በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከባሕር እስከ ባሕር የተዘረጋ “የብረት መቀነት”

ከባሕር እስከ ባሕር የተዘረጋ “የብረት መቀነት”

ከባሕር እስከ ባሕር የተዘረጋ “የብረት መቀነት”

ናዳ በዓለም ላይ ካሉት አገሮች በቆዳ ስፋት ሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ሲሆን ከ150 ዓመታት በፊት አብዛኛው የአገሪቱ ክፍል ሰው ያልደረሰበት ጠፍ ምድር ነበር። ታሪክ ፀሐፊው ፒየር በርተን ሲገልጹ “ከጠቅላላው ሕዝብ ሦስት አራተኛ የሚሆነው የሚኖረው በአንጻራዊ ሁኔታ ገለልተኛ በሆኑ የእርሻ መሬቶች ላይ” ሲሆን የመንገዶቹ ሁኔታ ደግሞ “ራቅ ወዳለ ቦታ ለመጓዝ ፈጽሞ የማያመች ነበር” ብለዋል። ሐይቆችና ወንዞች በዓመት ለአምስት ወር ያህል በበረዶ ስለሚሸፈኑ በእነዚህም ላይ እንደልብ መጓጓዝ አይቻልም ነበር።

ይህ ተፈታታኝ ሁኔታ ያሳሰባቸው የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ጆን ማክዶናልድ በ1871 የካናዳን የአትላንቲክ ዳርቻ ከፓስፊክ ዳርቻ ጋር የሚያገናኝ የባቡር ሐዲድ እንዲሠራ ሐሳብ አቀረቡ። እንዲህ ያለ የባቡር ሐዲድ በ1869 በዩናይትድ ስቴትስ ተሠርቶ ተጠናቅቋል፤ ሆኖም ካናዳ ብዙ ገንዘብ ስላልነበራት፣ የሚሠራው ሐዲድ የበለጠ ርዝመት ስለነበረውና የሕዝብ ብዛቷም ከዩናይትድ ስቴትስ 90 በመቶ ስለሚያንስ ይህን ሐዲድ መሥራት የማይመስል ነገር ነበር። እንዲያውም አንድ የካናዳ የፖለቲካ መሪ የታቀደውን ፕሮጀክት በተመለከተ “ፈጽሞ ሊታሰብ የማይችል የሞኝነት ሐሳብ” በማለት አጣጥለውታል። ሌላ ግለሰብ ደግሞ ከዚህ ቀጥሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ጨረቃ የሚደርስ ሐዲድ እንሥራ ሳይሉ አይቀሩም በማለት ተዘባብተውባቸዋል።

ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የሚጠይቅ ፕሮጀክት

ይሁን እንጂ መንግሥት የባቡር መስመሩን በአሥር ዓመት ውስጥ እንደሚጨርስ ቃል ገባ። የስኮትላንድ ባቡር መስመር መሐንዲስ የነበሩት ሳንድፈርድ ፍሌሚንግ የባቡር ሐዲዱን ሠርቶ ለማጠናቀቅ 100 ሚሊዮን የካናዳ ዶላር እንደሚፈጅ ገመቱ፤ ይህ ገንዘብ በዚያ ዘመን በጣም ብዙ ነበር። ሐዲዱ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ዩናይትድ ስቴትስን አቋርጦ ቢያልፍ ርዝመቱን ሊያሳጥረውና ሥራውን ሊያቀለው ቢችልም ማክዶናልድ ጦርነት ቢነሳ እንኳ የካናዳን ጥቅም ማስጠበቅ እንዲቻል በማሰብ መስመሩ ሙሉ በሙሉ በካናዳ ውስጥ እንዲሠራ ወሰኑ።

ብዙ ባለሀብቶች እንዲህ ባለ ውድና አስተማማኝ ባልሆነ ፕሮጀክት ላይ መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ፈቃደኛ አልሆኑም። ይሁን እንጂ በ1875 የካናዳ ፓስፊክ የባቡር ጣቢያ የዋናውን መስመር የግንባታ ሥራ አንድ ብሎ ጀመረ። ከአሥር ዓመት በኋላ ግን ፕሮጀክቱ ሙሉ በሙሉ የመቋረጥ አደጋ ተጋረጠበት። የካናዳ ፓስፊክ የባቡር ጣቢያ የነበረበትን የ400,000 የካናዳ ዶላር ዕዳ መክፈል አልቻለም ነበር፤ ዕዳውን እስከ ሐምሌ 10 ከቀኑ 9:00 ሰዓት ድረስ እንዲከፍል ይጠበቅበት ነበር። ይሁን እንጂ በዚያው ቀን 8:00 ሰዓት ላይ የካናዳ ፓርላማ ፕሮጀክቱ እንዳይስተጓጎል ሲል ተጨማሪ ብድር ለመስጠት ተስማማ።

በግንባታው ወቅት ያጋጠሙ ተፈታታኝ ችግሮች

ሠራተኞች በሰሜናዊ ኦንታርዮ ሐዲድ በሚዘረጉበት ጊዜ 30 ሴንቲ ሜትር ገደማ ጥልቀት ላይ ዐለት አገኙ። በዚህ ምክንያት መሬቱን ከፍ ለማድረግ ከረጅም ርቀት አፈር ማጓጓዝ አስፈልጓል። በማዕከላዊ ካናዳ ደግሞ የክረምቱ ቅዝቃዜ ከዜሮ በታች እስከ 47 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ስለሚወርድ በግንባታው ላይ በርካታ ችግሮች አስከትሏል። ከዚህም ሌላ በየዓመቱ በተወሰኑ ወራት የሚዘንበው በረዶ መጠን በመቶ ሴንቲ ሜትሮች የሚለካ ነበር። በተጨማሪም ሐዲዱ የሚያልፍበት ሮኪ ማውንቴን የሚባለው በስተ ምዕራብ የሚገኘው ተራራማ አካባቢ አደገኛ ከመሆኑ የተነሳ “ሞት ሳያስጠነቅቅ የሚመጣበት ቦታ” የሚል ስያሜ ተሰጥቶት ነበር። ከዚህም በላይ በርካታ ዋሻዎችንና ድልድዮችን መገንባት አስፈልጓል። ዝናብ፣ ጭቃና በረዶ ቢኖርም በቀን ውስጥ አሥር ሰዓት መሥራት የግድ ነበር።

በመጨረሻም ኅዳር 7, 1885 ብሪትሽ ኮሎምቢያ በተባለው የአገሪቱ ምዕራባዊ ክፍል በሚገኘው ኢግል ፓስ በተባለው ተራራማ ቦታ የመጨረሻው ሐዲድ ያለምንም ግርግር ተዘረጋ። ይህ ጣቢያ ስኮትላንድ ውስጥ በሚገኝ ክሬገልአኪ በተባለው የሩጫ መንደር ተሰየመ፤ የመንደሩ ስም አስቸጋሪ ሁኔታ ሲያጋጥም ጥርስን ነክሶ በከፍተኛ ወኔ ማሳለፍ የሚል ትርጉም አለው። የካናዳ ፓስፊክ ባቡር ጣቢያ ሥራ አስኪያጅ ንግግር እንዲያደርጉ ሲጠየቁ “ማለት የምችለው ነገር ቢኖር ሥራው በማንኛውም መልኩ በሚገባ ተሠርቷል ብቻ ነው” በማለት ተናግረዋል።

የሰዎችን ሕይወት ለውጧል

ለዚህ ፕሮጀክት ሲባል ከአገራቸው እንዲመጡ የተደረጉት በሺዎች የሚቆጠሩ ቻይናውያን የጉልበት ሠራተኞች በባቡር ጣቢያው ውስጥ ቋሚ ሥራ እንደሚያገኙ ቃል ተገብቶላቸው ነበር። አብዛኛውን ጊዜ ሥራው በተለይ ሮኪ ማውንቴን በተባለው አካባቢ እጅግ አደገኛ ነበር። በርካታ ሠራተኞች በቂ ገንዘብ አጠራቅመው ወደ አገራቸው መመለስ የቻሉት የሐዲዱ ሥራ ከተጠናቀቀ ከበርካታ ዓመታት በኋላ ነበር።

የሐዲዱ መዘርጋት ኢንዱስትሪና ንግድ ወደ ምዕራብ እንዲስፋፋ በማድረጉ የአካባቢው ነዋሪዎች ባሕላዊ አኗኗር በእጅጉ ተለወጠ። ትናንሽና ትላልቅ ከተሞች በመመሥረታቸው የአገሬው ተወላጆች ለእነሱ ብቻ በተወሰነ ክልል ውስጥ መኖር ጀመሩ። በጥንቶቹ የንግድ መስመሮች ላይ ተሠርተው የነበሩ እንደ መጠጥ ቤት ያሉ ትናንሽ የንግድ ቤቶች ተዘጉ። በበጎ ጎኑ ደግሞ ባቡሩ “ኅብረተሰቡን ከአቧራና ከጭቃ ገላግሏል” እንዲሁም “ከክረምት ባርነት ነፃ አውጥቷል” ተብሎ ይነገራል። በተጨማሪም ከሩቅ ምሥራቅ አገሮች በካናዳ የፓስፊክ ዳርቻዎች በኩል የሚገባው የምግብ ሸቀጥ በጥቂት ቀናት ውስጥ በስተ ምሥራቅ ወደሚገኙ ከተሞች መድረስ ቻለ።

ባቡር ዛሬም ትላልቅ ጭነቶችን በመላው ካናዳ በማጓጓዝ የሚጫወተውን ሚና የቀጠለ ቢሆንም በመኪና እንዲሁም በአውሮፕላን ምክንያት በባቡር የሚጓዙ ሰዎች ቁጥር በጣም ቀንሷል። ይሁን እንጂ ዛሬም ቢሆን ከቶሮንቶ እስከ ቫንኩቨር የሚጓዙ ምቹ ባቡሮችን ተሳፍረው የአካባቢውን ውበት በመቃኘት 21ኛው መቶ ዘመን ካመጣው ወከባ ከበዛበት ሕይወት እፎይ ለማለት የሚፈልጉ ብዙ ሰዎች አሉ። በመሆኑም ባቡር በአንድ ወቅት አድርጎት እንደነበረው የሕይወትን ሩጫ ከማፋጠን ይልቅ ተሳፋሪዎች በካናዳ “የብረት መቀነት” ላይ ከአንዱ የባሕር ዳርቻ ወደ ሌላው እየተጓዙ ዘና እንዲሉና የባቡር አገልግሎት ያሳለፈውን አስደናቂ ታሪክ መለስ ብለው እንዲያስታውሱ ያስችላል።

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

“በብረት መቀነት” ላይ እየተጓዙ ስለ ተስፋችን ለሌሎች ማካፈል

ዛሬም ቢሆን የባቡር ሐዲድ ለአንዳንድ የካናዳ ማኅበረሰቦች ዋነኛው መጓጓዣ ነው፤ በመሆኑም የይሖዋ ምሥክሮች ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ራቅ ብለው ወደሚገኙ አካባቢዎች ለማድረስ ይጠቀሙበታል። (ኢሳይያስ 9:6, 7፤ ማቴዎስ 6:9, 10) እነዚህ የይሖዋ ምሥክሮች እንደተናገሩት “ሰዎች ወዴትና ለምን እንደምንሄድ የማወቅ ፍላጎት ስላላቸው ባቡር ላይ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ አንስቶ መነጋገር ቀላል ነው።”

አንድ የይሖዋ ምሥክር በሰሜናዊ ኦንታርዮ፣ ኒፒጎን ሐይቅ አጠገብ ወደምትገኘው የኦጂብዋ መንደር ስላደረገው የባቡር ጉዞ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “የአካባቢው ውበትና ያየናቸው እንስሳት በጣም አስደናቂ ቢሆኑም ከሁሉ በላይ ትዝ የሚለን ያገኘናቸው ሰዎች ናቸው። ብዙ ጎብኚዎች ወደዚያ አካባቢ ስለማይሄዱ የእኛ መሄድ የማወቅ ጉጉታቸውን ቀስቅሶ ነበር። አንዳንዶቹ ታንኳቸውን አውሰውን የነበረ ሲሆን አንድን የመማሪያ ክፍል ያለምንም ክፍያ እንድንጠቀምበት ፈቅደውልናል። ሙሉ ቀን ከሰበክን በኋላ የማኅበረሰቡ አባላት ስለ ዓለም አቀፉ የስብከት ሥራችን የሚያሳየውን ቪዲዮ ለማየት በዚህ ክፍል ተሰበሰቡ።”

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሰር ጆን ማክዶናልድ

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የባቡር ሐዲድ መዘርጋት በጣም ከባድ ሥራ ነበር

[በገጽ 17 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ብዙ ድልድዮችና ዋሻዎች መገንባት ነበረባቸው

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የካናዳ የአሕጉር አቋራጭ የባቡር ሐዲድ የመዘርጋት ሥራ መጠናቀቁን የሚያበስረው የመጨረሻው መስመር ሲገጠም

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በዛሬው ጊዜ “በብረት መቀነት” ላይ መጓዝ

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Top: Canadian Pacific Railway (A17566); middle: Library and Archives Canada/C-006513

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Top, left to right: Canadian Pacific Railway (NS13561-2); Canadian Pacific Railway (NS7865); Library and Archives Canada/PA-066576; bottom: Canadian Pacific Railway (NS1960)

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Top: Canadian National Railway Company; right: Courtesy VIA Rail Canada Inc.