በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“በምድር ላይ በትልቅነቱ ተወዳዳሪ የሌለው ሕይወት ያለው በራሪ ማሽን”

“በምድር ላይ በትልቅነቱ ተወዳዳሪ የሌለው ሕይወት ያለው በራሪ ማሽን”

“በምድር ላይ በትልቅነቱ ተወዳዳሪ የሌለው ሕይወት ያለው በራሪ ማሽን”

አልባትሮስ የተባለው ወፍ “በምድር ላይ በትልቅነቱ ተወዳዳሪ የሌለው ሕይወት ያለው በራሪ ማሽን” ተብሏል፤ ይህ ወፍ እንዲህ ተብሎ የተጠራበት በቂ ምክንያት አለ። ከባሕር አእዋፍ በትልቅነቱ ተወዳዳሪ የሌለው ይህ ወፍ ክንፎቹ ከጫፍ እስከ ጫፍ ሦስት ሜትር ርዝመት ሲኖራቸው በሰዓት ከ115 ኪሎ ሜትር በላይ መብረር ይችላል። አልባትሮስ በየብስ ላይ ሲታይ ቀርፋፋ ቢመስልም በሰማይ ላይ ሲበር ግን በጣም አስደናቂ ነው።

እስካሁን ከታወቁት 20 የሚያህሉ የአልባትሮስ ዝርያዎች መካከል 15 የሚያህሉት የሚገኙት ኒውዚላንድን በሚከበው ውቅያኖስ አካባቢ ነው። በደቡባዊው ንፍቀ ክበብ አልባትሮሶች የሚራቡበት ብቸኛ ቦታ በኒው ዚላንድ፣ ሳውዝ አይላንድ በሚገኘው የኦታጎ ባሕረ ገብ መሬት ጫፍ ይኸውም በታይሮዋ ባሕረ ገብ መሬት ነው።

በዚያም የሰሜኑ ሮያል አልባትሮስ ዘር መተካት የሚጀምረው ከስድስት እስከ አሥር ዓመት ባለው ዕድሜ ክልል ውስጥ ነው። ወፎቹ ከዚያ ዕድሜያቸው አንስቶ ለረጅም ዓመታት ይኸውም እስከ ሕይወታቸው ፍጻሜ ድረስ መራባት ይችላሉ። ከእነዚህ አእዋፍ መካከል አንዳንዶቹ ከሃምሳ ዓመት በላይ እንደኖሩ ተደርሶበታል። አልባትሮሶች በየሁለት ዓመቱ አንድ እንቁላል የሚጥሉ ሲሆን በመሃል ያለውን እንቁላል የማይጥሉበትን ዓመት የሚያሳልፉት በባሕር ላይ ነው። አብዛኛውን ጊዜ እነዚህ ወፎች ዕድሜያቸውን ሙሉ ከአንድ ተጓዳኝ ጋር ይኖራሉ።

በመስከረም ወር በሚጀምረው የጎጆ ግንባታ ላይ ወንዱም ሆነ ሴቷ አልባትሮስ ይካፈላሉ። ከዚያም በኅዳር ወር ላይ እንስቷ አልባትሮስ እስከ ግማሽ ኪሎ ግራም የሚመዝን እንቁላል ትጥላለች። ሰማንያ ለሚያህሉ ቀናት ወንዱም ሆነ ሴቷ ወፍ እየተፈራረቁ እንቁላሉን ከታቀፉት በኋላ በየካቲት ወር መጀመሪያ ላይ ይፈለፈላል። ከዚያም አንደኛው ጫጩቱን ሲጠብቅ ሌላኛው ምግብ ያመጣል፤ ጫጩቱ የሚመገበው ወላጆቹ ከዋጡ በኋላ አድቅቀው የሚሰጡትን ዓሣና የባሕር ፍጥረት ነው። ጫጩቱ ስድስት ወር ሲሞላው 12 ኪሎ ግራም ያህል ስለሚመዝን አካለ መጠን ከደረሰ አልባትሮስ የበለጠ ክብደት ሊኖረው ይችላል!

ወላጆቹ አንድ ዓመት ከሚያህል ጊዜ በኋላ የታይሮዋን ባሕር ገብ መሬት ለቅቀው የመራቢያ ጊዜያቸው ከመጀመሩ በፊት ለአንድ ዓመት በባሕር ላይ ይቆያሉ። በዚህ ጊዜ ውስጥ ክብደት የሚቀንሰውና ላባዎቹ በሙሉ የሚያድጉለት ልጃቸው ከብዙ ሙከራ በኋላ ክንፎቹን ዘርግቶ በአየር ላይ መብረር ይጀምራል። የሚበረው ወዴት ነው? ወጣት አልባትሮሶች ለጥቂት ዓመታት ወደሚኖሩበት ውቅያኖስ ነው። ወፉ ለአካለ መጠን ሲደርስ ወደ ታይሮዋ ባሕረ ገብ መሬት ይመለሳል። በዚያም በዕድሜ አንጋፋ የሆኑት አእዋፍ ጎጆ የመሥራት፣ የመታቀፍና ጫጩቶችን የመንከባከብ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ደፋ ቀና ሲሉ ወጣቱ አልባትሮስ ግን ራሱን በማሰማመር፣ በመገለባበጥና የተራቀቀ የበረራ ችሎታውን በማሳየት ያሳልፋል።

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የሮያል አልባትሮስን የመራቢያ ስፍራ መጎብኘት

ከልጅነቴ ጀምሮ ስለ አልባትሮስ የሚነገሩ ታሪኮች በእጅጉ ያስደንቁኝ ስለነበረ የሮያል አልባትሮስን የመራቢያ ስፍራ ለመጎብኘት በጣም ጓጉቼ ነበር። ቀኑ ነፋሻ ነበር፤ እኔና ባልደረባዬ ወደ አካባቢው ስንጠጋ የአልባትሮሶችን የበረራ ትርዒት ለመመልከት ወደ ሰማይ አማተርን። ጥረታችን ከንቱ አልሆነም። አእዋፉ ይበልጥ እየቀረቡ ሲመጡ ባላቸው የተራቀቀ የበረራ ችሎታ እጅግ ተደነቅን።

ቦታው እንደደረስን ከሌሎች ሰዎች ጋር ሆነን በአስጎብኚ አማካኝነት ለአንድ ሰዓት ያህል ጉብኝት አደረግን። በናሙናዎች፣ በሥዕላዊ መግለጫዎችና በቪዲዮ ፊልሞች በመታገዝ የሰሜኑ ሮያል አልባትሮስ ውኃ ላይ መተኛትን ጨምሮ ሙሉ በሙሉ በባሕር ላይ መኖር እንደሚችል አወቅን። ይህ የወፍ ዝርያ በባሕር ላይም ሆነ በየብስ ላይ ሲታይ በእርግጥም እጅግ አስደናቂ ነው! “ሁሉንም ነገሮች” የፈጠረውን ይሖዋ አምላክን የምናወድስበት ተጨማሪ ምክንያት ሰጥቶናል።—ራእይ 4:11

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሁለቱም ወላጆች እየተፈራረቁ በስድስት ወር ዕድሜው 12 ኪሎ ግራም የሚመዝነውን ጫጩት ይጠብቃሉ እንዲሁም ይመግባሉ

[በገጽ 24 እና 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የታይሮዋ ባሕረ ገብ መሬት፣ የሰሜኑ ሮያል አልባትሮስ መኖሪያ

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሰሜኑ ሮያል አልባትሮስ ውኃ ላይ መተኛትን ጨምሮ ሙሉ በሙሉ በባሕር ላይ መኖር ይችላል

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Top: © David Wall/Alamy; bottom: © Kim Westerskov/Alamy

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Background: © davidwallphoto.com; page 24, top: Tui De Roy/Roving Tortoise Photos; page 24, bottom: Courtesy Diarmuid Toman; page 25, albatross in flight: © Naturfoto-Online/Wolfgang Bittmann