በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የእባብ አምልኮ—ጥንትና ዛሬ

የእባብ አምልኮ—ጥንትና ዛሬ

የእባብ አምልኮ—ጥንትና ዛሬ

የጥንት ግብፃውያን እንዲሁም ሚኖአን ተብለው የሚጠሩት የጥንቶቹ የቀርጤስ ነዋሪዎች እባቦችን ያመልኩ ነበር። አንዳንድ የጥንት እስራኤላውያንም ከናስ ለተቀረጸ የእባብ ምስል መሥዋዕት አቅርበው ነበር። ሌሎች እስራኤላውያን ደግሞ ‘በደረታቸው በሚሳቡ ፍጡራን’ ምስል ፊት የሚቃጠል መሥዋዕት ያቀርቡ ነበር።—ሕዝቅኤል 8:10-12፤ 2 ነገሥት 18:4

የእባብ አማልክትን ማምለክ በጥንቶቹ የሜክሲኮ ሕዝቦች ዘንድም በጣም የተለመደ ነበር። ማያ የሚባሉት ሕዝቦች እንደ ታላቅ አምላክ አድርገው ያመልኩት የነበረው ኢትሳምና የሚባለው ጣዖት አንዳንድ ጊዜ በእባብ ይወከል ነበር። ኬትሳልኮኣትል ማለትም “ባለ ላባው እባብ” የቶልቴክ ሕዝቦች የትምህርት፣ የባሕልና የፍልስፍና አምላክ ነበር። አዝቴክ የሚባሉ ሕዝቦችም ይህን ጣዖት የትምህርት አምላክ አድርገው ይመለከቱት የነበረ ከመሆኑም በላይ የሰዎች ፈጣሪ እንደሆነ አድርገው አምልኮታዊ ክብር ይሰጡት ነበር። አርኪኦሎኪኣ መኪካና (የሜክሲኮ አርኪኦሎጂ) የተባለው መጽሔት ይህ ጣዖት ያለውን በርካታ የሥራ ድርሻና ችሎታ አስመልክቶ ሲናገር “ይህ ባለ ላባው እባብ ምናልባትም ከማንኛውም ሌላ ጣዖት ይበልጥ ብዙ ትርጉም ይሰጠው ነበር” ብሏል።

የሜዞአሜሪካ ነዋሪዎች ለብዙ መቶ ዘመናት ባለ ላባውን እባብ አምልከው ነበር። ኮራ እና ሁቾል የሚባሉት የሜክሲኮ ሕዝቦች በአሁኑ ጊዜም እንኳ ይህን አምላክ ያመልካሉ። በአንዳንድ የበዓል ቀናት ሰዎች ራሳቸውን በላባ አስጊጠው የእባብ ዓይነት እንቅስቃሴ በማድረግ ይጨፍራሉ። ኪቼ የሚባሉት ሕዝቦች፣ የመራባት የአምልኮ ሥነ ሥርዓት በሚፈጽሙበት ጊዜ በሕይወት ያሉ እባቦችን ይዘው ይጨፍራሉ። በጓቲማላ የሚኖሩት ቾርቲ የሚባሉት የማያ ጎሣዎች ደግሞ አንድን ባለ ላባ እባብ ከአንዳንድ የካቶሊክ ቅዱሳን ጋር በማያያዝ አምልኮታዊ ክብር ይሰጡታል።

አሁን የሚነሳው ጥያቄ ‘እባቦችን ጨምሮ ሰውና እንስሳትን የፈጠረው አምላክ ለእባብ አማልክት የሚቀርበውን አምልኮ እንዴት ይመለከተዋል?’ የሚለው ነው።

አምላክ ለእባብ አምልኮ ያለው አመለካከት

ይሖዋ አምላክ ለጥንቱ የእስራኤል ሕዝብ የሚከተለውን ትእዛዝ ሰጥቶ ነበር፦ “በላይ በሰማይ ወይም በታች በምድር ካለው ወይም በውሃ ውስጥ ከሚኖሩት ነገሮች በማናቸውም ምስል ለራስህ ጣዖትን አታብጅ። አትስገድላቸው፤ አታምልካቸውም።”—ዘፀአት 20:4, 5

ይሖዋ ሕዝቦቹ እንደ እባብ ያሉ የእንስሳት ምስሎችን እንዳያመልኩ ከልክሏቸዋል። በመሆኑም የእሱን ሞገስ ማግኘት የሚፈልጉ ሁሉ እባቦችን ከማምለክ መራቅ እንዳለባቸው ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ አምላክ እባቦችን ማምለክ ጨምሮ የጣዖት አምልኮን የሚጠላው ለምንድን ነው? ምክንያቱ ግልጽ ነው፤ ለሰዎች፣ ለእባቦችና ሕይወት ላላቸው ነገሮች ሁሉ ሕይወት የሰጠው እሱ ስለሆነ ነው። ሁሉም የእሱ የእጅ ሥራዎች ስለሆኑ መመለክ የሚገባው አምላክ እንጂ እሱ የፈጠራቸው ነገሮች አይደሉም።

ይህን ለመረዳት አንድ ምሳሌ እንመልከት፤ አንድ መሐንዲስ ቤቶችን ገንብቶ በውስጡ እየኖሩ እንዲደሰቱበት ለአንዳንድ ሰዎች ሰጠ እንበል። እነዚህ ሰዎች ለመሐንዲሱ ሳይሆን ለቤቶቹ ምስጋናና ውዳሴ ቢያቀርቡ ምን ይሰማሃል? ይህ ሞኝነት አይሆንም? አልፎ ተርፎም ቤቶቹን ሠርቶ በልግስና የሰጣቸውን መሐንዲስ የሚያስቆጣ አይደለም? በተመሳሳይም የእንስሳትን ፈጣሪ ትቶ እንስሶቹን ማምለክ አምላክን የሚያስቆጣ ተግባር ነው።

ከዚህ በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው የአምላክን ሞገስ ለማግኘት የሚፈልጉ ሁሉ ሐዋርያው ዮሐንስ “ልጆቼ ሆይ፣ ራሳችሁን ከጣዖቶች ጠብቁ” በማለት የሰጠውን ማስጠንቀቂያ መከተል ይኖርባቸዋል።—1 ዮሐንስ 5:21

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

እባብ መያዝ የእውነተኛው አምልኮ ክፍል ሊሆን ይገባዋል?

በደቡባዊ ምሥራቅ ዩናይትድ ስቴትስ ያሉ በተአምር የሚያምኑ ጥቂት አብያተ ክርስቲያናት መርዛማ እባቦችን የመያዝ ልማድ አላቸው። አንዳንድ ሰዎች አንድን መርዛማ እባብ በትከሻቸው ላይ የሚያደርጉ ሲሆን ሌሎች ደግሞ ብዙ እባቦችን በአንድ ጊዜ አንስተው ይይዛሉ። ድንገት አንስቶ ማንቀሳቀስ እባቦቹን ስለሚያስደነግጣቸው ይናደፋሉ። ባለፉት ዓመታት በአምልኮ ሥነ ሥርዓታቸው ላይ እንዲህ ያለውን ልማድ የሚከተሉ አንዳንድ ሰዎች እንዲህ በማድረጋቸው ምክንያት በእባብ ተነድፈው ሞተዋል።

እባብ የሚይዙ ሰዎች ለዚህ ተግባራቸው መሠረት አድርገው የሚጠቅሱት ማርቆስ 16:17, 18ን ነው። እነዚህ ጥቅሶች “እባቦችን በእጃቸው ይይዛሉ” የሚል ሐሳብ አላቸው። ኪንግ ጄምስ ቨርሽን እና ሌሎች የጥንት ትርጉሞች እነዚህን ጥቅሶች የበኩረ ጽሑፉ ክፍል እንደሆኑ አድርገው ተርጉመዋቸዋል። ዘ ኒው ሪቫይዝድ ስታንዳርድ ቨርሽን፣ ዘ ኒው አሜሪካን ስታንዳርድ ባይብል እና ዘ ኒው ኪንግ ጀምስ ቨርሽን እባብን ስለመያዝ የሚናገሩት ጥቅሶች በአብዛኞቹ ጥንታዊ የማርቆስ ወንጌል ቅጂዎች ላይ እንዳልነበሩ ገልጸዋል።

የአምላክ ቃል፣ እባብን መያዝ ተቀባይነት ያለው የእውነተኛው አምልኮ ክፍል ነው ብሎ አያስተምርም። መጽሐፍ ቅዱስ “አምላክ ፍቅር ነው” ይላል። (1 ዮሐንስ 4:8) አፍቃሪው ፈጣሪያችን እውነተኛ አምላኪዎቹ እሱን ለማስደሰት ሲሉ አደገኛ የሆኑ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶችን እንዲፈጽሙ አይጠብቅባቸውም ቢባል አንተም ሳትስማማ አትቀርም። ልጁ ኢየሱስም “እናንተ የደከማችሁና ሸክም የከበዳችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም እረፍት እሰጣችኋለሁ” የሚል ግብዣ አቅርቧል። (ማቴዎስ 11:28, 29) እባቦችን መያዝ ምናልባትም በእባብ በመነደፍ ሊከተል የሚችለው ሥቃይና በሽታ አልፎ ተርፎም ሞት ይሖዋም ሆነ ኢየሱስ በተከታዮቻቸው ላይ እንዲደርስ የሚፈልጉት ነገር እንዳልሆነ ጥርጥር የለውም!

[ምንጭ]

REUTERS/Tami Chappell

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአዝቴክ ቤተ መቅደስ ግድግዳ ላይ የሚገኝ የባለ ላባው እባብ ጭንቅላት ቅርጽ

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኬትሳልኮኣትል የሚባለው የቶልቴክ ሕዝቦች የባለ ላባው እባብ አምላክ ውቅር ምስል

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ከላይ፦ REUTERS/Tami Chappell; ከታች፦ © Leonardo Díaz Romero/age fotostock