በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሞንት ብላንክ—የአውሮፓ “ጣሪያ”

ሞንት ብላንክ—የአውሮፓ “ጣሪያ”

ሞንት ብላንክ—የአውሮፓ “ጣሪያ”

የስዊስ ተወላጅ የሆነ ሆሬስ ቤነዲክት ደ ሶሱር (1740-1799) የተባለ የሥነ ተፈጥሮ ተመራማሪ ዛሬ ሞንት ብላንክ ተብለው የሚጠሩት ተራሮች ግርማ ሞገስ ከልጅነቱ ጀምሮ ያስደምመው ነበር። የአልፕስ ተራሮች ክፍል ወደሆኑት ወደ እነዚህ ረጃጅም ተራሮች መውጣት በጣም አስቸጋሪ በመሆኑ ይህ ተመራማሪ 4,807 ሜትር ከፍታ ወዳለው ረጅሙ ተራራ ቀድሞ ለወጣ ሰው ሽልማት እንደሚሰጥ ተናግሮ ነበር። ወደ ተራሮቹ አናት ለመውጣት ለመጀመሪያ ጊዜ ሙከራ የተደረገው በ1741 ነበር። ይሁን እንጂ ሞንት ብላንክ ጫፍ ላይ መውጣት የተቻለው በነሐሴ 1786 ሲሆን ይህንን አስቸጋሪ ጉዞ ያደረጉት ሻሞኒ የምትባለው የፈረንሳይ ከተማ ነዋሪዎች የሆኑ ሁለት ግለሰቦች ነበሩ፤ እነሱም ክሪስታል የተባለ ማዕድን በማውጣት ሙያ ላይ የተሰማራው ዣክ ባልማ እና ሚሼል ጋብሪኤል ፓካር የተባለው ዶክተር ናቸው። በቀጣዩ ዓመት ሶሱር ከአንድ የተመራማሪዎች ቡድን ጋር በመሆን በአውሮፓ ከፍተኛ ወደሆነው የተራሮቹ ጫፍ የደረሰ ሲሆን በ1788 ደግሞ ኮል ዱ ዢኦ የተባለው ተራራ ጫፍ ላይ በመውጣት በዚያ ለ17 ቀናት ቆይቷል። ከስፖርታዊ እንቅስቃሴ አንጻር ከተመለከትነው በጽሑፍ ተመዝግበው ከሚገኙትና ተራራ ላይ ለመውጣት ለሚደረጉት አስደናቂ ጉዞዎች ፈር ቀዳጅ የሆኑት እነዚህ ናቸው።

በ1855 በጣሊያናውያን የተመራ አንድ ቡድን ሞንት ብላንክ ወደተባሉት ተራሮች በሌላ አቅጣጫ የወጣ ሲሆን ይሄኛው ጉዞ ከመጀመሪያው የበለጠ ተፈታታኝ ነበር። በጣሊያን ክልል ወደሚገኘው የእነዚህ ተራሮች ጫፍ መድረስ የተቻለው ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ ነበር። ወደ እነዚህ ተራሮች በመውጣት ረገድ ቀዳሚ የሆኑት እነዚያ ደፋር ሰዎች ጉዟቸውን በሚያከናውኑበት ጊዜ ጫፋቸው ላይ ብረት ከተሰካባቸው ዘንጎች በስተቀር ምንም ዓይነት ዘመናዊ መሣሪያ አልነበራቸውም። በዚያን ጊዜ “ከተራራው ግርጌ ተነስቶ ጭራሽ የማይታወቁ አቅጣጫዎችን በመከተል የተራራው ጫፍ ላይ መድረስ ምናልባትም ዛሬ ያሉ ተራራ ወጪዎች ሊገምቱት የማይችሉት አካላዊ ብቃትና ውስጣዊ ጥንካሬ ይጠይቅ ነበር” በማለት የጂኦግራፊ ሊቅ የሆኑት ጆቶ ዳይኔሊ ተናግረዋል። እጅግ አስቸጋሪ ወደሚባሉት የተራራው ክፍሎችም እንኳ በአሁኑ ጊዜ ሰዎች በተደጋጋሚ መውጣት ችለዋል።

ሞንት ብላንክ በአውሮፓ እምብርት የሚገኝ ቢሆንም እንኳ በጥንት ጊዜ ሰዎች ያልደረሱበት ምድር እንደሆነ ተደርጎ ይቆጠር ነበር። ተራራውን ለይቶ የሚጠቅስ የመጀመሪያው የሚታወቅ ሰነድ የተጻፈው በ1088 ዓ.ም. ነው። በሻሞኒ የነበሩት መነኮሳት የሠሩት ካርታ ላይ ተራራው ሩፔስ አልባ ተብሎ የተጠራ ሲሆን ትርጉሙም “ነጭ ተራራ” ማለት ነው። ይሁን እንጂ በተራራው ላይ አጋንንትና ዘንዶዎች እንዳሉ በአፈ ታሪክ ይነገር ስለነበር የአካባቢው ሕዝቦች ለብዙ ዘመናት የተረገመ ተራራ ብለው ይጠሩት ነበር። ሞንት ብላንክ የሚለው ስያሜ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘው በ1744 በተዘጋጀ ካርታ ላይ ሲሆን ለተራራው ተሰጥቶት የነበረው መጥፎ መጠሪያ ከዚያ ወዲህ ቀስ በቀስ እየቀረ የመጣ ይመስላል።

የሞንት ብላንክ ተራሮች ከርቀት ሲታዩ

የሞንት ብላንክን ተራሮች ሙሉ በሙሉ ማየት የሚቻለው ከአውሮፕላን ላይ ሆኖ ነው። እነዚህ ተራሮች ወደ 600 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው አካባቢ የሚሸፍኑ ሲሆን ከመካከላቸው ከ4,000 ሜትር የሚበልጥ ከፍታ ያላቸው በርካታ ተራሮች ይገኛሉ፤ በተጨማሪም ጣሊያንን፣ ፈረንሳይንና ስዊዘርላንድን የሚያዋስነው ድንበር ላይ የሚገኙት ተራሮች ከ50 ኪሎ ሜትር የሚበልጥ ርቀት ድረስ እንደ ሰንሰለት እርስ በርስ የተያያዙ ናቸው። እነዚህ ተራሮች የተሠሩት እርስ በርስ ከተነባበሩ የባልጩትና የግራናይት ድንጋዮች ሲሆን ድንጋዮቹ የተፈጠሩት በምድር ውስጠኛው ክፍል ላይ ነው። ጂኦሎጂስቶች እነዚህ ተራሮች 350 ሚሊዮን ዓመታት “ብቻ” ያስቆጠሩ በመሆናቸው ከተፈጠሩ ብዙም እንዳልቆዩ ይናገራሉ። ከባቢው አየርና በተራሮቹ ላይ ያለው ግግር በረዶ ያሳደሩት ተጽዕኖ ድንጋዩ ለየት ያለ ቅርጽ እንዲይዝ አድርጎታል፤ በመሆኑም በአሁኑ ጊዜ በተራራው ላይ የሚታዩት የተሰነጣጠቁና ያፈጠጡ አለቶች እንዲሁም በውበታቸው ወደር የማይገኝላቸው ጉብታዎች ተራራ የሚወጡ ሰዎችን ትኩረት ይስባሉ።

ሞንት ብላንክ ከቅርበት ሲታይ

እነዚህን ተራሮች በቅርበት ለማየት ተራራ በመውጣት የተካኑ መሆን የግድ አያስፈልግም፤ ማንኛውም ሰው ቢሆን ከአንዱ የተራራው ጫፍ ወደ ሌላኛው ጫፍ በተወጠረ ሽቦ ላይ በተንጠለጠለውና ሰዎችን ለማሻገር በሚያገለግለው ሣጥን መሰል መጓጓዣ በመጠቀም የተራሮቹን ማዕከላዊ ክፍል መመልከት ይችላል። በ1958 ሥራውን የጀመረው ይህ መሻገሪያ ከሚደርስባቸው ቦታዎች ሁሉ ከፍተኛው ከባሕር ወለል በላይ 3,842 ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኘው ኤግዊል ዱ ሚዲ ነው፤ በዚህ ቦታ ሆኖ በዙሪያው ያለውን ውብ መልከዓ ምድር መመልከት የሚቻል ሲሆን ከሥሩም የሻሞኒ ሸለቆ ይገኛል።

በዛሬው ጊዜ ከመልክዓ ምድር አንጻር የሞንት ብላንክን ጓዳ ጎድጓዳ ማወቅ በመቻሉ የተደበቀ ሚስጥር የለም። በተለይ ጀንበሯ ስትወጣና ስትጠልቅ ብርሃኗ የአውሮፓ “ጣሪያ” በሚባሉት በእነዚህ በበረዶ የተሸፈኑ ተራሮች ላይ በሚያርፍበት ጊዜ የሚፈጥረው ነጸብራቅ ተራሮቹ ፍም መስለው እንዲታዩ ስለሚያደርግ አካባቢው ታይቶ የማይጠገብ ውበት ይላበሳል።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የሞንት ብላንክ የዋሻ መንገድ ሕልሙ እውን ሆነ

“ተመሳሳይ ቋንቋ የሚናገሩ አንድ ዓይነት ሕዝቦች ከተራራው ወዲያና ወዲህ ባሉ ሁለት ሸለቆዎች ውስጥ ይኖራሉ። የሞንት ብላንክን ተራራ ውስጥ ለውስጥ በማቋረጥ ሁለቱን ሸለቆዎች የሚያገናኝ መንገድ የሚሠራበት ቀን ይመጣል።” ይህ የሶሱር ሕልም እውን ሳይሆን ሁለት መቶ ዓመታት አለፉ። ይህን መንገድ ለመሥራት ለፒድሞንትና ለሳርዲኒያ ንጉሥ የመጀመሪያው ጥያቄ የቀረበው በ1814 ነበር፤ ይሁን እንጂ ሥራው የተጀመረው በ1959 ሲሆን በ1965 ተጠናቀቀ። * ይህ 11.6 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የዋሻ መንገድ ጣሊያን ውስጥ 1,381 ሜትር ከፍታ ላይ ጀምሮ ፈረንሳይ ውስጥ 1,274 ሜትር ከፍታ ላይ ያበቃል።

መጋቢት 24, 1999 በዋሻው ውስጥ አንድ የጭነት መኪና በእሳት በመያያዙ ከባድ ውድመት አስከትሏል። በዋሻው ውስጥ የሙቀቱ መጠን 1,000 ዲግሪ ሴልሲየስ በመድረሱ በርካታ ተሽከርካሪዎች ከጥቅም ውጭ ሆኑ። ሠላሳ ዘጠኝ ሰዎች ንጹሕ አየር በማጣታቸው የተነሳ ሲሞቱ 30 የሚያህሉ ደግሞ ጉዳት ደረሰባቸው። የአደጋውን መንስኤ ለማወቅ አንድ ዓመት የፈጀ ምርመራ ከተካሄደ በኋላ ዋሻውን እንደገና መገንባት ተጀመረ። ከባድ የጭነት መኪኖች በብዛት በዋሻው መጠቀማቸው የአካባቢ ብክለት ያስከትላል የሚል ሥጋት ያደረባቸው የአካባቢው ነዋሪዎችና የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾች ተቃውሞ ቢያሰሙም የዋሻ መንገዱ ሰኔ 25, 2002 እንደገና ተከፈተ። በቅርቡ በአራት ወራት ጊዜ ውስጥ 132,474 ተሽከርካሪዎች በዋሻው መንገድ ተጠቅመዋል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.12 ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የየካቲት 8, 1963 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ከገጽ 16-19 ተመልከት።

[ሥዕል]

በሻሞኒ፣ ፈረንሳይ የሚገኘው የሆሬስ ቤነዲክት ደ ሶሱር ሐውልት

[ምንጭ]

Library of Congress, Prints & Photographs Division, Photochrom Collection, LC-DIG-ppmsc-04985

[በገጽ 24,25 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ዙሪያ ገባውን የሚያስቃኝ የእግር ጉዞ

ወደ ሞንት ብላንክ ተራሮች ብዙውን ጊዜ የሚወጡት ልምድ ያላቸው ሰዎች ቢሆኑም እስከ ተራራው ጫፍ ወጥተው የማያውቁ ሰዎችም እንኳ ዙሪያውን በመጓዝ የእነዚህን ተራሮች ውበት መመልከት ይችላሉ። አብዛኛውን ጊዜ አንድን ተራራ ጥሩ ፎቶግራፍ ለማንሳት የተሻለ የሚሆነው ተራራው ላይ መውጣት ሳይሆን ከርቀት ሆኖ ማንሳት ነው። በሞንት ብላንክ ዙሪያ ተራሮቹን በተሻለ ሁኔታ ለማየት የሚያስችሉ የመመልከቻ ቦታዎች አሉ፤ በእነዚህ ቦታዎች ላይ ሆኖ ቀልብ የሚሰልበውን የተራሮቹን ውበት ከርቀት መመልከት ይቻላል። ተፈጥሮን የሚያደንቁና በእግራቸው ረጅም መንገድ መጓዝ የሚችሉ ሰዎች በተራሮቹ ዙሪያ በተለያዩ አቅጣጫዎች 130 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የእግር ጉዞ ማድረግ ይችላሉ። ሞንት ብላንክ ቱር በመባል በሚታወቀው የጉዞ ፕሮግራም ላይ ከእነዚህ የተለያዩ አቅጣጫዎች የተወሰኑት ተመርጠው በአንድ የጉብኝት ፕሮግራም ውስጥ እንዲታቀፉ ተደርጓል። ይህ የጉብኝት ፕሮግራም ፈረንሳይን፣ ጣሊያንንና ስዊዘርላንድን የሚያካልል የእግር ጉዞ ሲሆን ጎብኚዎቹ ወደ ተነሱበት ቦታ የሚመለሱት በሌላ አቅጣጫ ነው። በየቀኑ ከሦስት እስከ ሰባት ሰዓት መጓዝ የሚጠይቀው ይህ የጉብኝት ፕሮግራም በአጠቃላይ አስር ቀን የሚፈጅ ሲሆን ልብ የሚሰርቁትን የተራሮቹን ውበት ከተለያየ አቅጣጫ ለማየት የሚያስችሉ አጋጣሚዎች ይሰጣል። ይህንን ጉዞ ለማድረግ ብዙ ጊዜ የሌላቸው ሰዎች በሞንት ብላንክ ዙሪያ ከሚገኙት በርካታ ተራሮች በአንዱ ላይ በእግር መጓዝ ይችላሉ።

[ሥዕል]

ሰዎችን ለማሻገር የሚያገለግለው ሣጥን መሰል መጓጓዣ ከሚደርስባቸው ቦታዎች ሁሉ ከፍተኛው ኤግዊል ዱ ሚዲ ነው

[ምንጭ]

Courtesy Michel Caplain; http://geo.hmg.inpg.fr/mto/jpegs/020726/L/12.jpg

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ፈረንሳይ

ስዊዘርላንድ

ጣሊያን

ሞንት ብላንክ

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሶሱር በ1787 ሞንት ብላንክን ወጥቶት ነበር (አንድ አርቲስት በግምት የሳለው)

[ምንጭ]

© The Bridgeman Art Library International

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሞንት ብላንክ