በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሌሎች ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ምን ብለዋል?

ሌሎች ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ምን ብለዋል?

ፈረንሳይ፦

“የይሖዋ ምሥክሮች የሪፑብሊኩን ሕግ የሚያከብሩ ዜጎች ናቸው። . . . በሕዝቡ ደኅንነት ላይ ምንም ስጋት አይፈጥሩም። ሥራ ይሠራሉ፣ ግብር ይከፍላሉ፣ በአገራችን በሚካሄደው ኢኮኖሚያዊ ልማት ላይ ተሳትፎ ያደርጋሉ እንዲሁም ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች ይለግሳሉ። ሀብታም ድሃ ሳይል ከሁሉም ዘር የተውጣጡት እነዚህ ሰዎች በሰላም አንድ ላይ ተሰብስበው ማየት የሚያስደስት ነገር ነው። . . . ሁሉም ሰው የይሖዋ ምሥክር ቢሆን ኖሮ እኛ ፖሊሶች ሥራ እንፈታ ነበር።”—የፈረንሳይ ፖሊሶች ማኅበር ቃል አቀባይ

ዩክሬን፦

“የይሖዋ ምሥክሮች ከፍተኛ የሥነ ምግባር መመሪያዎችን ለልጆቻቸው ያስተምራሉ። ልጆቻቸው፣ ራሳቸውንም ሆነ ሌሎችን የሚጎዱ ሆኖም በዓለማችን ውስጥ ተቀባይነት ያላቸውን ጎጂ ጠባዮች፣ ተግባሮችና ዝንባሌዎች እንዲያስወግዱ ያስተምራሉ። በመሆኑም አደንዛዥ ዕፅ መውሰድ፣ ሲጋራ ማጨስና የአልኮል መጠጥ ከልክ በላይ መጠጣት ስለሚያስከትለው አደጋ ልጆቻቸውን ያስጠነቅቃሉ። ሐቀኝነትና በትጋት መሥራት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ይገነዘባሉ። . . . የይሖዋ ምሥክሮች ልጆቻቸው ጥሩ ሥነ ምግባር እንዲኖራቸው፣ ባለሥልጣናትንም ሆነ ሌሎችን እንዲያከብሩ እንዲሁም ለሰዎች ንብረት አሳቢነት እንዲያሳዩ ብሎም ሕግ አክባሪ ዜጎች እንዲሆኑ ያስተምሯቸዋል።”—የሃይማኖት ታሪክ በዩክሬን፣ በፕሮፌሰር ፔትሮ ያሮትስኪ የተዘጋጀ

ጣሊያን፦

“በኦሎምፒክ ስታዲየሙ ውስጥ የተሰበሰበው ሠላሳ ሺህ ሕዝብ ጸጥ ብሎ ተቀምጧል። . . . የወዳደቀ ቆሻሻ አይታይም፤ ጫጫታና ጩኸትም አይሰማም። በትናንትናው ዕለት በኦሎምፒክ ስታዲየሙ የታየው ሁኔታ ይህ ነበር። . . . እርስ በርስ መሰዳደብ የለም፤ የሲጋራ ቁራጭም ሆነ አንድም [የመጠጥ] ቆርቆሮ ወድቆ አይታይም። ሰዎቹ መጽሐፍ ቅዱሶቻቸውን ከመግለጥና ማስታወሻ ከመጻፍ ውጪ የሚያደርጉት ነገር አልነበረም፤ ልጆችም በጸጥታ ተቀምጠው ያዳምጡ ነበር።”—ሉኒታ፣ በሮም ስለተደረገው የይሖዋ ምሥክሮች ትልቅ ስብሰባ የቀረበ ዘገባ

ብሪታንያ፦

የቼልትነም ሊቀ ዲያቆናት፣ “[የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን] እንደ ይሖዋ ምሥክሮች . . . ያሉ ቀናተኛ የአገልጋዮች ቡድን ያስፈልጋታል” ብለዋል፤ ይህን የተናገሩት የይሖዋ ምሥክሮች ከቤት ወደ ቤት የሚያደርጉትን አገልግሎት አስመልክተው ሳይሆን አይቀርም።—ዘ ጋዜት፣ የግሎስተር ሀገረ ስብከት

ኔዘርላንድ፦

በሌቫርደ ከተማ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች እንዲህ የሚል ደብዳቤ ለይሖዋ ምሥክሮች ጽፈው ነበር፦ “ኖርደርቨክ [የኖርደር ጎዳና] ውበት እንዲላበስ ስላበረከታችሁት ትልቅ አስተዋጽኦ ልናመሰግናችሁ እንወዳለን። አባሎቻችሁ ሁልጊዜ ጥሩ አለባበስና ጥሩ ጠባይ አላቸው። ልጆቹ የታረመ ጠባይ ያላቸው ሲሆኑ ትልልቆቹ ደግሞ መኪናዎቻቸውን የሚያቆሙት በሥርዓት ነው። መንገድ ላይ ቆሻሻ አይጥሉም እንዲሁም በመንግሥት አዳራሹ ዙሪያ ያለው አካባቢ ምንጊዜም ንጹሕና ጽዱ ነው። በአካባቢያችን በመኖራችሁ በጣም ደስተኞች ስለሆንን የዕድሜ ልክ ጎረቤታሞች እንደምንሆን ተስፋ እናደርጋለን።”

ሜክሲኮ፦

የአንትሮፖሎጂና የታሪክ ብሔራዊ ትምህርት ቤት ፕሮፌሰርና ተመራማሪ የሆኑት ኤሊዮ ማስፌሬር የይሖዋ ምሥክሮች “ተገዶ መደፈር፣ በቤተሰብ አባል የሚፈጸም በደል እንዲሁም የመጠጥና የዕፅ ሱስ የመሳሰሉ ከባድ የቤተሰብ ቀውሶች የደረሱባቸውን” ሰዎች እንደረዱ ገልጸዋል። የይሖዋ ምሥክሮች የሚያስተምሩት ነገር “የከንቱነት ስሜት የሚሰማቸው ሰዎች ለራሳቸው ከፍ ያለ ግምት እንዲኖራቸው እንደሚያደርጋቸው” እንዲሁም “ከባድ ችግር ውስጥ ሳይገቡ አምላክን የሚያስደስተውን ነገር እያደረጉ እንዲኖሩ” እንደሚያስችላቸው ፕሮፌሰሩ ተናግረዋል።—ኤክሰልሲዮር የተባለ ጋዜጣ

ብራዚል፦

አንድ ጋዜጣ እንደሚከተለው በማለት ዘግቧል፦ “የይሖዋ ምሥክሮች ድርጅት በጣም የሚደንቅ ድርጅት ነው። የሚሰበሰቡበት ቦታ ምንጊዜም ንጹሕ ነው። ሁሉም ነገር በሚገባ የተደራጀ ነው። . . . ስብሰባቸውን ሲጨርሱ ቦታውን ከመጠቀማቸው በፊት ከነበረው የበለጠ ንጹሕ ያደርጉታል። ንግግር በሚቀርብበት ጊዜ ፍጹም ጸጥታ ይሰፍናል። ሌሎችን እየተጋፋ ወይም እየገፈታተረ የሚሄድ ሰው የለም። ሁሉም ጥሩ ምግባር አላቸው። . . . በእርግጥም ሥርዓታማ ሃይማኖት ነው። አምላክን ማምለክ ምን ማለት እንደሆነ ገብቷቸዋል።”—ኮሜርሲዮ ዳ ፍራንካ

የይሖዋ ምሥክሮች፣ ፈጣሪ ሰብዓዊ ፍጥረታቱ ሊመሩበት የሚገባው መሠረታዊ ሥርዓት ምን እንደሆነ ከማንም በላይ እንደሚያውቅ ያምናሉ። (ኢሳይያስ 48:17, 18) በመሆኑም የይሖዋ ምሥክሮች፣ ማንኛውም ሰው መልካም ባሕርያቸውን አስመልክቶ በጎ አስተያየት ሲሰነዝር ሊመሰገን የሚገባው ፈጣሪ እንደሆነ ይገልጻሉ። ኢየሱስ “ሰዎች መልካም ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራ” ብሏል።—ማቴዎስ 5:16

“የይሖዋ ምሥክሮች ልጆቻቸው ጥሩ ሥነ ምግባር እንዲኖራቸው . . . ብሎም ሕግ አክባሪ ዜጎች እንዲሆኑ ያስተምሯቸዋል።”