በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለራሴ ያለኝ ግምት ከፍ እንዲል ምን ላድርግ?

ለራሴ ያለኝ ግምት ከፍ እንዲል ምን ላድርግ?

የወጣቶች ጥያቄ

ለራሴ ያለኝ ግምት ከፍ እንዲል ምን ላድርግ?

አዎ | አይ

ራስህን በመስታወት ስትመለከት መልክህን ትወደዋለህ?

የሚደነቁ ችሎታዎች እንዳሉህ ይሰማሃል?

የእኩዮችን ተጽዕኖ መቋቋም ትችላለህ?

ተገቢ የሆኑ ትችቶችን ቅር ሳይልህ መቀበል ትችላለህ?

ሌሎች ተገቢ ያልሆነ አስተያየት ሲሰነዝሩብህ ችለህ ታልፋለህ?

ሌሎች እንደሚወዱህ ይሰማሃል?

ለጤንነትህ እንክብካቤ ታደርጋለህ?

ሌሎች ሲሳካላቸው ደስ ይልሃል?

ጠቅለል ባለ መልኩ ራስህን ስታየው የተሳካልህ ሰው እንደሆንክ ይሰማሃል?

ከላይ ከተጠቀሱት ጥያቄዎች ውስጥ ለአብዛኞቹ የሰጠኸው መልስ “አይ” የሚል ከሆነ ለራስህ ያለህ ዝቅተኛ ግምት ጠንካራ ጎኖችህ እንዳይታዩህ አሳውሮሃል ሊባል ይችላል። ይህ ርዕሰ ትምህርት ጠንካራ ጎኖችህን ለይተህ እንድታውቅ ይረዳሃል!

አብዛኞቹ ወጣቶች ስለ መልካቸውና ችሎታቸው በሚያስቡበት ወይም ራሳቸውን ከእኩዮቻቸው ጋር በሚያወዳድሩበት ጊዜ ከሚፈጠርባቸው የበታችነት ስሜት ጋር ይታገላሉ። አንተም ከእነዚህ ወጣቶች አንዱ እንደሆንክ ይሰማሃል? ከሆነ አይዞህ፣ ብቻህን አይደለህም!

“ፍጹም አለመሆኔ አንገቴን እንድደፋ አድርጎኛል። በራሴ ላይ ዋነኛዋ ስህተት ለቃቃሚ ሌላ ሳይሆን እኔው ነኝ።”—ሌቲስያ *

“የቱንም ያህል ቆንጆ ወይም መልከ መልካም ብትሆኑ ምንጊዜም በመልክ ከእናንተ የሚበልጡ ሰዎች ያጋጥሟችኋል።”—ሄሊ

“ከሌሎች ጋር ስሆን እሸማቀቃለሁ። ሰዎች ዝቅ አድርገው የሚመለከቱኝ ስለሚመስለኝ እጨነቃለሁ።”—ሪቸል

አንተም ከላይ እንደተጠቀሱት ወጣቶች የሚሰማህ ከሆነ ተስፋ አትቁረጥ። እርዳታ ማግኘት ትችላለህ። ለራስህ ያለህን ግምት ከፍ በማድረግ አዎንታዊ አመለካከት እንዲኖርህ የሚረዱህን ሦስት ዘዴዎች ተመልከት።

1. ጓደኞች አፍራ

ቁልፍ ጥቅስ። “ወዳጅ ምንጊዜም ወዳጅ ነው፤ ወንድምም ለክፉ ቀን ይወለዳል።”—ምሳሌ 17:17

ምን ማለት ነው? ጥሩ ወዳጅ ወይም ጓደኛ ችግር በሚያጋጥምህ ጊዜ አስተማማኝ ድጋፍ ሊሆንልህ ይችላል። (1 ሳሙኤል 18:1፤ 19:2) የሚያስብልህ ሰው እንዳለ ማወቅህ ብቻ እንኳ በራስ የመተማመን መንፈስ እንዲኖርህ ሊያደርግ ይችላል። (1 ቆሮንቶስ 16:17, 18) ስለዚህ በአንተ ላይ በጎ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ከሚችሉ ሰዎች ጋር ተቀራረብ።

“እውነተኛ ጓደኞች የተስፋ ቢስነት ስሜት ሲቆጣጠራችሁ እያዩ ዝም አይሉም።”—ዳነል

“አንዳንድ ጊዜ በጣም አስፈላጊ የሆነው ነገር ከልብ የሚያስብላችሁ ሰው መኖሩን ማወቅ ነው። ይህን ማወቃችሁ ዋጋ ቢስ እንዳልሆናችሁ እንዲሰማችሁ ሊያደርግ ይችላል።”—ሄዘር

መጠንቀቅ ያለብህ ነገር፦ የምትይዛቸው ጓደኞች፣ ከእነሱ ጋር ለመመሳሰል ብለህ ያልሆንከውን ሆነህ እንድትቀርብ የሚያደርጉ ሳይሆኑ እውነተኛ ማንነትህ እንዲወጣ የሚያደርጉ መሆን አለባቸው። (ምሳሌ 13:20፤ 18:24፤ 1 ቆሮንቶስ 15:33) የሌሎችን ትኩረት ለመሳብ ብለህ ጥበብ የጎደለው ነገር የምታደርግ ከሆነ በራስህ እንድታፍር ብሎም መጠቀሚያ እንደሆንክ እንዲሰማህ ከማድረግ ውጪ የሚፈይደው ነገር የለም።—ሮም 6:21

አሁን የአንተ ተራ ነው። ለራስህ ያለህ ግምት ከፍ እንዲል ሊረዳህ የሚችል የአንድ ጓደኛህን ስም ከታች ባለው ክፍት ቦታ ላይ ጻፍ።

․․․․․

ከላይ ስሙን ከጠቀስከው ሰው ጋር የተወሰነ ጊዜ ለማሳለፍ ለምን ቀጠሮ አትይዝም? ማስታወሻ፦ ግለሰቡ የግድ እኩያህ መሆን የለበትም።

2. ሌሎችን የሚጠቅም ነገር አከናውን

ቁልፍ ጥቅስ። “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል።”—የሐዋርያት ሥራ 20:35

ምን ማለት ነው? ሌሎችን ስትረዳ ራስህንም እየረዳህ ነው። እንዴት? አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “ለጋስ ይበለጽጋል፤ ሌሎችን የሚያረካም ራሱ ይረካል” ይላል። (ምሳሌ 11:25) ሌሎችን ስትረዳ ለራስህ ያለህ ግምት ከፍ እንደሚል ምንም ጥርጥር የለውም! *

“ለሌሎች ምን ላደርግላቸው እንደምችል ስለማስብ ባለሁበት ጉባኤ ያሉ ወንድሞችና እህቶች የሚያስፈልጋቸውን ነገር ለማሟላት እጥራለሁ። ለሌሎች ፍቅርና ትኩረት መስጠቴ ለራሴ ጥሩ ስሜት እንዲኖረኝ ያደርገኛል።”—ብሪአነ

“በክርስቲያናዊው አገልግሎት መካፈል ስለራሳችሁ ማሰብ ትታችሁ ስለ ሌሎች ማሰብ እንድትጀምሩ ስለሚያደርጋችሁ አርኪ ሥራ ነው።”—ጄቨን

መጠንቀቅ ያለብህ ነገር፦ ሌሎችን የምትረዳው በምላሹ አንድ ነገር ለማግኘት ብቻ ብለህ መሆን የለበትም። (ማቴዎስ 6:2-4) የተሳሳተ ዝንባሌ ይዘህ ሌሎችን መርዳትህ ምንም አይጠቅምህም። ሌሎችን የምትረዳው በመጥፎ ዝንባሌ ተነሳስተህ ከሆነ ብዙውን ጊዜ ሰዎች ይህን ማስተዋላቸው አይቀርም!—1 ተሰሎንቄ 2:5, 6

አሁን የአንተ ተራ ነው። እስቲ ከዚህ ቀደም ስለረዳኸው ሰው አስብ። ያ ሰው ማን ነበር? ያደረግክለት ነገርስ ምን ነበር?

․․․․․

ከዚያ በኋላ ምን ተሰማህ?

․․․․․

እስቲ ደግሞ ልትረዳው ስለምትችለው ሌላ ሰው አስብ። ይህን ሰው እንዴት ልትረዳው እንደምትችል ጻፍ።

․․․․․

3. ስህተት ብትሠራ ተስፋ አትቁረጥ

ቁልፍ ጥቅስ። “ሁሉም ኃጢአት ሠርተዋል፤ የአምላክንም ክብር ማንጸባረቅ ተስኗቸዋል።”—ሮም 3:23

ምን ማለት ነው? ፍጹም አለመሆንህ የማይታበል ሐቅ ነው። በሌላ አባባል ስህተት የሆኑ ነገሮችን የምትናገርበት ወይም የምታደርግበት ጊዜ ይኖራል ማለት ነው። (ሮም 7:21-23፤ ያዕቆብ 3:2) ስህተት ከመሥራት ሙሉ በሙሉ መራቅ ባትችልም ስህተት በምትሠራበት ጊዜ የሚሰማህን ስሜት ግን መቆጣጠር ትችላለህ። መጽሐፍ ቅዱስ “ጻድቅ ሰባት ጊዜ እንኳ ቢወድቅ ይነሣል” ይላል።—ምሳሌ 24:16

“አንዳንድ ጊዜ የበታችነት ስሜት የሚሰማን የራሳችንን ደካማ ጎን ከሌሎች ጠንካራ ጎን ጋር ስለምናወዳድር ነው።”—ኬቨን

“ሁሉም ሰው ጥሩም ሆነ መጥፎ ጎን አለው። ባሉን ጥሩ ባሕርያት ልንኮራ፣ መጥፎ ጎናችንን ደግሞ ለማስተካከል መጣር ይገባናል።”—ሎረን

መጠንቀቅ ያለብህ ነገር፦ ፍጹም አለመሆንህ ኃጢአት ለመሥራት ሰበብ ሊሆንህ አይገባም። (ገላትያ 5:13) ሆን ብለህ መጥፎ ነገር መፈጸምህ ፈጽሞ ልታጣው የማይገባውን ወዳጅነት ማለትም ከይሖዋ አምላክ ጋር ያለህን ዝምድና እንድታበላሸው ያደርግሃል!—ሮም 1:24, 28

አሁን የአንተ ተራ ነው። ልታሻሽለው የምትፈልገውን ባሕርይ ከታች ባለው ክፍት ቦታ ላይ ጻፍ።

․․․․․

ከጠቀስከው ባሕርይ አጠገብ የዛሬውን ቀን ጻፍ። ማሻሻል የምትችልበትን መንገድ በተመለከተ ምርምር አድርግ፤ ከዚያም ከአንድ ወር በኋላ ምን ያህል መሻሻል እንዳደረግህ ለማወቅ ራስህን ገምግም።

ዋጋማነትህ የሚለካው በምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ “አምላክ ከልባችን ይበልጥ ታላቅ” መሆኑን ይናገራል። (1 ዮሐንስ 3:20) ይህ ማለት ደግሞ አምላክ ለአንተ ሊታይህ የማይችለውን ውስጣዊ ማንነትህን መመልከት ስለሚችል በእሱ ዘንድ ያለህ ዋጋማነት አንተ ለራስህ ከምትሰጠው ዋጋ እጅግ ይበልጣል። ይሁን እንጂ ፍጹም አለመሆንህ በዋጋማነትህ ላይ የሚያመጣው ለውጥ አለ? እስቲ ትንሽ የተቀደደ የ100 ብር ኖት እንዳለህ አድርገህ አስብ። ትንሽ ስለተቀደደ ትጥለዋለህ? ወይም ምንም ዋጋ እንደሌለው አድርገህ ትመለከተዋለህ? ይህ ፈጽሞ የማይታሰብ ነው! ቀዳዳ ኖረውም አልኖረው ኖቱ ያው 100 ብር ነው።

አምላክ ለአንተ የሚሰጥህን ዋጋ በተመለከተም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። እሱን ለማስደሰት የምታደርገው ጥረት ላንተ ምንም ያህል ከቁብ የማይገባ ቢመስልህም እሱ ግን ያስተውለዋል፤ እንዲሁም ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል! መጽሐፍ ቅዱስም “[አምላክ] የምታከናውኑትን ሥራ እንዲሁም ለስሙ ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመፀኛ አይደለም” በማለት ያረጋግጥልናል።—ዕብራውያን 6:10

www.watchtower.org/ype በሚለው ድረ ገጽ ላይ “Young People Ask” በሚል አምድ ሥር ተጨማሪ ርዕሶችን ማግኘት ይቻላል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.15 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

^ አን.30 ከይሖዋ ምሥክሮች አንዱ ከሆንህ የመንግሥቱን መልእክት ለሌሎች በማካፈል ልታገኝ ስለምትችለው ታላቅ ደስታ አስብ።—ኢሳይያስ 52:7

ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች

ከዚህ በታች በተጠቀሱት ምክንያቶች የተነሳ ለራስህ ያለህ ግምት ዝቅ እንዳለ ሆኖ ቢሰማህ ምን ታደርጋለህ?

እኩዮችህ ቢተቹህ

ከሌሎች ጋር እኩል እንዳልሆንክ ቢሰማህ

የሚታይህ ደካማ ጎንህ ብቻ ቢሆን

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“አንድ ሰው በጣም የሚማርክ መልክ ኖሮትም እንኳ አስቀያሚ እንደሆነ ሊሰማው ይችላል። ወይም ደግሞ አንድ ሰው እምብዛም የማይማርክ መልክ ኖሮትም በጣም ቆንጆ እንደሆነ ሊሰማው ይችላል። ልዩነት የሚያመጣው አመለካከታችን ነው።”—አሊሰ

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

እኩዮችህ ምን ይላሉ?

በጣም ጠንካራ የሚባል ሕንፃ እንኳ ደግፎ ያቆመው ነገር አለ፤ ከዚህም በላይ አንዳንድ ጊዜ ጥገና ያስፈልገዋል። አንዲት ጓደኛዬ ለእኔ ፍቅር እንዳላት በሚያሳይ መንገድ ስታወራኝ ሌላው ቀርቶ ፈገግታ ስታሳየኝ ወይም እቅፍ ስታደርገኝ ብርታትና ድጋፍ እንዳገኘሁ ሆኖ ይሰማኛል።

ሌሎች ባላቸው በጎ ጎን ከመቅናት ይልቅ እነሱ በእኛ ጥሩ ባሕርይ ሊጠቀሙ እንደሚችሉ ሁሉ እኛም በመልካም ባሕርያቸው ልንጠቀም እንችላለን።

[ሥዕሎች]

ኦብሪ

ሎረን

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የብር ኖት ትንሽ ስለተቀደደ ብቻ ዋጋው አይቀንስም። በተመሳሳይም ፍጹም አለመሆንህ በአምላክ ዘንድ ያለህን ዋጋማነት አይቀንሰውም