በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መሰናክሎቹን ለማለፍ ዝግጁ ሁን

መሰናክሎቹን ለማለፍ ዝግጁ ሁን

መሰናክሎቹን ለማለፍ ዝግጁ ሁን

“አዲስ ለተወለደው ልጃችን ጤንነት ስል ማጨስ ለማቆም ወሰንኩ። በመሆኑም ‘ማጨስ ክልክል ነው’ የሚል ምልክት ቤታችን ውስጥ ለጠፍኩ። ልክ ከአንድ ሰዓት በኋላ የኒኮቲን ሱሴ ውስጤን እንደ ሱናሚ ሲያናውጠው ግን ሲጋራ ለኮስኩ።”—ዮሺሚትሱ፣ ጃፓን

የዮሺሚትሱ ተሞክሮ እንደሚያሳየው ማጨስ የማቆም ሂደት የራሱ የሆኑ መሰናክሎች አሉት። ከዚህም በላይ ሱሱ አገርሽቶባቸው በመሰናክሉ ከወደቁት አጫሾች መካከል 90 በመቶ የሚሆኑት ማጨሳቸውን መቀጠላቸውን ጥናቶች ያመለክታሉ። ስለዚህ ማጨስ ለማቆም እየጣርክ ከሆነ የሚያጋጥሙህን መሰናክሎች ለማለፍ አስቀድመህ ብትዘጋጅ ስኬታማ የመሆን ዕድልህ ከፍተኛ ይሆናል። ለመሆኑ ብዙ ጊዜ የሚያጋጥሙት መሰናክሎች የትኞቹ ናቸው?

የኒኮቲን ሱስ፦ ሱስህ በጣም የሚያይለው ሲጋራ ካቆምክ በኋላ ባሉት ሦስት ቀናት ውስጥ ሲሆን ከሁለት ሳምንት ገደማ በኋላ ግን ቀስ በቀስ እየጠፋ ይመጣል። ቀደም ሲል ያጨስ የነበረ አንድ ሰው እንደተናገረው ከሆነ ሱሱ በሚቀሰቀስበት ወቅት “የማጨስ ፍላጎቱ እንደ ባሕር ሞገድ አልፎ አልፎ የሚመጣ እንጂ ፋታ የማይሰጥ አይደለም።” ይሁን እንጂ ከዓመታት በኋላ እንኳን የማጨስ ፍላጎት ድንገት ሊመጣብህ ይችላል። እንዲህ ዓይነቱ ስሜት ሲመጣብህ ቶሎ እጅህን አትስጥ። ለአምስት ለስድስት ደቂቃ ብትታገሥ አምሮቱ ማለፉ አይቀርም።

ማጨስ ከማቆም ጋር ተያይዘው የሚመጡ ሌሎች ችግሮች፦ ማጨስ የሚያቆሙ ሰዎች መጀመሪያ ላይ ንቁ ሆኖ መቆየት ወይም በአንድ ነገር ላይ ማተኮር አስቸጋሪ ይሆንባቸዋል፤ እንዲሁም በቀላሉ ክብደታቸው ሊጨምር ይችላል። በተጨማሪም የሕመም ስሜት ሊሰማቸው፣ ሊያስላቸው እንዲሁም ሰውነታቸውን ሊያሳክካቸውና ሊያልባቸው ይችላል። ከዚህም ባሻገር ስሜታቸው ሊለዋወጥ ይኸውም ትዕግሥት ሊያጡና ቁጠኞች ሊሆኑ አልፎ ተርፎም የመንፈስ ጭንቀት ሊያጋጥማቸው ይችላል። ይሁን እንጂ ማጨስ ከማቆም ጋር ተያይዘው የሚመጡት አብዛኞቹ ችግሮች ከአራት እስከ ስድስት ባሉት ሳምንታት ውስጥ እየጠፉ ይሄዳሉ።

በዚህ ወሳኝ የሆነ ጊዜ ውስጥ ችግሮቹን እንድትቋቋም የሚረዱ አንዳንድ ነገሮችን ማድረግ ትችላለህ። ለምሳሌ ያህል፦

● ከወትሮ በተለየ ረዘም ላለ ሰዓት ለመተኛት ሞክር።

● ብዙ ውኃ ወይም ጭማቂ ጠጣ። ለጤና ተስማሚ የሆኑ ምግቦችን ተመገብ።

● መጠነኛ የሆነ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አድርግ።

● በረጅሙ ተንፍስ፤ እንዲህ በምታደርግበት ጊዜም ንጹሕ አየር ሳንባህን ሲሞላው በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ።

ሱስህን የሚቀሰቅሱ ነገሮች፦ የማጨስ ፍላጎትህ እንዲቀሰቀስ የሚያደርጉት እነዚህ ነገሮች ከአንዳንድ ድርጊቶችና ስሜቶች ጋር የተያያዙ ሊሆኑ ይችላሉ። ለምሳሌ አንዳንድ ነገሮችን ዘና ብለህ እየጠጣህ ሲጋራ የማጨስ ልማድ ይኖርህ ይሆናል። እንግዲያው ሲጋራ ለማቆም የምትፈልግ ከሆነ እንዲህ ያለውን ዘና ብሎ የመጠጣት ልማድ ማቆም አለብህ። ይዋል ይደር እንጂ ዘና ብለህ መጠጣት የምትችልበት ጊዜ መምጣቱ አይቀርም።

ይህ እንዳለ ሆኖ ኒኮቲኑ ከሰውነትህ ሙሉ በሙሉ ከወጣ በኋላም አእምሮህ ይህን ልማድ ለረጅም ጊዜ ሳይረሳው ሊቆይ ይችላል። ቀደም ባለው ርዕስ ላይ የተጠቀሰው ቶርበን “ማጨስ ካቆምኩ አሥራ ዘጠኝ ዓመት ቢሆነኝም አሁንም በእረፍት ሰዓት ቡና ስጠጣ ለማጨስ እፈተናለሁ” በማለት ሁኔታውን ሳይሸሽግ ተናግሯል። በአጠቃላይ ሲታይ ግን በአእምሮ ላይ የተቀረጸው በማጨስና በአንዳንድ ድርጊቶች መካከል ያለው ቁርኝት እየተዳከመ ስለሚመጣ ተጽእኖ የማሳደር ኃይሉ መጥፋቱ አይቀርም።

ከአልኮል መጠጥ ጋር በተያያዘ ግን ሁኔታው የተለየ ነው። ሰዎች የማጨስ ሱሳቸው በአብዛኛው የሚያገረሽባቸው በሚጠጡበት ወቅት በመሆኑ ማጨስ ለማቆም በምትሞክርበት ጊዜ ከአልኮልም ሆነ አልኮል ከሚጠጣባቸው ቦታዎች መራቅ ይኖርብህ ይሆናል። ይህ ሊሆን የቻለው ለምንድን ነው?

● ትንሽ አልኮል መጠጣት እንኳን በደም ውስጥ ያለው ኒኮቲን የሚፈጥረውን የእርካታ ስሜት ከፍ እንዲል ያደርጋል።

● በአብዛኛው ሰዎች ተሰባስበው በሚጠጡበት ጊዜ ማጨስ የተለመደ ድርጊት ነው።

● አልኮል የማመዛዘን ችሎታን የሚያዛባ ከመሆኑም በላይ ዓይን ያወጣ ድርጊት ወደ መፈጸም ይመራል። በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ ‘ወይን ጠጅ ማስተዋልን እንደሚወስድ’ መናገሩ የተገባ ነው።—ሆሴዕ 4:11, 12

አብረህ የምትውላቸው ሰዎች፦ መራጭ ሁን። ለምሳሌ ከሚያጨሱ ወይም እንድታጨስ ከሚገፋፉህ ሰዎች ጋር አላስፈላጊ ቅርርብ አትፍጠር። በተጨማሪም በማሾፍ ሊሆን ይችላል ማጨስ ለማቆም የምታደርገውን ጥረት ከሚያጣጥሉብህ ሰዎች ራቅ።

ስሜቶች፦ ሱሳቸው ካገረሸባቸው ሰዎች መካከል ሁለት ሶስተኛ የሚሆኑት በሱሱ ከመሸነፋቸው በፊት ውጥረት ውስጥ ገብተው ወይም ተበሳጭተው እንደነበረ አንድ ጥናት አመልክቷል። አንዳንድ ስሜቶች የማጨስ ፍላጎትህን ከቀሰቀሱብህ ውኃ በመጠጣት፣ ማስቲካ በማኘክ፣ የእግር ጉዞ በማድረግ ወይም በመሳሰሉት ነገሮች የማጨስ ስሜትህን ለመርሳት ጥረት አድርግ። ወደ አምላክ በመጸለይ፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥቂት ገጾችን በማንበብ ወይም በመሳሰሉት መንገዶች አእምሮህን አዎንታዊ በሆኑ ሐሳቦች ለመሙላት ሞክር።—መዝሙር 19:14

ሰበብ አስባቦችን አስወግድ

አንድ ጊዜ ብቻ ሳብ ባደርግስ?

እውነታው፦ አንድ ጊዜ ብቻ ሳብ ማድረግ እንኳ በአንጎልህ ውስጥ ከሚገኙት ኒኮቲን ተቀባይ ሴሎች መካከል 50 በመቶ የሚሆኑትን ለሦስት ሰዓት ያህል ሊያረካ ይችላል። ታዲያ ይህ ምን ውጤት ያስከትላል? በአብዛኛው ሱሱ ሙሉ በሙሉ ያገረሻል።

ማጨሴ የሚሰማኝን ውጥረት እንድቋቋም ይረዳኛል።

እውነታው፦ እንዲያውም ኒኮቲን በውጥረት ጊዜ የሚመነጩ ሆርሞኖችን መጠን እንደሚጨምር ጥናቶች አመልክተዋል። አንድ ሰው ማጨሱ የገጠመውን ውጥረት እንዳቃለለለት ሆኖ ይሰማው ይሆናል፤ ይሁንና በአብዛኛው እንዲህ እንዲሰማው የሚያደርገው ማጨስ ከማቆም ጋር ተያይዘው የሚመጡት ችግሮች ለጊዜው መወገዳቸው ሊሆን ይችላል።

ለረጅም ዓመታት ስላጨስኩ ከአሁን በኋላ ማቆም የምችል አይመስለኝም።

እውነታው፦ አፍራሽ አመለካከት መያዝ ወኔ ይሰልባል። መጽሐፍ ቅዱስ “በመከራ ጊዜ ፈራ ተባ ካልህ፣ ዐቅምህ ምንኛ ደካማ ነው!” ይላል። (ምሳሌ 24:10) ስለዚህ አይሆንልኝም የሚል አስተሳሰብ እንዳይጠናወትህ ተጠንቀቅ። ማጨስ ለማቆም ልባዊ ፍላጎት ያለውና በዚህ መጽሔት ውስጥ የተገለጹትን የመሰሉ ጠቃሚ መመሪያዎችን ሥራ ላይ የሚያውል ማንኛውም ሰው ሊሳካለት ይችላል።

ማጨስ ከማቆም ጋር ተያይዘው የሚመጡትን ችግሮች መቋቋም አልችልም።

እውነታው፦ ማጨስ ከማቆም ጋር ተያይዘው የሚመጡ ችግሮችን መቋቋም ከባድ እንደሆነ ባይካድም ችግሮቹ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ቀስ በቀስ እየጠፉ ይሄዳሉ። ስለዚህ አታወላውል! የማጨስ አምሮትህ ከወራት ወይም ከዓመታት በኋላ ቢቀሰቀስብህ እንኳን የደቂቃዎች ጉዳይ እንጂ ያልፋል፤ ብቻ ሲጋራ እንዳትለኩስ ተጠንቀቅ።

የአእምሮ ሕመም አለብኝ።

እውነታው፦ እንደ መንፈስ ጭንቀት ወይም ስኪዞፍሬንያ ያለ የአእምሮ በሽታ ካለብህና ሕክምና በመከታተል ላይ ከሆንክ ዶክተርህ ማጨስ እንድታቆም እንዲረዳህ ጠይቀው። ሐኪምህ ከጎንህ ለመቆም ፈቃደኛ ሊሆን ይችላል፤ ምናልባትም ማጨስ ማቆምህ በሕመምህ ወይም በምትወስዳቸው መድኃኒቶች ላይ የሚያሳድረውን ተጽእኖ ከግምት በማስገባት በምትከታተለው ሕክምና ላይ ለውጥ ሊያደርግ ይችላል።

አገርሽቶብኝ ዳግመኛ ባጨስ እንደማይሳካልኝ በማሰብ ተስፋ እቆርጣለሁ።

እውነታው፦ ብዙዎች ማጨስ ለማቆም በሚሞክሩበት ጊዜ እንደሚያጋጥማቸው አንተም አንድ ዓይነት መሰናክል አጋጥሞህ ብታጨስ ሁኔታህ ተስፋ ቢስ ነው ማለት አይደለም። ከወደቅክበት በመነሳት ጉዞህን ቀጥል። ወደቅክ ማለት አልተሳካልህም ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ አልተሳካልህም የሚባለው እንደወደቅክ ስትቀር ነው። ስለዚህ ጥረት ማድረግህን አታቁም። በመጨረሻ ድል ማድረግህ አይቀርም!

ለ26 ዓመታት ያጨሱትና ካቆሙ ከ30 ዓመት በላይ የሆናቸውን የሮሙአልዶን ተሞክሮ እንመልከት። እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “ለምን ያህል ጊዜ እንዳገረሸብኝ መቁጠር ያዳግተኛል። ሱሴ ባገረሸብኝ ቁጥር ተስፋ ቢስ እንደሆንኩ ስለሚሰማኝ በራሴ ክፉኛ አዝን ነበር። ከይሖዋ አምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና እንዲኖረኝ ለማድረግ ቁርጥ አቋም ከወሰድኩና በጥረቴ እንዲረዳኝ ደጋግሜ ከጸለይኩ በኋላ ግን ሙሉ በሙሉ እርግፍ አድርጌ ለመተው ቻልኩ።”

በዚህ ተከታታይ ርዕስ የመጨረሻው ክፍል ላይ ከሲጋራ ሱስ የተላቀቀ ደስተኛ ሰው እንድትሆን የሚያስችሉህን አንዳንድ ሐሳቦች እንመለከታለን።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

በዚያም ሆነ በዚህ ገዳይ ነው

ትንባሆ በብዙ መንገዶች ጥቅም ላይ ይውላል። እንዲያውም አንዳንድ የትንባሆ ምርቶች ለጤና ይጠቅማሉ የሚባሉ ምግቦችና የዕፅዋት መድኃኒቶች በሚሸጡባቸው መደብሮች ውስጥ ይገኛሉ። ይሁን እንጂ “ትንባሆ በምንም መልክ ይቅረብ ገዳይ ነው” በማለት የዓለም የጤና ድርጅት ገልጿል። በትንባሆ አማካኝነት የሚመጡ ለምሳሌ የካንሰር፣ የልብና የደም ሥር በሽታዎች ሞት ሊያስከትሉ ይችላሉ። በተጨማሪም የሚያጨሱ ነፍሰ ጡር ሴቶች በፅንሱ ላይ ጉዳት ሊያደርሱ ይችላሉ። የትንባሆ ውጤቶች ብዙ ጊዜ የሚዘጋጁት በምን መልክ ነው?

ቤት ውስጥ የሚዘጋጅ ሲጋራ፦ እነዚህ በእጅ የሚጠቀለሉ ትናንሽ ሲጋራዎች ኢትዮጵያን ጨምሮ በአንዳንድ አገሮች ይጨሳሉ። በእስያ አገሮች ውስጥ ቢዲ በመባል የሚታወቁት እነዚህ ሲጋራዎች በእነዚህ አካባቢዎች በብዛት ጥቅም ላይ ይውላሉ። እንዲህ ያሉ ሲጋራዎች ከመደበኛው ሲጋራ ጋር ሲነጻጸር በጣም ብዙ ኒኮቲንና ካርቦን ሞኖክሳይድ እንዲሁም ታር የተባለ መርዛማ ንጥረ ነገር ወደ ሳንባ ያስገባሉ።

ሲጋር፦ ሲጋር የሚዘጋጀው ትንባሆውን በራሱ በትንባሆ ቅጠል ወይም ከትንባሆ በተሠራ ወረቀት በመጠቅለል ሲሆን ከመደበኛ ሲጋራ በተለየ በጣም ጥቅጥቅ ያለ ነው። የአሲድነት ባሕርይ ካለው ሲጋራ በተለየ መልኩ በትንሹ የአልካላይነት ባሕርይ ያላቸው ሲጋሮች ሳይለኮሱ እንኳን አፍ ላይ እንዳሉ ኒኮቲኑ ወደ ሰውነት ውስጥ ሊገባ ይችላል።

ክሪቴክ ወይም የቅርንፉድ ሲጋራ፦ በኢንዶኔዥያ በብዛት የተለመደው ይህ የትንባሆ ዓይነት 60 በመቶው ትንባሆ ሲሆን 40 በመቶው ደግሞ ቅርንፉድ ነው። እንዲህ ያለው ሲጋራ ከመደበኛው ሲጋራ የበለጠ ኒኮቲንና ካርቦን ሞኖክሳይድ እንዲሁም ታር የተባለ መርዛማ ንጥረ ነገር ወደ ሳንባ ያስገባል።

ፒፓ፦ ፒፓ ማጨስ የሚያስከትለው ጉዳት ሲጋራ ከማጨስ የሚተናነስ አይደለም። ምክንያቱም ሁለቱም ተመሳሳይ የሆኑ የካንሰር ሕመሞችንና ሌሎች በሽታዎችን ሊያስከትሉ ይችላሉ።

ጭስ አልባ ትንባሆ፦ ይህ ትንባሆ ማኘክን ወይም ሱረት በአፍንጫ መሳብን ይጨምራል። በደቡብ ምሥራቅ እስያ የተለመደው ማጣፈጫ የገባበት ጉትከ ከጭስ አልባ ትንባሆ ይመደባል። ትንባሆው በአፍ ላይ እንዳለ ኒኮቲኑ ወደ ደም ሥር ይገባል። ጭስ አልባ ትንባሆ መጠቀምም ቢሆን ሌሎች የትንባሆ ዓይነቶችን ከማጨስ ባልተናነሰ ጎጂ ነው።

ጋያ እና ሺሻ፦ በእነዚህ መሣሪያዎች አማካኝነት ትንባሆው ወደ አፍ ከመግባቱ በፊት በውኃ ውስጥ ያልፋል። ይሁን እንጂ ይህ ሂደት ካንሰር አምጪ የሆኑትን ጨምሮ ወደ ሳንባ የሚገቡትን መርዛማ ንጥረ ነገሮች መጠን ላይቀንስ ይችላል።

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

አንድ ሰው ማጨሱን እንዲያቆም መርዳት

አዎንታዊ አመለካከት ይኑርህ። ከመነዝነዝና ከመጨቅጨቅ ይልቅ ማመስገን ብሎም መሸለምን ጨምሮ በተለያዩ መንገዶች አድናቆትህን መግለጽ የተሻለ ውጤት ያስገኛል። “አገረሸብህ እንዴ!” ከማለት ይልቅ “እንደገና ብትሞክር እንደሚሳካልህ እርግጠኛ ነኝ” ማለትህ ይበልጥ ይረዳዋል።

ይቅር ባይ ሁን። ማጨሱን ለማቆም የሚሞክር ሰው ቢቆጣህ ወይም ቢበሳጭብህ ችለህ ለማለፍ የበኩልህን ጥረት አድርግ። “በጣም ከባድ እንደሚሆንብህ አውቃለሁ፤ ነገር ግን እንዲህ ያለ ጥረት በማድረግህ እኮራብሃለሁ” እንደሚሉ ያሉ ደግነት የሚንጸባረቅባቸውን አስተያየቶች ሰንዝር። “ከአንተ ጋር ሰላም የምንሆነው ስታጨስ ሳይሆን አይቀርም!” እንደሚሉ ያሉ አባባሎችን በምንም ዓይነት እንዳትናገር ተጠንቀቅ።

እውነተኛ ወዳጅ ሁን። መጽሐፍ ቅዱስ “ወዳጅ ምንጊዜም ወዳጅ ነው፤ ወንድምም ለክፉ ቀን ይወለዳል” ይላል። (ምሳሌ 17:17) እውነት ነው፣ ማጨስ ለማቆም በመጣጣር ላይ ለሚገኝ ሰው “ምንጊዜም” ይኸውም ሰዓቱ ምንም ይሁን ምን ወይም የግለሰቡ ስሜት ምንም ያህል ቢቀያየር ታጋሽና አፍቃሪ ለመሆን ጥረት ማድረግ ይኖርብሃል።