በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ማሸነፍ ትችላለህ!

ማሸነፍ ትችላለህ!

ማሸነፍ ትችላለህ!

አሁን ‘በርትተህ የምትሠራበት’ ጊዜ ላይ ደርሰናል። (1 ዜና መዋዕል 28:10) ስኬታማ የመሆን ዕድልህን ለማስፋት ምን የመጨረሻ እርምጃዎችን መውሰድ ትችላለህ?

ቀን ቁረጥ። የዩናይትድ ስቴትስ የጤና እና ሰብዓዊ አገልግሎት ቢሮ ከሰጠው ሐሳብ መመልከት እንደምንችለው ማጨስ ለማቆም ከቆረጥክ ይህን ውሳኔህን ባደረግህ በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ከሲጋራ በመራቅ አዲስ የሕይወት ምዕራፍ መጀመር አለብህ። እንዲህ ማድረግህ ሲጋራ የማቆም ፍላጎትህ ሳይቀዘቅዝ በውሳኔህ እንድትገፋ ይረዳሃል። ማጨስ የምታቆምበትን ዕለት በቀን መቁጠሪያህ ላይ ምልክት አድርግ። ከዚያም ቀኑን ለወዳጆችህ ንገራቸው፤ እንዲሁም ሁኔታዎችህ ቢለዋወጡም እንኳን ከዚህ ቀን ውልፍት አትበል።

ካርድ አዘጋጅ። ይህ ካርድ ከታች የተዘረዘሩትን መረጃዎች ጨምሮ ያለህን ጠንካራ ፍላጎት የሚያጠናክሩ ሌሎች ሐሳቦችን የያዘ ሊሆን ይችላል።

ማጨስ ለማቆም ያሰብክበት ምክንያት

ልትሸነፍ እንደሆነ በሚሰማህ ጊዜ የምትደውልላቸው ሰዎች ስልክ ቁጥር

እንደ ገላትያ 5:22, 23 ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ጨምሮ ወደ ግብህ እንድትደርስ የሚረዱ አንዳንድ ጠቃሚ ሐሳቦች

ማጨስ ለማቆም የሚረዳህን ካርድ ከእጅህ አትለየው፤ እንዲያውም በቀን ውስጥ ደጋግመህ አንብበው። ማጨስ ካቆምክ በኋላም ቢሆን ፍላጎቱ በሚቀሰቀስብህ ጊዜ ሁሉ ይህን ካርድ መለስ ብለህ ተመልከተው።

ከሱስህ ጋር የሚዛመዱ ልማዶችን በዘዴ ለማዛባት ሞክር። ማጨስ ለማቆም የወሰንክበት ቀን ከመድረሱ በፊት ከሱስህ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ልማዶች ሆን ብለህ ለማዛባት ሞክር። ለምሳሌ ጠዋት ከመኝታ እንደተነሳህ የማጨስ ልማድ ካለህ ማጨስህን በአንድ ሰዓት አራዝመው። በምትመገብበት ወቅት ወይም ከምግብ በኋላ የማጨስ ልማድ ካለህ ደግሞ ከዚህ ልማድ ለመውጣት ጥረት አድርግ። እንዲሁም የሚያጨሱ ሰዎች ባሉበት አካባቢ አትገኝ። በተጨማሪም ብቻህን ስትሆን ድምፅህን ከፍ አድርገህ “አመሰግናለሁ፣ ማጨስ አቁሜያለሁ” ማለትን ተለማመድ። እንደነዚህ ያሉ እርምጃዎችን መውሰድህ ማጨስ ለምታቆምበት ቀን ከማዘጋጀት ያለፈ ፋይዳ የላቸውም። ከዚህም ባሻገር ከሲጋራ ሱስ የምትላቀቅበት ቀን ቅርብ መሆኑን እንድታስታውስ ይረዱሃል።

ተዘጋጅ። ማጨስ የምታቆምበት ቀን እየቀረበ ሲመጣ እንደ ካሮት፣ ማስቲካ፣ ኦቾሎኒና ቆሎ ያሉ ሲጋራን የሚተኩ ነገሮችን በብዛት ገዝተህ አዘጋጅ። ማጨስ የምታቆምበትን ቀን ለጓደኞችህና ለቤተሰቦችህ አስታውሳቸው፤ እንዲሁም በምን መንገድ ድጋፍ ሊያደርጉልህ እንደሚችሉ ንገራቸው። አንድ ቀን ሲቀረው ደግሞ መኮስተሪያዎችንና የሲጋራ መለኮሻዎችን እንዲሁም የሲጋራ ፍላጎትህን የሚቀሰቅሱ ሌሎች ነገሮችን አስወግድ፤ በተጨማሪም ቤትህ፣ መኪናህ ወይም ኪስህ ውስጥ አሊያም በሥራ ቦታህ የቀሩ ሲጋራዎች ካሉ አስወግድ። ሲጋራን ከመሳቢያ ውስጥ ሳብ አድርጎ ማውጣት ሄዶ ከመግዛት ወይም ሌላ ሰው እንዲሰጥህ ከመጠየቅ እንደሚቀል የታወቀ ነው! በተጨማሪም አምላክን እንዲረዳህ ሳታሰልስ ለምነው፤ በተለይ ለመጨረሻ ጊዜ ካጨስክ በኋላ ልባዊ ጸሎት ማቅረብህ በጣም አስፈላጊ ነው።—ሉቃስ 11:13

ይህ ነው የማይባል ቁጥር ያላቸው ሰዎች የማይጠቅም ብሎም ጨካኝ ከነበረው ጓደኛቸው ማለትም ከሲጋራ ጋር ያላቸው ወዳጅነት እንዲያከትም አድርገዋል። አንተም እንደነሱ ማድረግ ትችላለህ። የተሻለ ጤና የሚኖርህ ከመሆኑም በላይ ከፊትህ ታላቅ ነፃነት ይጠብቅሃል።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ማጨስ ለማቆም የሚረዳህን ካርድ ከእጅህ አትለየው፤ እንዲያውም በቀን ውስጥ ደጋግመህ አንብበው