በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጥሩ ገንዘብ ያስገኝልኝ የነበረውን ሥራዬን የተውኩበት ምክንያት

ጥሩ ገንዘብ ያስገኝልኝ የነበረውን ሥራዬን የተውኩበት ምክንያት

ጥሩ ገንዘብ ያስገኝልኝ የነበረውን ሥራዬን የተውኩበት ምክንያት

ማርታ ቴሬሳ ማርከስ እንደተናገረችው

መዝፈን ሁልጊዜ ያስደስተኝ የነበረ ሲሆን ልጅ እያለሁ የምዘፍነው ዘፈን በሬዲዮ ይተላለፍ ነበር። ከመዋዕለ ሕፃናት በኋላ ትምህርት አልተማርኩም፤ በኋላ ላይ ግን በሜክሲኮ ሲቲ የሲምፎኒ ሙዚቃ ጓድ ዳይሬክተር የሚሰጠውን የድምፅ ትምህርት ተከታተልኩ።

በ1969 በ24 ዓመቴ ዳንሰኛ የሆነች አንዲት ጓደኛዬ በዚያን ጊዜ ስመ ጥር በነበረው ላ ራምፓ አሱል ተብሎ በሚጠራ ሆቴል ውስጥ በሚደረገው የዘፈን ውድድር ላይ እንድካፈል ጋበዘችኝ። በዚያም የሜክሲኮው የሙዚቃ ደራሲ ቶማስ ሜንዴስ ያዘጋጀውን ኩኩሩኩኩ ፓሎማ የተሰኘ የታወቀ ዘፈን የዘፈንኩ ሲሆን በዚያ የነበሩት ሰዎችም በአዘፋፈኔ ተደሰቱ። ወደ ዘፋኝነት ሙያ የገባሁት በዚህ ሁኔታ ነበር። ሮሜሊያ ሮሜል በሚል ስም ብቻዬን በመዝፈን እታወቅ ነበር።

ቶማስ ሜንዴስ፣ ኩኮ ሳንቼዝና ክዋን ጋብሪኤልን ጨምሮ ከሌሎች እውቅ የሜክሲኮ የዘፈን ደራሲዎችና ዘፋኞች ጋር ሠርቻለሁ። ስሜን በማስታወቂያዎች፣ በጋዜጣና በመጽሔት ላይ ማየት ያስደስተኝ ነበር። የምዘፍነው ዘፈን በሬዲዮ ይተላለፍ የነበረ ከመሆኑም ሌላ በምሽት ክበቦች እንዲሁም በሜክሲኮና በቤሊዝ በተደረጉ የተለያዩ ኮንሰርቶች ላይ እዘፍን ነበር። በተጨማሪም ታዋቂ ከነበረችው ሊኦኖሪልዳ ኦኮኣ ከተባለች የሜክሲኮ ኮሜዲያን ጋርም ሠርቻለሁ፤ በወቅቱ እሷ የምታቀርበው የቴሌቪዥን ፕሮግራም በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ በሜክሲኮ አዲስ ነበር።

በዚህ ጊዜ ታዋቂ በመሆኔ ብዙ ገንዘብ አገኝ ስለነበር ከከበሩ ድንጋዮች የተሠሩ ጌጣጌጦችንና የፈር ኮቶች አደርግ ነበር፤ እንዲሁም በጣም ውድ በሆነ አፓርታማ ውስጥ እኖር ነበር። ሰው ሊያገኘው የሚፈልገው ነገር ሁሉ ያለኝ ቢመስልም እኔ ግን ደስተኛ አልነበርኩም። የባዶነት ስሜት ይሰማኝ ነበር። የሮማ ካቶሊክ ሃይማኖት ተከታይ ሆኜ ያደግኩ ቢሆንም ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄድ ያሳፍረኝ ነበር። በሥነ ምግባር የረከሰ አኗኗር እመራ ስለነበር በጣም ቆሻሻ እንደሆንኩ ይሰማኝ ነበር።

ይሖዋን መውደድ የጀመርኩበት መንገድ

ለመጀመሪያ ጊዜ ዘፈኖቼን ለማስቀረጽ ልምምድ በማደርግበት ወቅት ራንቼራ የተባለ የሜክሲኮ የባሕል ሙዚቃ ትጫወት ለነበረች ሎሬና ዎንግ ለምትባል አንዲት ጓደኛዬ የሚሰማኝን ነገርኳት። መነኩሴ ሆኜ የተቸገሩ ሰዎችን መርዳት እንደምፈልግ አጫወትኳት። “መነኩሴ? አብደሻል!” አለችኝ።

ከዚያም “የአምላክን ስም ታውቂዋለሽ?” ብላ ጠየቀችኝ።

“ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ነዋ” ብዬ መለስኩላት።

“አይደለም፤ የአምላክ ስም ይሖዋ ነው፤ ኢየሱስ ደግሞ ልጁ ነው” አለችኝ።

“ይሖዋ?” በማለት ጠየቅኳት። ይህን ስም ፈጽሞ ሰምቼው አላውቅም ነበር። ሎሬና መጽሐፍ ቅዱስ ሰጠችኝና ከይሖዋ ምሥክሮች አንዱ የሆነው አስተማሪዋ እኔ ጋር እንዲመጣ እንደምታደርግ ቃል ገባችልኝ። *

ሎሬናን ባገኘኋት ቁጥር “አስተማሪሽን የምትልኪልኝ መቼ ነው?” በማለት እጠይቃት ነበር። በመንፈሳዊ ተርቤ ነበር።

በዚህ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ የጀመርኩ ሲሆን የአምላክ ስም በእርግጥ ይሖዋ መሆኑን ተረዳሁ። (መዝሙር 83:18 NW) ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የአምላክን ስም ስመለከት በጣም ገረመኝ። በተጨማሪም አሥርቱን ትእዛዛት ሳነብ “አታመንዝር” የሚለው ትእዛዝ ጭንቅላቴን መታኝ። (ዘፀአት 20:14) በዚያን ጊዜ ከስምንት ወር ልጄ አባት ጋር እኖር የነበረ ሲሆን እሱም ባለ ትዳር ነበር። የመጀመሪያውን ልጄንም የወለድኩት ካላገባሁት ሰው ነው።

አንድ ቀን የማቀርበውን አዲስ ዘፈን እየተለማመድኩ ሳለሁ የቤቴ በር ተንኳኳ። የሎሬና አስተማሪ የሆነው ማውሪስዮ ሊናሬስና ባለቤቱ ነበሩ። አምላክ ለሰው ዘር ስላለው ዓላማ አስረድተውኝ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራው እውነት * የተሰኘውን መጽሐፍ ትተውልኝ ሄዱ። አንዳንድ ቃላት ለመረዳት አስቸጋሪ ስለሆኑብኝ ጥረት ቢጠይቅብኝም መጽሐፉን ከዳር እስከ ዳር በአንድ ሌሊት አንብቤ ጨረስኩት። ይሖዋን መውደድ የጀመርኩት ያን ጊዜ ነበር።

አኗኗሬን መለወጥ

የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስ ሲያስጠኑኝና የማንበብ ችሎታዬን እንዳሻሽል ሲረዱኝ ይሖዋን ለማስደሰት በአኗኗሬ ላይ ለውጥ ማድረግ እንዳለብኝ ተገነዘብኩ። ከወርቅ የተሠሩ ቢሆኑም እንኳ የነበሩኝን ሃይማኖታዊ ምስሎች፣ ሜዳሊያዎችና መልካም ዕድል ያስገኛሉ ተብለው የሚታሰቡ ጌጣጌጦች አስወገድሁ።

በተለይ ከባድ የሆነብኝ ማጨስና ብዙ የመጠጣት ልማዴን ማቆም ነበር። በመጠጥ ቤት አጠገብ ሳልፍ አፌ ምራቅ ይሞላ ነበር። ጓደኞቼ በጣም ውድ በሆኑ ምግብ ቤቶች ውስጥ ከእነሱ ጋር እንድበላና እንድጠጣ ይጋብዙኝ ስለነበር ከሁሉም ጋር ያለኝን ግንኙነት ማቋረጥ ነበረብኝ። ግብዣቸውን ብቀበል ከልክ በላይ ለመጠጣት እንደምፈተን አውቅ ነበር።

በተጨማሪም ሀብታምና ታዋቂ የሆኑ ሰዎች ወደሚያዘጋጇቸው ድግሶች መሄድን መተው ለእኔ ከባድ ነበር። አንድ ታዋቂ የኩባ ቦክሰኛ በልደት በዓሉ ላይ እንድገኝ በጠራኝ ጊዜ እንዲህ ብዬ ጸልዬ ነበር፦ “ይሖዋ፣ ይህ የመጨረሻዬ ይሁን። ከእንግዲህ እንዲህ ዓይነት ግብዣ ላይ አልገኝም፤ እንዲሁም አንተን በማያስደስት ድርጊት ላይ አልካፈልም።” ደግሞም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ቃሌን ጠብቄያለሁ።

ከሁለተኛው ልጄ አባት ጋር ያለኝን ግንኙነት አቋረጥኩ። በጣም ሀብታም የነበረና ትቼው ካልሄድኩ ብዙ ነገር እንደሚያደርግልኝ ቃል ቢገባልኝም ከእሱ ጋር የነበረኝን ግንኙነት አቋረጥኩ። እወደው ስለነበር ለእኔ ይህን ማድረግ ከባድ ነበር፤ እሱም ቢሆን ይህን ያውቅ ነበር። እንዲያውም “አምላክሽ እኔ ነኝ! ያንቺ ክርስቶስ እኔ ነኝ!” በማለት በትዕቢት ተናገረ።

እኔም “እስካሁን ሆነህ ሊሆን ይችላል፤ አሁን ግን አምላኬ ይሖዋ ነው” ብዬ መለስኩለት። ከእሱ የወለድኩትን ልጄን እንደሚወስድብኝና አካላዊ ጥቃት እንደሚያደርስብኝ አስፈራራኝ።

በወቅቱ አንዳንድ ሰዎች ዘፋኝነት ልክ እንደማንኛውም ሥራ ስለሆነ የይሖዋ ምሥክር ሆኜም ዘፋኝ መሆን እንደምችል ነግረውኝ ነበር። ሌሎች ግን “በዘፋኝነትሽ ከቀጠልሽ እንድታጨሺ፣ እንድትጠጪና ከአድናቂዎችሽ የሚመጣብሽን የሥነ ምግባር ፈተና መቋቋም እንድትችዪ አቅም ታጫለሽ” ብለው አሳሰቡኝ። እኔም ይኼኛው አስተያየት ጥበብ ያዘለ መሆኑን ተገነዘብኩ።

ታዋቂ ዘፋኝ በነበርኩበት ጊዜ ሰዎች ከእኔ ጋር ለመሆን ጥረት ያደርጉ ነበር። ከዚህ በኋላ ግን እንዲህ ላለው ፈተና ራሴን ላለማጋለጥ ቁርጥ ውሳኔ አደረግሁ። በመሆኑም በ1975 በቻይና ውስጥ እየተዘዋወርኩ ለመዝፈን የገባሁትን ውል ሰረዝኩ፤ ከስድስት ወር በኋላም ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ።

ተፈታታኝ ሁኔታዎችና ያገኘሁት ደስታ

ታዲያ ራሴንም ሆነ ቤተሰቤን ማስተዳደር የምችለው እንዴት ነው? በትምህርቴ ያልገፋሁ ከመሆኑም በላይ ከመዝፈን ሌላ ምንም ሙያ አልነበረኝም። ታላቅ እህቴን ኢርማንና ሦስት ልጆቿን እንዲሁም የእኔን ሁለት ልጆች የማስተዳድረው እኔ ነበርኩ። በጣም ውድ ከነበረው አፓርታማ ለቀን ሁለት ትንንሽ ክፍሎች ወዳሉት ቤት መዛወር ነበረብን። ከተንደላቀቀ ኑሮ ወደ ዝቅተኛ ኑሮ መውረድ በእርግጥም ተፈታታኝ ነበር። ለተወሰነ ጊዜ የተበሳጩት እህቴና ልጆቹ በዘፋኝነት እንድቀጥል ጫና ቢያሳድሩብኝም ይሖዋን ለማገልገል ማድረግ ያለብኝን ነገር ሁሉ ለመፈጸም ባደረግሁት ውሳኔ ጸናሁ።

የነበሩኝን ውድ ንብረቶች ማለትም ጌጣጌጦቼን፣ ከፈር የተሠሩ ኮቶቼን እንዲሁም መኪናዬን በመሸጥ ለተወሰነ ጊዜ በዚህ ገንዘብ መኖር ጀመርን። ከጊዜ በኋላ ግን ይህ ገንዘብ አለቀ። የሁለተኛው ልጄ አባት የሚያደርስብኝን ችግር ለመሸሽ ስል በ1981 ቤተሰቤን ይዤ ሊያገኘን ወደማይችልበት በአገሪቱ ሌላ ጫፍ ወደሚገኝ አንድ ከተማ ተዛወርን።

በዚህ ከተማ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ተማሊ፣ ዶናትና ሌሎች ምግቦችን እየሠራሁ መሸጥ እንድችል የምግብ አዘገጃጀት አስተማሩኝ። በኋላም በፋብሪካ ውስጥ የሌሊት ፈረቃ ሥራ አግኝቼ ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ሥራ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት እንዳልችል እንቅፋት የሆነብኝ ሲሆን ለአምላክ የማቀርበውንም አገልግሎት አስተጓጎለብኝ። በመሆኑም ከጊዜ በኋላ ከዚህ ሥራ ወጥቼ ቤት ውስጥ ተማሊ ማዘጋጀት ጀመርኩ። የሠራሁትን ተማሊ በቅርጫት ወስጄ መንገድ ላይ እሸጥ ነበር። በዚህ መንገድ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መካፈል ችያለሁ።

ፈጽሞ የማልቆጭበት ምርጫ

ሰዎች ብዙ ገንዘብ ያስገኝልኝ የነበረውን የዘፋኝነት ሥራ በማቆሜ ምን እንደሚሰማኝ ሲጠይቁኝ ስለ ይሖዋና አስደናቂ ስለሆኑት ዓላማዎቹ ለመማር ያገኘሁትን አጋጣሚ በምንም ነገር እንደማለውጠው እነግራቸዋለሁ። ወንዶች ልጆቼ በመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት እድገት አድርገው ሕይወታቸውን ለይሖዋ ሲወስኑና በኋላም የእምነት አጋሮቻቸውን ሲያገቡ ማየቴ ለእኔ ትልቅ ደስታ ነው። ሁለቱም ልጆቼ ከትዳር ጓደኞቻቸው ጋር በመሆን ልጆቻቸው አምላካችንን ይሖዋን የሚያገለግሉ እንዲሆኑ አድርገው እያሳደጉ ነው።

አቅኚ ሆኜ (ሙሉ ጊዜያቸውን በስብከቱ ሥራ የሚያሳልፉ የይሖዋ ምሥክሮች የሚጠሩበት መጠሪያ ነው) ወደ ሠላሳ ለሚጠጉ ዓመታት ይሖዋን አገልግያለሁ። በአምላክ እርዳታ ኢርማና ሴቶች ልጆቿን ጨምሮ ብዙ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንዲማሩ ብሎም ሕይወታቸውን ለአምላክ እንዲወስኑ መርዳት ችያለሁ። ከእነዚህ “መንፈሳዊ ልጆቼ” ጋር ስገናኝና በእውነት ውስጥ እየተመላለሱ እንዳሉ እንዲያውም አንዳንዶቹ አቅኚዎች እንደሆኑ ሳውቅ በጣም ደስ ይለኛል። (3 ዮሐንስ 4) አሁን በ64 ዓመቴ 18 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን እየመራሁ ነው።

ወጣት ዘፋኝ ሳለሁ ይሰማኝ የነበረው መንፈሳዊ ባዶነት ተወግዶልኛል፤ እንዲሁም ሌሎችን የመርዳት ፍላጎቴ ኢየሱስ ‘ሂዱና ደቀ መዛሙርት አድርጉ’ ብሎ የሰጠውን ትእዛዝ በመፈጸም ተሟልቶልኛል። (ማቴዎስ 28:19, 20) ይሖዋ በእነዚህ ሁሉ ዓመታት ደግፎ ስላቆመኝና አሁንም እየረዳኝ በመሆኑ እጅግ አመስጋኝ ነኝ! ይሖዋ በእርግጥ ‘ቸር እንደሆነ ቀምሼ ማየት’ ችያለሁ።—መዝሙር 34:8

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.12 ሎሬና ዎንግ ከጊዜ በኋላ የይሖዋ ምሥክር ሆናለች።

^ አን.15 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ፤ አሁን ግን መታተም አቁሟል።

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከወንዶች ልጆቼ፣ ከሚስቶቻቸውና አብራኝ በአቅኚነት ከምታገለግለው ከታላቅ እህቴ ጋር

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመካፈል ስል ተማሊ እየሠራሁ በመንገድ ላይ መሸጤን ቀጥያለሁ