በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ውጥረትን መቆጣጠር የምንችልበት መንገድ

ውጥረትን መቆጣጠር የምንችልበት መንገድ

ውጥረትን መቆጣጠር የምንችልበት መንገድ

መጽሐፍ ቅዱስ ‘አስቸጋሪ ስለሆነና ከፍተኛ ውጥረት ስላለበት አደገኛ ዘመን’ ይናገራል። የምንኖረው ከፍተኛ ውጥረት በነገሠበት ዘመን ውስጥ ነው ቢባል ሳትስማማ አትቀርም።—2 ጢሞቴዎስ 3:1 ዚ አምፕሊፋይድ ባይብል

እንደምታውቀው ከፍተኛ የእሳት ቃጠሎን ከማጥፋት ይልቅ ትንሽ እሳትን ማጥፋት ቀላል ነው። በተመሳሳይም ለብዙ ጊዜ ከተከማቸ ከፍተኛ ውጥረት ይልቅ አነስተኛ መጠን ያለውን ውጥረት መቆጣጠር ቀላል ነው። አንድ የሕክምና ዶክተር “በሥራ በተወጠረ ሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥመንን ውጥረት ለመቆጣጠር በየዕለቱ ጥረት ማድረጋችን አንገብጋቢ ነው” በማለት ተናግረዋል። *

ውጥረትን ለመቆጣጠር በየዕለቱ ጥረት ማድረጋችን ሁለት ጥቅሞች አሉት። አንደኛው በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥሙንን ልንቀንሳቸው የምንችላቸውን ውጥረት የሚያስከትሉ ሁኔታዎች ለመቀነስ ይረዳናል። ሁለተኛው ደግሞ ከአቅማችን በላይ በሆኑ ነገሮች ምክንያት ውጥረት ሲያጋጥመን ውጥረቱን መቋቋም እንድንችል ይረዳናል።

መጽሐፍ ቅዱስ ውጥረትን ለመቋቋም የሚረዳ መመሪያ ሊሰጠን ይችላል?

የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ትልቅ ቦታ አለው

በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኘውን እውነት በመቅሰም መንፈስን የሚያድሰውንና አጽናኝ የሆነውን የፈጣሪያችንን ሐሳብ ማግኘት እንችላለን። የአምላክ ቃል እጅግ ጠቃሚ የሆነ መመሪያ ይዟል። በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ ውጥረትን የሚያስታግሱ መንፈሳዊ እውነቶች ምንጭ ነው! እነዚህ እውነቶች ‘ፍርሃትንና ድንጋጤን’ እንድናስወግድ እንዲሁም በየዕለቱ የሚያጋጥሙንን ውጥረት የሚፈጥሩ ሁኔታዎች በተሳካ መንገድ እንድንወጣ ሊረዱን ይችላሉ።—ኢያሱ 1:7-9

መጽሐፍ ቅዱስ፣ የሰማዩ አባታችን ይሖዋ “ከአንጀት የሚራራና መሐሪ” አምላክ እንደሆነ የሚገልጽ ማረጋገጫ በመስጠት የሚሰማን ውጥረት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀንስ ይረዳናል። (ያዕቆብ 5:11) በካሊፎርኒያ በሚገኝ አንድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በፕሮፌሰርነት ያገለገሉት ፐትሪሸ የተባሉ ሴት እንዲህ በማለት ተናግረዋል፦ “በጣም የረዳኝ ነገር ስለ አምላክ ፈቃድና አምላክ እያከናወናቸው ስላሉት ድንቅ ነገሮች ማሰላሰሌ ነው።”

ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገራቸው ርኅራኄ የተሞላባቸው ቃላትና ያደረጋቸው ነገሮች በጊዜው ተጨቁነውና ውጥረት በዝቶባቸው የነበሩ አድማጮቹን መንፈስ በእጅጉ አድሰውላቸው እንደነበር መገመት አያዳግትም። “እናንተ የደከማችሁና ሸክም የከበዳችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም [መንፈሳዊ] እረፍት እሰጣችኋለሁ” በማለት በሚማርክ መንገድ ጋብዟቸዋል።—ማቴዎስ 11:28-30

በእርግጥም ኢየሱስ ክፉ ሰው አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ለደቀ መዛሙርቱ ስሜታዊና አካላዊ ፍላጎት ያስብ ነበር፤ እንዲያውም ከስብከት ሥራቸው ደክሟቸው ሲመለሱ እንዲያርፉ ዝግጅት ያደርግላቸው ነበር። (ማርቆስ 6:30-32) በአሁኑ ጊዜ በሰማይ ንጉሥ ሆኖ በመግዛት ላይ የሚገኘው ኢየሱስ እኛም አቅም የሚያሳጣ ውጥረት ሲያጋጥመን እንደሚራራልን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። “እርዳታ በሚያስፈልገን ጊዜ” በርኅራኄ ተገፋፍቶ ይደርስልናል።—ዕብራውያን 2:17, 18፤ 4:16

ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ ያለው ሚና

ውጥረትን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመቆጣጠር እጅግ አስፈላጊ ከሆኑት መሣሪያዎች አንዱ ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ምክር ሲጓደል ዕቅድ ይፋለሳል፤ በብዙ አማካሪዎች ግን ይሳካል” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 15:22) በመሆኑም ብዙ ሰዎች ውጥረት ስለፈጠረባቸው ነገር ከትዳር አጋራቸው፣ ከጓደኛቸው፣ ወይም ከሥራ ባልደረባቸው ጋር መማከራቸው ውጥረትን ለመቀነስ በእጅጉ እንደሚረዳ ተገንዝበዋል።

በቀላሉ ስሜታችንን ለሌላ አካል ልንገልጽ ከምንችልባቸው መንገዶች አንዱ ጸሎት ነው። እጅግ አስፈላጊና ጠቃሚ በሆነው በዚህ ዝግጅት አዘውትረህ መጠቀምህ ‘ስለ ምንም ነገር እንዳትጨነቅ’ ሊረዳህ ይችላል። ብዙ ሰዎች የጸሎት ሰው መሆናቸው ‘ከማሰብ ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነውን የአምላክ ሰላም’ እንዲያገኙ እንደረዳቸው ተገንዝበዋል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደተናገረው ‘ልባቸውና አእምሯቸው ተጠብቆላቸዋል።’—ፊልጵስዩስ 4:6, 7፤ ምሳሌ 14:30

ውጥረትን በተመለከተ የተዘጋጀ አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንዲህ ብሏል፦ “የሚደግፏቸው የቅርብ ጓደኞች ያሏቸው ሰዎች ሁሉንም ነገር ራሳቸው ለማድረግ ከሚጥሩ ሰዎች ይልቅ ውጥረትን የመቋቋም አቅም ያላቸው ሲሆን የተሻለ የአእምሮ ጤንነትም ይኖራቸዋል።” እውነተኛውን አምላክ ይሖዋን የሚያመልኩ ሰዎችን ያህል እርስ በርስ የሚደጋገፉ ወዳጆች የሉም። እነዚህ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር ተግባራዊ በማድረግ አዘውትረው አብረው በመሰብሰብ እርስ በርስ ይበረታታሉ። (ዕብራውያን 10:24, 25) እንዲህ ባሉ ስብሰባዎች ላይ ከሚካፈሉ ሰዎች መካከል አንዱ “አንዳንድ ጊዜ ለረጅም ሰዓት ስለምሠራ ከፍተኛ ውጥረት ያጋጥመኛል። ሆኖም በስብሰባ ላይ ከተገኘሁ በኋላ የመደምደሚያ ጸሎት ሲቀርብ የነበረኝ ውጥረት ሁሉ ለቆኝ መንፈሴ ይታደሳል” በማለት ተናግሯል።

ውጥረትን በመቋቋም ረገድ ተጫዋች መሆን ያለው ጠቀሜታም የሚናቅ አይደለም። መክብብ 3:4 “ለማልቀስ ጊዜ አለው፤ ለመሣቅም ጊዜ አለው” በማለት ይናገራል። ሣቅ መንፈስን የሚያድስ ከመሆኑም በላይ ለጤና ጥሩ ነው፤ ምክንያቱም አንድ ዶክተር እንደገለጹት “ስንስቅ ሰውነታችን ኢንዶርፊን የሚባሉትን ሆርሞኖች በማመንጨት አድሬናሊን ሆርሞን እንዳያመነጭ ያግደዋል።” አንዲት ባለ ትዳር “በጣም ውጥረት ባለበት ሁኔታ ውስጥም እንኳ ባለቤቴ የሚያስቅ ነገር መናገር ወይም ማድረግ ይመጣለታል፤ ይህ ደግሞ በእርግጥ ይረዳል” በማለት ገልጻለች።

ውጥረትን የሚቀንሱ ባሕርያት

መጽሐፍ ቅዱስ ውጥረትን የሚቀንሱ ባሕርያት እንዲኖሩን ያበረታታናል። ከእነዚህ ባሕርያት መካከል ‘የአምላክ መንፈስ ፍሬ’ ተብለው የሚጠሩት “ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ደግነት፣ ጥሩነት፣ እምነት፣ ገርነት፣ ራስን መግዛት” ይገኙበታል። ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ ‘የመረረ ጥላቻን፣ ቁጣን፣ ንዴትን፣ ጩኸትንና ስድብን’ እንድናስወግድ ያሳስበናል። አክሎም “አንዳችሁ ለሌላው ደጎችና ከአንጀት የምትራሩ ሁኑ፤ . . . እርስ በርሳችሁ በነፃ ይቅር ተባባሉ” በማለት ይናገራል።—ገላትያ 5:22, 23፤ ኤፌሶን 4:31, 32

አንድ ዶክተር በተለይም በዛሬው ጊዜ እንደነዚህ ያሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች በሥራ ላይ ማዋል ያለውን ጠቀሜታ ሲገልጹ “ሰዎችን በአክብሮት መያዝ ፍቱን የውጥረት ማስታገሻ ነው” ብለዋል። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ትሑቶች እንድንሆን ወይም ልካችንን እንድናውቅ ይረዳናል፤ ልክን ማወቅ ሲባል ስለ ችሎታዎቻችን ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ ማለት ነው።—ሚክያስ 6:8

አምላክ አካላዊ፣ አእምሯዊና ስሜታዊ ገደቦች እንዳሉብን እንዲሁም የምንፈልገውን ሁሉ ማድረግ እንደማንችል በትሕትና አምነን እንድንቀበል ይጠብቅብናል። ይህን ማድረግ አስቸጋሪ ሊሆን ቢችልም አቅማችን ከሚፈቅደው በላይ እንድንሠራ የሚቀርብልንን ጥያቄ ለመቀበል ፈቃደኞች አለመሆናችንን መቼና እንዴት መናገር እንዳለብን መማር ያስፈልገን ይሆናል።

እርግጥ ነው፣ ይህ ሲባል ከላይ የተገለጹትን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ምክሮች በሙሉ ተግባራዊ ካደረግህ ውጥረት ከተባለ ነገር ሁሉ ነፃ ትሆናለህ ማለት አይደለም። ሰይጣን ዲያብሎስ፣ አምላክን የሚያመልኩ ሰዎች ከፍተኛ ውጥረት ካጋጠማቸው እውነተኛውን አምልኮ ይተዋሉ ብሎ ላነሳው ክርክር ማስረጃ ለማቅረብ ሲል ትኩረቱን በአምላክ አገልጋዮች ላይ እንዳደረገ ማስታወስ ይኖርብናል። (ራእይ 12:17) ያም ሆኖ ቀደም ብለን እንደተመለከትነው አምላክ ያለብንን ውጥረት ለመቀነስ ብሎም ለመቋቋም እንድንችል የሚረዱ ወቅታዊ መመሪያዎች የሚሰጥባቸው ብዙ መንገዶች አሉ። *

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.3 የሚሰማህ ውጥረት ለረጅም ጊዜ ከዘለቀ ወይም ተባብሶ የጤና ችግር ካስከተለብህ ሕክምና ለማግኘት ወደ ጤና ባለሙያ መሄድህ ተገቢ ሊሆን ይችላል።

^ አን.20 ውጥረትን ለመቋቋም የሚቻልባቸውን ተጨማሪ መንገዶች ለማወቅ በሚያዝያ 2005 ንቁ! ላይ የወጣውን “ከውጥረት እረፍት ማግኘት!” የተሰኘውን ርዕስና በየካቲት 8, 2001 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ላይ የወጣውን “ሩጫ በበዛበት በዛሬው ጊዜ ውጥረትን መቋቋም” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ውጥረትን መቀነስ የሚቻልባቸው አንዳንድ መንገዶች

ከራስህም ሆነ ከሌሎች ፍጽምናን አትጠብቅ።—መክብብ 7:16

ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገባቸውን ነገሮች አስቀድም።—ፊልጵስዩስ 1:10, 11

አዘውትረህ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አድርግ።—1 ጢሞቴዎስ 4:8

በይሖዋ ፍጥረታት ተደሰት። —መዝሙር 92:4, 5

ፀጥታ የሰፈነበት ጊዜ እንዲኖርህ የሚያስችልህን ሁኔታ ዘወትር አመቻች።—ማቴዎስ 14:23

ዘና የምትልበትና የምትተኛበት በቂ ጊዜ ይኑርህ።—መክብብ 4:6

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ውጥረትን ለመቀነስ የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ አስፈላጊ ነው

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አምላካዊ ባሕርያትን ማዳበር ውጥረትን ለመቀነስ ይረዳል