በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በላይኛው አማዞን የሚገኙ የተለያዩ አስደናቂ ፍጥረታት

በላይኛው አማዞን የሚገኙ የተለያዩ አስደናቂ ፍጥረታት

በላይኛው አማዞን የሚገኙ የተለያዩ አስደናቂ ፍጥረታት

በደቡብ አሜሪካ አህጉር ከፔሩ የአንዲስ ተራሮች ግርጌ ጀምሮ በምሥራቅ አቅጣጫ 3,700 ኪሎ ሜትር ገደማ ድረስ ያለውን ምድር ጥቅጥቅ ያለ ደን ልክ እንደ ብርድ ልብስ ሸፍኖታል። ከላይ ሲታይ አረንጓዴ ባሕር የሚመስለው ይህ ጥቅጥቅ ያለ ደን ሰማያዊ ከሆነው የአትላንቲክ ውቅያኖስ ጋር ይገናኛል።

በፔሩ የሚገኘው የዚህ ጥቅጥቅ ያለ የአማዞን ደን ክፍል ከአገሪቱ የቆዳ ስፋት ወደ 60 በመቶ የሚያህለውን ይሸፍናል። በዚህ አካባቢ የሚኖረው ሕዝብ ከፔሩ አጠቃላይ ሕዝብ አንጻር ሲታይ በጣም ጥቂት ቢሆንም 35 ሜትር ከፍታ ባለው በዚህ ደን ውስጥ በርከት ያሉ እፅዋትና እንስሳት ይኖራሉ። እንዲያውም የአማዞን ደን በምድር ላይ ካሉት የበለጸጉ ሥነ ምህዳሮች መካከል አንዱ እንደሆነ ይነገራል። ከ3,000 በላይ የሚሆኑት የቢራቢሮ ዓይነቶች በሞቃታማ አየር ውስጥ ከወዲያ ወዲህ ብር ብር ይላሉ። ወደ 4,000 ገደማ የሚሆኑ የኦርኪድ ዓይነቶች የሚያማምሩ አበቦቻቸውን ዘርግተው ይታያሉ። ከ90 በላይ የሚሆኑ የእባብ ዝርያዎች በዛፍ ቅርንጫፎችና በጫካው ውስጥ ይርመሰመሳሉ። እንዲሁም ኢል የተባለውን እባብ መሳይ ዓሣና ፒራንየ የሚባለውን ዓሣ ጨምሮ በግምት ወደ 2,500 የሚደርሱ የዓሣ ዝርያዎች ወንዞችንና ጅረቶችን ተቆጣጥረዋቸዋል።

በዚህ አካባቢ ከሚገኙት የውኃ አካላት መካከል ትልቁ የአማዞን ወንዝ ነው። በአንዳንድ ስፍራዎች በየዓመቱ የሚጥለው ከ2.5 እስከ 3 ሜትር የሚደርስ ዝናብ አማዞንና 1,100 የሚያህሉ ገባር ወንዞች ከአፍ እስከ ገደፋቸው እንዲሞሉ ስለሚያደርግ ጫካው በጎርፍ ይጥለቀለቃል። ሞቃት የሆነው አየር ከእርጥበት ተዳምሮ ለተክሎች ተስማሚ የሆነ አየር ይፈጥራል። የሚገርመው ነገር እፅዋቱ በጣም የሚመቻቸው በምድር ላይ ካሉት የአፈር ዓይነቶች ሁሉ ለእርሻ ሥራ ተስማሚ እንዳልሆነ በሚነገርለት የሸክላ አፈር ላይ ነው።

የሰፋሪዎቹ አመጣጥ

እንዲህ ባለው ስፍራ መኖር የሚመርጥ ማን ይኖራል? አርኪኦሎጂስቶች፣ ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት በአማዞን ወንዝ አካባቢ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ይኖሩ እንደነበር ያምናሉ። በአሁኑ ጊዜ ከ40 በሚበልጡ ጎሣዎች ውስጥ የታቀፉ በግምት 300,000 የሚሆኑ ሰዎች በፔሩ የአማዞን ክልል ውስጥ ይኖራሉ። በተጨማሪም ከእነዚህ ጎሣዎች መካከል 14 የሚያህሉት ከቀረው ዓለም ሙሉ በሙሉ ተገልለው ይኖራሉ። እነዚህ ሰዎች “ከሠለጠነ” ኅብረተሰብ ጋር ለአጭር ጊዜ ከኖሩ በኋላ ከዚያ ወዲያ ምንም ዓይነት ግንኙነት ላለማድረግ ሲሉ ከሰው ሸሽተው ወደ ጫካው ዘልቀው ገብተዋል።

እነዚህ በጫካ ውስጥ የሚኖሩ ጎሣዎች ወደዚህ አካባቢ የመጡት መቼ ነው? የመጡትስ ከየት ነው? ክርስቶስ ከመወለዱ ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት ሰዎች ከሰሜን አቅጣጫ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደዚህ አካባቢ እንደፈለሱ ተመራማሪዎች ይገምታሉ። ሂቫሮዎች (ያረዷቸውን ጠላቶቻቸውን ጭንቅላት በመጨፍለቅ ይታወቃሉ) የመጡት ከካሪቢያን ሲሆን አረዋኮች የመጡት ደግሞ ከቬኔዙዌላ ነበር። ሌሎች ጎሣዎች ከአማዞን በስተ ምሥራቅ ከምትገኘው ከብራዚልና በስተ ደቡብ ከምትገኘው ከፓራጉዋይ እንደመጡ ይታመናል።

አብዛኞቹ ጎሣዎች ተደላድለው መኖር ከጀመሩ በኋላ በተወሰኑ አካባቢዎች ውስጥ ተዘዋውረው እያደኑና እየሰበሰቡ የሚኖሩ ይመስላል። በተጨማሪም አሲድ የበዛበት አፈር የሚስማማቸውን እንደ ካሳቫ፣ ሚጥሚጣ፣ ሙዝና በቆሎ ያሉ ጥቂት ሰብሎችን ያለሙ ነበር። ስፔናውያን ታሪክ ጸሐፊዎች እንደዘገቡት ከሆነ ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ በሚገባ ተደራጅተው ብሎም ቀለብ የሚያከማቹበትን ዘዴ ፈልስፈው ይኖሩ የነበሩ ከመሆኑም ሌላ የዱር እንስሳትን የሚያረቡበት ዘዴ ነበራቸው።

የባሕል ግጭት

በ16ኛውና በ17ኛው መቶ ዘመን ስፔናውያን ቅኝ ገዥዎች አማዞንን ወረሩ። የእነዚህን ቅኝ ገዥዎች እግር ተከትለው የአማዞን ተወላጆችን ወደ ሮማ ካቶሊክ ሃይማኖት ለመቀየር የፈለጉ የካቶሊክ ሚስዮናውያን መጡ። እነዚህ ሚስዮናውያን፣ አውሮፓውያን ወደ አማዞን እንዲመጡ ጥርጊያ መንገድ የከፈተ ግሩም ካርታ አዘጋጁ። ይሁን እንጂ ሚስዮናውያኑ መንገድ የከፈቱት ለበሽታና ለጥፋትም ጭምር ነበር።

ለምሳሌ ያህል፣ በ1638 በአሁኑ ጊዜ ማይናስ በሚባለው ግዛት አንድ ሚስዮን ተቋቁሞ ነበር። ሚስዮናውያኑ የአገሩን ተወላጆች ከወረሯቸው በኋላ ተቀናቃኝ ጎሣዎችን አንድ ላይ በማቧደን በኅብረተሰብ መልክ ተዋሕደው እንዲኖሩ አስገደዷቸው። የሚስዮናውያኑ ዓላማ ምን ነበር? የአገሩን ተወላጆች ያልተማሩና የበታች እንደሆኑ አድርገው ስለሚመለከቷቸው ለሚስዮናውያኑም ሆነ ለቅኝ ገዥዎቹ አስገድደው ሥራ ለማሠራት ነበር። የአገሩ ተወላጆች ከአውሮፓውያኑ ጋር ተቀራርበው በመኖራቸው የተነሳ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በኩፍኝ፣ በፈንጣጣ፣ በትክትክና በሥጋ ደዌ በሽታ አልቀዋል። ሌሎች በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ በረሀብ ሞተዋል።

ብዙ ሕንዳውያን በተለያዩ ሃይማኖታዊ ድርጅቶች ከተቋቋሙት ሚስዮኖች ያመለጡ ሲሆን በተነሳው ረብሻ በርካታ ሚስዮናውያን ተገድለዋል። እንዲያውም በ19ኛው መቶ ዘመን የመጀመሪያዎቹ አሥርተ ዓመታት ውስጥ በአንድ ወቅት በአማዞን ክልል አንድ ቄስ ብቻ ቀርቶ ነበር።

የአሁኑ አኗኗራቸው

በዛሬው ጊዜ በርካታ የአገሬው ተወላጆች በባሕላቸው መሠረት መኖራቸውን ቀጥለዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ቤቶቻቸውን የሚሠሩት ሲወርድ ሲዋረድ በመጣ ዘዴ አማካኝነት ሲሆን ከጫካ ውስጥ አጣናዎችን ቆርጠው ግድግዳውንና ጣሪያውን ካዋቀሩ በኋላ ጣሪያውን በዘንባባ ቅጠሎች ወይም በሌሎች የሣር ዓይነቶች ይከድኑታል። እነዚህ ቤቶች ከመሬት ከፍ ብሎ በተሠራ ርብራብ ላይ ስለሚቆሙ በየዓመቱ በሚከሰተው ጎርፍ የማይጥለቀለቁ ከመሆናቸውም በላይ ብዙውን ጊዜ አደገኛ እንስሳት አይገቡባቸውም።

የተለያዩ ጎሣዎች የተለያየ ዓይነት አለባበስና አጋጌጥ አላቸው። እልም ባለ ጫካ ውስጥ የሚኖሩ ወንዶችና ሴቶች የሚለብሱት የሚገለደሙ ልብሶችን ወይም አጫጭር ጉርድ ቀሚሶችን ሲሆን ልጆቻቸው ግን ምንም ልብስ አይለብሱም። ከውጪው ዓለም ጋር ይበልጥ ግንኙነት ያላቸው ጎሣዎች ደግሞ የምዕራባውያንን አለባበስ ይከተላሉ። አንዳንዶቹ የአገሬው ተወላጆች አፍንጫቸውን ወይም ጆሮዎቻቸውን ተበስተው ቀለበት እንዲሁም የእንጨት፣ የአጥንት ወይም የላባ ጌጦችን ያደርጋሉ። እንደ ማዮሩና ያሉት ሌሎች ጎሣዎች ደግሞ ጉንጫቸውን ይበሳሉ። አንዳንድ የቱኩና እና የሂቫሮ ተወላጆች ጥርሳቸውን ያስሞርዳሉ። በተለያዩ ጎሣዎች ውስጥ ያሉ ብዙ ሰዎች የሰውነታቸውን ፀጉር ተላጭተው ቆዳቸውን ይነቀሱታል።

የአማዞን ሕዝቦች በሺህ የሚቆጠሩ የእፅዋት ዓይነቶችን ስለሚያውቁ ጫካውን እንደ መድኃኒት መደብር አድርገው ይጠቀሙበታል። ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል በእባብ ለተነደፈ፣ ለተቅማጥና ለተለያዩ የቆዳ በሽታዎች ከእፅዋት መድኃኒት ያዘጋጃሉ። ምዕራባውያን ጎማ ከመፈልሰፋቸው ከረጅም ጊዜ በፊት የአማዞን ሕዝቦች የጎማ ዛፎችን በስተው ወተቱን በማጠራቀም ለሥራ የሚጠቀሙባቸውን ቅርጫቶች ለመለቅለቅና የመጫወቻ ኳስ ለመሥራት ይጠቀሙበት ነበር። በተጨማሪም ነዋሪዎቹ ከጫካው ውስጥ ሩቅ አካባቢ ለሚኖሩ ሰዎች መልእክት ለማስተላለፍ የሚረዱና ለመጓጓዣነት የሚያገለግሉ መሣሪያዎችን ለመሥራት የሚያስችሉ ጥሬ ዕቃዎችን ያገኛሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ወንዶች ዛፍ ቆርጠው በወንዝ ላይ ለመጓጓዝ የሚያገለግሉ ታንኳዎችን ይሠራሉ። እንዲሁም ትላልቅ ግንዶችን በመቦርቦር ሩቅ ቦታ ላይ ለሚገኙ ሰዎች መልእክት ለማስተላለፍ የሚያስችሏቸውን ከበሮዎች ይሠራሉ።

ቃልቻዎችና አጉል እምነት የሚያሳድሩት ተጽዕኖ

የአማዞን ነዋሪዎች ጫካው በሌሊት በሚንከራተቱ ነፍሶች፣ ሕመም በሚያስከትሉ መንፈሶችና ወንዝ ላይ አድብተው ሰለባዎቻቸውን በሚለክፉ አማልክት የተሞላ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ለአብነት ያህል፣ በፔሩ ከሚገኙት ትላልቅ ጎሣዎች መካከል አንዱ የሆነውን አግዋሩናን እንመልከት። አግዋሩናዎች “አባት ተዋጊ፣” “አባት ውኃ፣” “እናት ምድር፣” “አባት ፀሐይ” እና “ቃልቻ አባት” የሚባሉ አምስት አማልክት አሏቸው። ሰዎች ከሞቱ በኋላ ወደ እፅዋትነትና እንስሳትነት ይቀየራሉ ብለው የሚያምኑ ብዙ ሰዎች አሉ። የአገሬው ሰዎች መንፈሳዊ ፍጡራንን ላለማስቆጣት ሲሉ አንዳንድ እንስሳትን ከመግደል የሚቆጠቡ ከመሆኑም በላይ ሌሎች እንስሳትን የሚያድኑት አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ብቻ ነው።

ከጥንት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን ሃይማኖታዊና ማኅበራዊ ሕይወት የሚመሩት አዋቂዎች እንደሆኑ ተደርገው የሚታመኑት ቃልቻዎች ናቸው። እነዚህ ቃልቻዎች ለመመርቀን ሲሉ የሚያቃዡ እፅዋትን ይጠቀማሉ። አንዳንድ የመንደሮቹ ነዋሪዎች ከሕመማቸው ለመፈወስ፣ የአደንና የእርሻ ሥራቸው ምን ውጤት እንደሚኖረው ለመረዳት እንዲሁም ስለ ወደፊቱ ጊዜ ለማወቅ ወደ ቃልቻዎች ይሄዳሉ።

አማዞን ይጠፋ ይሆን?

የአማዞን ሕዝቦች የሚኖሩበት ጫካ በፍጥነት እየተመናመነ ነው። ጫካውን አቋርጠው የሚያልፉ አዳዲስ መንገዶች ተሠርተዋል። በእርሻና በኮካ ልማት መስፋፋት ምክንያት ደኑ ከጊዜ ወደጊዜ እየተመናመነ ነው። በሕገ ወጥ የደን ምንጠራ ሳቢያ በየቀኑ 1,200 የእግር ኳስ ሜዳዎች የሚያህል ስፋት ያለው ደን እየወደመ ነው! ማዕድን በሚያወጡ ሕጋዊ ተቋማትና ሕገ ወጥ በሆኑ የኮኬይን ምርቶች ምክንያት ወደ አማዞን ወንዝ የሚገቡ ገባር ወንዞች እየተበከሉ በመሆኑ የውኃ አካላት አደጋ ተደቅኖባቸዋል።

በእርግጥም ከሌሎች ተገልለው የሚኖሩት የአማዞን ሕዝቦች መጽሐፍ ቅዱስ “ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን” ብሎ በተናገረለት ጊዜ ውስጥ መኖር የሚያሳድረውን ተጽዕኖ እየተመለከቱ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) አማዞን ሙሉ በሙሉ ይጠፋ ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ ይህ እንደማይሆን ዋስትና ይሰጣል። በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር መላዋ ምድር በፈጣሪያችን ዓላማ መሠረት ወደ ገነትነት ትለወጣለች።—ኢሳይያስ 35:1, 2፤ 2 ጴጥሮስ 3:13

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአማዞን ወንዝ

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የላማስ ሴቶች

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አግዋሩናዎች አምስት አማልክትን ያመልካሉ

[በገጽ 18, 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ የአማዞን ተወላጅ በትንፋሽ በሚሠራ መሣሪያ ቀስት ሲያስፈነጥር

[ምንጭ]

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የተለመደው የቤት አሠራር

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በየቀኑ 1,200 የእግር ኳስ ሜዳዎች የሚያህል ስፋት ያለው ደን በሕገ ወጥ መንገድ ይመነጠራል

© Renzo Uccelli/PromPerú

[ምንጭ]

© José Enrique Molina/age fotostock

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

© Alfredo Maiquez/age fotostock

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Top: © Terra Incógnita/PromPerú; bottom: © Walter Silvera/PromPerú