በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከኢንዶኔዥያው “የጫካ ሰው” ጋር እናስተዋውቅህ

ከኢንዶኔዥያው “የጫካ ሰው” ጋር እናስተዋውቅህ

ከኢንዶኔዥያው “የጫካ ሰው” ጋር እናስተዋውቅህ

ግዙፍ አካሉን ሊሸከም የማይችል በሚመስል የዛፍ ቅርንጫፍ ላይ የተንጠለጠለው ግዙፍ ፍጥረት ትኩር ብሎ ተመለከተን። እኛም መልሰን ትኩር ብለን ተመለከትነው። እሱ ከቁብ የቆጠረን ባይመስልም እኛ ግን በአድናቆት ተመሰጥን። እያየነው ያለነው ፍጥረት በፕላኔታችን በዛፍ ላይ ከሚኖሩ እንስሳት ሁሉ በትልቅነቱ ተወዳዳሪ የሌለውን ኦራንጉተን የተባለውን እንስሳ ነው።

ኦራንጉተን እንደ ጎሪላና ቺምፓንዚ ካሉ ትልልቅ የዝንጀሮ ዝርያዎች የሚመደብ እንስሳ ነው። መናኝ የሚመስሉት እነኚህ ረጋ ያሉ ፍጥረታት የሚኖሩት በደቡባዊ ምሥራቅ እስያ ከሚገኙት ትልልቅ ደሴቶች መካከል በሁለቱ ይኸውም ጥቅጥቅ ያላ ጫካ ባላቸው በቦርንዮና በሱማትራ ደሴቶች ነው። ስማቸው የተገኘው “የጫካ ሰው” የሚል ትርጉም ካለው ኦራንግ እና ሁታን ከተባለ ሁለት የኢንዶኔዥያ ቃላት የተገኘ ነው።

አስደናቂ ስለሆኑት ስለ እነዚህ ግዙፍ ቀያይ የዝንጀሮ ዝርያዎች ይበልጥ ማወቅ ትፈልጋለህ? እንግዲያው ተፈጥሯዊ መኖሪያቸው ወደሚገኝበት ወደ ቦርንዮ ደን አብረን እንሂድና እንጎብኛቸው።

ኦራንጉተኖችን አገኘን

ኦራንጉተኖችን ለማየት ብዙ እንስሳት ወደሚገኙበት ወደ ታንጁንግ ፑቲንግ ብሔራዊ ፓርክ ተጓዝን። በዚያ የሚኖሩት በሺህ የሚቆጠሩ ኦራንጉተኖች ዋነኞቹ መስህቦች ናቸው።

ጉብኝታችንን የጀመርነው ክሎቶክ የሚባል ከእንጨት የተሠራ የሞተር ጀልባ ከተሳፈርንበት ኩማይ ከሚባል ትንሽ ወደብ ነው። ወንዙ ወደሚነሳበት አቅጣጫ በመጓዝ ጠመዝማዛ በሆኑ ቦዮች እያለፍን ጥቅጥቅ ባለው ደን ውስጥ ገባን። በወንዙ ዳርቻዎች ጥቅጥቅ ያሉ ኒፓ የተባሉ የዘንባባ ዛፍ ዝርያዎች የሚገኙ ሲሆን በተኛው ጥቁር ወንዝ ውስጥ አደገኛ አዞዎች ይርመሰመሳሉ። በደኑ ውስጥ የሚያስተጋባው እንግዳ የሆነ ድምፅ በውስጣችን ልዩ ስሜት ቀሰቀሰብን።

ከጀልባው እንደወረድን ነፍሳት የሚያባርር ሽታ ያለው ቅባት ከተቀባን በኋላ ወደ ጫካው ገባን። ጥቂት ደቂቃዎች እንደተጓዝን ከላይ የጠቀስነውን ትልቁን ወንድ ኦራንጉተን አየን። ጭብርር ያለው ቀይ ፀጉሩ የከሰዓቱ ፀሐይ ሲያርፍበት የተወለወለ መዳብ ይመስላል። ከፀጉሩ ሥር የሚታየው ፈርጠም ያለ ጡንቻ በእርግጥም ኦራንጉተንን ግርማ አላብሶታል!

በጫካ ውስጥ የሚኖሩት ወንድ ኦራንጉተኖች ቁመታቸው 1.7 ሜትር፣ ክብደታቸው ደግሞ ወደ 90 ኪሎ ግራም የሚደርስ ሲሆን ከሴቶቹ በእጥፍ ይበልጣሉ። ለአካለ መጠን የደረሱ ወንዶች ፊታቸው በጎንና በጎን አበጥ አበጥ ስለሚል ፊታቸው ክብ ቅርጽ ያለው እንዲሆን አድርጎታል። በተጨማሪም ከአገጫቸው ሥር የሚገኘውን ኩልኩልት ለማጉረምረምና ለመጮኽ ይጠቀሙበታል። አንዳንድ ጊዜ ለአምስት ደቂቃ ያህል የሚቆይና ከሁለት ኪሎ ሜትር በላይ የሚሰማ የማያቋርጥ ድምፅ ያሰማሉ፤ ይህ ድምፅ “ረጅም ጥሪ” የሚል ስያሜ ማግኘቱ የሚያስደንቅ አይደለም። አብዛኛውን ጊዜ ወንዶቹ የሚጮሁት እንስቶቹን ለመማረክና ተፎካካሪ ወንዶችን ለማስፈራራት ነው።

በዛፍ አናት ላይ ይኖራሉ

ጉዟችንን እየቀጠልን ስንሄድ ከዛፍ ዛፍ የሚንጠላጠሉ ኦራንጉተኖችን አየን። እጅና እግራቸው ጠንካራና እንደልብ የሚተጣጠፍ ከመሆኑም ሌላ እንደ መንጠቆ ያለ ቅርጽ አለው፤ ጣቶቻቸው ረጃጅም ሲሆኑ የእጃቸው አውራ ጣት አጭር፣ የእግራቸው አውራ ጣት ደግሞ ትልቅ ነው። ከዛፍ ዛፍ ሲንጠላጠሉ እንቅስቃሴያቸው ግርማ ሞገስ ያለው ሲሆን ቅርንጫፎችንም የሚይዙት ያላንዳች ችግር እንዲሁም እርጋታ በሰፈነበት መንገድ ነው።

ኦራንጉተኖች በዛፎቹ አናት ላይ በሚሆኑበት ጊዜ ከቅርንጫፎቹ ጥላ ጋር ስለሚመሳሰሉ በቀላሉ አይለዩም። መሬት ላይ ሲሆኑ ቀስ ብለው ስለሚራመዱ ሰዎች በቀላሉ ሊቀድሟቸው ይችላሉ።

እነዚህ እንስሳት መላ ሕይወታቸውን የሚያሳልፉት በዛፍ አናት ላይ ነው ማለት ይቻላል፤ ይህ ደግሞ ከትላልቆቹ የዝንጀሮ ዝርያዎች የተለዩ ያደርጋቸዋል። አብዛኛውን ጊዜ ምሽት ላይ ፀሐይ ስትጠልቅ እንደ ባላ ያሉ ጠንካራ ቅርንጫፎችን መርጠው በዚያ ላይ ቅጠላ ቅጠሎችን ከጎዘጎዙ በኋላ እስከ 20 ሜትር በሚደርስ ከፍታ ላይ ምቹ የሆነ መኝታ በየጊዜው ይሠራሉ። አንዳንድ ጊዜ ከዝናብ የሚጠለሉበት “ጣሪያ” ይሠራሉ፤ ቺምፓንዚዎችና ጎሪላዎች ግን ፈጽሞ እንዲህ አያደርጉም። ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ ሥራ ከአምስት ደቂቃ የበለጠ ጊዜ አይወስድባቸውም።

ኦራንጉተኖች በጣም የሚወዱትን ምግብ ማለትም ፍራፍሬዎችን የሚያገኙት ከዛፎች ነው። በጣም ጥሩ የሆነ የማስታወስ ችሎታ ስላላቸው የበሰለ ፍሬ የትና መቼ እንደሚገኝ ያውቃሉ። በተጨማሪም ቅጠሎችን፣ የግንድ ልጦችን፣ ቀንበጦችን፣ ማርንና ነፍሳትን ይመገባሉ። ኦራንጉተኖች ከዛፍ ቀዳዳዎች ውስጥ ማርና ነፍሳትን ለማውጣት በልምጭ ይጠቀማሉ። በአጠቃላይ ኦራንጉተኖች ከ400 የሚበልጡ የተለያዩ የምግብ ዓይነቶችን ይመገባሉ።

መንገዳችንን ስንቀጥል ደግሞ ሌላ ትዕይንት ተመለከትን፤ ኦራንጉተኖች የተከመረ ሙዝ እየተመገቡ ነው። እነዚህ ኦራንጉተኖች በእንስሳት መንከባከቢያ ውስጥ ካደጉ በኋላ ወደ ዱር የተለቀቁ ናቸው። በጫካ ያደጉት ኦራንጉተኖች ያላቸው ዓይነት ችሎታ ስለሌላቸው ራሳቸው ፈላልገው ከሚያገኙት ምግብ በተጨማሪ ሌላ ምግብ ይሰጣቸዋል።

የኦራንጉተን የቤተሰብ ሕይወት

የሚያማምሩ የኦራንጉተን ሕፃናት እናታቸው ላይ ተለጥፈው፣ ከፍ ከፍ ያሉት ደግሞ መሬት ላይና ዛፍ ላይ ሲቦርቁ ተመለከትን። እንስቶቹ ኦራንጉተኖች እስከ 45 ዓመት ድረስ ይኖራሉ። ዕድሜያቸው 15 ወይም 16 ከሆነና ለአካለ መጠን ከደረሱ በኋላ በሰባት ወይም በስምንት ዓመት ውስጥ አንድ ልጅ ብቻ ይወልዳሉ። አንዲት እንስት ኦራንጉተን በሕይወት ዘመኗ ከሦስት ልጆች በላይ አትወልድም። ይህም በፕላኔታችን ላይ ዘገምተኛ የመራባት ችሎታ ካላቸው አጥቢ እንስሳት መካከል አንዱ ያደርጋቸዋል።

የሚያስገርመው ነገር፣ በእናቶችና በልጆቻቸው መካከል ያለው ትስስር ጠንካራ ነው። እንስት ኦራንጉተኖች ልጆቻቸውን ለስምንት ወይም ከዚያ ለሚበልጡ ዓመታት ይንከባከቧቸዋል እንዲሁም ያሠለጥኗቸዋል። አንድ ኦራንጉተን ከተወለደ በኋላ እስከ አንድ ዓመት ድረስ ከእናቱ ላይ ፈጽሞ አይወርድም። ከዚያም በኋላ ቢሆን እናቱ ሌላ እስክትወልድ ድረስ ከእሷ ርቆ አይሄድም። በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ እንስት ኦራንጉተኖች እናታቸው ሥር ሥር እየሄዱ አዲስ የወለደችውን ልጅ እንዴት እንደምትንከባከብ ይመለከታሉ።

ወጣት ወንዶቹን ግን ልጅ እንደተወለደ እናቶቻቸው ያባርሯቸዋል። ከዚያም ጫካ ውስጥ ብቻቸውን በመባዘን እስከ 15 ካሬ ኪሎ ሜትር ወይም ከዚያ በላይ ርቀው ይሄዳሉ። ከሌሎች ወንዶች ጋር ፈጽሞ የማይቀራረቡ ሲሆን ከእንስቶቹም ጋር የሚገናኙት የመራቢያ ጊዜያቸው ሲደርስ ብቻ ነው።

እንስቶቹ በአብዛኛው ዕድሜያቸውን ሙሉ ከተወሰነው የደኑ ክፍል ርቀው አይሄዱም። አልፎ አልፎ ከሌሎች እንስት ኦራንጉተኖች ጋር በአንድ ዛፍ ላይ አብረው የሚመገቡ ቢሆንም አብዛኛውን ጊዜ እርስ በርስ አይቀራረቡም። ኦራንጉተኖች የብቸኝነት ሕይወት መምራታቸው ከሌሎች የዝንጀሮ ዝርያዎች የተለዩ ያደርጋቸዋል። ይሁን እንጂ ስለ ‘ጫካው ሰው’ ይበልጥ ለማወቅ ልንጎበኘው የሚገባ አንድ ሌላ ቦታ ነበር።

ለመጥፋት በቋፍ ላይ የሚገኝ የዝንጀሮ ዝርያ

በብሔራዊ ፓርኩ ውስጥ ሉዊስ ሊኪ በተባሉት አንትሮፖሎጂስት ስም የተሰየመ ካምፕ ሊኪ የሚባል የኦራንጉተን የማገገሚያ፣ የምርምርና የጥበቃ ማዕከል ይገኛል። በዚህ ማዕከል ውስጥ ኦራንጉተኖችን በቅርብ ማየት ይቻላል። አንዳንዶቹ አጠገባችን ድረስ መጥተው የቆሙ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ መገለባበጥ ጀመሩ። እንዲያውም አንደኛዋ ኦራንጉተን የጓደኛዬን ጃኬት ያዝ አደረገችው። እነዚህን የሚያማምሩ እንስሳት ይህን ያህል ቀርበን ለማየት በመቻላችን በጣም ተደሰትን።

ይሁን እንጂ ካምፕ ሊኪ፣ ኦራንጉተኖች ቁጥራቸው ተመናምኖ ለመጥፋት እየተቃረቡ መሆኑን የሚጠቁም ማስጠንቀቂያ እያሰማ ነው። አንዳንድ የአካባቢ ተመራማሪዎች በዱር የሚኖሩ ኦራንጉተኖች ከአሥር ወይም ከዚያ ባነሱ ዓመታት ውስጥ እንደሚጠፉ ይሰማቸዋል። ለዚህ መንስኤ የሚሆኑ ሦስት ሁኔታዎችን እንመልከት።

የደን መጨፍጨፍ፦ ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ ለኦራንጉተኖች መኖሪያነት ተስማሚ ከሆነው አካባቢ 80 በመቶ የሚሆነው ጠፍቷል። ኢንዶኔዥያ በየቀኑ በአማካይ 51 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው ደን ታጣለች፤ ይህም በእያንዳንዱ ደቂቃ አምስት የእግር ኳስ ሜዳ የሚያህል ደን ይወድማል ማለት ነው።

ሕገ ወጥ አደን፦ በደን ውስጥ የሚኖሩት ሰዎች ቁጥር በጨመረ መጠን ኦራንጉተኖች ለአዳኞች ይበልጥ ይጋለጣሉ። አንድ የኦራንጉተን የራስ ቅል ሕገ ወጥ በሆነ የቅርሶች ገበያ እስከ 70 የአሜሪካ ዶላር ያወጣል። አንዳንዶች ኦራንጉተኖችን ፀረ-ሰብል እንደሆኑ አድርገው ይመለከቷቸዋል። ሌሎች ደግሞ ለምግብነት ሲሉ ይገድሏቸዋል።

የለማዳ እንስሳት ንግድ፦ ሕገ ወጥ በሆነ ገበያ አንዲት የምታምር ሕፃን ኦራንጉተን ከመቶዎች እስከ በርካታ ሺዎች በሚቆጠር ዶላር ትሸጣለች። በየዓመቱ እስከ አንድ ሺህ የሚደርሱ ሕፃን ኦራንጉተኖች እንደሚሸጡ ይገመታል።

መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ኦራንጉተኖችን ከጥፋት ለመታደግ ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው። ከሚያደርጓቸው ጥረቶች መካከል የማገገሚያ ማዕከሎችን ማቋቋም፣ በትምህርታዊ ፕሮግራሞች አማካኝነት ግንዛቤ ማስፋት፣ ብሔራዊ ፓርኮችንና መጠበቂያዎችን ማቋቋም እንዲሁም በሕገ ወጥ ደን ጭፍጨፋ ላይ ቁጥጥር ማድረግ ይገኙበታል።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ በቅርቡ ‘ምድርን እያጠፉ ያሉትን እንደሚያጠፋና’ መላዋን ምድር ገነት እንደሚያደርጋት ይናገራል። (ራእይ 11:18፤ ኢሳይያስ 11:4-9፤ ማቴዎስ 6:10) መዝሙራዊው “የዱር ዛፎች ሁሉ በደስታ ይዘምራሉ” በማለት የተናገራቸው ቃላት በዚያን ጊዜ ፍጻሜያቸውን ያገኛሉ። (መዝሙር 96:12) ይህ ትንቢት ፍጻሜውን ሲያገኝ የኢንዶኔዥያው “የጫካ ሰው” እንደሚባለው እንደ ኦራንጉተን ያሉ እንስሳት የሰው ልጅ ምንም ስጋት ሳይፈጥርባቸው ተራብተው እንደ ልባቸው ይኖራሉ።

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ማሌዥያ

ቦርንዮ

ኢንዶኔዥያ

ሱማትራ

አውስትራሊያ

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለአካለ መጠን የደረሰው ወንድ በጎንና በጎን አበጥ ያለ ለየት ያለ ፊት አለው

[ምንጭ]

© imagebroker/Alamy

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕሎች]

ኦራንጉተኖች በዛፍ ላይ እንደ ልባቸው ይንጠላጠላሉ፤ መሬት ላይ ሲሆኑ ግን ፈጣኖች አይደሉም

[ምንጮች]

Top: © moodboard/Alamy; bottom: Orangutan in the Camp Leakey of Tanjung Puting National Park, managed by BTNTP, UPT Ditjen PHKA Dephut

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Orangutan in the Camp Leakey of Tanjung Puting National Park, managed by BTNTP, UPT Ditjen PHKA Dephut

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Orangutan in the Camp Leakey of Tanjung Puting National Park, managed by BTNTP, UPT Ditjen PHKA Dephut