ነገር ሁሉ ለእኛ ትምህርት እንዲሆን ተጽፏል።” (ሮም 15:4) ይህ ጥቅስ መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው ለእኛ ጥቅም እንደሆነ ቢናገርም የተጻፈበት ዓላማ ይህ ብቻ አይደለም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት በመንፈስ መሪነት የተጻፉት ሐሳቦች በሲና ምድረ በዳ፣ በተስፋይቱ ምድር፣ በባቢሎን ግዞትና በሮም ግዛት የነበሩትን እንዲሁም በዛሬው ጊዜ በምድር ዙሪያ ያሉትን ጨምሮ በአጠቃላይ ከ3,500 በሚበልጡ ዓመታት ውስጥ የኖሩትን የአምላክ ሕዝቦች ሲመሩ፣ ሲያስተምሩና ሲገሥጹ ኖረዋል። እንዲህ ሊባልለት የሚችል ሌላ መጽሐፍ የለም። እንደ ፖም ዛፍ ሥሮች ሁሉ የአንዳንዶቹን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ጠቀሜታ ወዲያውኑ ማየት አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። እንዲህ ያለውን ጥቅም በግልጽ ለማየት ትንሽ ቁፋሮ ማድረግ ሊያስፈልግ ቢችልም የሚደረገው ጥረት በእጅጉ የሚክስ ነው!

ይህን አስተውለኸዋል?

ጢሞቴዎስ ‘ቅዱሳን መጻሕፍትን’ ያወቀው ከመቼ ጀምሮ ነበር?2 ጢሞቴዎስ 3:15

በመንፈስ መሪነት የተጻፉትና ጠቃሚ የሆኑት የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ናቸው?2 ጢሞቴዎስ 3:16

‘ቀደም ብሎ ከተጻፈው ነገር ሁሉ’ ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?—ሮም 15:4

[በገጽ 29 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት ዝርዝር ሐሳቦች ኢየሱስ ላቀረበው መሥዋዕት ያለንን አድናቆት ከፍ ያደርጉልናል