የሰሜኑ ራሰ በራ ጋጋኖ እንዳይፈልስ ታገደ
የሰሜኑ ራሰ በራ ጋጋኖ እንዳይፈልስ ታገደ
አምስት አባላት ያሉት አንድ ቤተሰብ ረጅም ጉዞ ለመጀመር የተዘጋጀ ሲሆን ሸኚዎቹም ሊሰናበቱ መጥተዋል። ቤተሰቡ ለረጅም ጊዜ የኖረበትን አካባቢ ለመጨረሻ ጊዜ ዞር ዞር ብሎ ከቃኘ በኋላ ጉዞውን ጀመረ። ሸኚዎቹ ቆመው እየተመለከቱ እያለ እነዚህ አምስት ተጓዦች ርቀው በመሄድ ከዓይናቸው ተሰወሩ።
ያለነው በቱርክ አገር ከኤፍራጥስ ወንዝ አቅራቢያ በሚገኘው በብሪጂክ ከተማ ውስጥ ባለ ራሰ በራ ጋጋኖ በሚራባበት ጣቢያ ነው። ጉዞውን የጀመረው ይህ “ቤተሰብ” የመጥፋት አደጋ ከተጋረጠባቸው የአእዋፍ ዝርያዎች መካከል አንዱ የሆነው የሰሜኑ ራሰ በራ ጋጋኖ ነው። እያንዳንዱ ወፍ፣ የሚገኝበትን ቦታ የሚጠቁም የሳተላይት መሣሪያ እግሩ ላይ ተደርጎለታል። የጣቢያው ሠራተኞችና ጎብኚዎች የሆኑት ሸኚዎች፣ ወፎቹ ወዳልታወቀ አካባቢ ሲበሩ ዳግመኛ ይመለሱ ይሆን ወይስ በዚያው ጠፍተው ይቀሩ ይሆን የሚል ስጋት አስጨንቋቸዋል።
የሰሜኑ ራሰ በራ ጋጋኖ ምን ዓይነት ወፍ ነው? የሚፈልሰውስ ወዴት ነው? የዚህ ወፍ ፍልሰት ይህን ያህል ትኩረት የሳበው ለምንድን ነው?
ከባለ ላባው ወዳጃችን ጋር እናስተዋውቅህ
የሰሜኑ ራሰ በራ ጋጋኖ በሚፈለፈልበት ወቅት ራሱ በላባ የተሸፈነ ነው። ይሁን እንጂ እያደገ ሲሄድ ራሱ ላይ ያለው ላባ ይረግፋል። ራሰ በራው የሚል ስያሜ የተሰጠው በዚህ ምክንያት ነው። በቀረው የአካል ክፍሉ ላይ ያለው ጥቁር ላባ የፀሐይ ብርሃን ሲያርፍበት ወደ ወርቃማ አረንጓዴና ሰማያዊ ወይን ጠጅ የሚያደላ ቀለም ይኖረዋል። ከአናቱ በስተቀር ቆዳውና ምንቃሩ ቀይ ነው። በተጨማሪም በማጅራቱ ቁልቁል የሚወርዱ ረዘም ረዘም ያሉ ላባዎች አሉት።
ጋጋኖ ለአካለ መጠን የሚደርሰው ከሦስት ወይም ከአራት ዓመት በኋላ ነው። የሕይወት ዘመኑ ከ25 እስከ 30 ዓመት ይደርሳል። ባለ ሦስት አጽቄ ነፍሳትን፣ እንሽላሊቶችንና ትናንሽ አጥቢ እንስሳትን ይመገባል። እንስቶቹ ጋጋኖዎች በዓመት ከአንድ እስከ ሦስት የሚደርሱ እንቁላሎች ይጥሉና ለአንድ ወር ያህል ይታቀፏቸዋል። እነዚህ ወፎች አንድ በጣም አስደናቂ የሆነ ባሕርይ አላቸው፤
ወንዱና ሴቷ ዕድሜያቸውን ሙሉ አይለያዩም። አንደኛው ሲሞት በሕይወት የቀረው ወፍ አምርሮ ያዝናል። እንዲያውም በሕይወት የቀረው ወፍ ብዙውን ጊዜ ምግብ አልበላም ብሎ በረሃብ ሲሞት ወይም ከገደል አፋፍ ተወርውሮ ራሱን ሲገድል ታይቷል።የብሪጂክ ነዋሪዎች እስከ 20ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ ድረስ የጋጋኖዎች ከፍልሰት መመለስ በዓል ተደርጎ ይከበር እንደነበር ይናገራሉ። የወፎቹ መመለስ የጸደይን መቃረብ የሚያበስር እንደሆነ ተደርጎ ይታይ ነበር። በየካቲት ወር አጋማሽ ላይ በሚከበረው በዚህ በዓል ላይ ከበሮ እየተመታና እየተጨፈረ ጀልባዎች ከኤፍራጥስ ወንዝ እየተሳቡ ወደ ደረቅ ምድር እንዲመጡ ይደረግ ነበር።
በዚያ ዘመን የጋጋኖዎቹ መንጋ በጣም ብዙ ከመሆኑ የተነሳ በሰማይ ላይ ትልቅ ጥቁር ደመና መስለው ይታዩ ነበር። ይሁን እንጂ ባለፈው መቶ ዘመን በተለይ ደግሞ ባለፉት 50 ዓመታት ቁጥራቸው በጣም ተመናምኗል። በአንድ ወቅት በብሪጂክ ብቻ ከ500 እስከ 600 የሚደርሱ መራቢያ ዕድሜ ላይ የደረሱ ጥንዶች ነበሩ፤ ለእርሻ የሚያገለግሉ ፀረ ተባይ መድኃኒቶች ከተሠሩበት ከ1950ዎቹ ዓመታት ወዲህ ግን የወፎቹ ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ አሽቆልቁሏል። ዛሬ በመላው ዓለም የቀሩት የዚህ ወፍ ዝርያዎች በጣም ጥቂት ናቸው።
በቱርክ ወፎቹን ለመጠበቅ የተደረገ ጥረት
በብሪጂክ የራሰ በራ ጋጋኖዎች ማራቢያ ጣቢያ የተቋቋመው በ1977 ነው። አንድ ወፍ ብቻ እስከተመለሰበት እስከ 1990 ድረስ ወፎቹ በየዓመቱ እንዲፈልሱ ይፈቀድላቸው የነበረ ሲሆን ከዚያ በኋላ ግን እንዳይፈልሱ ታገዱ። የጣቢያው ሠራተኞች ወፎቹ መፍለስ በሚጀምሩባቸው በሐምሌና በነሐሴ ወራት በሽቦ ወደታጠረ የአእዋፍ ማቆያ ስፍራ ያስገቧቸዋል። ወፎቹ ከፍልሰት በሚመለሱበት ወቅት ይኸውም በየካቲት ወይም በመጋቢት ወር ይለቀቃሉ።
በ1997 ወፎቹ ለሙከራ እንዲፈልሱ ተደረገ። የሚያሳዝነው ግን ከተለቀቁት 25 ወፎች መካከል አንዳቸውም አልተመለሱም። ከ1998 ወዲህ ሁሉም ወፎች እንዳይፈልሱ ለማድረግ በአእዋፍ ማቆያ አጥር ውስጥ እንዲቆዩ ተደረገ። ያም ሆኖ ቁጥራቸው ጨምሯል። በአሁኑ ጊዜ በጣቢያው ውስጥ የሚገኙት ወፎች ቁጥር ወደ አንድ መቶ ተጠግቷል።
የሰሜኑ ራሰ በራ ጋጋኖ የወደፊት ዕጣ
የሚያሳዝነው፣ በመግቢያው ላይ ከተጠቀሱት አምስት ወፎች መካከል ሊመለሱ የቻሉት ሁለቱ ብቻ ናቸው። ከዚያ በኋላ በ2008 ሌላ የአእዋፍ ቡድን እንዲፈልስ ተደረገ። የሚያሳዝነው ነገር እነዚህም ሳይመለሱ ቀሩ። ወፎቹ እስከ ደቡብ ዮርዳኖስ ድረስ ተጉዘው ወደ ሰውነታቸው በገባው መርዝ ምክንያት እንደሞቱ ባለሥልጣናት ተናግረዋል። የሳይንስ ሊቃውንትና የመንግሥት ባለሥልጣናት ባደረጉት ጥረት በማራቢያ ጣቢያው ውስጥ የሚገኙት አእዋፍ ቁጥር ቢጨምርም የሰሜኑ ራሰ በራ ጋጋኖ የወደፊት ዕጣ አደጋ የተጋረጠበት መሆኑ አልቀረም።
ለራሳቸው ደኅንነት ሲባል እንዳይፈልሱ ቢደረግም የቅርብ ጊዜ ሙከራዎች እንዳረጋገጡት ራሰ በራ ጋጋኖዎች የመፍለስ ባሕርያቸውን አልረሱም። ይህ ደግሞ በኤርምያስ 8:7 ላይ የሚገኘውን የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ እውነተኝነት ያረጋግጥልናል፦ “ሽመላ እንኳ በሰማይ፣ የተወሰነ ጊዜዋን ታውቃለች፣ ዋኖስ፣ ጨረባና ዋርዳም፣ የሚሰደዱበትን ጊዜ ያውቃሉ።”
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Left: Richard Bartz; right: © PREAU Louis-Marie/age fotostock