በፍጥነት የሚሰናዳ ምግብ ለነፍሳት
በፍጥነት የሚሰናዳ ምግብ ለነፍሳት
● ነፍሳት ከፍተኛ ካሎሪ ያላቸውን በቀላሉ የሚገኙ ምግቦች መመገብ ይወዳሉ። እንዲህ ዓይነት ምግብ የሚገኝበት አንዱ ምቹ ስፍራ የአበቦች መካከለኛው ክፍል ነው። በፍጥነት የሚዘጋጁ ምግቦችን የሚያቀርቡ በርካታ ድርጅቶች እንደሚያደርጉት ሁሉ አበቦችም ደማቅ በሆነው ቀለማቸው ነፍሳትን ይማርካሉ። ነፍሳት በአበቦች ላይ እንዳረፉ የአበባውን ዱቄት በአበባው ማር እያወራረዱ መመገብ ይጀምራሉ።
ነፍሳት በተለይ ሌሊት በርዷቸው ካደሩ ሰውነታቸው እስርስር ይላል። ስለዚህ እነዚህ ደመ ቀዝቃዛ ፍጥረታት የወትሮውን እንቅስቃሴያቸውን ለመቀጠል ከፀሐይ የሚገኘው ሙቀት ያስፈልጋቸዋል። ብዙ አበቦች ለነፍሳቱ የተሟላ መስተንግዶ ያደርጉላቸዋል፤ በሌላ አባባል ለሰውነት ገንቢ የሆነ ምግብና ፀሐይ የሚሞቁበት ቦታ ያቀርቡላቸዋል። እስቲ አንድን የተለመደ ክንውን እንደ ምሳሌ እንመልከት።
ኦክሴይ ዴይዚ የሚባለው አበባ በአብዛኞቹ የአውሮፓና የሰሜን አሜሪካ ክፍሎች በብዛት የሚገኝ ተክል ነው። ይህ አበባ ሲታይ የተለየ ነገር ያለው ባይመስልም ጊዜ ወስደህ ብትመለከተው ብዙ እንቅስቃሴዎች እንደሚካሄዱበት ልታስተውል ትችላለህ። ይህ የዴይዚ አበባ ዝርያ፣ ነፍሳት የዕለቱን እንቅስቃሴያቸውን ከመጀመራቸው በፊት ጎራ የሚሉበት ተስማሚ ቦታ ነው። ነጭ ቀለም ያላቸው የአበባው ክፍሎች የፀሐይዋን ሙቀት የሚያንፀባርቁ ሲሆን ቢጫ ቀለም ያለው የአበቦቹ መካከለኛ ክፍል ደግሞ የሰበሰበውን የፀሐይ ሙቀት ለነፍሳቱ ስለሚያካፍላቸው ምቹ ማረፊያ ስፍራ ይሆንላቸዋል። *
በአበቦቹ መሃል ላይ የሚገኘው የአበባ ዱቄትና የአበባ ማር ለብዙ ነፍሳት ዕድገት የሚጠቅም ገንቢ ምግብ በብዛት የሚገኝበት መሆኑ ነፍሳቱ ወደ ዴይዚ አበባ መምጣትን ይበልጥ አስደሳች ያደርግላቸዋል። ነፍሳት ፀሐይ እየሞቁ ጥሩ ቁርስ ከሚመገቡበት ከዚህ የተሻለ ቦታ የት ሊያገኙ ይችላሉ?
በመሆኑም ቀኑን ሙሉ የተለያዩ ነፍሳት ወደ ኦክሴይ ዴይዚ አበቦች ሲጎርፉ ይውላሉ። ከእነዚህም መሃል ጥንዚዛዎችን፣ በቀለማት ያሸበረቁ ቢራቢሮዎችን፣ ሺልድ ባግስ የሚባሉ ነፍሳትን፣ ፌንጣዎችን እንዲሁም ዝንቦችን ጨምሮ የተለያዩ ትንኞችን መመልከት ትችላለህ። እርግጥ ነው፣ አስተዋይ ካልሆንክ ለነፍሳት “በፍጥነት የሚሰናዳ ምግብ በሚያቀርቡት ድርጅቶች” ላይ የሚታየውን አስደናቂ እንቅስቃሴ ጭራሹንም ልብ ላትል ትችላለህ።
እንግዲያው በአካባቢህ የሚገኙትን የዴይዚ አበባዎች ስትመለከት ይህንን አስገራሚ ተፈጥሯዊ ክንውን ለማስተዋል ለምን ጥረት አታደርግም? እንዲህ ማድረግህ የእነዚህ ፍጥረታት ሁሉ ንድፍ አውጪ ለሆነው ፈጣሪ ያለህ አድናቆት እንዲጨምር ያደርጋል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.4 የሳይንስ ሊቃውንት በአንዳንድ አበቦች ላይ ያለው ሙቀት ከአካባቢው ሙቀት በብዙ ዲግሪዎች እንደሚበልጥ ደርሰውበታል።