መጀመሪያ የሠራው ማነው?
መጀመሪያ የሠራው ማነው?
በ1973 ዶክተር ማርቲን ኩፐር በእጅ የሚያዝ ሞባይል ስልክ እንዴት እንደሚሠራ ለማሳየት የመጀመሪያው ሰው ሆኑ። እሳቸው የሠሩት ስልክ ባትሪ፣ ሬዲዮና ማይክሮፕሮሰሰር (አነስተኛ ኮምፒውተር) ነበረው። ኩፐር መንገድ ላይ ሆነው በስልክ ሲነጋገሩ የኒው ዮርክ ነዋሪዎች በአድናቆት አፋቸውን ከፍተው ይመለከቷቸው ነበር። ይሁን እንጂ እሳቸው ይህን መሣሪያ ሊፈለስፉ የቻሉት ቀደም ሲል በ1800 አለሳንድሮ ቮልታ አስተማማኝ የሆነ ባትሪ ፈልስፎ ስለነበረ ነው። በተጨማሪም ስልክ በ1876፣ ሬዲዮ በ1895 እንዲሁም ኮምፒውተር በ1946 ተፈልስፎ ነበር። በመጨረሻም በ1971 ማይክሮፕሮሰሰር በመፈልሰፉ ሞባይል ስልክ ሊሠራ ቻለ። ይሁን እንጂ የተራቀቁ መሣሪያዎችን በመጠቀም መነጋገር መቻል በእርግጥ አዲስ ነገር ነው? ብለን እንጠይቅ ይሆናል።
የሰው ድምፅ አብዛኛውን ጊዜ ብዙም ግምት የማይሰጠው መነጋገሪያ መሣሪያ ነው። በአንጎልህ ውስጥ በሚገኘው ሞተር ኮርቴክስ ውስጥ ካሉት በቢሊዮን የሚቆጠሩ ኒውሮኖች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ለመነጋገር የሚያስችሉህን የአካል ክፍሎች ይቆጣጠራሉ። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ምላስህ፣ ከንፈሮችህ፣ መንጋጋህ፣ ጉሮሮህና ደረትህ ውስብስብ የሆነ ሥራ ማከናወን የሚችሉት ወደ 100 በሚጠጉ ጡንቻዎች አማካኝነት ነው።
ጆሮህም የዚህ የመነጋገሪያ ሥርዓት አንድ ክፍል ነው። ጆሮ የድምፅ ሞገዶችን ወደ ኤሌክትሪክ ሞገድ የሚቀይር ሲሆን አንጎል ደግሞ ይህን ተቀብሎ ይተረጉማል። አንጎል የድምፆችን ዓይነት መለየት ስለሚችል ሰዎችን በድምፃቸው ብቻ ማወቅ ትችላለህ። በተጨማሪም አንጎል አንደኛው ጆሯችን የሰማው ድምፅ ወደ ሁለተኛው ጆሯችን ከመድረሱ በፊት ያለውን የጊዜ ልዩነት በአንድ ሴኮንድ ሚሊዮንኛ ክፋዮች መለካት ይችላል፤ በመሆኑም ድምፅ ከየት አቅጣጫ እንደመጣ በትክክል ማወቅ ይችላል። ብዙ ሰዎች እየተናገሩ ባሉበት ጊዜም እንኳ አንድን ሰው ብቻ ማዳመጥ እንድትችል ከሚረዱህ ችሎታዎች መካከል እነዚህ ሁለቱ ብቻ ናቸው።
ስለዚህ የደዋዩን ማንነት ማወቅ የሚያስችል የተራቀቀ ገመድ አልባ የመነጋገሪያ መሣሪያ አዲስ ነገር አይደለም። ይህ መሣሪያ በሕያዋን ፍጥረታት ዓለም ውስጥ ማለትም በተፈጥሮ ውስጥ ይገኛል።
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
1800
አስተማማኝ ባትሪ
1876
ስልክ
1971
ማይክሮፕሮሰሰር
1973
ሞባይል ስልክ የሠሩት ዶክተር ማርቲን ኩፐር
[ምንጭ]
ዶክተር ኩፐርና ሞባይል ስልክ፦ © Mark Berry
[በገጽ 2 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ገጽ 2 በቀኝ በኩል፣ ከፊት ወደኋላ፣ በቅደም ተከተል የተቀመጡት ፎቶዎች፦ ጉሊየልሞ ማርኮኒ ከሠራው ሬዲዮ ጋር፤ ቶማስ ኤዲሰንና አምፑል፤ የመገናኛ መሣሪያ የፈለሰፈው ግራንቪል ዉድስ፤ ዊልበርና ኦርቪል ራይት እና በ1903 የሠሩት ራይት ፍላየር የሚባል አውሮፕላን