ልዩ በሆነ ዘዴ የተገናኙት የፌሮ ደሴቶች
ልዩ በሆነ ዘዴ የተገናኙት የፌሮ ደሴቶች
በተነዋዋጩ የሰሜን አትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ እጅብ ብለው የሚገኙ 18 ትናንሽ ደሴቶች ያሉባቸው የፌሮ ደሴቶች ፋሮኢስ የሚባል ቋንቋ የሚናገሩ ሕዝቦች ይኖሩባቸዋል። እጅግ ውብ በሆኑት በእነዚህ ደሴቶች ላይ የሚገኙት ሾጣጣና ወጣ ገባ የሚበዛባቸው ተራሮች በቀጥታ ከባሕሩ ጋር ይገናኛሉ። በባሕሩ አቅራቢያ ባሉ መንደሮች ውስጥ የሚገኙት ቤቶች በተለያዩ ቀለማት ያሸበረቁ ናቸው። በክረምት ወራት ኮረብቶች በሣር ስለሚሸፈኑ ምድሩ ሁሉ ልዩ ውበት ይላበሳል።
በእነዚህ ደሴቶች ላይ የሚኖሩ 48,000 የሚያህሉት ሕዝቦች የሚሠሩት እንደ አንድ ማኅበረሰብ ቢሆንም እርስ በርስ መገናኘት ሁልጊዜ ቀላል አልነበረም። ቀደም ሲል ሰዎችም ሆኑ ዕቃዎች ከአንዱ ደሴት ወደ ሌላው የሚጓጓዙት መቅዘፊያ ባላቸው ጀልባዎች ነበር። ሰዎች ከአንድ መንደር ወደ ሌላ መንደር የሚሄዱት ቀጥ ያሉ ዳገቶችንና ዥው ያሉ ገደሎችን በእግር በማቋረጥ ነበር። ቤት መሥራትም ቀላል አልነበረም፤ ምክንያቱም የግንባታ ቁሳቁሶቹን በሙሉ በጀልባ ማጓጓዝ ያስፈልጋል። ነዋሪዎቹ የቤቱን ሥራ ከመጀመራቸው በፊት ቁሳቁሶቹን በባሕሩ ዳርቻ ላይ ከሚገኝ የተፈጥሮ ወደብ ጭነው ቤቱ ወደሚሠራበት ቦታ ማጓጓዝ ይጠይቅባቸዋል።
የመጀመሪያዎቹ ሰፋሪዎች
ስለ ፌሮ ደሴቶች ታሪክ የሚያወሱት ጥንታዊ የሚባሉት ዘገባዎች የተጻፉት በ825 ዓ.ም. አካባቢ በአንድ አየርላንዳዊ መነኩሴ ነበር። እኚህ መነኩሴ እሳቸው ከኖሩበት ጊዜ ከአንድ መቶ ዓመት በፊት በደሴቶቹ ላይ ብቻቸውን የሚኖሩ አየርላንዳውያን መነኮሳት እንደነበሩ ገልጸዋል። ከመነኮሳቱ በተጨማሪ ሌሎች ሰዎች በደሴቶቹ ላይ መስፈር የጀመሩት ግን ግሪሙር ካምበን የሚባሉ ሰው ከኖርዌይ መምጣታቸውን ተከትሎ በዘጠነኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ እንደነበር ይነገራል።
የቀድሞዎቹ የደሴቶቹ ነዋሪዎች ይተዳደሩ የነበሩት ዓሣ በማጥመድ ቢሆንም በጎችንም ያረቡ ነበር። በፋሮኢስ ቋንቋ ፎረያር (የፌሮ ደሴቶች) የሚለው ቃል ትርጉሙ “የበጎች ደሴቶች” ማለት ሲሆን በግ ማርባት አሁንም ድረስ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ሥራ ነው። ከበጎቹ የሚገኘው ሱፍ ከነፋስ፣ ከዝናብና ከብርድ ለመከላከል ሲያገለግል ቆይቷል። እንዲያውም ‘ሱፍ የፋሮኢሳውያን ወርቅ ነው’ ተብሎ ይነገር ነበር።
በዛሬው ጊዜም በደሴቶቹ ላይ የሚኖሩት በጎች ቁጥር ከሕዝቡ ይበልጣል። በጎች በባሕላዊው መንገድ ከታረዱ በኋላ ሥጋቸው ነፋስ እንደልብ በሚተላለፍበት ጥላ ሥር ተሰቅሎ እንዲደርቅ ይደረጋል። ይህ ደግሞ ግሩም ጣዕም ያለው ቋንጣ እንዲሆን ያደርጋል።
ከሌሎች ራቅ ብለው በሚኖሩ አናሳ ማኅበረሰቦች ላይ እንደሚታየው የፌሮ ሕዝቦችም ሕልውናቸው የተመሠረተው አንዳቸው ከሌላው ጋር ባላቸው ትስስር ላይ እንደሆነ እስኪሰማቸው ድረስ በጣም ይቀራረባሉ። ይህ ስሜት የደሴቶቹ ነዋሪዎች እርስ በርስ እንደልብ እንዲገናኙ የሚያስችሉ ዘመናዊ የመጓጓዣና የመገናኛ ዘዴዎች በተፈለሰፉበት በዚህ ዘመንም አልጠፋም።
እርስ በርስ ለመገናኘት የሚያስችሉ መሿለኪያዎች
በፌሮ ደሴቶች የመጀመሪያው መሿለኪያ ለአገልግሎት ክፍት የሆነው በ1963 ነበር። ሁለት መንደሮችን የሚያገናኘው ይህ መሿለኪያ የተሠራው በስተ ደቡብ ሱዘሮይክ በሚባለው የመጨረሻው ደሴት ላይ የሚገኘውን አንድ ተራራ በመቦርቦር ነው። መሿለኪያውን ለመሥራት ከፍተኛ የሆነ ቁፋሮ፣ ስርሰራና ድማሚት ማፈንዳት የጠየቀ ሲሆን ሥራው የተካሄደው በሁለት ተቃራኒ አቅጣጫ ነበር።
በቅርቡ የተሠራ አንድ ሌላ መሿለኪያ ደግሞ ሁለት ትላልቅ ደሴቶችን የሚያገናኝ ሲሆን ከባሕር ወለል በታች 150 ሜትር ዝቅ ብሎ ይገኛል። ይህን የመኪና መንገድ ለመሥራት ዓለቶችን የሚቦረቡር 5 ሜትር ርዝመት ያለው መሰርሰሪያ መጠቀም ግድ ሆኗል። ተራራው ከተቦረቦረ በኋላ በመሿለኪያ ቀዳዳው ጫፍ ላይ ድማሚት እንዲፈነዳ ተደረገ። ከፍንዳታው በኋላ ዓለቶቹንና ትላልቆቹን ቋጥኞች በማውጣት 5 ሜትር ርዝመት ያለው የመሿለኪያው ክፍል ክፍት ሆነ። በአጠቃላይ 6 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውን ይህን መሿለኪያ ለመሥራት ይህን አሠራር በተደጋጋሚ መጠቀም አስፈልጓል። በመጨረሻም መንገዱ ሚያዝያ 29, 2006 ለትራፊክ ክፍት ሆነ።
በአሁኑ ጊዜ የፌሮ ደሴቶች 18 መሿለኪያዎች ያሏቸው ሲሆን ከእነዚህ መካከል ሁለቱ ከባሕር በታች የተሠሩና ደሴቶችን የሚያገናኙ ናቸው። ከነዋሪዎቹ ቁጥር አንፃር ሲታይ በዓለም ላይ ይህን ያህል ርዝማኔ ያለው መሿለኪያ ያለው ሌላ አገር የለም። ይሁንና አዳዲስ መሿለኪያዎችን ለመሥራት እቅድ ተይዟል። ፓርላማው ዋና ዋናዎቹን ደሴቶች የሚያገናኙ ሁለት ተጨማሪ መሿለኪያዎችን ለመሥራት ወስኗል። በ2012 እንደሚጠናቀቅ የሚጠበቀው አንደኛው መሿለኪያ 11.9 ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚኖረው ሲሆን ይህም እስካሁን በዓለም ላይ ከውኃ በታች ከተሠሩት የመኪና መተላለፊያዎች ሁሉ በርዝመታቸው ተወዳዳሪ የሌላቸው ከሚባሉት አንዱ ያደርገዋል።
በዓይነቱ ለየት ያለ ትስስር
በፌሮ ደሴቶች ላይ በዓይነቱ ለየት ባለ ሁኔታ የተሳሰረ አንድ ቡድን አለ፤ በዚህ ቡድን ይኸውም በይሖዋ ምሥክሮች መካከል ጠንካራ የሆነ መንፈሳዊ ትስስር ይታያል። ደሴቶቹን ለመርገጥ የመጀመሪያ የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች በ1935 ከዴንማርክ የመጡ ሁለት ለአምላክ ያደሩ ሴቶች ነበሩ፤ የበጋውን ወራት በእነዚህ ደሴቶች ላይ ያሳለፉት እነዚህ ሴቶች ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ለሰዎች ሰብከዋል። ከጊዜ በኋላ ከደሴቶቹ ነዋሪዎች ጥቂቶቹ ይህን አጽናኝ መልእክት ተቀብለው እነሱም ለሌሎች መስበክ ጀመሩ።—ማቴዎስ 24:14
በዛሬው ጊዜ በደሴቶቹ ላይ ባሉት አራት የመንግሥት አዳራሾች የሚሰበሰቡ መቶ የሚያህሉ የይሖዋ ምሥክሮች አሉ። እነዚህ የይሖዋ ምሥክሮች ተነዋዋጭ በሆነው የሰሜን አትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ የሚገኙትን ማራኪ ደሴቶች ለማገናኘት በተሠሩ ግሩም መንገዶችና መሿለኪያዎች ታግዘው አገልግሎታቸውን በቅንዓት ያከናውናሉ።
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይህ መሿለኪያ ከባሕር ወለል በታች 150 ሜትር ዝቅ ብሎ የተሠራ ሲሆን ሁለት ትላልቅ ደሴቶችን ያገናኛል