በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ሊቀ ጳጳስ ቤኔዲክት አሥራ ስድስተኛ የጻፉት አንድ ደብዳቤ እንዲህ ይላል፦ “በመንግሥታት መካከል የቤተሰባዊነት መንፈስ እንዲኖር የማድረጉ ሐሳብ እውን እንዲሆን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደዚሁም በኢኮኖሚ ተቋማትና በዓለም አቀፉ ኢኮኖሚ ላይ ተሐድሶ ማካሄድ በእጅጉ ያስፈልጋል።”—ሎሴርቫቶሬ ሮማኖ፤ ፊደላቱን ጋደል አድርገው የጻፉት እነሱ ናቸው።

“ከሦስት ዩክሬናውያን አንዱ በየቀኑ አንድ ፓኬት ሲጋራ ያጨሳል።”—ኤክስፕረስ፣ ዩክሬን

በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ጥናት ከተካሄደባቸው በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ከሚገኙ ወንዶች ልጆች መካከል 44 በመቶ የሚሆኑት “የክፍላቸው ተማሪ የሆነች የአንዲትን ሴት ዕርቃን የሚያሳይ ቢያንስ አንድ ፎቶ በኢንተርኔት ወይም በሞባይል ስልካቸው እንዳዩ” ተናግረዋል።—ታይም፣ ዩናይትድ ስቴትስ

“አሳሳቢ ደረጃ”

ጦርነት፣ ድርቅ፣ የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ የምግብ ዋጋ መናርና ድህነት የሰውን ዘር “አሳሳቢ ደረጃ” ላይ እንዳደረሱት አሶሺዬትድ ፕሬስ ይናገራል። የዓለም ረሃብተኞች ቁጥር አሁን ከአንድ ቢሊዮን በልጧል። የተባበሩት መንግሥታት የዓለም የምግብ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ጆዜት ሺረን እንደገለጹት ከሆነ “የተራበ ሕዝብ አደገኛ ነው። ምግብ ከሌለ ሰዎች ያላቸው አማራጭ ሦስት ብቻ ነው፦ ወይ ማመፅ አሊያም መሰደድ ወይም ደግሞ መሞት። ከእነዚህ አማራጮች ውስጥ አንዱም ተፈላጊ አይደለም።” ከዚህም በላይ የረሃብተኞች ቁጥር የዓለም ሕዝብ ብዛት ከሚጨምርበት ፍጥነት በበለጠ እያደገ ነው። ባደጉት አገሮችም እንኳን ሳይቀር በቂ ምግብ የማያገኙ ሰዎች ቁጥር በ15.4 በመቶ ጨምሯል።

ለልጆች ከመኝታ በፊት ማንበብ ጠቃሚ ነው

ወላጆች ለልጆቻቸው ከመኝታ በፊት ማንበባቸው ልጆቹ እንቅልፍ እንዲወስዳቸው ከማድረግ ያለፈ ጥቅም አለው። ተመራማሪዎች እንደገለጹት እንዲህ ማድረግ የልጆችን የቋንቋ ችሎታ ያሳድጋል፣ ገጾቹን በእጃቸው ስለሚይዙና ስለሚገልጡ የአእምሮና የአካል ቅልጥፍናቸውን ያሳድግላቸዋል እንዲሁም ፈጣን የማስታወስ ችሎታ እንዲኖራቸው ያደርጋል። “ከሁሉም በላይ ግን ጮክ ብሎ ማንበብ ወላጅና ልጅ አንዳቸው ለሌላው ትኩረት ለመስጠትና ስሜታቸውን ለመግለጽ አጋጣሚ ይሰጣቸዋል” በማለት ዘ ጋርዲያን የተሰኘው ጋዜጣ ተናግሯል። አክሎም “ይህ ደግሞ ልጁ ማንበብ እንዲወድ ያደርገዋል” ብሏል። ጥናቱን የመሩት ፕሮፌሰር ባሪ ዙከርመን እንደሚሉት ከሆነ “ልጆች መጻሕፍትን የሚያነቡት ከሚወዷቸው ሰዎች ጋር በመሆኑ ለመጻሕፍቱ ፍቅር እያደረባቸው ይሄዳል።”

በእንክብካቤ የተያዙ ላሞች ብዙ ወተት ይሰጣሉ

“ስም ያላት ላም ስም ከሌላት ላም ይበልጥ ብዙ ወተት ትሰጣለች” በማለት በእንግሊዝ ኒውካስል ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚገኙ የሳይንስ ሊቃውንት ይናገራሉ። እንዲያውም ለእያንዳንዱ ላም በግል ትኩረት መስጠት የወተት ምርታቸው በዓመት በ280 ሊትር ያህል እንዲጨምር ሊያደርገው ይችላል። ለምን? በዩኒቨርሲቲው ሥር ባለው የእርሻ፣ የምግብና የገጠር ልማት ትምህርት ቤት ውስጥ የሚሠሩት ዶክተር ካትረን ዳግላስ እንደተናገሩት “አንድ ሰው ሌሎች በግለሰብ ደረጃ አሳቢነት ሲያሳዩት ጥሩ ምላሽ እንደሚሰጥ ሁሉ ላሞችም በመጠኑም ቢሆን በግል ትኩረት ከተሰጣቸው የበለጠ ደስተኛ የሚሆኑ ሲሆን ሰውነታቸውም ዘና ይላል።” አክለውም ዶክተሯ “ጥናታችን ያረጋገጠው፣ ጥሩና ተንከባካቢ የሆኑ በርካታ ገበሬዎች ከረጅም ዘመናት በፊት ሲያምኑበት የነበረውን ነገር ነው” በማለት ገልጸዋል። “ላሚቱን በስም እንደመጥራት፣ ወይም እያደገች በመጣች መጠን በደንብ እንደ መቅረብ ያሉ ነገሮችን በማድረግ የበለጠ ትኩረት መስጠት ይበልጥ የደህንነት ስሜት እንዲሰማትና ሰዎችን ለይታ እንድታውቅ ማስቻል ብቻ ሳይሆን የምትሰጠው የወተት ምርትም እንዲጨምር ያደርጋል።”