በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ቴሌቪዥን

ቴሌቪዥን

ቴሌቪዥን

ሰዎች ድምፅ ማሰራጨት እንደቻሉ ወዲያውኑ ተንቀሳቃሽ ምስሎችንም ለማሰራጨት መመራመር ጀመሩ። ይህ ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ ለመረዳት በአሁኑ ጊዜ ቴሌቪዥን እንዴት እንደሚሠራ እንመልከት።

በመጀመሪያ የቴሌቪዥን ካሜራ አንድን ትዕይንት፣ ምስሎችን “ወደሚያነብ” መሣሪያ እንዲገባ ያደርጋል፤ ይህም አንተ የታተሙ ገጾችን እንደምታነበው ማለት ነው። ይሁን እንጂ መሣሪያው ምስሎቹን የሚያነበው፣ አንተ ቃላትን በምታነብበት መንገድ ሳይሆን በሥዕሉ ውስጥ የሚገኙ ነጥቦችን (ወይም ፒክስል) በማንበብ ነው። መሣሪያው የተመለከተውን ምስል ወደ ሌላ ቦታ ማሰራጨት እንዲቻል ወደ ኤሌክትሮኒክ ቪዲዮ መረጃ ይለውጠዋል። በኋላም የመቀበያው መሣሪያ የደረሰውን መረጃ ወደ ተንቀሳቃሽ ምስል ይቀይራል።

የቴሌቪዥንን አሠራር ያሳየው የመጀመሪያው ሰው ስኮትላንዳዊው ጆን ሎጊ ቤርድ እንደሆነ ይታመናል። በጤና እክል ምክንያት የኤሌክትሪክ ምሕንድስና ሥራውን ካቆመ በኋላ ትኩረቱን ከወጣትነቱ ጀምሮ ቀልቡን ስቦት ወደነበረ ጉዳይ አዞረ። ይህም ተንቀሳቃሽ ምስሎችን የሚያስተላልፍ መሣሪያ መሥራት ነበር።

የቤርድ የቴሌቪዥን ካሜራ መጀመሪያ ላይ፣ በጥቅልል መልክ የተዘጋጀ ወደ 30 የሚጠጉ ቀዳዳዎች ያሉት ክብ መሣሪያ (ዲስክ) ነበረው። ዲስኩ በሚሽከረከርበት ጊዜ ቀዳዳዎቹ ተከታትለው የሚመጡትን ምስሎች በማንበብ ብርሃኑ፣ የብርሃን ጨረርን ወደ ኤሌክትሪክ ኃይል ሊለውጥ በሚችል ባትሪ ላይ እንዲያርፍ ያደርጋሉ። ባትሪው ደግሞ ወደ መቀበያ መሣሪያ የሚተላለፍ የቪዲዮ መረጃ ያስገኛል። በመቀበያ መሣሪያው ውስጥ መረጃው እንዲጎላ ይደረግና ተመሳሳይ በሆነ አንድ የሚሽከረከር ዲስክ በስተጀርባ፣ ተለዋዋጭ መጠን ያለው ብርሃን እንዲበራ በሚደረግበት ጊዜ የተቀረጸው ምስል ይታያል። ትልቁ ችግር ዲስኮቹ ተቀናጅተው እንዲሠሩ ማድረግ ነበር። ቤርድ በዚህ ፕሮጀክት ላይ በሚሠራበት ወቅት የሚተዳደረው ጫማ በመጥረግ ነበር።

ቤርድ ጥቅምት 2, 1925 የመጀመሪያውን የቴሌቪዥን ምስል ከነበረበት ቤት አንደኛው ጫፍ ወደ ሌላኛው ጫፍ አስተላለፈ። አምስት ሽልንግ ተከፍሎት ለመጀመሪያ ጊዜ በቴሌቪዥን የታየው፣ በታችኛው ፎቅ ላይ ተላላኪ ሆኖ የሚሠራ አንድ በሁኔታው የተደናገጠ ወጣት ነበር። በ1928 ቤርድ የመጀመሪያዎቹን የቴሌቪዥን ምስሎች ከአትላንቲክ ማዶ ማስተላለፍ ቻለ። ዓይን አፋር የሆነው ስኮትላንዳዊ ጆን ቤርድ ኒው ዮርክ ሲደርስ ሙሉ የሙዚቃ ጓድ እሱን ለመቀበል እየተጠባበቀ መሆኑን ሲመለከት የሚገባበት ጠፋው። ቤርድ ታዋቂ ሰው ለመሆን በቃ። ይሁን እንጂ ተንቀሳቃሽ ምስል ለማስተላለፍ እሱ የመጀመሪያ ነበር?