በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በጫካ ውስጥ ቺምፓንዚዎችን መጎብኘት

በጫካ ውስጥ ቺምፓንዚዎችን መጎብኘት

በጫካ ውስጥ ቺምፓንዚዎችን መጎብኘት

አፍሪካ የምድር ወገብ አካባቢ በሚገኝ ጥቅጥቅ ያለ ደን ውስጥ አንድ ጠባብ የእግር መንገድ ተከትለን መጓዝ ስንጀምር በቅጠሎችና በቅርንጫፎች መካከል ሾልኮ የሚገባውን የፀሐይ ጨረር ዓይናችን ቀስ በቀስ እየለመደው መጣ። የፌንጣዎችን የማያቋርጥ ድምፅ ስንሰማ እንዲሁም በሐረግ የተሸፈኑ ከ55 ሜትር በላይ ርዝመት ያላቸውን ረጃጅም ዛፎች ስንመለከት በአድናቆት ተመሰጥን። እምብዛም ብርሃን በማይደርስበት በዚህ አካባቢ ነቃ ብለን በቀስታ መራመድ ጀመርን። በድንገት ቶሎ ቶሎ ትንፋሽ ወደ ውስጥ እየሳበ ሁ ሁ ሁ እያለ የሚጮህ ኃይለኛ ድምፅ ሰማን። ይህ ድምፅ መጠኑና ቅላጼው ጆሮ እስከሚያደነቁር ድረስ እየጨመረ መጣ፤ ከዚያም በድንገት ጸጥ አለ። አድካሚ የእግር ጉዞ ካደረግን በኋላ ያሰብንበት አስደሳች ቦታ ይኸውም ቺምፓንዚዎች በቡድን ወደሚገኙበት ቦታ ደረስን።

ቁና ቁና እየተነፈሱ ድምፅ ማሰማትን፣ መጮኽን አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የዛፉን ግንድ እንደ ታምቡር ደጋግሞ መምታትን ጨምሮ እንዲህ ያለው የተደበላለቀ ስሜት ቺምፓንዚዎች እርስ በርስ ሐሳብ የሚለዋወጡበት ወይም የሚጠራሩበት መንገድ ነው። አንድ ቺምፓንዚ አብዛኛውን ጊዜ በዚህ መንገድ ቡድኑን በአፋጣኝ የሚጠራው የበሰለ ጣፋጭ በለስ በብዛት ሲያገኝ ነው። የተንዠረገገ ቅርንጫፎች ወዳሉት አንድ ረጅም የበለስ ዛፍ አናት አንጋጠን ስንመለከት ቁጥራቸው 20 ወይም 30 የሚሆኑ ቺምፓንዚዎች በሰላም በለሱን እየለቀሙ ሲመገቡ አየን። በጣም የሚያምረው ጥቁሩ ፀጉራቸው የፀሐይ ብርሃን ሲያርፍበት ያብረቀርቃል። ከእነዚህ ቺምፓንዚዎች መካከል አንዱ ቀንበጦችን ወረወረብን፤ ብዙም ሳይቆይ የቀንበጥ መዓት ይዘንብብን ጀመር። ቺምፓንዚዎቹ ይህን ማድረጋቸው ምግባቸውን ለማካፈል እንደማይፈልጉ የሚያሳይ ግልጽ ምልክት ነበር።

ቺምፓንዚዎችን በጫካ ውስጥ በቀላሉ ማግኘት የሚቻለው ፍራፍሬ በብዛት በሚደርስበት ወቅት ነው። በሌላ ጊዜ ግን ጥቂት ጥቂት ሆነው ዱር ውስጥ ስለሚበታተኑ እነሱን በብዛት ማግኘት በጣም አስቸጋሪ ነው። ቺምፓንዚዎች ብዙ ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ባለው ጫካ ውስጥ ከቦታ ወደ ቦታ እየተዘዋወሩ አብዛኛውን ጊዜ ቀኑን ሙሉ ሲበሉ ይውላሉ። ከፍራፍሬ በተጨማሪ ቅጠሎችን፣ የዘር ፍሬዎችንና ግንዶችን ይመገባሉ። ከዚህም በተጨማሪ ጉንዳኖችን፣ የወፎችን እንቁላልና ምስጦችን ይበላሉ። አልፎ አልፎ ደግሞ ጦጣዎችን ጨምሮ ትንንሽ እንስሳትን አድነው ሊበሉ ይችላሉ።

ወደ እኩለ ቀን ሲቃረብ ቺምፓንዚዎቹ እየጨመረ የመጣው ሙቀት ስለተሰማቸው አንደኛው ቺምፓንዚ ከዛፉ ላይ መውረድ ጀመረ። በዚህ ጊዜ ሌሎቹም ቀስ በቀስ እሱን ተከትለው በመውረድ ተያይዘው ጥቅጥቅ ወዳለው ጥሻ ውስጥ ገቡ። በዕድሜ አነስ ያለ አንድ ተንኮለኛ ቺምፓንዚ እኛን ጠጋ ብሎ ለማየት ከቅርንጫፍ ወደ ቅርንጫፍ እየዘለለ ቀረብ አለ። ይህ ቺምፓንዚ ያለውን የማወቅ ጉጉትና ተጫዋችነቱን ስንመለከት ሁላችንም ፈገግ አልን።

አስደናቂ ባሕርያት

መንገዳችንን ይዘን ወደመጣንበት ስንመለስ ከቡድናችን አባላት አንዱ “ወደ ኋላችሁ እዩ” አለን። ዞር ብለን ስንመለከት አንድ ቺምፓንዚ በዛፍ ግንድ ተከልሎ አጮልቆ ሲመለከተን አየነው። ወደ አንድ ሜትር ገደማ ርዝመት ባላቸው ሁለት እግሮቹ ቆሞ ነበር። ስናየው ቀስ ብሎ በዛፉ ተከለለ፤ ጥቂት ቆይቶ ደግሞ እንደገና ብቅ አለ። ለማወቅ ያለው ጉጉት እንዴት ያስደስታል! አዎን፣ ቺምፓንዚዎች በሁለት እግራቸው ሊቆሙ አልፎ ተርፎም አጭር ርቀት በሁለት እግራቸው ሊራመዱ ይችላሉ። ይሁን እንጂ አብዛኛውን ጊዜ ሚዛናቸውን መጠበቅ የሚችሉት አራቱንም እግሮቻቸውን ሲጠቀሙ ነው። የቺምፓንዚ አከርካሪ ከታች በኩል ልክ እንደ ሰው ቀጥ ብሎ ለመቆም የሚያስችለው የታጠፈ ቦታ የለውም። በተጨማሪም በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ደካማ የሆኑት የታፋ ጡንቻዎቹ ይበልጥ ረጅምና ጠንካራ ከሆኑት ክንዶቹ ጋር ተጋግዘው በአራት እግሮቹ እንዲራመድ፣ ዛፎች ላይ እንዲወጣና እንዲንጠላጠል ያስችሉታል። የቺምፓንዚዎች የሰውነት አወቃቀር ይህ እንስሳ ለዚህ እንደተፈጠረ ያሳያል።

ቺምፓንዚዎች ቢወጡባቸው እንኳ በቀላሉ ሊሰበሩ በሚችሉ ቅርንጫፎች ላይ ፍራፍሬ ሲያገኙ ተንጠራርተው ለመልቀም ረጃጅም በሆኑት እጆቻቸው ይጠቀማሉ። ቺምፓንዚዎች እጆቻቸውና እግሮቻቸው ቅርንጫፎችን አጥብቆ መያዝ የሚያስችል ትክክለኛ ቅርጽ አላቸው። ትላልቆቹ የእግሮቻቸው ጣቶች ወደጎን አጠፍ ያሉ ሲሆኑ ቺምፓንዚዎች ዛፎች ላይ እንዲወጡ፣ ልክ እንደ እጆቻቸው በእግሮቻቸውም አንድን ነገር በቀላሉ መያዝ ወይም መሸከም እንዲችሉ ይረዷቸዋል። ይህ ችሎታቸው ደግሞ አመሻሹ ላይ የሚያድሩበትን ቦታ ለማዘጋጀት ይረዳቸዋል። ቺምፓንዚዎች ምሽት ላይ ቅጠሎችንና ቅርንጫፎችን በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ አስተካክለው ምቹና የማይጎረብጥ መኝታ ይሠራሉ።

ከሰው ጋር ተመሳሳይ የሆነ የሰውነት አወቃቀርና በርካታ አስደናቂ ባሕርያት ያሏቸውን በጫካ የሚገኙ ቺምፓንዚዎችን መመልከትና ስለ እነሱ ማጥናት እነዚህን እንስሳት ይበልጥ ትኩረት የሚስቡ እንዳደረጋቸው ምንም አያጠራጥርም። ይሁን እንጂ አንዳንድ ሰዎች ስለ ቺምፓንዚዎች ለማወቅ የሚፈልጉት ሰው በዝግመተ ለውጥ አማካኝነት ከቺምፓንዚ የተገኘ መሆኑን ለማረጋገጥ የሚያስችል ምርምር ለማካሄድ ብለው ብቻ ነው። በመሆኑም እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎች ሊነሱ ይችላሉ፦ በሰዎችና በቺምፓንዚዎች መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው? ሰው ከእንስሳት በተለየ መንገድ ‘በአምላክ አምሳል’ የተሠራው እንዴት ነው?—ዘፍጥረት 1:27

የማይረሳ ጊዜ

በጫካ ውስጥ የሚገኙ ቺምፓንዚዎች በቀላሉ የማይገኙ ከመሆናቸውም በላይ አብዛኛውን ጊዜ ሰው መምጣቱን ሲያዩ ቀስ ብለው ከአካባቢው ይሰወራሉ። ይሁን እንጂ ጥበቃ እንዲደረግላቸውና ዝርያቸው ከምድር እንዳይጠፋ ለማድረግ ሲባል አንዳንድ የቺምፓንዚ ቡድኖች ሰው ባለበት አካባቢ መኖር እንዲችሉ ለማዳ ተደርገዋል።

ቺምፓንዚዎች ወደሚኖሩበት ጫካ ሄደን ያደረግነው አጭር ጉብኝት የማይረሳ ነበር። ሌላው ቢቀር በአራዊት መጠበቂያዎች ወይም በቤተ ሙከራዎች ካሉት በተለየ መልኩ ቺምፓንዚዎች ምን እንደሚመስሉ መጠነኛ እውቀት እንድናገኝ ረድቶናል። ቺምፓንዚዎች፣ አምላክ ለሚኖሩበት አካባቢ መልካምና ተስማሚ አድርጎ ከሠራቸው ‘በምድር ላይ ከሚሳቡ ፍጡራንና የዱር እንስሳት’ መካከል የሚቆጠሩ በጣም አስደናቂ የሆኑ እንስሳት ናቸው።—ዘፍጥረት 1:24, 25

[በገጽ 14 እና 15 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ቺምፓንዚ እና ሰው

ዶክተር ጄን ጉድኦል የተባሉ አንዲት የሥነ እንስሳት ጥናት ሊቅ፣ ኢን ዘ ሻዶው ኦቭ ማን በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ በ1960ዎቹ ዓመታት ውስጥ ስለተመለከቷቸው “መሣሪያዎችን መሥራት” ስለሚችሉ ቺምፓንዚዎች የሰጡት አስተያየት እንዲህ ይላል፦ “በርካታ የሳይንስ ሊቃውንት የሰውን ተፈጥሮ ከበፊቱ የበለጠ የተራቀቀ መመዘኛ ተጠቅመው መገምገም እንደሚያስፈልጋቸው አሳምኗቸዋል።” ቺምፓንዚዎች ቅጠልን እንደ ስፖንጅ፣ ድንጋይን ወይም እንጨትን ልዩ ልዩ የለውዝ ዓይነቶችን ለመፈርከስ እንዲሁም ምስጦችን ከኩይሳ ውስጥ ለማውጣት ከልምጭ ላይ ቅጠሉን የሚመለምሉበት መንገድ በእርግጥም የሚያስገርም ነው። ይሁን እንጂ በርካታ እንስሳት በመሣሪያዎች የመጠቀም አስገራሚ ችሎታ እንዳላቸው ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ማስተዋል ተችሏል። ቲኦዶር ዜነፈን ባርበር የተባሉ ዶክተር፣ ዘ ሂውመን ኔቸር ኦቭ በርድስ—ኤ ሳይንቲፊክ ዲስከቨሪ ዊዝ ስታርትሊንግ ኢምፕሊኬሽንስ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ብለዋል፦ “ዝንጀሮዎችና ዶልፊኖች ብቻ ሳይሆኑ ጉንዳኖችንና ንቦችን ጨምሮ ጥልቅ ምርምር የተካሄደባቸው እንስሳት በሙሉ ፈጽሞ ያልተጠበቀ መሠረታዊ ግንዛቤና ብልህነት እንዳላቸው ታይቷል።”

ይሁንና ይህ ሁኔታ ሰው ተወዳዳሪ የማይገኝለት ፍጡር የመሆኑን ሐቅ በምንም መንገድ አይለውጠውም። ፕሮፌሰር ዴቪድ ፕሪመክ “የሰው ቋንቋ የሚመራበት የሰዋስው ሕግ ወይም አገባብ በእርግጥም ልዩ ነው” በማለት ጽፈዋል። አዎን፣ በሰዎች ዘንድ ወሳኝ ቦታ ያለው ውስብስብ የሆነው ቋንቋና ንግግር ከተለያየ ባሕል ጋር ተዳምሮ በእርግጥም እኛን ከእንስሳት ልዩ ያደርገናል።

ጄን ጉድኦል በጫካ ውስጥ ስለሚኖሩ ቺምፓንዚዎች ለዓመታት ጥናት ካደረጉ በኋላ እንደሚከተለው በማለት ጽፈዋል፦ “ቺምፓንዚዎች ከፍቅር በመነጨ ስሜት የሚደረጉ እንደ አሳቢነት፣ ወገናቸውን ከአደጋ እንደ መጠበቅ፣ እንደ መቻቻልና ጥልቅ መንፈሳዊ እርካታ እንደ ማሳየት ያሉ ከውስጥ ፈንቅለው የሚወጡ ባሕርያት የሏቸውም፤ እነዚህ ባሕርያት የሰው ዓይነተኛ መለያ ናቸው።” በተጨማሪም እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “ሰው ያለው ራሱን የማወቅ ችሎታ አንድ እንስሳ ስለ ራሱ አካል ካለው አነስተኛ ግንዛቤ እጅግ የላቀ ነው። ሰው ስለ ማንነቱ፣ በዙሪያው ስላሉት አስደናቂ ፍጥረታትና ከበላዩ ስላለው ዓለም ማብራሪያ ማግኘት ይፈልጋል።”

መጽሐፍ ቅዱስ ሰው “በእግዚአብሔር መልክ” እንደተፈጠረ በመናገር በእንስሳትና በሰዎች መካከል ልዩነት እንዳለ ይገልጻል። (ዘፍጥረት 1:27) በመሆኑም ከእንስሳት በተለየ መልኩ ሰው የሠሪውን መንፈሳዊ መልክ ማንጸባረቅ የሚችል ሲሆን ይህንንም የሚያደርገው የፈጣሪውን ባሕርያት በማሳየት ነው፤ ከአምላክ ባሕርያት መካከል ዋነኛው ፍቅር ነው። በተጨማሪም ሰው ብዙ ነገር የማወቅና ያገኘውን እውቀት ከማንኛውም እንስሳ በላቀ መልኩ በማስተዋል ተግባራዊ የማድረግ ችሎታ አለው። በተጨማሪም ሰው የተፈጠረው እንደ እንስሳት በደመ ነፍስ እንዲመራ ሳይሆን ነፃ ምርጫ እንዲኖረው ተደርጎ ነው።

[በገጽ 15 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ቺምፓንዚዎች ለሚኖሩበት አካባቢ ፍጹም ተስማሚ ሆነው የተፈጠሩ ተጫዋችና የማወቅ ጉጉት ያላቸው ፍጥረታት ናቸው

[ምንጭ]

Chimpanzees, top right: Corbis/Punchstock/Getty Images; lower left and right: SuperStock RF/SuperStock; Jane Goodall: © Martin Engelmann/age fotostock

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

© Photononstop/SuperStock