አውቶማቲክ አቅጣጫ ጠቋሚ መሣሪያ
አውቶማቲክ አቅጣጫ ጠቋሚ መሣሪያ
በማታውቀው ከተማ ውስጥ አንድን ቦታ ፈልጎ ማግኘት ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ ታውቅ ይሆናል። ታዲያ አንድ በባሕር ላይ የሚጓዝ ሰው ምንም ዓይነት ምልክት በሌለው ውቅያኖስ ላይ የሚጓዝበትን መንገድ የሚያውቀው እንዴት ነው? ተጓዡ ከመዳረሻ ቦታው አንጻር የት ቦታ ላይ እንዳለ ካላወቀ በስተቀር ኮምፓስ ወይም የአቅጣጫ ጠቋሚ መሣሪያ ብቻውን ምንም ሊጠቅመው አይችልም። አንግል ለመለካት የሚያስችል ሴክስታንት የተባለ መሣሪያና ለባሕር ላይ ጉዞ የሚያገለግል ክሮኖሜትር የሚባል ሰዓት በ1730ዎቹ እስኪፈለሰፉ ድረስ የባሕር ላይ ተጓዦች የሚገኙበትን ቦታ በትክክል ማወቅና የሚሄዱበትን መስመር ካርታ ላይ ማመልከት አይችሉም ነበር። መሣሪያዎቹ ከተፈለሰፉ በኋላም ቢሆን አቅጣጫን ማወቅ ብዙ ሰዓት የሚፈጅ ስሌት ይጠይቅ ነበር።
በዛሬው ጊዜ በብዙ አገሮች የሚኖሩ አሽከርካሪዎች ከግሎባል ፖዚሽኒንግ ሲስተም (GPS) ጋር ግንኙነት ባላቸው በጣም ውድ ናቸው በማይባሉ መሣሪያዎች በመጠቀም መንገዳቸውን ማወቅ ይችላሉ። የሚያስፈልግህ ነገር ቢኖር የምትሄድበትን ቦታ መሣሪያው ላይ መሙላት ብቻ ነው። መሣሪያው ያለህበትን ትክክለኛ ቦታ ሰሌዳው ላይ ማመልከት ይችላል። ከዚያም መድረስ የምትፈልግበትን ቦታ ያመለክትሃል። ይህ መሣሪያ የሚሠራው እንዴት ነው?
ጉዞ አመልካች የሳተላይት መሣሪያዎች ሳተላይቱ የሚገኝበትን ቦታና ሰዓቱን ለአንድ ቢሊዮንኛ ሴኮንድ እንኳ ዝንፍ በማይል ትክክለኛነት በሚያስተላልፉ 30 የሚያክሉ ሳተላይቶች ላይ የተመኩ ናቸው። የያዝከው መሣሪያ ከጥቂት ሳተላይቶች ጋር ከተገናኘ በኋላ ከሳተላይቱ የተላለፈው መረጃ መሣሪያው ጋር እስኪደርስ ድረስ የሚፈጀውን ጊዜ በትክክል ይለካል። ይህን መረጃ መሠረት በማድረግ የምትገኝበትን ቦታ ማወቅ ይችላል። ይህ ስሌት ምን ያህል ውስብስብ እንደሆነ መገመት ትችላለህ? በጥቂት ሴኮንዶች ውስጥ የሦስት ሳተላይቶችን ርቀት ያሰላል፤ እነዚህ ሦስት ሳተላይቶች በሺዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ርቀው የሚገኙ ከመሆኑም በላይ በተለያየ አቅጣጫ በሴኮንድ ብዙ ኪሎ ሜትሮች የሚጓዙ ናቸው።
ጂፒኤስን በ1960ዎቹ መጀመሪያ የፈለሰፉት ፕሮፌሰር ብራድፎርድ ፓርኪንሰን እና ኢቫን ጌቲንግ ናቸው። በመጀመሪያ የተፈለሰፈው ለወታደራዊ አገልግሎት ቢሆንም በኋላ ላይ ግን ለሕዝብ አገልግሎት እንዲውል ተደርጎ በ1996 ሙሉ በሙሉ አገልግሎት መስጠት ጀመረ። የጂፒኤስ መቀበያ በእርግጥም በጣም አስደናቂ የሆነ የኮምፒውተር ቴክኖሎጂ ውጤት ነው። ይሁን እንጂ ጂፒኤስ የመጀመሪያው አውቶማቲክ አቅጣጫ ጠቋሚ መሣሪያ ነው?
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
ሉል፦ Based on NASA photo