በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከባድ የአካል ጉዳት ቢኖርብኝም ደስተኛ ነኝ

ከባድ የአካል ጉዳት ቢኖርብኝም ደስተኛ ነኝ

ከባድ የአካል ጉዳት ቢኖርብኝም ደስተኛ ነኝ

ሆሴ ጎዶፍሬዶ ቫርጌስ እንደተናገረው

ስወለድ ጤነኛ የነበርኩ ሲሆን በልጅነቴም ቢሆን ምንም ችግር አልነበረኝም። በ17 ዓመቴ በአንድ ፋብሪካ ውስጥ በያጅ ሆኜ መሥራት ጀመርኩ። ከሁለት ዓመት በኋላ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ባለበት አካባቢ እየበየድኩ ሳለ ዝናብ መጣል ጀመረ። በድንገት ኃይለኛ ኤሌክትሪክ የነዘረኝ ሲሆን ንዝረቱም 14 ሜትር ከፍታ ካለው ከዚህ ቦታ አሽቀንጥሮ ወደ መሬት ጣለኝ፤ ከዚያም ራሴን ሳትኩ። ለሦስት ወር ያህል ራሴን አላውቅም ነበር። ስነቃ ግን ማንቀሳቀስ የምችለው ጭንቅላቴን ብቻ ነበር። እጆቼና እግሮቼ ሽባ ሆነው ስለነበር በጣም አዘንኩ!

ጀመሪያ ላይ አምላክ በሕይወት እንድኖር በመፍቀዱ በጣም የተበሳጨሁ ከመሆኑም በላይ አምላክን አማርረው ነበር። ሌላው ቀርቶ ራሴን ለማጥፋት አስቤ ነበር። መጽናናት ለማግኘት ወደ ተለያዩ የሃይማኖት ድርጅቶች ሄጄ ነበር፤ ይሁን እንጂ አንዳቸውም ቢሆኑ እውነተኛ ማጽናኛ አልሰጡኝም ወይም መንፈሳዊ ፍላጎቴን አላረኩልኝም። እነዚህ ሃይማኖቶች ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርትና መሥፈርቶች በሥራ ላይ እንዲያውሉ እንኳ አያበረታቱም! እናቴ በ1981 ስትሞት ጠጪና ቁማርተኛ ሆንኩ። አምላክ ያለሁበትን ሁኔታ አገናዝቦ እንደሚያዝንልኝና ጠጪ ብሆንም ይቅር እንደሚለኝ አስብ ነበር። እንዲሁም ካላገባኋት ሴት ጋር በመኖር ሥነ ምግባር የጎደለው ሕይወት እመራ ነበር።

በአመለካከቴ ላይ ትልቅ ለውጥ አደረግሁ

በ37 ዓመቴ ለመጀመሪያ ጊዜ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኘሁ። እናቴ፣ ሰዎች ስለ ይሖዋ ምሥክሮች የሚያናፍሱት የሐሰት ወሬ ተጽዕኖ አሳድሮባት ስለነበር የይሖዋ ምሥክሮች ከሁሉም የከፉ እንደሆኑ ሁልጊዜ ትናገር ነበር። ያም ሆኖ ወደ ቤት ሲመጡ ወደ ውስጥ እንዲገቡ ጋበዝኳቸው፤ ይህን ያደረግኩበት ምክንያት ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ እንደማውቅ ይሰማኝ ስለነበር የተሳሳቱ እንደሆኑ ላሳምናቸው ነበር። የሚገርመው ነገር ያለኝ እውቀት ከእነሱ ጋር ሲነጻጸር በጣም ትንሽ እንደሆነ ተገነዘብኩ! ከሁሉም ያስገረመኝ ደግሞ እነዚህ ሰዎች ለሁሉም ጥያቄዎቼ መልስ የሰጡኝ በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅመው ነበር። እውነትን እንዳገኘሁ ለማመን ብዙ ጊዜ አልወሰደብኝም።

የሚያሳዝነው ነገር አብራኝ ትኖር የነበረችው ሴት አዲሱን እምነቴን ስላልወደደችው ተለያየን። አኗኗሬ ንጹሕ እንዲሆን መጣር እንዲሁም ዝንባሌዬንና አመለካከቴን ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ጋር እንዲስማማ ለውጥ ማድረጌን ቀጠልኩ። በተጨማሪም በአምላክ እርዳታ የደረሰብኝ አደጋ ያስከተለብኝን አእምሯዊና ስሜታዊ ጉዳት መቋቋም ችያለሁ፤ በመሆኑም ላለፉት 20 ዓመታት የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ ሆኜ በማገልገል ከፍተኛ እርካታ አግኝቻለሁ። ብዙ ሰዎች ያለብኝን የአካል ጉዳት በመመልከት ደስታዬን እንዴት ጠብቄ መኖር እንደቻልኩ ይገርማቸዋል። የምኖረው ዳውን ሲንድሮም የሚባለው የአእምሮ ዘገምተኝነት በሽታ ካለበት ታናሽ ወንድሜ ከኡባልዶ ጋር ነው። ኡባልዶም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ተቀብሎ አብሮኝ ይሖዋን እያገለገለ ነው።

እኔና ኡባልዶ አንዳችን የሌላውን ጉድለት በማሟላት አብረን የምናገለግል ሲሆን እርስ በርስም እንተሳሰባለን። በአገልግሎት በምንካፈልበት ጊዜ ኡባልዶ ተሽከርካሪ ወንበር ይገፋልኛል፤ እንዲሁም በር ያንኳኳልኛል። በተጨማሪም እኔ ከቤቱ ባለቤቶች ጋር ስነጋገር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ በማውጣት የሚረዳኝ ሲሆን የሚበረከቱትን ጽሑፎችም ያሳይልኛል። ሌሎች አካላዊ ፍላጎቶቼንም ያሟላልኛል። እኔም የመዋቢያ ዕቃዎችን በመሸጥ ለሁለታችንም ለሚያስፈልጉን ነገሮች የሚሆን ገንዘብ አገኛለሁ። በተጨማሪም በአካባቢያችን ያለው የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ አባላት ምግብ በማብሰል፣ የቤት ውስጥ ሥራዎችን በመሥራት እንዲሁም ሐኪም ጋር በመውሰድ ይረዱናል፤ እኔና ኡባልዶ ለዚህ አመስጋኞች ነን።

በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ሽማግሌ ሆኖ የማገልገል መብት አግኝቻለሁ፤ መንፈሳዊ ወንድሞቼ በመጽሐፍ ቅዱስ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ምርምር ሳደርግ ምንጊዜም እኔን ለመርዳት ፈቃደኞች ናቸው። እኔም በአፌ እርሳስ ይዤ ለማጥናት በሚያገለግሉ ጽሑፎች ላይ ሊጎሉ የሚገባቸውን ነጥቦች ከሥራቸው ማስመር እችላለሁ።

ሰዎች ደስተኛ እንደሆንኩ ሲጠይቁኝ ምንጊዜም በሙሉ ልብ አዎን! ብዬ እመልሳለሁ። ደግሞስ ደስተኛ የማልሆንበት ምን ምክንያት አለ? እውነተኛውን የሕይወት ትርጉም ማወቅ ችያለሁ፤ እንዲሁም አምላክ ለታማኝ አምላኪዎቹ የዘረጋውን ግሩም ተስፋ ማለትም በመጪው ምድራዊ ገነት ውስጥ ፍጹም ጤንነት አግኝቶ መኖርን እየተጠባበቅሁ ነው።—ኢሳይያስ 35:5, 6፤ ሉቃስ 23:43

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሆሴ በ18 ዓመቱ፣ አደጋው ከመድረሱ ከአንድ ዓመት በፊት

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እኔና ወንድሜ ኡባልዶ አንዳችን የሌላውን ጉድለት በማሟላት አብረን በሜክሲኮ ስናገለግል

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ንግግር ሳቀርብ አንድ የእምነቴ ባልደረባ ከመጽሐፍ ቅዱሴ ላይ ጥቅስ ማውጣት ሲረዳኝ

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአካባቢያችን ያለው ጉባኤ አባላት ምግብ በማብሰልና የቤት ውስጥ ሥራዎችን በመሥራት ሲረዱን