በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አብርሃም ማን ነበር?

አብርሃም ማን ነበር?

“የኬንትሮስን ችግር” ለመፍታት የተደረገ ጥረት

ጥቅምት 22, 1707 አንድ የብሪታንያ የባሕር ኃይል መርከቦች ቡድን ኢንግሊሽ ቻነል ወደሚባል ባሕር ተጉዞ ነበር። ይሁን እንጂ የሚጓዝበትን አቅጣጫ ለማወቅ የተጠቀመበት ስሌት ትክክል አልነበረም። ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? በእንግሊዝ አገር ላንድስ ኤንድ ተብሎ ከሚጠራው ቦታ በስተ ደቡብ ምዕራብ በሚገኙት አይል ኦቭ ሲሊ በሚባሉት በአትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ ባሉ ደሴቶች አካባቢ አራት መርከቦች ከቋጥኝ ጋር ተጋጭተው ተሰባበሩ። በዚህም ሳቢያ ወደ 2,000 የሚጠጉ ሰዎች አለቁ።

በዚያ ዘመን የነበሩ መርከበኞች ያሉበትን የኬክሮስ መስመር ማለትም ከምድር ወገብ በስተ ሰሜን ወይም በስተ ደቡብ የት ቦታ ላይ እንደሚገኙ በቀላሉ ማስላት ይችሉ ነበር። ይሁን እንጂ የሚገኙበትን ኬንትሮስ ማለትም ከግሪንዊች በስተ ምሥራቅ ወይም በስተ ምዕራብ ምን ያህል ርቀት እንደተጓዙ የሚያውቁበት ትክክለኛ መለኪያ አልነበራቸውም። በ18ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ በአትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ በየዓመቱ በመቶ የሚቆጠሩ መርከቦች ይጓዙ የነበሩ ሲሆን የመርከብ አደጋም የተለመደ ነበር። ይሁን እንጂ በ1707 የደረሰው ከፍተኛ አደጋ እንግሊዛውያን ለኬንትሮስ ችግር መፍትሔ እንዲያፈላልጉ አነሳስቷቸዋል።

በ1714 የብሪታንያ ፓርላማ በባሕር ላይ አንድ ቦታ በምን ያህል ኬንትሮስ ላይ እንደሚገኝ በትክክል ለይቶ ለማወቅ የሚያስችል መሣሪያ ለሚፈለስፍ ሰው የ20,000 ፓውንድ ሽልማት እንደሚሰጥ ገለጸ። ይህ ሽልማት በዛሬው ጊዜ ወደ አሜሪካ ዶላር ቢመነዘር ብዙ ሚሊዮን ዶላር ያወጣል።

ተፈታታኝ ችግር

አንድ ቦታ በባሕር ላይ በምን ያህል ኬንትሮስ ላይ እንደሚገኝ ማወቅ በጣም ተፈታታኝ ነው፤ ምክንያቱም ዝንፍ የማይል ሰዓት ያስፈልጋል። ይህን ሁኔታ ለመረዳት አንድ ምሳሌ እንመልከት፤ የምትኖረው በለንደን ነው እንበል። እኩለ ቀን ላይ አንተ ካለህበት ቦታ ጋር ተመሳሳይ በሆነ የኬክሮስ መሥመር ላይ ከምትገኝ ከአንዲት ዘመድህ ስልክ ተደወለልህ፤ ይሁን እንጂ እሷ በምትኖርበት ቦታ ላይ ሰዓቱ ከማለዳው 12 ሰዓት ነው። በሌላ አነጋገር እሷ ያለችበት ቦታ አንተ ካለህበት አካባቢ በስድስት ሰዓት ወደኋላ ይቀራል። የጂኦግራፊ እውቀት ስላለህ እሷ የምትኖረው ጀምበር ገና እየወጣች ባለችበት በሰሜን አሜሪካ እንደሆነ በትክክል ትረዳለህ። አሁን በዓለም አቀፉ የጊዜ አቆጣጠር መሠረት ሳይሆን ከፀሐይ አቀማመጥ አንጻር ሴትየዋ ያለችበትን ቦታ አንዲትም ሴኮንድ ሳታዛንፍ ትክክለኛውን ሰዓት እንደምታውቅ አድርገህ አስብ። እንዲህ ከሆነ እሷ ያለችበትን የኬንትሮስ መሥመር በትክክል ማስላት ትችላለህ።

በመቶ ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት በምድር ላይ በየትኛውም ቦታ የሚገኝ አንድ መርከበኛ እኩለ ቀን መሆኑን ማወቅ የሚችለው ጀምበሯ አናት ላይ መሆኗን በመመልከት ነበር። መርከበኛው በተነሳበት ቦታ ሰዓቱ ስንት እንደሆነ በትክክል ካወቀ በ50 ኪሎ ሜትር ክልል ውስጥ በስንተኛው የኬንትሮስ መስመር ላይ እንደሚገኝ ማስላት ይችላል። እርግጥ ነው፣ ቀደም ሲል የተጠቀሰውን ሽልማት ለማግኘት ስድስት ሳምንት በሚፈጀው የባሕር ጉዞ መሣሪያው መፈተን አለበት።

ይሁን እንጂ ተፈታታኝ የሚሆነው ነገር በደረሱበት ቦታ ሆነው የተነሱበትን ቦታ ትክክለኛ ሰዓት ማወቅ ነው። መርከበኛው የፔንዱለም ሰዓት ይዞ መሄድ ይችል የነበረ ቢሆንም እንዲህ ያለው ሰዓት በሚናወጠው ባሕር ላይ በትክክል አይሠራም፤ በሞላና በሽክርክሪት የሚሠሩ ሰዓቶችም ኋላ ቀርና በትክክል የማይሠሩ ነበሩ። በተጨማሪም የአየሩ ጠባይ መለዋወጡ ሰዓቶቹ በትክክል እንዳይሠሩ ያደርጋቸው ነበር። ይሁን እንጂ ጊዜን ለማወቅ የሚረዱትን እንደ ጨረቃ ያሉ ሌሎች የሰማይ አካላትን በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል?

ከባድ ሥራ

የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች የጨረቃን ርቀት የመለካት ዘዴ ተብሎ የሚጠራ አንድ ንድፈ ሐሳብ አቅርበው ነበር። ይህ ንድፈ ሐሳብ ጨረቃ ከአንዳንድ ከዋክብት አንጻር የምትገኝበትን ቦታ መሠረት በማድረግ መርከበኞች የደረሱበትን የኬንትሮስ መስመር ለማወቅ የሚያስችላቸውን ሰንጠረዥ ማዘጋጀትንም ያካትታል።

ከአንድ መቶ ለሚበልጡ ዓመታት ያህል የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች፣ የሒሳብ ሊቃውንትና መርከበኞች ችግሩን ለማሸነፍ ትግል ሲያደርጉ ቢቆዩም የጉዳዩ ውስብስብነት ወደፊት እንዳይራመዱ ጋሬጣ ሆኖባቸው ነበር። ይህ እንቅፋት የማይገፋ ከመሆኑ የተነሳ “የኬንትሮስ ችግር” የሚለው አገላለጽ መፍትሔ የሌለው የሚመስልን ማንኛውንም ጉዳይ ለማመልከት ይሠራበት ጀመር።

አንድ አናጺ ችግሩን ለመፍታት ራሱን አቀረበ

በሮ ኧፖን ኸምበር የሚባለው የሊንኮንሺር ተወላጅ የሆነ ጆን ሃሪሰን የሚባል አንድ አናጺ የኬንትሮስን ችግር ለመፍታት ቆርጦ ተነሳ። በ1713 ሃሪሰን 20 ዓመት ሳይሞላው ሙሉ በሙሉ የእንጨት ነው ሊባል የሚችል የፔንዱለም ሰዓት ሠራ። በኋላም ሰበቃን የሚቀንስ እንዲሁም የአየር ጠባይ መለዋወጥ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ መቋቋም የሚያስችል ዘዴ ፈለሰፈ። በዚያን ጊዜ በዓለም ላይ በጣም ግሩም የሚባሉት ሰዓቶች በቀን ውስጥ አንድ ደቂቃ ይስቱ የነበሩ ሲሆን የሃሪሰን ሰዓት ግን የሚስተው በወር አንድ ሴኮንድ ብቻ ነበር። *

ከዚያም ሃሪሰን በባሕር ላይ ትክክለኛውን ሰዓት ለማወቅ እንቅፋት የሚሆነውን ችግር በመፍታት ላይ ትኩረት አደረገ። ለአራት ዓመታት በጉዳዩ ላይ ካወጣ ካወረደ በኋላ ወደ ለንደን በመሄድ ሐሳቡን የኬንትሮስን ችግር እንዲከታተል ለተቋቋመውና ሽልማቱን እንዲሰጥ ሥልጣን ለተሰጠው ቦርድ አቀረበ። በዚያም ሃሪሰን የታወቀ ሰዓት ሠሪ ከነበረው ከጆርጅ ግራሃም ጋር የተዋወቀ ሲሆን እሱም ሰዓት ለመሥራት የሚያስፈልገውን ከወለድ ነፃ የሆነ ጠቀም ያለ ገንዘብ በብድር ሰጠው። በ1735 ሃሪሰን በባሕር ላይ በትክክል በመሥራት ረገድ በዓለም ላይ የመጀመሪያው የሆነውን ሰዓት በብሪታንያ ውስጥ በጣም ታዋቂ ለሆነው የሳይንቲስቶች ማኅበር አቀረበ። ሰዓቱ 34 ኪሎ ግራም የሚመዝን ሲሆን በነሐስ የተለበጠ ነበር።

ሃሪሰን ሽልማቱ ይገባው እንደሆነና እንዳልሆነ ለመወሰን ለሙከራ ከሰዓቱ ጋር ወደ ዌስት ኢንዲስ ሳይሆን ወደ ሊዝበን ተላከ፤ ሰዓቱ በሚገርም ሁኔታ በትክክል ሠራ። ሃሪሰን ሰዓቱ ሽልማት የሚገባው መሆኑን ለማሳየት አትላንቲክ ውቅያኖስን ማቋረጡ በቂ እንደሆነ መናገር ይችል ነበር። እንዲያውም የኬንትሮስን ችግር እንዲከታተል ከተቋቋመው ቦርድ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ስብሰባ ባደረገበት ወቅት ሰዓቱን የተቸው እሱ ብቻ ነበር! በቀላሉ የማይረካው ሃሪሰን የሰዓቱን ሞዴል ማሻሻል እንደሚችል ተሰማው። በመሆኑም ይበልጥ ጥሩ የሆነ ሰዓት ለመሥራት ጥቂት ገንዘብና ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጠው ብቻ ጠየቀ።

ሃሪሰን አያሌ ማሻሻያዎችን አድርጎ ከስድስት ዓመት በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ ያቀረበው 39 ኪሎ ግራም የሚመዝነው ሰዓት የሳይንቲስቶችን ማኅበር ሙሉ ድጋፍ አገኘ። ይሁንና በጊዜው የ48 ዓመት ሰው የነበረው ሃሪሰን በሥራው በፍጹም አልረካም። ወደ ሥራው ቦታ ተመልሶ ሦስተኛውንና ለየት ያለ ሞዴል ያለውን ሰዓት ለመሥራት 19 ዓመት ሲለፋ ቆየ።

ሃሪሰን በጣም ከባድ የሆነውን ይህን ሦስተኛውን ሞዴል በሚሠራበት ጊዜ እንዳጋጣሚ አንድ ሐሳብ ብልጭ አለለት። አንድ ሰዓት ሠሪ ሃሪሰን በሠራው ሞዴል ላይ ተመሥርቶ በኪስ የሚያዝ ሰዓት ሠርቶ ነበር። በዚያ ዘመን በኪስ ከሚያዙ ሰዓቶች ይልቅ ትልልቆቹ ሰዓቶች ትክክለኛ እንደሆኑ ተደርጎ ይታሰብ ነበር። ይሁን እንጂ ሃሪሰን በአዲሱ ሰዓት ትክክለኛነት ተገረመ። በ1761 በአትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ የሙከራ ጉዞ ዝግጅት በተደረገ ወቅት ሃሪሰን ሙሉ እምነቱን የጣለው ለሦስተኛ ጊዜ በሠራው ሞዴሉ ላይ ሳይሆን በኪስ በሚያዘውና አንድ ኪሎ ግራም በሚመዝነው በአራተኛው ሰዓቱ ላይ ነበር። ሃሪሰን “ሁሉን ቻይ አምላክ ይህን ሰዓት ሠርቼ እንድጨርስ እስከ ዛሬ እንድኖር ስለፈቀደ ከልብ አመሰግነዋለሁ” በማለት ተናግሯል።

ተገቢ ያልሆነ ፍርድ

ይሁን እንጂ በዚህ ጊዜ የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች የኬንትሮስን ችግር ለመፍታት ተቃርበው ነበር። በተጨማሪም በዳኞች ችሎት ላይ የበላይነት የነበረው ሰው የሽልማቱ ገንዘብ ኔቨል ማስከሊን ለሚባለው የሥነ ፈለክ ተመራማሪ እንዲሰጥ ትእዛዝ አስተላልፎ ነበር። የሃሪሰን ሰዓት በአትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ በተደረገ የ81 ቀን ጉዞ ተፈተነ። ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? ይህ ሰዓት የሳተው አምስት ሴኮንዶች ብቻ ነበር! ይሁን እንጂ ዳኞቹ አንዳንድ ደንቦች ተጥሰዋል እንዲሁም ሰዓቱ በትክክል ሊሠራ የቻለው በአጋጣሚ ነው በሚል ሰበብ ለሃሪሰን ሽልማቱን በወቅቱ ሳይሰጡ ቀሩ። በመጨረሻም ከሽልማቱ ገንዘብ ውስጥ ከፊሉ ብቻ እንዲሰጠው ተወሰነ። በዚህ መሃል በ1766 ማስከሊን፣ ጨረቃ ሊኖራት ይችላል ተብሎ የሚታሰበውን አቀማመጥ የሚያሳይ ሠንጠረዥ አዘጋጀ፤ ይህ ሠንጠረዥ መርከበኞች የሚገኙበትን የኬንትሮስ መስመር በግማሽ ሰዓት ውስጥ አስልተው ለማወቅ የሚያስችላቸው ነበር። ሃሪሰን፣ ሽልማቱ ለማስከሊን ይሰጠዋል ብሎ ፈርቶ ነበር።

በ1772 ደግሞ ብሪታንያዊው አሳሽ ካፒቴን ጄምስ ኩክ ወደ መድረኩ ብቅ አለ። ኩክ ለሁለተኛ ጊዜ ባደረገው ታሪካዊ የባሕር ጉዞ ላይ ሃሪሰን በፈለሰፈው ሞዴል የተሠራውን ሰዓት ተጠቅሞ ስለነበር ይህ ሰዓት ከተጠበቀው በላይ በትክክል የሚሠራ መሆኑን ሪፖርት አደረገ። በዚህ ወቅት የ79 ዓመት ሰው የሆነው ሃሪሰን የኬንትሮስን ችግር ለመፍታት በተቋቋመው ቦርድ በመበሳጨቱ ለእንግሊዝ ንጉሥ ይግባኝ ጠይቆ ነበር። በዚህም የተነሳ ሃሪሰን ቀሪው የሽልማት ገንዘብ በ1773 ተሰጠው፤ ይሁንና አሸናፊ መሆኑ በይፋ አልተነገረለትም። ጆን ሃሪሰን ከሦስት ዓመት በኋላ በተወለደ በ83 ዓመቱ ሞተ።

ከጥቂት ዓመታት በኋላ ለባሕር ላይ ጉዞ የሚያገለግል ትክክለኛ ሰዓት በ65 ፓውንድ ይሸጥ ጀመር። አዎን፣ በአንዲት ትንሽ መንደር ይኖር የነበረ አናጺ ባሳየው ብልሃትና ሕይወቱን በሙሉ ለዚህ ተግባር በማዋሉ የማይቻል የነበረው ነገር እውን እንዲሆን አድርጓል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.13 ሃሪሰን በወንድሙ እየታገዘ አንዳንድ ኮከቦች በጎረቤቱ የጪስ መውጫ የሚሸፈኑበትን ትክክለኛ ጊዜ በመመዝገብ የሠራውን ሰዓት ትክክለኝነት ለብዙ ሌሊቶች ሲከታተል ቆይቷል።

[በገጽ  21 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ሰዓት ተጠቅሞ ያለህበትን ኬንትሮስ ማወቅ

ከጠዋቱ 12 ሰዓት ከቀኑ 6 ሰዓት

ሰሜን አሜሪካ ብሪታንያ

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሰዓት ሠሪው ጆን ሃሪሰን

[ምንጭ]

SSPL/Getty Images

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሃሪሰን የሠራው 34 ኪሎ ግራም የሚመዝነው የመጀመሪያው ሰዓት

[ምንጭ]

National Maritime Museum, Greenwich, London, Ministry of Defence Art Collection

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሃሪሰን ለአራተኛ ጊዜ የሠራው አንድ ኪሎ ግራም የሚመዝነው ሰዓት (ትክክለኛ መጠኑ)

[ምንጭ]

SSPL/Getty Images

 

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

በችግር ላይ ያለች መርከብ፦ © Tate, London/Art Resource, NY; ኮምፓስ፦ © 1996 Visual Language