በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አንድ ጠበቃ የይሖዋ ምሥክሮችን እምነት መረመሩ

አንድ ጠበቃ የይሖዋ ምሥክሮችን እምነት መረመሩ

አንድ ጠበቃ የይሖዋ ምሥክሮችን እምነት መረመሩ

“ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ምንም አላውቅም ነበር ማለት እችላለሁ።” ይህን የተናገሩት ሌስ ሲቨን የተባሉ በደቡብ አፍሪካ ያለ የአንድ ሕግ ተቋም ዲሬክተርና ጠበቃ ናቸው። እኚህ ሰው የይሖዋ ምሥክሮችን እምነት እንዲመረምሩ ያነሳሳቸው ምንድን ነው? የይሖዋ ምሥክሮች ከሚያምኑት ነገር በመነሳት ምን መደምደሚያ ላይ ደረሱ? ከንቁ! ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስ ከዚህ ቀጥሎ ቀርቧል።

ሃይማኖትዎ ምን ነበር?

አይሁዳዊ የነበርኩ ቢሆንም በ1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ የአንግሊካን እምነት ተከታይ የነበረችውን ካሮልን አገባሁ። በወቅቱ ካሮል ለሃይማኖት ምንም ደንታ ስላልነበራት ሃይማኖት በሕይወታችን ውስጥ እምብዛም ቦታ አልነበረውም። ይሁን እንጂ ልጃችን አንድሩ ስምንት ዓመት ሲሆነው ካሮል፣ ልጃችን አንድ ሃይማኖት እንዲይዝ ማድረግ እንዳለብን ተሰማት። ካሮል ወደ አይሁድነት ከተቀየረች፣ አንድሩ ያላንዳች ጥያቄ አይሁዳዊ እንደሚሆንና በ13 ዓመቱ ባር ሚትስቨ (አንድ ልጅ ለአቅመ አዳም እንደደረሰ ለማሳወቅ የሚደረግ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ነው) ሊደረግለት እንደሚችል አንድ የአይሁድ መሪ ነገረኝ። ስለዚህ ወደ ምኩራብ በየሳምንቱ እየሄድን ወደ አይሁድ እምነት ለመለወጥ የሚያስፈልገውን ትምህርት መከታተል ጀመርን።

ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር የተገናኙት እንዴት ነበር?

የይሖዋ ምሥክሮች ቤታችን ሲመጡ “እኔ አይሁዳዊ ስለሆንኩ በአዲስ ኪዳን አላምንም” ብዬ ውይይቱን በአጭሩ ለመቅጨት እሞክር ነበር። አንድ ቀን ካሮል ከጓደኞቿ አንዷ የይሖዋ ምሥክር እንደሆነችና መጽሐፍ ቅዱስን በደንብ እንደምታውቀው ነገረችኝ። ካሮል ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ጥቂትም ቢሆን እንድንማር ሐሳብ አቀረበች። እያቅማማሁም ቢሆን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ለማጥናት ተስማማሁ።

ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትዎ ምን ዓይነት አመለካከት ነበርዎት?

በጣም ትዕቢተኛ ነበርኩ። የአይሁድ እምነቴን አጥብቄ ለመያዝ ስል እንደገና መመርመር ጀመርኩ፤ ይህም የተመረጠው ዘር ክፍል እንደሆንኩ እንዲሰማኝ አደረገኝ። ‘አሁን እነዚህ ሰዎች ምን ሊያስተምሩኝ ይችላሉ?’ ብዬ አሰብኩ። ቤታችን ከመጣው የይሖዋ ምሥክር ጋር ባደረግነው በመጀመሪያው ውይይት ላይ “የተወለድኩት አይሁዳዊ ሆኜ ነው፤ አሁንም አይሁዳዊ ነኝ፤ የምሞተውም አይሁዳዊ እንደሆንኩ ነው። ምንም ብትለኝ አልለወጥም” አልኩት። እሱም አመለካከቴን እንደሚያከብርልኝ በደግነት ነገረኝ። ስለዚህ ዓርብና ሰኞ ምሽት ወደ አይሁድ እምነት ለመለወጥ የሚያስፈልገውን ትምህርት እንከታተል የነበረ ሲሆን እሁድ ጠዋት (መሸሽ ካልቻልኩ) ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር እናጠና ነበር። በነገራችን ላይ በምኩራቡ ከሚሰጠው ትምህርት በተለየ የይሖዋ ምሥክሮች የሚያስተምሩት በነፃ ነው።

የይሖዋ ምሥክሮች ለራሳቸው የሚስማማቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም እንደሚጠቀሙ ስለተሰማኝ ከእነሱ ጋር ስወያይ የምጠቀመው የራሴን የአይሁድ መጽሐፍ ቅዱስ ነበር። ይሁን እንጂ ሁለቱ መጽሐፍ ቅዱሶች ምን ያህል እንደሚመሳሰሉ ሳውቅ በጣም ገረመኝ። ይህን ማወቄ የይሖዋ ምሥክሮቹ እንደተሳሳቱ ለማሳመን ይበልጥ ቆርጬ እንድነሳ አደረገኝ።

ከአይሁድ ረቢዎቹ ጋር የሚደረገውን ጥናት ለጥቂት ጊዜ ከተከታተልን በኋላ ካሮል ረቢው የራሱን መጽሐፍ ቅዱስ በደንብ ያውቀዋል ብላ እንደማታስብ ነገረችኝ። በመሆኑም ከእንግዲህ ወዲህ ወደ እነሱ መሄድም ሆነ ክርስቶስን መካድ እንደማትፈልግ ነገረችኝ። በጣም ከመናደዴ የተነሳ ትዳራችንን ለማፍረስ አስቤ ነበር። ብስጭቱ ሲለቀኝ ግን የተለየ ስልት ለመጠቀም ይኸውም የሕግ ሙያዬን ተጠቅሜ እነዚህ ‘ወፈፌ መናፍቃን’ ትክክል እንዳልሆኑ ለካሮል ላረጋግጥላት ወሰንኩ።

ታዲያ ተሳካልዎት?

አንድ የአይሁድ ረቢ መሲሐዊ ትንቢቶች በኢየሱስ ላይ እንዳልተፈጸሙ ለማሳየት የተጻፈ አንድ መጽሐፍ ሰጠኝ። ለዓመት ከመንፈቅ ያህል እኔና ካሮል መጽሐፉን አንድ ላይ አጠናነው። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር በየሳምንቱ የምናደርገውን ጥናትም ቀጠልን። ይሁን እንጂ ረቢው በሰጠን መጽሐፍ ላይ የተገለጸውን እያንዳንዱን ትንቢት በመረመርን ቁጥር ጥርጣሬ እያደረብኝ መጣ። መጽሐፉ ካቀረበው መከራከሪያ ነጥብ በተቃራኒ ስለ መሲሑ የሚናገሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች በሙሉ ወደ አንድ ሰው ይኸውም ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ እንደሚያመለክቱ አስተዋልኩ። ሙሉ በሙሉ የቆረጠልኝ መሲሑ በ29 ዓ.ም. * እንደሚገለጥ የሚናገረውን በዳንኤል 9:24-27 ላይ የሚገኘውን ትንቢት ባጠናን ጊዜ ነበር። የሚያስጠናን የይሖዋ ምሥክር ከእያንዳንዱ የዕብራይስጥ ቃል ግርጌ የእንግሊዝኛውን ቃል በቃል ትርጓሜ የያዘ አንድ የዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ አምጥቶልኝ ነበር። ቃላቱን ካስተያየሁ በኋላ የዘመናቱን ስሌት እኔ ራሴ አሰላሁት፤ ከዚያም “እሺ፣ ትንቢቱ የሚመራን 29 ዓ.ም. ላይ ነው። ታዲያ ይህ ከኢየሱስ ጋር ምን ግንኙነት አለው?” ብዬ ጠየቅሁ።

የይሖዋ ምሥክሩም “ኢየሱስ የተጠመቀው በዚያ ዓመት ነበር” በማለት መለሰልኝ።

በጣም ደነቀኝ! የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ምን ያህል ትክክለኛ እንደሆኑና እርስ በርስ እንደሚስማሙ ሳውቅ ደግሞ ይበልጥ ተገረምኩ።

አመለካከትዎ ሲለወጥ ጓደኞችዎ ምን አሉ?

አንዳንዶቹ ሁኔታው በጣም ስላሳሰባቸው የይሖዋ ምሥክሮች እምነታችንን በግድ እያስለወጡን እንደሆነ ሊያረጋግጡልን ከሚችሉ ሰዎች ጋር እንደሚያስተዋውቁን ቃል ገቡልን። እኛ ግን ሃይማኖታችንን ለመቀየር የተነሳሳነው ተገደን ሳይሆን ከዚህ በተቃራኒ አንድ በአንድ ምርምር አድርገን አሳማኝ ማስረጃ ስላገኘን ነው።

የይሖዋ ምሥክር ለመሆን እንዲወስኑ ያደረግዎት ምንድን ነው?

በወቅቱ ተጠምቃ የይሖዋ ምሥክር ከሆነችው ባለቤቴ ጋር በመንግሥት አዳራሽ በሚደረጉት ስብሰባዎች ላይ አልፎ አልፎ መገኘት ጀመርኩ። * የይሖዋ ምሥክሮች ከተለያየ ዘርና ጎሣ የመጡ ቢሆኑም የሚያሳዩት ወዳጃዊ መንፈስና እርስ በርስ ያላቸው ፍቅር አስደነቀኝ። በራሴ ሃይማኖት ውስጥ እንዲህ ያለ ነገር አይቼ አላውቅም። በመሆኑም ለሦስት ተጨማሪ ዓመታት ካጠናሁ በኋላ ተጠመቅሁ።

የይሖዋ ምሥክር ለመሆን ስላደረጉት ውሳኔ ምን ይሰማዎታል?

“የይሖዋ ምሥክር ነኝ” ብሎ መናገር መቻል ለእኔ ትልቅ ክብር ነው። ይሁን እንጂ እውነትን ላለመቀበል ምን ያህል ግብግብ እንደፈጠርኩ መለስ ብዬ ሳስብ ይሖዋ የማይገባኝን መንፈሳዊ በረከት እንደሰጠኝ ይሰማኛል። የይሖዋ ምሥክር ለመሆን ባደረግኩት ውሳኔ ፈጽሞ አልቆጭም።

ምን በረከት አግኝተዋል?

በጣም ብዙ ነው። በመጀመሪያ በጉባኤ ውስጥ ሽማግሌ ወይም መንፈሳዊ እረኛና አስተማሪ ሆኜ የማገልገል መብት በማግኘቴ በጣም ደስተኛ ነኝ። በተጨማሪም ደቡብ አፍሪካ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ የሕግ ክፍል ውስጥ እገዛ ማበርከት ችያለሁ። ይሖዋንና ልጁን ማወቄ እንዲሁም የዘመናችንንም ሆነ ዓለምን እያናወጧት ያሉትን ታላላቅ ክስተቶች ትክክለኛ ትርጉም መረዳት መቻሌ ካገኘኋቸው በረከቶች ሁሉ እጅግ የላቀ ነው ብዬ መናገር እችላለሁ።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.12 ዳንኤል ስለ መሲሑ የተናገረው ትንቢት ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? በተሰኘው መጽሐፍ ገጽ 197 ላይ ተብራርቷል።

^ አን.18 ካሮል በ1994 የሞተች ሲሆን ሌስ ሲቨን እንደገና አግብተዋል።

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ምን ያህል ትክክለኛ እንደሆኑና እርስ በርስ እንደሚስማሙ ሳውቅ . . . ይበልጥ ተገረምኩ