ከዓለም አካባቢ
ከዓለም አካባቢ
“በጥር ወር 2009 ስምንት አገሮች ከ23 300 የሚበልጡ የኒውክሌር መሣሪያዎች ባለቤት ሆነዋል።”—የስቶክሆልም ዓለም አቀፍ የሰላም ምርምር ተቋም፣ ስዊድን
በአፍሪካ በቅርቡ በውጭ እርዳታ ከተቆፈሩት በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ጥልቅ ጉድጓዶችና የውኃ መሳቢያ መሣሪያዎች መካከል ብዙዎቹ “በጥገና ጉድለትና በቀላሉ ሊስተካከሉ በሚችሉ ችግሮች የተነሳ” ከአገልግሎት ውጭ ሆነዋል።—የአካባቢና የልማት ዓለም አቀፍ ተቋም፣ ብሪታንያ
ሳይንቲስቶች የማሞዝን ግልገል በስካን መረመሩ
የሩሲያ ሳይንቲስቶች ማሞዝ በመባል የሚታወቀውን የዝሆን ዝርያ ውስጣዊ አካላት በዝርዝር ማየት ችለዋል። በሞተበት ጊዜ ከሦስት እስከ አራት ወር ዕድሜ የነበረው ይህ ግልገል ሰውነቱ ሳይፈርስ በበረዶ ውስጥ የተገኘው በሩሲያ የማለነኔትስ በሚባለው የአርክቲክ ክልል ውስጥ ነው። የሩሲያ የሥነ እንስሳት ተቋም ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት አሊክስዬ ቲዪኮኖቭ “እንደዚህ ባለ ሁኔታ ሳይፈራርስ ተጠብቆ የቆየ የዚህ ዓይነት እንስሳም ሆነ ሌላ ጥንታዊ ዝርያ ተገኝቶ አያውቅም” ብለዋል። የሰውን የውስጥ አካል ለመመርመር ከሚያስችል መሣሪያ ጋር በሚመሳሰል የኮምፒውተር ቶሞግራፊ ታይቶ ምንም ዓይነት ጉዳት እንዳልደረሰበት ተረጋግጧል። የዚህ እንስሳ የመተንፈሻ ቧንቧና የምግብ መፍጫ አካላቱ ደለል በሚመስል ነገር ተዘግቶ በመገኘቱ ሳይንቲስቶች ይህ እንስሳ የሞተው “ሰምጦ” መሆን አለበት ወደሚል መደምደሚያ ደርሰዋል።
አስቸኳይ ፍቺ
ኤል ኡኒቨርሳል የተባለው ጋዜጣ እንደዘገበው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሜክሲኮ ሲቲ መፋታት በጣም ቀላል ሆኗል። በ2008 እንደ መወስለት፣ ድብደባና ወዘተ ያሉት ለመፋታት የሚያበቁ 21 ምክንያቶች ከሕግ መጻሕፍት እንዲሰረዙ ተደርገዋል። በአሁኑ ጊዜ አንድ ሰው ፍቺ ለማግኘት የሚያስፈልገው 400 የአሜሪካ ዶላር የሚያህል ገንዘብ በአንድ የሕግ ቢሮ የባንክ ሂሣብ ውስጥ ማስያዝና ከኢንተርኔት በሚያገኘው ቅጽ ላይ የትዳር ጓደኛውን እንደማይወድ የሚገልጽ ማመልከቻ ሞልቶ በመፈረም ለፍርድ ቤት መላክ ብቻ ነው። ዳኛ ፊት ቀርቦ ማስረጃ ማቅረብ አያስፈልገውም። ቀደም ባለው ጊዜያት ዓመታት ይፈጅ የነበረው የፍቺ ሂደት አሁን ከሁለት እስከ አራት ባሉት ወራት ውስጥ ያልቃል። ልጅ የማሳደግ መብት፣ ተቆራጭ የመስጠት፣ ንብረት የመከፋፈልና ሌሎች ጉዳዮች ከፍቺ በኋላ እልባት ያገኛሉ።
ሃሚንግበርድ ‘ከተዋጊ ጀት የበለጠ ፍጥነት አላት’
በበርክሌይ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘው የካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ምርምር የሚያደርጉ አንድ ሰው እንደገለጹት ቁልቁል የምትወረወረው ሃሚንግበርድ የተባለች ወፍ በሴኮንድ የምትጓዘው ርቀት ከአካሏ ርዝመት ጋር ተነጻጽሮ ቢሰላ ከተዋጊ ጀት የሚበልጥ ፍጥነት አላት። ክሪስቶፈር ክላርክ፣ አና የተባለው የሃሚንግበርድ ዝርያ ሴቷን ለማማለል የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በፊልም ካነሱ በኋላ ወንዱ ሴቷን ለመማረክ ሲል ቁልቁል በሚወረወርበት ጊዜ “ፍጥነቱ በሴኮንድ የቁመቱን 400 እጥፍ እንደሚደርስ” አስልተዋል። ክላርክ ይህ ፍጥነት በሙሉ ኃይሉ ከሚበር “ተዋጊ ጀት” ፍጥነት ጋር ሲነጻጸር “በጣም ከፍተኛ” እንደሆነ ገልጸዋል። ይህ ወፍ ቁልቁል ከተወረወረ በኋላ ወደ ላይ በሚመለስበት ጊዜ ከስበት ኃይል አሥር እጥፍ የሚበልጥ ግፊት መቋቋም ይኖርበታል፤ የተዋጊ ጀት አብራሪዎች በዚህ ፍጥነት ቢመለሱ ራሳቸውን ይስታሉ።