በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ፍጥረት ቀድሟቸዋል

ፍጥረት ቀድሟቸዋል

ፍጥረት ቀድሟቸዋል

“የሚሰሙ ጆሮዎች፣ የሚያዩ ዐይኖች፣ ሁለቱንም እግዚአብሔር ሠርቷቸዋል።”—ምሳሌ 20:12

ዓይኖችህ አነስተኛ የቴሌቪዥን ካሜራዎች ናቸው ሊባል ይችላል። ምስሎችን ወደ ኤሌክትሪክ መረጃ ይቀይሩና በኦፕቲክ ነርቮች አማካኝነት የማየቱ ሂደት ወደሚከናወንበት ወደ አንጎልህ የኋለኛ ክፍል ያስተላልፋሉ።

እያንዳንዱ ዓይን መጠኑ አነስተኛ ቢሆንም አሠራሩ በጣም አስደናቂ ነው፤ ሃያ አራት ሚሊ ሜትር ስፋትና 7.5 ግራም ክብደት ያለው ዓይናችን አፈጣጠሩ በጣም የረቀቀ ነው። ለምሳሌ ደማቅና ደብዛዛ ነገሮችን የሚያይበት የተለያየ አሠራር ስላለው ጨለማ ክፍል ውስጥ በገባህ በ30 ደቂቃ ውስጥ ዓይንህ ብርሃን የመለየት ኃይሉ 10,000 ጊዜ ይጨምራል።

በቂ ብርሃን ባለበት አካባቢ ጥርት ያለ ምስል እንድታይ የሚያስችልህ ምንድን ነው? ዓይንህ ያለው የብርሃንን መጠን መለየት የሚችሉ ሴሎች (ፒክስሎች) ብዛት ከአብዛኞቹ የቪዲዮ ካሜራዎች ከ100 እጥፍ በላይ ነው። በተጨማሪም ከእነዚህ ሴሎች መካከል አብዛኞቹ ከፍተኛ የሆነ አጥርቶ የማየት ችሎታ ባለው ፎቪያ በሚባለው የሬቲና መካከለኛ ክፍል ውስጥ ነጥብ በሚያህል አነስተኛ ቦታ ላይ ታምቀው ይገኛሉ። የእይታ ትኩረትህ በሴኮንድ ውስጥ ብዙ ጊዜ ስለሚዘዋወር በእይታ አድማስህ ውስጥ የሚገኙ ነገሮች ሁሉ ጥርት ብለው የሚታዩህ ይመስልሃል። የሚያስገርመው ነገር የዓይንህ ፎቪያ በዚህ ዓረፍተ ነገር መጨረሻ ላይ ከሚገኙት አራት ነጥቦች አንዱን ቢያክል ነው።

ብርሃን መለየት ከሚችሉት ከእነዚህ ሴሎች የሚነሱ የኤሌክትሪክ ምልክቶች ከአንዱ ሴል ወደሌላው እየተላለፉ ወደ ኦፕቲክ ነርቭ ይደርሳሉ። ይሁን እንጂ የነርቭ ሴሎቹ ሥራ ምልክቶቹን በማስተላለፍ ብቻ የተወሰነ አይደለም። የማጣራት ሥራም የሚያከናውኑ ሲሆን በዚህ ሂደት አስፈላጊ የሆኑትን መረጃዎች ያዳብራሉ፤ አላስፈላጊ ዝርዝሮችን ደግሞ አፍነው ያስቀራሉ።

በአንጎልህ ውስጥ የሚገኘው የእይታ ኮርቴክስ በጣም ውስብስብ ከሆነ የቪዲዮ መቀበያ መሣሪያ ጋር ይመሳሰላል። ጠርዞችን በማድመቅ ምስሎች ጥርት ብለው እንዲታዩ ያደርጋሉ። መሠረታዊ ቀለሞችን ማለትም ቀይ፣ አረንጓዴና ሰማያዊ ቀለሞችን መለየት ከሚችሉ ሴሎች የሚመጡትን ምልክቶች ስለሚያነጻጽሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ቀለሞችን መለየት ትችላለህ። በተጨማሪም አንጎልህ ሁለቱ ዓይኖችህ በሚያዩዋቸው ነገሮች መካከል ያለውን ጥቃቅን ልዩነት ስለሚያነጻጽር የአንድን ነገር ርቀት መገንዘብ ትችላለህ።

ዓይኖችህ በርቀት የሚገኙ የብዙ ሰዎችን ፊት እንዴት እንደሚመለከቱና የኤሌክትሮኒክ ምልክቶችን ወደ አንጎልህ ከላኩ በኋላ ምልክቶቹ ጥርት ወዳሉ ምስሎች እንዴት እንደሚቀየሩ ልብ በል። በተጨማሪም እነዚህ ፊቶች ያላቸውን ጥቃቅን ልዩነቶች አእምሮህ ከሚያስታውሳቸው ፊቶች ጋር ተነጻጽረው የጓደኛህን መልክ ወዲያውኑ መለየት የምትችለው እንዴት እንደሆነ አስብ። ይህ ሁሉ ሂደት አስደናቂ አይደለም?

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዓይናችን የሚደርሱትን መረጃዎች የሚያጣራበት ሂደት በጥበብ እንደተሠራ ያረጋግጣል