በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከፍ ወዳለ አካባቢ መውጣት ያለው አደጋ—ተራራ ላይ የሚያጋጥምን አጣዳፊ ሕመም ማስታገስ

ከፍ ወዳለ አካባቢ መውጣት ያለው አደጋ—ተራራ ላይ የሚያጋጥምን አጣዳፊ ሕመም ማስታገስ

ከፍ ወዳለ አካባቢ መውጣት ያለው አደጋ—ተራራ ላይ የሚያጋጥምን አጣዳፊ ሕመም ማስታገስ

“ፔሩ ውስጥ ፓሪያካካ የሚባል በጣም ከፍ ያለ ተራራ አለ። . . . ወደዚህ ተራራ አናት እየወጣሁ እያለ በቅጽበት መሬት ላይ ወድቄ የምዘረር እስኪመስለኝ ድረስ ኃይለኛ ሕመም ተሰማኝ። . . . ከዚያም [የምሞት] እስኪመስለኝ ድረስ ወደላይ ይለኝና ያስታውከኝ ጀመር። በዚህ ሁኔታ ብቆይ ኖሮ አልተርፍም ነበር ማለት እችላለሁ፤ ይሁን እንጂ ተስማሚ የአየር ሁኔታ ወዳለበት ወደ ዝቅተኛ ቦታ በመውረዳችን እንዲህ ያለው ሁኔታ የቆየብኝ ለሦስት ወይም ለአራት ሰዓት ብቻ ነበር።”—ሆሴ ዴ አኮስታ፣ ናቹራል ኤንድ ሞራል ሂስትሪ ኦፍ ዚ ኢንዲስ

በአሥራ ስድስተኛው መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ ሆሴ ዴ አኮስታ የተባለ አንድ ስፔናዊ የካቶሊክ ሚስዮናዊ በፔሩ በአንዲስ ተራራማ አካባቢ ያለውን ፓሪያካካን በሚወጣበት ጊዜ ከላይ የተገለጸው አደገኛ ሁኔታ ገጥሞት ነበር። በዚያ ወቅት ሰዎች እንዲህ ያለው ሕመም የሚያጋጥማቸው በተራራው ላይ የሚገኙት ማዕድናት በሚያመነጩት መርዛማ ንጥረ ነገሮች ወይም በክፉ አማልክት ትንፋሽ ምክንያት እንደሆነ ይታመን ነበር። አሁን ባለን እውቀት ግን አኮስታ ያጋጠመው፣ ተራራ ላይ የሚያጋጥም አጣዳፊ ሕመም እንደሆነ ተደርሶበታል።

ሰዎች እንዲህ ያለ ሕመም የሚሰማቸው ከፍ ወዳለ አካባቢ በመውጣታቸው ምክንያት ሰውነታቸው የኦክስጅን እጥረት ስለሚያጋጥመው ነው። ወደ ላይ ከፍ እየተባለ ሲኬድ የአየሩ ግፊት ስለሚቀንስ ወደ ሳንባ የሚገባው ኦክስጅን አነስተኛ ይሆናል። *

ተራራ ላይ የሚያጋጥም አጣዳፊ ሕመም ምልክቶች በአብዛኛው መታየት የሚጀምሩት አንድ ሰው ከፍተኛ ቦታ ላይ ከደረሰ ከአራት ሰዓት በኋላ ነው፤ ሕመሙ ከአንድ እስከ አራት ቀን ድረስ ሊቆይ ይችላል። በዚህ ጊዜ በደም ውስጥ የሚገኘው ውስን ኦክስጅን ተጨማሪ ቀይ የደም ሴሎች እንዲፈጠሩ ያደርጋል፤ ይህ ደግሞ በደም አማካኝነት ተጨማሪ ኦክስጅን በሰውነት ውስጥ እንዲሰራጭ ያስችላል።

ይሁን እንጂ አንድ ሰው ከፍ ወዳለ ቦታ በፍጥነት ቢወጣ ወይም ከአየሩ ሁኔታ ጋር ራሱን ሳያለማምድ በጣም እስኪደክም ቢጓዝ በሳንባው ውስጥ ወይም በአንጎሉ አካባቢ ፈሳሽ ሊጠራቀም ይችላል። ተገቢው እርምጃ ካልተወሰደ እንዲህ ያለው ሁኔታ ለሞት ሊዳርግ ይችላል።

መከላከል የሚቻልበት መንገድ

ተጓዦችና ተራራ የሚወጡ ሰዎች እንዲህ ያለው አጣዳፊ ሕመም እንዳያጋጥማቸው ለመከላከል ወይም ከደረሰ በኋላ ለማስታገስ ብዙ ዘዴዎችን ሞክረዋል። አንዳንዶቹ የሚከተሉት ናቸው፦

● የመተንፈሻ አካላት ችግር ወይም ደም ማነስ ካለብህ ከፍ ወዳሉ ቦታዎች አትውጣ።

● ይህን ሕመም ለመከላከል ወይም ለማስታገስ ሽንት የሚያሸኑ፣ የሰውነትን መቆጣት የሚያስታግሱ ወይም ሌሎች መድኃኒቶች ብዙ ጊዜ ይታዘዛሉ። የሕክምና ባለሙያ አማክር።

● ይህን ሕመም ለማስታገስ ከሁሉ የተሻለው ዘዴ ዝቅተኛ ወደሆነ አካባቢ መመለስ ነው። የሚቻል ከሆነ በምትወርድበት ጊዜ እንዲሞቅህ ደራርብ፤ እንደደረስክም እረፍት አድርግ።

በዓለም ተወዳዳሪ ከማይገኝላቸው ማራኪ አካባቢዎች አንዳንዶቹ የሚገኙት በከፍታ ቦታዎችና በተራሮች ላይ ነው። (መዝሙር 148:9, 13) በጥንቃቄ ከተጓዝክ ጤንነትህ ሳይቃወስ የተፈጥሮን ውበት በማየት ልትደሰት ትችላለህ።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.4 አብዛኞቹ ሰዎች ምንም የሕመም ስሜት ሳይሰማቸው ከባሕር ጠለል በላይ እስከ 1,800 ሜትር ከፍታ ድረስ መውጣት ይችላሉ።

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ ]

ተራራ ላይ የሚያጋጥም አጣዳፊ ሕመም በአብዛኛው መታየት የሚጀምረው አንድ ሰው ከፍተኛ ቦታ ላይ ከደረሰ ከአራት ሰዓት በኋላ ነው፤ ሕመሙ ከአንድ እስከ አራት ቀን ድረስ ሊቆይ ይችላል

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ ]

ተራራ ላይ የሚያጋጥመውን አጣዳፊ ሕመም ለማስታገስ ከሁሉ የተሻለው ዘዴ ዝቅተኛ ወደሆነ አካባቢ መመለስ ነው