በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከተፈጥሮ ምን እንማራለን?

ከተፈጥሮ ምን እንማራለን?

ከተፈጥሮ ምን እንማራለን?

“እግዚአብሔር ሆይ፤ ሥራህ እንዴት ብዙ ነው! ሁሉን በጥበብ ሠራህ።” —መዝሙር 104:24

ብዙ ሰዎች የሕያዋን ፍጥረታት ንድፍ ምንጭ ማን እንደሆነ ለማመልከት “ተፈጥሮ” የሚለውን ቃል ይጠቀማሉ። ለምሳሌ፣ ሳይንቲፊክ አሜሪካን የተባለው መጽሔት በመጋቢት 2003 እትሙ ላይ “ተፈጥሮ ንድፍ ካወጣላቸው የአካል መሸፈኛዎች ሁሉ የላባን ያህል ዓይነቱ የበዛና እጅግ ሚስጥራዊ የሆነ ነገር የለም” ብሏል። የዚህ መጽሔት ፀሐፊ፣ ተፈጥሮን እንደ አንድ ኃይል አድርገው ቢመለከቱትም ለላባዎቹ “ንድፍ” ያወጣው ተፈጥሮ እንደሆነ ተናግረዋል። ታዲያ አንድ ኃይል ለነገሮች ንድፍ ሊያወጣ ይችላል?

“ንድፍ” ማውጣት ሲባል “አንድን ዓላማ ወይም ሐሳብ በአእምሮ ይዞ (አንድን ነገር) ማቀድ” ማለት ነው። (ዘ ኒው ኦክስፎርድ ዲክሽነሪ ኦቭ ኢንግሊሽ) ንድፍ ማውጣትና መፈልሰፍ የሚችለው አካል ያለው ነገር ብቻ ነው። ነገሮችን የሚፈለስፉ ሰዎች ስም እንዳላቸው ሁሉ ፈጣሪም ስም አለው። ለተፈጥሮ ንድፍ ያወጣው ይሖዋ ነው። “በምድር ሁሉ ላይ ልዑል” የሆነውና ‘ሁሉን ነገር የፈጠረው’ እሱ ብቻ ነው።—መዝሙር 83:18፤ ራእይ 4:11

ከፍጥረት ምን መማር እንችላለን? ከፍጥረት የምናገኘው ከሁሉ የላቀው ትምህርት ስለ ይሖዋ ብሎም ጥበብን ጨምሮ አስደናቂ ስለሆኑ ባሕርያቱ ነው። የአምላክ ቃል “የማይታዩት ባሕርያቱ ይኸውም ዘላለማዊ ኃይሉና አምላክነቱ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ በግልጽ ይታያሉ፤ ምክንያቱም ባሕርያቱን ከተሠሩት ነገሮች ማስተዋል ይቻላል” ይላል። (ሮም 1:20) የአምላክ ጥበብ ከእኛ በእጅጉ እንደሚልቅ ከተፈጥሮ እንማራለን። አምላክ ነገሮችን ከፈለሰፉ ሰዎች በላቀ ሁኔታ ንድፍ የሚያወጣ ከሆነ ከሰብዓዊ መካሪዎች የተሻለ ምክር ሊሰጠን ይችላል ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ አይሆንም?

አምላክ በዋነኝነት ምክር የሚሰጠን በተፈጥሮ ብቻ ሳይሆን በጽሑፍ በሰፈረው ቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ነው። እርስ በርስ ሐሳብ ለመለዋወጥ የሚያስችሉ የአካል ክፍሎችን ንድፍ ያወጣው አምላክ፣ ከእኛ ጋር ሊነጋገር የሚፈልግ ይመስልሃል? ይፈልጋል ብሎ ማሰቡ ምክንያታዊ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ቅዱስ መጽሐፉ ሁሉ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ ነው” ይላል።—2 ጢሞቴዎስ 3:16

ነገሮችን ስለፈለሰፉ ሰዎች ማወቅ አስደሳች ከሆነልህ ስለ ፈጣሪ ማወቅ ይበልጥ አስደሳች እንደሚሆንልህ ምንም ጥርጥር የለውም። ለምሳሌ ያህል፣ እንደሚከተሉት ላሉ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት ትፈልግ ይሆናል፦ መከራና ሥቃይ የሚደርስብንና በኋላም የምንሞተው ለምንድን ነው? አምላክ ለሰዎች የነበረው ዓላማ ይህ ነው? ካልሆነስ አምላክ መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው?

የሳይንስ ሊቃውንት ተቀበሉም አልተቀበሉ የፈለሰፏቸውን ነገሮች ንድፍ የወሰዱት ይሖዋ ከፈጠራቸው ነገሮች ነው። አንተም ከፈጣሪያችን ብዙ ትምህርት ልታገኝ ትችላለህ። ለምሳሌ፣ ጠንካራ መሠረት ያለው ትዳር መመሥረት የሚቻልበትን መንገድ፣ ልጆችን በጥሩ ሁኔታ ማሳደግ የሚቻልበትን ዘዴ፣ አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ ምን እንደሆነ እንዲሁም ሕይወትህ ትርጉም ያለው እንዲሆን የሚያስችሉ በርካታ ነገሮችን መማር ትችላለህ። በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀው ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለው መጽሐፍ ከአምላክ ቃል ብዙ ጥቅም እንድታገኝ ያስችልሃል።