በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የኦዴሳ ዋሻዎች—መግቢያ መውጫው የሚያደናግር የመሬት ውስጥ መተላለፊያ

የኦዴሳ ዋሻዎች—መግቢያ መውጫው የሚያደናግር የመሬት ውስጥ መተላለፊያ

የኦዴሳ ዋሻዎች—መግቢያ መውጫው የሚያደናግር የመሬት ውስጥ መተላለፊያ

በአዲስ መልክ በተሠራ አንድ አፓርታማ ግድግዳ ላይ ስንጥቅ መታየት ጀመረ። የሕንፃው ባለቤት ይህን ሲመለከት “አሄሄ፣ እነዚያ ዋሻዎች ሕንፃችን እንዲያዘምም እያደረጉት ነው” በማለት በብስጭት ተናገረ።

በዚህ አካባቢ የውኃ ቧንቧ ሲፈነዳ ወይም መንገዶች ወደ ውስጥ ሲሰረጉዱ አሊያም ሌላ ማንኛውም ችግር ሲፈጠር የሚመካኘው በኦዴሳ ከተማ ሥር በሚገኙት ዋሻዎች ነው፤ በጥቁር ባሕር ዳርቻ ላይ የተቆረቆረችው ይህች ውብ ከተማ በዩክሬን ትገኛለች። መግቢያ መውጫቸው የሚያደናግረው የኦዴሳ ዋሻዎች ወደ 2,500 ኪሎ ሜትር የሚጠጋ ርዝመት እንዳላቸው የሚታሰብ ሲሆን ይህ የመሬት ውስጥ መተላለፊያ በዓለማችን ላይ ካሉት ዋሻዎች ሁሉ ትልቁ ሳይሆን አይቀርም።

‘ለመሆኑ እነዚህ ዋሻዎች የተፈጠሩት እንዴት ነው? ከበላያቸው በሚኖሩት ሰዎች ሕይወት ላይስ ምን ተጽዕኖ ያሳድራሉ?’ ብለን አሰብን። ዋሻዎቹን መጎብኘታችን ለጥያቄዎቻችን መልስ ለማግኘት አስችሎናል።

ከመሬት በታች ውስጥ ለውስጥ ያደረግነው ጉዞ

ለጉብኝት የሚወስደን አውቶቡስ ከኦዴሳ ባቡር ጣቢያ የተነሳው ተማሪዎችንና አገር ጎብኚዎችን አሳፍሮ ሲሆን ሁሉም በጉጉት ስሜት ተውጠው ነበር። በጉዞ ላይ ሳለን አስጎብኚያችን ስለ ዋሻዎቹ ታሪክ አንዳንድ መረጃዎችን ነገረችን።

አስጎብኚዋ ከሰጠችን ማብራሪያ እንደተረዳነው የዋሻዎቹ ቁፋሮ የተጀመረው በ1830ዎቹ ዓመታት ይመስላል፤ በወቅቱ የከተማዋ ነዋሪዎች በቀላሉና በርካሽ ዋጋ የሚገኙ የግንባታ ቁሳቁሶችን ይፈልጉ ነበር። ከተማዋ ከተቆረቆረችበት መሬት በታች ሰፊ ቦታ የሚሸፍን ቀላል ክብደት ያለውና ጠንካራ የሆነ ቢጫ የበሃ ድንጋይ መኖሩ ለግንባታው አመቺ ሆነላቸው። በዚህም የተነሳ በማደግ ላይ ለነበረችው ለኦዴሳ ከተማ ድንጋይ እየፈለጡ ማውጣት አትራፊ ንግድ ሆኖ ነበር። በዚህ መንገድ ድንጋዩ እየተፈለጠ ሲወጣ ዋሻዎቹ ዛሬ ያላቸውን ቅርጽ መያዝ ጀመሩ።

ሁሉም በፈለገው አቅጣጫ ቁፋሮውን ያካሂድ ስለነበር ብዙም ሳይቆይ ከከተማዋ ሥር መግቢያ መውጫው የሚያደናግር መተላለፊያ ተፈጠረ። ዋሻዎቹ የሚገኙት ከመሬት በታች ከ35 ሜትር የሚበልጥ ርቀት ላይ ነበር። እነዚህ መተላለፊያዎች ጥልቀታቸው የተለያየ በመሆኑ ከሥር ወይም ከላይ አንዱ በሌላው ላይ የሚያልፉ መንገዶች አሏቸው። ሰዎቹ በዋሻው ውስጥ የሚፈልጡት በሃ ድንጋይ ሲያልቅባቸው የጀመሩትን ጉድጓድ በመተው ሌሎች አዳዲስ ጉድጓዶችን ይቆፍሩ ነበር። ከጊዜ በኋላ እነዚህ እንደ ሸረሪት ድር የተጠላለፉ መተላለፊያ ጉድጓዶች ከከተማዋ ወጣ ብለው እስከሚገኙት አካባቢዎች ድረስ ዘልቀው ሄዱ።

የተወሰነ ርቀት ከተጓዝን በኋላ የተሳፈርንበት አውቶቡስ ከኦዴሳ በስተ ሰሜን ወደምትገኝ ኔሩባይስክ የምትባል አነስተኛ መንደር ደረሰ። ብዙም ሳይቆይ ወደ ዋሻው መግቢያ ደረስን፤ መግቢያው ግዙፍ በሆነ ብረት በር ተዘግቷል። “አሁን የምንገባው በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የሶቪየት የደፈጣ ተዋጊዎች ይኖሩበት ወደነበረ አካባቢ ነው። ቦታውን ስትጎበኙ እነዚያ ሰዎች በዚያን ጊዜ ኑሯቸው ምን ይመስል እንደነበረ ፍንጭ ይሰጣችኋል” በማለት አስጎብኚያችን ነገረችን። ስለ ዋሻዎች ጥናት የሚያካሂዱት አንድሪ ክራስኖዦን እንደገለጹት አንድ የደፈጣ ተዋጊዎች ቡድን እዚህ ዋሻ ውስጥ 13 ወራት አሳልፏል።

አስጎብኚያችን አክላም እንዲህ አለችን፦ “በተለያዩ ወቅቶች ሌሎች በርካታ ቡድኖችም በተለያዩ የዋሻው ክፍሎች ውስጥ ይኖሩ ነበር። ከእነዚህም መካከል ሽፍቶች፣ የባሕር ላይ ዘራፊዎችና የፖለቲካ ጥገኞች ይገኙበታል። በመሠረቱ ሁሉም በዋሻው ውስጥ ያሳለፉት ሕይወት ተመሳሳይ ነበር።”

ጨለምለም ወዳለው መተላለፊያ ገባን። “የደፈጣ ተዋጊዎቹ ይኖሩባቸው የነበሩት እነዚህ ዋሻዎች መደበቂያ ከመሆንም አልፈው በተቻለ መጠን ምቾት እንዲኖራቸው ተደርገው ተዘጋጅተው ነበር” በማለት አስጎብኚያችን ነገረችን። “በመዝናኛ ክፍሎቹ ውስጥ ወንዶች ሻማ አብርተው ዳማ፣ ቼዝ ወይም ዶሚኖ ይጫወቱ ነበር። የዋናውን ዋሻ ግድግዳ በመፈልፈል ለወንዶችና ለሴቶች የሚሆኑ ክፍሎች ይዘጋጁ ነበር። በእያንዳንዱ ክፍል ውስጥ ደግሞ ግድግዳውን በመቦርቦር እንደ መደርደሪያ ያለ መደብ ይሠራና የሣር ድርቆሽ ይጎዘጎዝበት ነበር። ይህም ለመኝታነት ያገለግላል። እንደ ሆስፒታል የሚጠቀሙበት ክፍል ደንበኛ አልጋዎች የነበሩት ሲሆን ቀዶ ሕክምናም ይደረግበት ነበር። ሴቶች ከቢጫ በሃ ድንጋይ በተሠሩ የእንጨት ምድጃዎች ላይ ምግብ ያበስሉ የነበረ ሲሆን ጭሱ ደግሞ ከላይ ወዳለው መተላለፊያ እንዲሄድ ተደርጎ ነበር።”

የዋሻው ጣሪያ ሲነኩት ጠጣር ከመሆኑ በቀር አንድ ትልቅ ሰፍነግ ይመስል ነበር። ግድግዳውን ስንመለከተው ድንጋዮች ተቆርጠው በወጡባቸው ቦታዎች ላይ የመጋዝ ምልክት ይታያል። ግድግዳዎቹን ስትዳስሷቸው በጣም ሻካራ የሆነ የብርጭቆ ወረቀት የነካችሁ ይመስላችኋል። አስጎብኚያችን “የደፈጣ ተዋጊዎቹ ከዋሻው መውጣት ሲፈልጉ ጀርመኖች በልብሳቸው ጠረን ለይተው እንዳይዟቸው ልብሳቸውን ይቀይሩ ነበር” አለችን። “በዋሻዎቹ ውስጥ ያለው እርጥበት አዘል አየር ለየት ያለ ጠረን ስለሚፈጥር ሽታው ልብሶቹ ላይ ይቀራል።”

“በዋሻው ውስጥ መኖር ለየት የሚያደርገው ሌላው ነገር ብርሃን የሚባል ነገር አለመኖሩ” እንደሆነ አስጎብኚያችን ገለጸችልን። አስጎብኚያችን መብራቱን ስታጠፋው በድቅድቅ ጨለማ ተዋጥን። “በጋዝ የሚሠራውን ኩራዝ ማብራት የሚችሉት ሁልጊዜ አልነበረም” አለችን። የግድግዳውን ጥግ ይዘን በዳበሳ እየሄድን ሳለን “ዓለቶቹ ድምፅ ውጠው ስለሚያስቀሩ መንገዱ ቢጠፋችሁና ለእርዳታ ብትጣሩ ማንም አይሰማችሁም” በማለት አክላ ነገረችን። ደግነቱ አስጎብኚያችን እንደገና መብራቱን አበራችልን!

“በፈረቃ የሚጠብቁት ዘቦች በሥራ ላይ የሚቆዩት ለሁለት ሰዓት ብቻ ነበር” በማለት ገለጻዋን ቀጠለች። “ምክንያቱም አንድ ሰው ጸጥ ረጭ ባለ አካባቢ በጨለማ ውስጥ ረጅም ሰዓት ከቆየ ምንም ድምፅ ሳይኖር ድምፅ የሰማ ሊመስለው ይችላል።” በዋሻው ጣሪያ ላይ ባለው ቀዳዳ በኩል ወደ ላይ ስናይ ከበላያችን እኛ ያለንበትን ዋሻ አቋርጦ የሚያልፍ ዋሻ እንዳለ ለመረዳት ቻልን። እኔም ‘ይህ ደግሞ መነሻው የት ይሆን? ወዴትስ ይወስድ ይሆን?’ ብዬ አሰብኩ። ገብቼም ለማየት ጉጉት አደረብኝ። “ከዋሻዎቹ ውስጥ በካርታ ላይ የሠፈረው 1,700 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው ብቻ እንደሆነና ገና ብዙ ሥራ እንደሚቀር” አስጎብኚያችን ገለጸችልን።

አሳሾች በቅርብ ጊዜ አዳዲስ ዋሻዎችን አግኝተዋል። ከተጻፉ መቶ ዓመት የሚሆናቸው ጋዜጦችን፣ ከአብዮቱ በፊት ሰዎች ይገለገሉባቸው የነበሩ በጋዝ የሚሠሩ ኩራዞችንና በዛሮች አገዛዝ ወቅት ይሠራበት የነበረ ገንዘብ በዋሻዎቹ ውስጥ አግኝተዋል። ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ሳይነኩ የቆዩት እነዚህ ግኝቶች ጥልቅና ጨለማ በሆኑትና ሰፊ ቦታ በሚሸፍኑት የኦዴሳ ዋሻዎች ውስጥ የኖሩት ሰዎች ንብረት ነበሩ።—ተጽፎ የተላከልን

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

አስደናቂ የሕንፃ ጥበብ

ከዋሻዎቹ ውስጥ ተፈልጦ በወጣ ቢጫ በሃ ድንጋይ የተሠሩ ውብ ሕንፃዎች በኦዴሳ መሃል ከተማ አሁንም ድረስ ይታያሉ። የአንዳንዶቹ ሕንፃዎች ምድር ቤቶች በቀጥታ ወደ ዋሻዎቹ የሚያስገቡ በሮች አሏቸው። በበሃ ድንጋይ ሕንፃዎችን መሥራት አሁንም ቀጥሏል።

[በገጽ 24 እና 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሶቭየቶች በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ይጠቀሙባቸው የነበሩ የሆስፒታል አልጋዎች

[በገጽ 24 እና 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የኦዴሳ ዋሻዎች ወደ 2,500 ኪሎ ሜትር የሚጠጋ ርዝመት ያለው የውስጥ ለውስጥ መተላለፊያ እንዳላቸው ይታሰባል