በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የመንተባተብን ችግር ማሸነፍ የሚቻለው እንዴት ነው?

የመንተባተብን ችግር ማሸነፍ የሚቻለው እንዴት ነው?

የመንተባተብን ችግር ማሸነፍ የሚቻለው እንዴት ነው?

“በምንተባተብበት ጊዜ ስለምጨነቅ መንተባተቡ ይብስብኛል። መውጣት በማልችልበት ጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ እንደገባሁ ይሰማኛል። በአንድ ወቅት የሥነ ልቦና ባለሙያ እርዳታ ለማግኘት ሞክሬ ነበር። ለራሴ ያለኝ ግምት ከፍ እንዲል የሴት ጓደኛ መያዝና የፆታ ግንኙነት መፈጸም እንዳለብኝ ነገረችኝ። ከዚያ በኋላ ወደ እሷ አልተመለስኩም። እኔ የምፈልገው ሰዎች በእኔነቴ እንዲቀበሉኝ ነው።”—የ32 ዓመቱ ራፋኤል

የአውቶቡስ ቲኬት መጠየቅ እንኳ ከባድ ነገር ሆኖብህ በላብ የምትጠመቅ እንዲሁም መናገር ስትጀምር የምትለው ጠፍቶህ የመጀመሪያውን ቃል የምትደጋግም ቢሆን ምን ሊሰማህ እንደሚችል እስቲ አስበው። በዓለም ዙሪያ ስልሳ ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ማለትም በምድር ላይ ከሚኖሩ መቶ ሰዎች መካከል አንዱ እንዲህ ያለ ሁኔታ ያጋጥመዋል። የመንተባተብ ችግር ያለባቸው እነዚህ ሰዎች ብዙ ጊዜ ይፌዝባቸዋል እንዲሁም ይገለላሉ። ለመጥራት የሚያስቸግሯቸውን ቃላት ቀለል ባሉ ቃላት እየተኩ ስለሚናገሩ የመረዳት ችሎታቸው ዝቅተኛ እንደሆነ ተደርጎም ይታያል።

መንተባተብ የሚመጣው በምን ምክንያት ነው? ችግሩ መፍትሔ አለው? ችግሩ ያለበት ሰው የአነጋገር ቅልጥፍናውን ለማሻሻል ሊያደርግ የሚችለው ነገር ይኖራል? * ሌሎችስ እንዲህ ያለውን ሰው ለመርዳት ሊያደርጉት የሚችሉት ነገር አለ?

ምክንያቱ ይታወቃል?

በጥንት ጊዜ ይኖሩ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች አንድ ሰው የሚንተባተበው ክፉ መንፈስ ስለያዘው እንደሆነና ይህ መንፈስ ከግለሰቡ ሊወጣ እንደሚገባ ያምኑ ነበር። በመካከለኛው ዘመን ደግሞ ችግሩ ያለው ምላስ ላይ እንደሆነ ይታመን ነበር። ለዚህ መፍትሔ ተደርጎ ይታሰብ የነበረው ምንድን ነው? በጋለ ብረት መተኮስና በተለያዩ ቅመማት ማቃጠል! በኋለኞቹ ዘመናት ደግሞ ሐኪሞች የመንተባተብ ችግርን ለማስወገድ ሲሉ የምላስን ጡንቻዎችና ነርቮች በቀዶ ሕክምና አማካኝነት ይቆርጡ አልፎ ተርፎም በጉሮሮ ግራና ቀኝ የሚገኙትን ዕጢዎች (ቶንሲል) ቆርጠው ያወጡ ነበር። ይሁን እንጂ እነዚህ አሰቃቂ ዘዴዎች በሙሉ የታለመላቸውን ግብ ሊመቱ አልቻሉም።

ዘመናዊ ተመራማሪዎች የመንተባተብ መንስኤ አንድ ነገር ብቻ ሳይሆን ሌሎች ምክንያቶች እንዳሉ ይናገራሉ። አንደኛው መንስኤ ግለሰቡ ውጥረት ሲያጋጥመው ምላሽ የሚሰጥበት መንገድ ሊሆን ይችላል። መንተባተብ በዘር የሚተላለፍ ችግር ሊሆን እንደሚችልም ይታሰባል፤ ምክንያቱም ከሚንተባተቡ ሰዎች መካከል 60 በመቶ የሚሆኑት ተመሳሳይ ችግር ያለበት ዘመድ አላቸው። ከዚህም በላይ በአእምሯችን ውስጥ ያሉትን ነርቮች እንቅስቃሴ በራጅ በመመልከት የተደረገ ምርምር እንዳመለከተው የሚንተባተብ ሰው አንጎሉ ቋንቋን የሚያቀናብረው ለየት ባለ መንገድ ነው። ዶክተር ኔተን ላቪድ፣ አንደርስታንዲንግ ስታተሪንግ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ አንዳንዶች “የሚናገሩትን ቃል እንዴት ሊጠሩት እንደሚገባ አንጎላቸው መልእክት ከማስተላለፉ በፊት እነሱ መናገር ይጀምሩ ይሆናል” ብለዋል። *

ከዚህ ለማየት እንደሚቻለው በአንድ ወቅት ላይ ይታሰብ እንደነበረው የመንተባተብ ዋነኛው መንስኤ ሥነ ልቦናዊ ላይሆን ይችላል። “በሌላ አነጋገር መንተባተብ አንድ ሰው ከሚያምንበት ነገር ጋር ምንም ግንኙነት የለውም፤ እንዲሁም የሚንተባተቡ ሰዎችን ችግሩን ማሸነፍ እንደሚችሉ በማሳመን አንደበተ ርቱዕ እንዲሆኑ ማድረግ አይቻልም” በማለት ኖ ሚራክል ኪዩርስ የተባለው መጽሐፍ ይናገራል። ይሁን እንጂ የሚንተባተቡ ሰዎች ይህ ሁኔታቸው የሚያሳድርባቸው ሥነ ልቦናዊ ጫና ሊኖር ይችላል። በአንዳንድ ሁኔታዎች ውስጥ ለምሳሌ በሕዝብ ፊት ወይም በስልክ መናገር ሊያስፈራቸው ይችላል።

ለሚንተባተቡ ሰዎች የሚሆን እርዳታ

የሚገርመው ነገር፣ የሚንተባተቡ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ አለምንም ችግር መዘመር፣ በሹክሹክታ መናገር፣ ከራሳቸው ወይም ከቤት እንስሳቸው ጋር ማውራት፣ ከብዙ ሰዎች ጋር በአንድነት መናገር ወይም ሌሎችን አስመስሎ ማውራት ይችላሉ። ከዚህም በላይ የመንተባተብ ችግር ከነበረባቸው ልጆች መካከል 80 በመቶ የሚሆኑት ውሎ አድሮ መንተባተብ ያቆማሉ። ይሁንና 20 በመቶ የሚሆኑትስ?

በዛሬው ጊዜ የአነጋገር ቅልጥፍናን ሊያሻሽሉ የሚችሉ ፕሮግራሞች አሉ። አንዳንዶቹ ዘዴዎች መንጋጋን፣ ከንፈርንና ምላስን ዘና ማድረግን እንዲሁም አየር በደንብ መሳብን የሚጠይቁ ናቸው። በተጨማሪም የመንተባተብ ችግር ያለበት ሰው በረጅሙ ያስገባውን ትንፋሽ በሚናገርበት ጊዜ ቀስ በቀስ እንዲያስወጣ ሥልጠና ይሰጠዋል። አናባቢዎችንና አንዳንድ ተነባቢ ሆሄያትን ዝግ ብሎ እንዲናገር ማበረታቻ ይሰጠው ይሆናል። የአነጋገር ቅልጥፍናው እየተሻሻለ ሲሄድ የንግግሩ ፍጥነት ቀስ በቀስ ይጨምራል።

እንደነዚህ ያሉትን ችሎታዎች ለማዳበር ጥቂት ሰዓታት ብቻ በቂ ሊሆኑ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ከፍተኛ ውጥረት በሚኖርበት ጊዜ እነዚህን ዘዴዎች ተግባራዊ ለማድረግ በሺህ ለሚቆጠሩ ሰዓታት ልምምድ ማድረግ ሊያስፈልግ ይችላል።

ሥልጠናው መጀመር ያለበት መቼ ነው? አንድ ልጅ መንተባተቡን ሲያድግ እንደሚተወው በማሰብ ዝም ብሎ መጠበቅ ጥበብ ይሆናል? ለአምስት ዓመት ያህል ሲንተባተቡ ከቆዩ ልጆች መካከል ከ20 በመቶ የሚያንሱት ሲያድጉ ችግሩ እንደሚተዋቸው ጥናቶች ያሳያሉ። ኖ ሚራክል ኪዩርስ የተባለው መጽሐፍ እንደሚለው “ልጁ በስድስተኛው ዓመት የንግግር ሥልጠና ሳይሰጠው በራሱ የመሻሻል አጋጣሚው አነስተኛ ነው።” ስለዚህ “የሚንተባተቡ ልጆች በተቻለ ፍጥነት የሥነ ንግግርና የቋንቋ ባለሙያ ፊት ሊቀርቡ ይገባል” በማለት መጽሐፉ አክሎ ይናገራል። አዋቂ ሲሆኑም መንተባተባቸውን ከማይተዉት 20 በመቶ የሚሆኑ ልጆች መካከል ከ60 እስከ 80 በመቶ ገደማ የሚሆኑት የንግግር ሥልጠና ሲሰጣቸው ለውጥ ያደርጋሉ። *

ምክንያታዊ ሁን

የሥነ ንግግር ባለሙያ የሆኑትና የመንተባተብ ችግር ያለባቸው ዶክተር ሮበርት ኬሳል እንደተናገሩት የመንተባተብ ችግር ያለባቸው አብዛኞቹ ሰዎች በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ በተቀላጠፈ መንገድ መናገር እንደሚችሉ ማሰብ የማይሆን ነገር ነው። በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው ራፋኤል የንግግር ቅልጥፍናው በእጅጉ የተሻሻለ ቢሆንም ችግሩን ሙሉ በሙሉ ማሸነፍ አልቻለም። እንዲህ ብሏል፦ “በሕዝብ ፊት መናገር ወይም ማንበብ በሚኖርብኝ ጊዜ አሊያም ቆንጆ ሴት አጠገብ በምሆንበት ጊዜ ችግሩ ይባባስብኛል። ሰዎች ስለሚቀልዱብኝ በጣም እፍረት ይሰማኝ ነበር። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ማንነቴን ተቀብዬ ለመኖርና ስለ ራሴ ከሚገባው በላይ ላለማሰብ እየሞከርኩ ነው። ስለዚህ አንድ ቃል መጥራት አቅቶኝ በምንተባተብበት ጊዜ በራሴ እስቅና ዘና ብዬ ንግግሬን ለመቀጠል እጥራለሁ።”

ራፋኤል የሰጠው ሐሳብ የመንተባተብ ችግር ያለባቸውን ሰዎች ለመርዳት የተቋቋመው የአሜሪካ ድርጅት ከሰጠው ከሚከተለው አስተያየት ጋር ይስማማል፦ “አብዛኛውን ጊዜ መንተባተብን ለማሸነፍ የሚረዳው ችግሩን ለማስወገድ ብርቱ ጥረት ማድረግ ሳይሆን ‘እንተባተብ ይሆን’ የሚለውን ፍርሃት ማስወገድ ነው።”

መንተባተብን ለማሸነፍ ከሚታገሉ ሰዎች መካከል ብዙዎቹ ይህ ችግራቸው ትርጉም ያለው ሕይወት ለመምራት እንቅፋት እንዲሆንባቸው አልፈቀዱም። እንዲያውም አንዳንዶቹ ዝነኛ እስከ መሆን ደርሰዋል፤ የፊዚክስ ሊቅ የሆኑትን ሰር አይዛክ ኒውተንን፣ የብሪታንያ መሪ የነበሩትን ዊንስተን ቸርችልንና አሜሪካዊ ተዋናይ የሆነውን ጄምስ ስቱዋርትን እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። ሌሎቹ ደግሞ የሙዚቃ መሣሪያ እንደመጫወት፣ ሥዕል እንደመሳልና የምልክት ቋንቋ እንደ መማር ያሉትን የንግግር ችሎታ የማይጠይቁ ክህሎቶች አዳብረዋል። የመንተባተብ ችግር የሌለብን ሰዎች፣ የሚንተባተቡ ግለሰቦች ሐሳባቸውን ለመግለጽ የሚያደርጉትን ከፍተኛ ጥረት ልናደንቅ ይገባል። እንግዲያው የምንችለውን ያህል ማበረታቻና ድጋፍ እንስጣቸው።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.4 የመንተባተብ ችግር ካለባቸው ሰዎች መካከል 80 በመቶ የሚሆኑት ወንዶች በመሆናቸው ይህ ጽሑፍ ችግሩ ስላለበት ግለሰብ ሲናገር በተባዕታይ ፆታ ይጠቀማል።

^ አን.7 ስለመንተባተብ መንስኤዎችና ይህን ችግር ለማስተካከል ስለሚሰጡ ተገቢ ሕክምናዎች የሚሰነዘሩ ጽንሰ ሐሳቦች የሚስማሙባቸው ነገሮች ቢኖሩም የሚለያዩባቸው ጊዜያትም አሉ። ንቁ! ይህ አመለካከት ወይም የሕክምና ዓይነት ከዚህኛው ይሻላል የሚል ሐሳብ አይሰጥም።

^ አን.13 አንዳንድ ጊዜ ሐኪሞች አንድ ሰው የሚናገረው ነገር ወዲያውኑ እንዳይሰማው የሚያደርጉ መንተባተብን ለማስወገድ የሚረዱ መሣሪያዎችን ወይም ከንግግር ጋር የተያያዘ ውጥረትን የሚያረግቡ መድኃኒቶች ሊያዙ ይችላሉ።

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የሚንተባተብን ሰው እንዴት መርዳት ትችላለህ?

● ዘና ያለና ወከባ የሌለበት ሁኔታ እንዲሰፍን አድርግ። ውጥረትና ጥድፊያ የበዛበት የዘመኑ አኗኗር ችግሩን ያባብሰዋል።

● የሚንተባተበው ሰው ዝግ ብሎ እንዲናገር ከመጠየቅ ይልቅ አንተ ራስህ ዝግ ብለህ በመናገር ይህን ማድረግ እንደሚቻል አሳየው። በትዕግሥት አዳምጠው እንዲሁም አታቋርጠው። የሚናገረውን ዓረፍተ ነገር አትጨርስለት። መልስ ከመስጠትህ በፊት ትንሽ ጠብቀው።

● እርማትና ትችትን አስወግድ። ለአነጋገሩ ሳይሆን ለሚናገረው ነገር ትልቅ ቦታ እንደምትሰጥ በዓይንህ፣ ፊትህ ላይ በሚነበበው ስሜት እንዲሁም በአካላዊ መግለጫዎች አሳየው።

● መንተባተብ ጨርሶ ሊነሳ የማይገባ ርዕሰ ጉዳይ መሆን የለበትም። ወዳጃዊ ስሜት የሚንጸባረቅበት ፈገግታ እንዲሁም አልፎ አልፎ ችግሩን አንስቶ በደግነት ማውራት ግለሰቡ ይበልጥ ዘና እንዲል ሊያደርገው ይችላል። “አንዳንድ ጊዜ የምንፈልገውን መናገር ቀላል ላይሆንልን ይችላል” እንደሚለው ያለ ሐሳብ መሰንዘር ትችላለህ።

● ከሁሉ በላይ ደግሞ እሱን በእሱነቱ እንደምትቀበለው እንዲያውቅ አድርግ።

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

“ቀስ በቀስ መንተባተቤን ቀነስኩ”

በቤተሰቡ ውስጥ ከባድ ችግር በነበረበት ወቅት ለበርካታ ዓመታት በጣም ይንተባተብ የነበረው ቪክቶር ይህን ችግሩን ያለምንም የሕክምና እርዳታ ማሸነፍ ችሏል። ቪክቶር የይሖዋ ምሥክር በመሆኑ በሁሉም ጉባኤዎች በየሳምንቱ በሚካሄደው የቲኦክራሲያዊ አገልግሎት ትምህርት ቤት መካፈል ጀመረ። ትምህርት ቤቱ የንግግር ሕክምና ለመስጠት ታስቦ የተዘጋጀ ባይሆንም ተማሪዎቹ የመናገር ችሎታቸውን እንዲያሻሽሉና በራስ የመተማመን ስሜት እንዲያዳብሩ ይረዳል።

በዚህ ትምህርት ቤት ተማሪዎቹ የሚጠቀሙበት መጽሐፍ በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም ይባላል። መጽሐፉ “የመንተባተብን ችግር መቋቋም” በሚለው ርዕስ ሥር እንደሚከተለው ይላል፦ “ሳይታክቱ መሞከር በጣም አስፈላጊ ነው። . . . ንግግር የምትሰጥ ከሆነ በደንብ ተዘጋጅ። በምታቀርበው ትምህርት ተመሰጥ። . . . እየተናገርህ ሳለ መንተባተብ ከጀመርህ በተቻለ መጠን ድምፅህንም ሆነ ንግግርህን ዝግ አድርግ። የመንገጭላህ ጡንቻዎች ዘና እንዲሉ አድርግ። አጫጭር ዓረፍተ ነገሮችን ተጠቀም። በንግግር መሀል እ-እ-እ ማለትን የመሳሰሉ ልማዶችን ቀንስ።”

ታዲያ ትምህርት ቤቱ ቪክቶርን ሊረዳው ችሏል? ቪክቶር እንዲህ ይላል፦ “እንዴት እንደምናገር ከመጨነቅ ይልቅ በምናገረው ነገር ላይ ይበልጥ ትኩረት ስለማደርግ ችግር እንዳለብኝ እንኳ እረሳው ነበር። በተጨማሪም ንግግሬን ደግሜ ደጋግሜ እለማመድ ነበር። ቀስ በቀስ መንተባተቤን ቀነስኩ።”