በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የማይጠቅም ጓደኛ

የማይጠቅም ጓደኛ

የማይጠቅም ጓደኛ

ወጣት ሳለህ የተዋወቅከው አንድ “ጓደኛ” አለህ። ይህ ጓደኛህ ትልቅ ሰው እንደሆንክ እንዲሰማህ ያደረገህ ከመሆኑም በላይ በሌሎች ዘንድም ተቀባይነት እንድታገኝ አስችሎሃል። ውጥረት በተሰማህ ቁጥር “ዘና” እንዲያደርግህ የምትሄደው ወደ እሱ ነው። በአብዛኛው ያለሱ መንቀሳቀስ አልሆንልህ እያለህ መጥቷል።

ከጊዜ በኋላ ግን ይህ “ጓደኛህ” መጥፎ ጠባይ እንዳለው ደረስክበት። ከእሱ ጋር መሆንህ ተገቢ በማይሆንባቸው ቦታዎች እንኳ ሳይቀር ሁልጊዜ አብሬህ ካልሆንኩ ይልሃል። ትልቅ ሰው እንደሆንክ እንዲሰማህ ያደረገህ ቢሆንም እንኳን ለዚህ ያበቃህ ጤንነትህን እየጎዳ ነው። ይህ ሁሉ እንዳይበቃው ከደሞዝህ የተወሰነውን ይሰርቅሃል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከእሱ ጋር ያለህን ጓደኝነት ለማቆም ብትሞክርም የሙጥኝ ብሎ ይዞሃል። በሌላ አባባል ጌታህ ሆኗል ማለት ነው። አሁን አሁን ከእሱ ጋር የተዋወቅክበትን ቀን መርገም ጀምረሃል።

ብዛኞቹ አጫሾች ከሲጋራ ጋር ያላቸው ዝምድና ይህን ይመስላል። ለ50 ዓመታት ያህል አጭሳ የነበረች ኧርሊን የተባለች አንዲት ሴት ሁኔታውን ስታስታውስ እንዲህ ብላለች፦ “ከሰው ጋር ከምሆን ይልቅ ከሲጋራ ጋር መሆን ይበልጥ ያረጋጋኝ ነበር። የረጅም ጊዜ ጓደኛዬ ብቻ ሳይሆን ያለሱ ጓደኛ እንደሌለኝ የሚሰማኝ ጊዜ ነበር።” ይሁን እንጂ ኧርሊን ኋላ ላይ እንደተገነዘበችው ሲጋራ የማይጠቅም ጓደኛ ብቻ ሳይሆን ጨካኝም ነው። በእርግጥም ከአንድ ነገር በስተቀር በመግቢያው ላይ የተጠቀሱት ነገሮች በሙሉ በእሷ ሕይወት ውስጥ ተፈጽመዋል ማለት ይቻላል። ኧርሊን፣ ማጨስ አምላክ የሰጠንን አካል የሚበክል በመሆኑ በእሱ ዘንድ የተጠላ እንደሆነ ስታውቅ ይህን ልማዷን አቆመች።—2 ቆሮንቶስ 7:1

ፍራንክ የተባለ አንድ ሰውም አምላክን ለማስደሰት ሲል ማጨሱን ለማቆም ወሰነ። ማጨሱን ካቆመ ከአንድ ከሁለት ቀን በኋላ ግን በቤቱ ወለል ላይ በእንብርክክ እየሄደ በሳንቃዎቹ መካከል የተሾጎጠ የሲጋራ ቁራጭ መፈለግ ጀመረ። “ቁርጥ ያለ ውሳኔ ያደረግኩት በዚህ ጊዜ ነበር” በማለት ፍራንክ ተናግሯል። “በእጄና በእግሬ እየዳህኩ የሲጋራ ቁራጭ ለማግኘት በስንጥቆቹ መሃል የተጋገረውን አቧራ ስጭር ራሴን ታዘብኩት። ሁኔታዬ ስለዘገነነኝ ከዚያ በኋላ አንድም ሲጋራ አላጨስኩም።”

ሲጋራ ማጨስን ማቆም ይህን ያህል አስቸጋሪ የሆነው ለምንድን ነው? ተመራማሪዎች ለዚህ ምክንያት የሚሆኑ በርካታ ነገሮች እንዳሉ ደርሰውበታል፦ (1) የትንባሆ ምርቶች ከሕገ ወጥ ዕፆች ያላነሰ ሱስ ሊያሲዙ ይችላሉ። (2) ወደ ሳንባ የገባ ኒኮቲን በሰባት ሴኮንድ ውስጥ ወደ አንጎል ይደርሳል። (3) የሚያጨሱ ሰዎች በሚመመገቡበት፣ በሚጠጡበት፣ ከሌሎች ጋር በሚጨዋወቱበት፣ ጭንቀታቸውን በሚያስታግሱበትና በመሳሰሉት ጊዜያት ሁሉ ስለሚያጨሱ ሲጋራ ከዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው።

ይሁን እንጂ ከኧርሊንና ከፍራንክ ሕይወት መመልከት እንደሚቻለው ከዚህ ጎጂ ሱስ መላቀቅ ይቻላል። የምታጨስ ብትሆንም ለማቆም የምትፈልግ ከሆነ ቀጥሎ ያሉትን ተከታታይ ርዕሶች ማንበብህ ሕይወትህን በአዲስ መልክ ለመምራት ጥሩ ጅማሮ ሊሆንልህ ይችላል።