በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጥሩ ወይም ክፉ ሰዎች እንድንሆን የሚያደርገን ምንድን ነው?

ጥሩ ወይም ክፉ ሰዎች እንድንሆን የሚያደርገን ምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ጥሩ ወይም ክፉ ሰዎች እንድንሆን የሚያደርገን ምንድን ነው?

ታሪክ መዝገብ ስለ ጥላቻና ደም መፋሰስ በሚገልጹ ዘገባዎች የተሞላ ነው። እንደዚያም ሆኖ ብዙውን ጊዜ አሳዛኝ ክስተቶች በሚፈጠሩበት ወቅት ሰዎች ደግነትና ራስን መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ የሚንጸባረቅባቸውን አስደናቂ ነገሮች ሲያከናውኑ ይስተዋላል። ሆኖም አንደኛው ርኅራኄ የሌለው ነፍሰ ገዳይ የሚሆነውና ሌላኛው ከልብ በመራራት ሰዎችን ለመርዳት የሚነሳሳው ለምንድን ነው? አንዳንድ ጊዜ ሰዎች እንስሳዊ የሆኑ ባሕርያትን የሚያንጸባርቁትስ ለምንድን ነው?

አለፍጽምናና ሕሊና

መጽሐፍ ቅዱስ “ሰው ገና ከልጅነቱ ጀምሮ ሐሳቡ ወደ ክፋት ያዘነበለ” እንደሆነ በግልጽ ይናገራል። (ዘፍጥረት 8:21) በመሆኑም ልጆች ተንኮል መሥራት ይቀናቸዋል። (ምሳሌ 22:15) ሁላችንም ስንወለድ ጀምሮ የሚቀናን ትክክል ያልሆነ ነገር ማድረግ ነው። (መዝሙር 51:5) የወንዝ ውኃ ከሚመጣበት አቅጣጫ በተቃራኒ መቅዘፍ ቀላል እንዳልሆነ ሁሉ ጥሩ ነገር ማድረግም ብርቱ ጥረት ይጠይቃል።

ያም ሆኖ ሁላችንም ሕሊና አለን። ይህ በተፈጥሮ ያገኘነው ትክክልና ስህተት የሆነውን የመለየት ችሎታ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ባለው የሥነ ምግባር ደንብ መሠረት እንድንመራ ይገፋፋናል። በዚህም ምክንያት በሥነ ምግባር ረገድ ምንም ሥልጠና ያላገኙ ሰዎችም እንኳ ደግነት በሚንጸባረቅበት ድርጊታቸው የሚታወቁ ሊሆኑ ይችላሉ። (ሮም 2:14, 15) ይሁንና ከላይ እንደተገለጸው ልባችን ወደ ክፋት ያዘነበለ መሆኑ በውስጣችን ትግል እንዲፈጠር ሊያደርግ ይችላል። ጥሩ በማድረግና ክፉ በማድረግ መካከል በውስጣችን ትግል እንዲፈጠር የሚያደርገው ሌላው ምክንያት ምንድን ነው?

የተበከለ አካባቢ

እስስት አካባቢዋን ለመምሰል የቆዳዋን ቀለም እንደምትለዋውጥ ሁሉ ዓመፀኛ የሆኑ ሰዎችን ወዳጆቻቸው የሚያደርጉ ግለሰቦችም የእነሱን እኩይ ምግባር ማንጸባረቃቸው አይቀርም። መጽሐፍ ቅዱስ “ክፉ በማድረግ ብዙዎችን አትከተል” በማለት ያስጠነቅቃል። (ዘፀአት 23:2) በሌላ በኩል ደግሞ ሐቀኞችና ቅኖች ከሆኑ እንዲሁም ጥሩ ሥነ ምግባር ካላቸው ሰዎች ጋር ዘወትር መቀራረብ ጥሩ የሆነውን ለማድረግ ያነሳሳል።—ምሳሌ 13:20

ይሁን እንጂ ‘መጥፎ ድርጊት ከሚፈጽሙ ሰዎች ጋር ወዳጅነት እስካልመሠረትኩ ድረስ ክፋት እንድፈጽም የሚያደርገኝ ምንም ነገር አይኖርም’ ብለን ማሰብ አንችልም። ፍጹማን ስላልሆን ክፋት በአእምሯችን ጓዳ ውስጥ ተደብቆ ሊቆይ ይችላል፤ አጋጣሚውን ያገኘ ዕለት ግን ይፋ ይሆናል። (ዘፍጥረት 4:7) ከዚህም በላይ ክፋት በመገናኛ ብዙኃን አማካኝነት ቤታችን ድረስ ሊመጣ ይችላል። የቪዲዮ ጨዋታዎች፣ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችና ፊልሞች ብዙውን ጊዜ ዓመፀኝነትንና በቀለኝነትን ያራግባሉ። የውጭም ይሁን የአገር ውስጥ ዜናዎችን አዘውትረን መከታተላችን እንኳ ሰዎችን ለመከራና ሰቆቃ በሚዳርጉ የክፋት ድርጊቶች መዘግነናችንን እንድናቆም ሊያደርገን ይችላል።

ለመሆኑ አካባቢያችን በመጥፎ ድርጊት እንዲበከል መንስኤ የሆነው ነገር ምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “መላው ዓለም ግን በክፉው ኃይል ሥር ነው” በማለት መልሱን ይሰጠናል። (1 ዮሐንስ 5:19) መጽሐፍ ቅዱስ “ክፉው” የተባለው ሰይጣን ዲያብሎስ ውሸታምና ነፍሰ ገዳይ እንደሆነ በግልጽ ይናገራል። (ዮሐንስ 8:44) ሰይጣን ዲያብሎስ ይህ ዓለም በሚያሳድረው ተጽዕኖ በመጠቀም ክፋትን ያስፋፋል።

‘በአመለካከታችንና በተግባራችን ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ እነዚህ ሁሉ ምክንያቶች ስላሉ ለምናደርጋቸው ነገሮች ልንወቀስ አይገባም’ በማለት አንዳንዶች ለክፋት ድርጊታቸው ሰበብ ለማቅረብ ይሞክሩ ይሆናል። እውነታው ግን ምንድን ነው? የመኪና ወይም የመርከብ መሪ አቅጣጫን እንደሚቆጣጠር ሁሉ አእምሮም ሰውነትን ይቆጣጠራል።

ጥሩ ወይም ክፉ ማድረግ—ምርጫው የአንተ ነው

ሰዎች ሆነ ብለው የሚፈጽሙት ነገር ጥሩም ይሁን ክፉ ከድርጊት በፊት ሐሳብ ይቀድማል። አንድ ሰው መልካም ዘር ከዘራ ጥሩ ፍሬ እንደሚያጭድ ሁሉ እኛም የምናስበው ነገር አዎንታዊና ንጹሕ ከሆነ ጥሩ ነገር ለመሥራት እንነሳሳለን። በተቃራኒው ደግሞ በአእምሯችን ውስጥ የራስ ወዳድነት ምኞት እንዲያቆጠቁጥ ከፈቀድን መጥፎ ፍሬ ማጨዳችን ማለትም የተለያዩ የክፋት ድርጊቶችን መፈጸማችን አይቀርም። (ሉቃስ 6:43-45፤ ያዕቆብ 1:14, 15) በመሆኑም አንድ ሰው ጥሩ ወይም ክፉ የሚሆነው በራሱ ምርጫ ነው ሊባል ይችላል።

ደስ የሚለው ነገር፣ መጽሐፍ ቅዱስ መልካም ማድረግን መማር እንደሚቻል ይናገራል። (ኢሳይያስ 1:16, 17) ፍቅር ጥሩ የሆነውን ነገር ለማድረግ የሚገፋፋ ኃይል ነው፤ ምክንያቱም “ፍቅር በባልንጀራው ላይ ክፉ አያደርግም።” (ሮም 13:10) ለሰዎች ፍቅር ካዳበርን በማንም ላይ ክፉ መሥራት የማይታሰብ ነገር ይሆናል።

በፔንሲልቬንያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ የሚኖረው ሬይ ይህንን ከራሱ ተሞክሮ ተገንዝቧል። ሬይ ድብድብ ተምሮ ስላደገ ገና በልጅነቱ ፓንች (ቡጢኛው) የሚል ቅጽል ስም አትርፎ ነበር። በተጨማሪም የግልፍተኝነት ባሕርይው ያስቸግረው ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ ሲያውል ግን ቀስ በቀስ ለውጥ አደረገ። ይሁን እንጂ ይህን ማድረግ ለእሱ ሁልጊዜ ቀላል አልነበረም። ሬይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ጳውሎስ “ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ ስፈልግ ከእኔ ጋር ያለው ግን መጥፎ ነገር ነው” በማለት የተናገረው ዓይነት ስሜት የሚሰማው ጊዜ ነበር። (ሮም 7:21) ለዓመታት ከፍተኛ ጥረት ካደረገ በኋላ ግን ‘ክፉን በመልካም ማሸነፍ’ ችሏል።—ሮም 12:21

ጥሩ ወይም ‘ደጋግ በሆኑ ሰዎች ጎዳና ለመሄድ’ ጥረት ማድረግ አስፈላጊ ነው የምንለው ለምንድን ነው? (ምሳሌ 2:20-22) ምክንያቱም የኋላ ኋላ ጥሩነት በክፋት ላይ ድል ይቀዳጃል። መጽሐፍ ቅዱስ “ክፉ ሰዎች ይጠፋሉ፤ . . . ለአፍታ እንጂ፣ ክፉ ሰው አይዘልቅም፤ . . . ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፤ በታላቅ ሰላምም ሐሤት ያደርጋሉ” በማለት ይናገራል። (መዝሙር 37:9-11) አምላክ የክፋትን ርዝራዦች በሙሉ ያስወግዳል። ጥሩ የሆነውን ነገር ዘወትር ለማድረግ ከልባቸው የሚጥሩ ሰዎች ከፊታቸው እንዴት ያለ ታላቅ ተስፋ ይጠብቃቸዋል!

ይህን አስተውለኸዋል?

ለምናደርገው ነገር ኃላፊነቱን መውስድ ያለበት ማን ነው?—ያዕቆብ 1:14

አካሄዳችንን ማስተካከል እንችላለን?—ኢሳይያስ 1:16, 17

ክፋት ማብቂያ ይኖረው ይሆን?—መዝሙር 37:9, 10፤ ምሳሌ 2:20-22

[በገጽ 21 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

አንድ ሰው ጥሩ ወይም ክፉ የሚሆነው በራሱ ምርጫ ነው