ውጥረት—አሳሳቢ የጤና ጠንቅ
ውጥረት—አሳሳቢ የጤና ጠንቅ
“የተወሰነ የሥራ ሰዓት ሳይኖረኝ ቀንም ሆነ ሌሊት ለረጅም ሰዓት እሠራለሁ። ብዙውን ጊዜ በአንድ ሆስፒታል ቀዶ ሕክምና ሳደርግ እቆይና ሌላ ቀዶ ሕክምና ለማድረግ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ አልፌ ወደ ሌላ ሆስፒታል እሄዳለሁ።” —ዶክተር ፒተር ስቱዋርት፣ ደቡብ አፍሪካ
አንተን ውጥረት የፈጠረብህ ነገር ከዶክተር ስቱዋርት ፈጽሞ የተለየ ቢሆንም የዶክተሩን ስሜት ትረዳለት ይሆናል። አንተን ውጥረት ያስከተለብህ፣ በተጨናነቀ ትራፊክ መሃል መኪና መንዳት፣ በቤት ወይም በሥራ ቦታ ሰላም ማጣትህ ወይም ሌላ ነገር ሊሆን ይችላል። ይሁንና ውጥረት በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ አዲስ ነገር አይደለም።
ከ3 ሺህ ዓመታት በፊት፣ ጦርነት ምንም የማይመስለው የነበረ አንድ ወታደር “እንቅጥቃጤ መጣብኝ፤ ሽብርም ዋጠኝ” በማለት የተሰማውን ሳይሸሽግ ተናግሯል። (መዝሙር 55:5) ይህ ሰው ውጥረት ምን እንደሆነ ያውቅ ነበር። ገና በልጅነቱ እረኛ ሳለ ከአንበሳ፣ ከድብና ሊገድለው ካሰበ አስፈሪ ጦረኛ ጋር ተፋጦ ነበር።—1 ሳሙኤል 17:4-10, 23, 24, 34-36, 41-51
እውነት ነው፣ ውጥረት በራሱ መጥፎ አይደለም። አንድን ተፈታታኝ ሁኔታ እንድንጋፈጥ ኃይል ይሰጠናል። ሰዎች ለሕይወት አስጊ የሆኑ ሁኔታዎች ሲያጋጥሟቸው ውስጣቸው የሚፈጠረው ውጥረት እናደርገዋለን ብለው ጨርሶ አስበው የማያውቁትን ነገር እንዲፈጽሙ አስችሏቸዋል። አንድ ወሳኝ ሥራ ተሰጥቶህ በነበረበት ወቅት ሥራውን በሰዓቱ መጨረስ የቻልከው የተሰማህ ውጥረት በሰውነትህ ውስጥ ብዙ አድሬናሊን እንዲመነጭ ስላደረገ ይሆናል። *
ይሁን እንጂ ችግር የሚፈጠረው ውጥረቱ ፋታ የሌለው ሲሆንና ሰውነታችን ዘና ማለት ሲያቅተው ነው። አንድ ተመራማሪ “ውጥረት በጤንነታችንና በደኅንነታችን ላይ ስጋት የሚፈጥር ቁጥር አንድ ችግር ነው” ብለዋል። ያጋጠመህን ውጥረት ልትቋቋመው እንዳልቻልክ ከተሰማህ ወይም ያለብህ ውጥረት እዚያ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ካልፈለግክ “ከውጥረት እፎይ የምልበት መንገድ ይኖር ይሆን?” ብለህ ትጠይቅ ይሆናል።
ደግነቱ ውጥረትን መቀነስ የሚቻልበት ዘዴ አለ! ማንኛውም ሰው፣ ብዙዎች ውጥረትን እንዲቋቋሙ የረዳቸውን ዘዴ መጠቀም ይችላል። ይህ ዘዴ የሚገኘው በማትጠብቀው ቦታ ይኸውም የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ራስ አገዝ የሕክምና መጽሐፍ ባይሆንም እንኳ ሊረዳን የሚችል ተግባራዊ ጥበብ ይዟል። በዛሬው ጊዜ ውጥረት የበዛው ለምን እንደሆነ የሚናገር ሲሆን ለውጥረት መንስኤ ሊሆኑ አሊያም አስተዋጽኦ ሊያደርጉ የሚችሉ ምክንያቶችን ለይቶ ይገልጻል። በተጨማሪም ውጥረትን ለመቀነስና ለመቆጣጠር የሚረዱንን ጠቃሚ የመፍትሔ ሐሳቦች ይዟል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.5 አድሬናሊን፣ ከአድሬናል ዕጢዎችህ የሚመነጭና ድንገተኛ ሁኔታ ሲያጋጥምህ እንድትቋቋም የሚረዳህ ሆርሞን ነው።