በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአብሪ ጥንዚዛ ሙቀት አልባ ብርሃን

የአብሪ ጥንዚዛ ሙቀት አልባ ብርሃን

ንድፍ አውጪ አለው?

የአብሪ ጥንዚዛ ሙቀት አልባ ብርሃን

በቆላና በወይና ደጋ አካባቢዎች አብሪ ጥንዚዛ ተጓዳኝ ለመሳብ በሚያበራው መብራት ተለይቶ ይታወቃል። በጣም የሚያስደንቀው ግን አብሪ ጥንዚዛ የሚያመነጨው መብራት የሰው ልጆች ከሠሩት የኢንካንደሰንት እና የፍሎረሰንት መብራት እጅግ የላቀ ነው። እንዲያውም በሚቀጥለው ጊዜ የመብራት ሒሳብ እንድትከፍል ስትጠየቅ እነዚህ አነስተኛ ነፍሳት ብርሃን ለማመንጨት ምን እንደሚያደርጉ ቆም ብለህ አስብ።

እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ አንድ የኢንካንደሰንት አምፑል ወደ ብርሃን የሚለውጠው 10% የሚሆነውን የኤሌክትሪክ ኃይል ብቻ ሲሆን የቀረው ግን ወደ ሙቀትነት ተቀይሮ ባክኖ ይቀራል። የፍሎረሰንት አምፑል ግን 90% የሚሆነውን የኤሌክትሪክ ኃይል ወደ ብርሃን የመለወጥ ችሎታ ስላለው በጣም የተሻለ አገልግሎት ይሰጣል። ይሁን እንጂ አንዳቸውም ቢሆኑ ከአብሪ ጥንዚዛ ጋር ሊወዳደሩ አይችሉም። እነዚህ ነፍሳት የሚያመነጩት ብርሃን በጣም ጥቂት የአልትራቫዮሌት ወይም የኢንፍራሬድ ጨረሮች ስላሉት የሚጠቀሙበትን ኃይል ወደ 100% ገደማ ወደ ብርሃን ይለውጡታል።

የአብሪ ጥንዚዛ ሚስጥር ያለው ሉሲፈሪን የሚባለው ንጥረ ነገር፣ ሉሲፈሬስ የሚባለው ኢንዛይምና ኦክሲጅን አንድ ላይ ሲዋሃዱ በሚፈጥሩት ኬሚካላዊ ለውጥ ላይ ነው። ኦክሲጅንን እንደ ነዳጅ ተጠቅመው በሉሲፈሬስ አማካኝነት ይህ ኬሚካላዊ ውህደት እንዲፈጠር የሚያደርጉት ፎቶሳይት የሚባሉ ለየት ያሉ ሴሎች ናቸው። በውጤቱም ምንም ዓይነት ሙቀት የሌለው ብርሃን ይፈጠራል። የእፅዋትና የአካባቢ ሳይንስ አስተማሪ የሆኑት ሳንድራ ሜሰን፣ አምፑልን የፈለሰፈው ቶማስ ኤዲሰን “በአብሪ ጥንዚዛዎች በእጅጉ ሳይቀና አልቀረም” ብለዋል።

ታዲያ ምን ይመስልሃል? ሙቀት የሌለው የአብሪ ጥንዚዛ ብርሃን እንዲሁ በአጋጣሚ የተገኘ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ብርሃን የመስጠት ችሎታ

የኢንካንደሰንት አምፑል 10%

የፍሎረሰንት አምፑል 90%

አብሪ ጥንዚዛ 96%

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Firefly on leaf: © E. R. Degginger/Photo Researchers, Inc.; firefly in flight: © Darwin Dale/Photo Researchers, Inc.