በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በተወሰነ መጠን ነፃነት መፈለግ ስህተት ነው?

በተወሰነ መጠን ነፃነት መፈለግ ስህተት ነው?

የወጣቶች ጥያቄ

በተወሰነ መጠን ነፃነት መፈለግ ስህተት ነው?

የሚከተሉት ሁኔታዎች ቢያጋጥሙህ ልትሰጠው በምትችለው ምላሽ ላይ አድርግ።

1. ያለኸው መኝታ ቤትህ ውስጥ ነው እንበል፤ ወንድምህ ወይም እህትህ ሳያንኳኩ በሩን በርግደው ገቡ።

○ ‘ምንም ችግር የለውም፤ . . . እኔም እነሱ ክፍል ስገባ እንዲሁ አደርጋለሁ።’

○ ‘ይሄማ በጣም ያናድዳል! ልብሴን እየቀየርኩ ቢሆን ኖሮስ?’

2. ከጓደኛህ ጋር በስልክ እያወራህ ነው እንበል፤ እናትህ በቅርብ ርቀት ላይ ሆና የምትናገረውን እያዳመጠች ነው።

○ ‘ምንም ችግር የለውም፤ . . . ከእሷ የምደብቀው ምንም ነገር የለኝም።’

○ ‘ይሄማ በጣም ይደብራል! ፖሊስ እንደሆነችብኝ ይሰማኛል!’

3. ቤት እንደደረስህ ሁለቱም ወላጆችህ በጥያቄ ያዋክቡህ ጀመር። “የት ሄደህ ነበር? ምን ስትሠራ ነበር? ከማን ጋር ነበርክ?”

○ ‘ምንም ችግር የለውም፤ . . . እንዲያውም አብዛኛውን ጊዜ ሳይጠይቁኝ ነው ሁሉንም ነገር የምነግራቸው።’

○ ‘በጣም ያበሳጨኛል! ወላጆቼ ጨርሶ አያምኑኝም ማለት ነው!’

ንሽ እያለህ ነፃነት ማግኘት ያን ያህል የሚያሳስብህ ነገር አልነበረም። ታናናሾችህ የክፍልህን በር በርግደው ቢገቡ ምንም አይመስልህ ይሆናል። ወላጆችህ አንድ ነገር ሲጠይቁህ ምንም ቅር ሳይልህ መልስ ትሰጥ ነበር። በዚያን ጊዜ ልክ ተከፍቶ እንደተቀመጠ መጽሐፍ በውስጥህ ያለውን ሐሳብ ማንበብ ቀላል ነበር። አሁን ግን መጽሐፉን ለመክደን በሌላ አባባል ሰዎች ስለ አንተ ሁሉንም ነገር እንዳያውቁ ለማድረግ የምትፈልግበት ጊዜ ሊኖር ይችላል። “የተወሰኑ ነገሮችን ሰዎች ባያውቁብኝ ደስ ይለኛል” በማለት የ14 ዓመቱ ኮሪ * ይናገራል።

አሁን በድንገት ድብቅ መሆን የጀመርከው ለምን ይሆን? ይህ የሆነበት አንዱ ምክንያት እያደግህ በመሆኑ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በጉርምስና ዕድሜ በሰውነት ላይ የሚከሰቱት ለውጦች ስለ ቁመናህ ከመጠን በላይ እንድትጨነቅ ሊያደርጉህ ይችላሉ፤ ሌላው ቀርቶ በፊት ምንም የማይመስልህ የነበረው የቁመናህ ነገር አሁን ከቤተሰብህ ጋር ስትሆን እንኳ ያሳፍርህ ይሆናል። በተጨማሪም እያደግህ ስትሄድ ከወትሮው በተለየ በአንዳንድ ነገሮች ላይ ለብቻህ ሆነህ ማሰብ እንደሚያስፈልግህ ይሰማህ ይሆናል። ይህ ደግሞ “ልባም” እየሆንክ ወይም የማመዛዘን ችሎታ እያዳበርክ እንደሆነ የሚያሳይ ምልክት ነው፤ መጽሐፍ ቅዱስ ወጣቶች ይህን ባሕርይ እንዲያዳብሩ ያበረታታል። (ምሳሌ 1:1, 4፤ ዘዳግም 32:29) ኢየሱስም እንኳ በጥልቅ ለማሰብና ለማሰላሰል “ገለል ወዳለ ስፍራ” ሄዶ ነበር።—ማቴዎስ 14:13

እርግጥ ነው፣ አሁን ያለኸው በወላጆችህ ሥር ስለሆነ እነሱ በሕይወትህ ውስጥ እየተከናወኑ ያሉትን ነገሮች የማወቅ መብት አላቸው። (ኤፌሶን 6:1) ይሁን እንጂ እነሱ ስለ አንተ ማወቅ የሚያስፈልጋቸው መሆኑ አንተ ትልቅ ሰው ለመሆን ካለህ ፍላጎት ጋር ስለማይጣጣም በመካከላችሁ ግጭት ሊፈጠር ይችላል። ታዲያ ይህን ተፈታታኝ ሁኔታ እንዴት ልትወጣው ትችላለህ? ችግሮች ሊነሱ የሚችሉባቸውን ሁለት አቅጣጫዎች እስቲ እንመልከት።

ለብቻህ መሆን ስትፈልግ

ለብቻህ መሆን የምትፈልግባቸው በርካታ ተገቢ ምክንያቶች አሉ። ምናልባት “ትንሽ አረፍ” ለማለት ፈልገህ ይሆናል። (ማርቆስ 6:31) ወይም ደግሞ ኢየሱስ “ስትጸልይ ወደ ክፍልህ ግባ፤ በርህንም ዘግተህ በስውር ወዳለው አባትህ ጸልይ” በማለት ለደቀ መዛሙርቱ የሰጠውን ምክር መከተል ፈልገህ ሊሆን ይችላል። (ማቴዎስ 6:6፤ ማርቆስ 1:35) ችግሩ የክፍልህን በር (የራስህ ክፍል ካለህ) ስትዘጋው ወላጆችህ እየጸለይክ መሆኑን ላያስቡ ይችላሉ! እህቶችህና ወንድሞችህ ደግሞ ለብቻህ መሆን መፈለግህን ላይረዱልህ ይችላሉ።

ማድረግ የምትችለው ነገር። በዚህ ጉዳይ ላይ ከቤተሰብህ ጋር በመነታረክ መኝታ ክፍልህን የጦር ሜዳ ከማድረግ ይልቅ የሚከተሉትን ነጥቦች ተግባራዊ አድርግ።

ወንድሞችህንና እህቶችህን በተመለከተ፣ ለብቻህ መሆን በምትፈልግባቸው አንዳንድ ጊዜያት እንዳይረብሹህ የተወሰኑ ምክንያታዊ ደንቦችን ለማውጣት ሞክር። ካስፈለገ በዚህ ረገድ ወላጆችህ እንዲረዱህ ጠይቃቸው።

ከወላጆችህ ጋር በተያያዘ ደግሞ የእነሱን አመለካከት ለመረዳት ጥረት አድርግ። “ወላጆቼ የማደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች የሚከታተሉኝ ጊዜ አለ” በማለት የ16 ዓመቷ ሬቤካ ትናገራለች። “እውነቱን ለመናገር እኔም በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች ቢኖሩኝ፣ በተለይ ወጣቶች በዛሬው ጊዜ ከሚያጋጥሟቸው ተፈታታኝ ሁኔታዎች አንጻር የልጆቼን እንቅስቃሴ መከታተሌ አይቀርም ነበር!” አንተም እንደ ሬቤካ ወላጆችህ የአንተ ሁኔታ የሚያሳስባቸው ለምን እንደሆነ ማስተዋል ትችላለህ?—ምሳሌ 13:15

እንደሚከተለው በማለት ራስህን በሐቀኝነት መርምር፦ ‘ወላጆቼ በር ዘግቼ ለብቻዬ በምሆንበት ጊዜ መጥፎ ነገር ይሠራል ብለው እንዲጠረጥሩ የሚያደርጋቸው ምን የፈጸምኩት ነገር አለ? ወላጆቼ በሆነ ዘዴ ተጠቅመው ስለ እኔ ለማወቅ እስኪገደዱ ድረስ በግል ሕይወቴ በጣም ድብቅ ነኝ?’ በአብዛኛው ለወላጆችህ ይበልጥ ግልጽ በሆንክላቸው መጠን እነሱም ጥርጣሬያቸው ይቀንሳል። *

ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች። ይህን ጉዳይ አንስቼ ከወላጆቼ ጋር ለመነጋገር እንዲህ እላቸዋለሁ፦

․․․․․

ጓደኛ ስትይዝ

በጉርምስና ዕድሜ ላይ ስትሆን ከቤተሰብህ ውጭ ጓደኛ ለመያዝ መፈለግህ ያለ ነገር ነው። ወላጆችህም ቢሆኑ ጓደኞችህ እነማን እንደሆኑና ከእነሱ ጋር ምን እንደምታደርግ ለማወቅ መፈለጋቸው ያለ ነገር ነው። ወላጅ እንደመሆናቸው መጠን ሊያደርጓቸው ከሚገቡት ነገሮች አንዱ ይህ ነው። አንተ ግን የወላጆችህ ጭንቀት ገደቡን ያለፈ ሊመስልህ ይችላል። የ16 ዓመቷ ኤሚ “በሞባይል ሳወራ ወይም ኢ-ሜይል ስላላክ ወላጆቼ ከማን ጋር እንደማወራ በየደቂቃው እየመጡ እንዲጠይቁኝ አልፈልግም፤ ነፃነት እንዲሰጡኝ እፈልጋለሁ” በማለት ትናገራለች።

ማድረግ የምትችለው ነገር። ከሌሎች ጋር የመሠረትከው ጓደኝነት በአንተና በወላጆችህ መካከል ክፍተት እንዲፈጥር ከመፍቀድ ይልቅ የሚከተሉትን ነጥቦች በተግባር ለማዋል ሞክር።

ጓደኞችህ እነማን እንደሆኑ ተናገር፤ እንዲሁም ከወላጆችህ ጋር አስተዋውቃቸው። ወላጆችህ፣ ጓደኞችህ እነማን እንደሆኑ ለማወቅ ሲሉ እንደ መርማሪ ፖሊስ እንዲከታተሉህ አትፈልግም አይደል? ታዲያ የጓደኞችህ ማንነት ሚስጥር ከሆነባቸው እንዲህ ከማድረግ ሌላ ምን ምርጫ ይኖራቸዋል? መርሳት የሌለብህ ነገር ደግሞ ወላጆችህ የጓደኛ ምርጫህ በአንተ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር የሚያውቁ መሆኑን ነው። (1 ቆሮንቶስ 15:33) ወላጆችህ ከማን ጋር እንደምትውል በግልጽ የሚያውቁ ከሆነ በጓደኛ ምርጫህ ረገድ ያለባቸው ጭንቀት ይቀንሳል።

ስለ ጉዳዩ ወላጆችህን በአክብሮት አነጋግራቸው። አለቦታቸው በአንተ ጉዳይ ጣልቃ እንደገቡ አድርገህ አትውቀሳቸው። ከዚህ ይልቅ እንዲህ ልትላቸው ትችላለህ፦ “ከጓደኞቼ ጋር የማወራውን ነገር ሁሉ ለመስማት እንደምትሞክሩና ስለ እኔ መጥፎ ግምት እንደምትይዙ ሆኖ ይሰማኛል። ከጓደኞቼ ጋር ምንም ነገር ማውራት አስቸጋሪ እየሆነብኝ ነው።” ምናልባትም ወላጆችህ ከጓደኞችህ ጋር ባለህ ግንኙነት ረገድ ተጨማሪ ነፃነት ሊሰጡህ ይችሉ ይሆናል።—ምሳሌ 16:23

እስቲ ራስህን በሐቀኝነት መርምር፦ የሚያሳስብህ ነፃነት የማግኘትህ ጉዳይ ነው ወይስ ለመደበቅ የምትፈልገው ነገር አለ? የ22 ዓመቷ ብሪትኒ እንዲህ ትላለች፦ “የምትኖሩት ከወላጆቻችሁ ጋር ከሆነና አንድ የሚያስጨንቃቸው ነገር ካለ ‘መጥፎ ነገር እያደረግሁ እስካልሆነ ድረስ ለምን እደብቃቸዋለሁ?’ ብላችሁ ልታስቡ ይገባል። በሌላ በኩል ግን የምታደርጉትን ነገር መደበቅ እንዳለባችሁ የሚሰማችሁ ከሆነ የሆነ ችግር አለ ማለት ነው።”

ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች። ይህን ጉዳይ አንስቼ ከወላጆቼ ጋር ለመነጋገር እንዲህ እላቸዋለሁ፦

․․․․․

ነፃነት ለማግኘት አንተ ራስህ ልትወስዳቸው የምትችላቸው እርምጃዎች

ነፃነት ከማግኘት ጋር በተያያዘ አንተን ለሚያሳስቡህ ጉዳዮች አንዳንድ የመፍትሔ ሐሳቦችን ለማፍለቅ የሚረዱህ ነጥቦች ከዚህ በታች ቀርበውልሃል።

እርምጃ 1፦ የሚያሳስብህን ጉዳይ ለይ።

የበለጠ ነፃነት ብታገኝ ደስ የሚልህ መቼ መቼ ነው?

․․․․․

እርምጃ 2፦ የወላጆችህን ስሜት ተረዳላቸው።

ወላጆችህን የሚያሳስባቸው ነገር ምን ይመስልሃል?

․․․․․

እርምጃ 3፦ መፍትሔ ፈልግ።

(ሀ) ለችግሩ መፈጠር ሳይታወቅህ አስተዋጽኦ አድርገህ ሊሆን ከሚችልባቸው መንገዶች ቢያንስ አንዱን ለማሰብ ሞክር፤ ከዚያም ከታች አስፍረው።

․․․․․

(ለ) ከላይ የጠቀስከውን ነገር ለማስተካከል ምን ልታደርግ ትችላለህ?

․․․․․

ሐ) ወላጆችህ ለሚያሳስብህ ነገር መፍትሔ እንዲሰጡህ የምትፈልገው በምን መንገድ ነው?

․․․․․

እርምጃ 4፦ ከወላጆችህ ጋር ተነጋገርበት።

ተገቢ የሆነ ጊዜ ምረጥና ከላይ በጻፍከው ጉዳይ ላይ ከወላጆችህ ጋር ተወያዩበት።

www.watchtower.org/ype በሚለው ድረ ገጽ ላይ “Young People Ask” በሚል ዓምድ ሥር ተጨማሪ ርዕሶችን ማግኘት ይቻላል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.13 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

^ አን.21 እንዲህ አድርገህም ወላጆችህ የማያምኑህ ከመሰለህ የሚሰማህን ነገር በእርጋታና በአክብሮት ንገራቸው። የሚያሳስባቸውን ነገር ሲናገሩ ልብ ብለህ አዳምጥ፤ እንዲሁም እንዲጠራጠሩህ የሚያደርግ ምንም ነገር አትሥራ።—ያዕቆብ 1:19

ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች

ወላጆችህ በሕይወትህ ውስጥ እየተከናወኑ ስላሉት ነገሮች የማወቅ መብት አላቸው የምንለው ለምንድን ነው?

ከወላጆችህ ጋር ሐሳብ የመለዋወጥ ችሎታ ለማዳበር ጥረት ማድረግህ የኋላ ኋላ በሕይወትህ ውስጥ ከሌሎች ሰዎች ጋር ሐሳብ ለመለዋወጥ ሊረዳህ የሚችለው እንዴት ነው?

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

እኩዮችህ የሰጡት አስተያየት

“ወጣቶች ለወላጆቻቸው ግልጽ ቢሆኑ ወላጆቻቸውም በልጆቻቸው ሕይወት ውስጥ ምን እየተፈጸመ እንዳለ ለማወቅ ሲሉ የኢ-ሜይልና የስልክ መልእክቶቻቸውን ለማንበብ ላይነሳሱ ይችላሉ።”

“ወላጆቼ የኢ-ሜይል መልእክቶቼን ቢያነቡ አልናደድም። አንድ አሠሪ የሠራተኛውን የኢ-ሜይል መልእክት የማንበብ መብት ካለው ወላጆችም የልጆቻቸውን ኢ-ሜይል ማንበብ የማይችሉበት ምን ምክንያት አለ?”

“ወላጆቻችሁ በእናንተ ላይ ምንም ዓይነት ክፉ ነገር እንዲደርስ ስለማይፈልጉ አንዳንድ ጊዜ የሚያደርጉት ነገር ነፃነት እንዳሳጧችሁ እንዲሰማችሁ ሊያደርጋችሁ ይችላል። ትክክል እንዳልሆኑ ይሰማችሁ ይሆናል። እውነቱን ለመናገር ግን፣ እኔም ወላጅ ብሆን ኖሮ እንዲሁ የማደርግ ይመስለኛል።”

[ሥዕሎች]

ኤደን

ኬቪን

አላና

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ለወላጆች የቀረበ ሐሳብ

ወንድ ልጃችሁ መኝታ ክፍሉ ውስጥ ነው፤ በሩም ዝግ ነው። ሳታንኳኩ ዘው ብላችሁ ትገባላችሁ?

ሴት ልጃችሁ ትምህርት ቤት ለመሄድ ስትጣደፍ ሞባይሏን ረስታ ወጥታለች። ስልኳን አንስታችሁ ከሌሎች ጋር የተጻጻፈቻቸውን መልእክቶች ታነባላችሁ?

ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ መስጠት ቀላል አይደለም። በአንድ በኩል፣ በጉርምስና ዕድሜ ላይ በሚገኙት ልጆቻችሁ ሕይወት ውስጥ ምን እየተፈጸመ እንዳለ የማወቅ መብትም ሆነ ልጆቻችሁን ከጉዳት የመጠበቅ ግዴታ አለባችሁ። በሌላ በኩል ደግሞ ተጠራጣሪ በመሆን እያንዳንዱን የልጆቻችሁን እንቅስቃሴ ለማወቅ ሁልጊዜ መግቢያ መውጪያቸውን ልትከታተሉ አትችሉም። ታዲያ በዚህ ረገድ ሚዛናችሁን መጠበቅ የምትችሉት እንዴት ነው?

አንደኛ፣ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኝ ልጅ የተወሰነ ነፃነት ለማግኘት የሚፈልገው ሁልጊዜ መጥፎ ነገር ሊያደርግ አስቦ እንዳልሆነ ተገንዘቡ። አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ ያለው ፍላጎት ከእድገት ጋር ተያይዞ የሚመጣ ነገር ነው። በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች፣ ነፃነት ማግኘታቸው በራሳቸው ጓደኝነት መመሥረት እንደሚችሉ ራሳቸውን ለመፈተን እንዲሁም ችግር ሲያጋጥማቸው ‘የማሰብ ችሎታቸውን’ ተጠቅመው መፍትሔውን ለመፈለግ ይረዳቸዋል(ሮም 12:1, 2) በተጨማሪም በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች ነፃነት ማግኘታቸው የማመዛዘን ችሎታ እንዲያዳብሩ ይረዳቸዋል፤ ይህ ደግሞ ትልቅ ሲሆኑ ኃላፊነት የሚሰማቸው ሰዎች እንዲሆኑ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል። (1 ቆሮንቶስ 13:11) የማመዛዘን ችሎታ ማዳበራቸው አስቸጋሪ ለሆኑ ጥያቄዎች መልስ ከመስጠታቸው በፊት ለማሰላሰልም አጋጣሚ ይሰጣቸዋል።—ምሳሌ 15:28

ሁለተኛ፣ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኘውን ልጃችሁን በጥቃቅኗ ጉዳይ ሁሉ ለመቆጣጠር መሞከር ቅሬታ እንዲያድርበትና እንዲያምፅ ሊያደርግ እንደሚችል ተገንዘቡ። (ኤፌሶን 6:4፤ ቆላስይስ 3:21) ታዲያ ይህ ሲባል ልጃችሁን መቆጣጠሩን እርግፍ አድርጋችሁ መተው አለባችሁ ማለት ነው? አይደለም፤ ምክንያቱም ልጃችሁ ቢጎረምስም አሁንም ወላጆቹ ናችሁ። ይሁን እንጂ ግባችሁ፣ ልጃችሁ የሠለጠነ ሕሊና እንዲኖረው መርዳት ይሁን። (ዘዳግም 6:6, 7፤ ምሳሌ 22:6) በመጨረሻም፣ ለልጃችሁ አስፈላጊውን ምክር መስጠት በድብቅ ከመከታተል የበለጠ ውጤታማ መሆኑን ተረዱ።

ሦስተኛ፣ ጉዳዩን በጉርምስና ዕድሜ ላይ ከሚገኘው ልጃችሁ ጋር ተወያዩበት። የሚያሳስቡትን ነገሮች ሲነግራችሁ አዳምጡት። አንዳንድ ጊዜ ልትፈቅዱለት የምትችሏቸው ነገሮች ይኖሩ ይሆን? (ፊልጵስዩስ 4:5) ልጃችሁ የጣላችሁበትን እምነት እስካላጎደለ ድረስ መጠነኛ የሆነ ነፃነት እንደምትሰጡት እንዲገነዘብ አድርጉ። አለመታዘዝ የሚያስከትለውን ውጤት ግለጹለት፤ እንዲሁም አስፈላጊ ከሆነ ቅጣቱን አስፈጽሙ። በአንድ ነገር እርግጠኞች ሁኑ፦ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኘውን ልጃችሁን የመንከባከብ ኃላፊነታችሁን ችላ ሳትሉ የተወሰነ ነፃነት ልትሰጡት ትችላላችሁ።

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መታመን ከደሞዝ ጋር ይመሳሰላል፤ ሁለቱንም ለማግኘት ጥረት ይጠይቃል