በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አጋንንት እነማን ናቸው?

አጋንንት እነማን ናቸው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

አጋንንት እነማን ናቸው?

የሙታን መናፍስት፣ ርኩስ መናፍስት፣ ጂኒዎች፣ አጋንንት የሚሉት ስያሜዎች በተለያዩ ሃይማኖቶች ውስጥ ያሉ ሰዎች መጥፎ፣ ጥሩ ወይም ሁለቱንም እንደሆኑ አድርገው የሚመለከቷቸውንና የሚያምኑባቸውን መንፈሳዊ አካላት ያመለክታሉ። ሌሎች ሰዎች ደግሞ መናፍስት አሉ የሚለውን አመለካከት አጉል እምነት ወይም ፈጠራ እንደሆነ አድርገው በመመልከት ያጣጥሉታል። ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ ፈጣሪ ራሱ መንፈስ እንደሆነና የመጀመሪያ ፍጥረቶቹም መናፍስት ወይም መላእክት እንደሆኑ ያስተምራል። (ዮሐንስ 4:24፤ ዕብራውያን 1:13, 14) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ክፉ መናፍስት እንዳሉ የሚናገር ሲሆን አንዳንድ ጊዜ አጋንንት እያለ ይጠራቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 10:20, 21፤ ያዕቆብ 2:19) ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ አጋንንትን እንደፈጠራቸው አያስተምርም። ታዲያ አጋንንት እነማን ናቸው? ወደ ሕልውና የመጡትስ እንዴት ነው?

‘ኃጢአት የሠሩ መላእክት’

አምላክ መንፈሳዊ ፍጥረታትን የፈጠራቸው ነፃ ምርጫ ያላቸውና ጥሩም ሆነ መጥፎ የሆነውን በማድረግ ረገድ የራሳቸውን ውሳኔ ማድረግ የሚችሉ አድርጎ ነው። የሚያሳዝነው ግን ሰዎች ከተፈጠሩ በኋላ ቁጥራቸው በውል ተለይቶ ያልተጠቀሰ መላእክት በአምላክ ላይ በማመፅ መጥፎ የሆነውን ለማድረግ መረጡ።

ለማመፅ የመጀመሪያው የሆነውና በመጥፎ ስሙ የታወቀው መንፈሳዊ አካል ሰይጣን ሆነ። “[እሱ] በእውነት ውስጥ ጸንቶ አልቆመም” በማለት ኢየሱስ ክርስቶስ ተናግሯል። (ዮሐንስ 8:44) ሰይጣን በአምላክ ላይ እንዲያምፅ ያነሳሳው ምንድን ነው? ለፈጣሪ ብቻ የሚገባውን አምልኮ የተመኘ ሲሆን ይህን ምኞቱን እውን ለማድረግ ሲል ራሱን አምላክ ለማድረግ በመሞከር የፈጣሪ ተቀናቃኝ ሆነ። በዚህ መንገድ ራሱን “ሰይጣን” አደረገ፤ ሰይጣን የሚለው ቃል “ተቃዋሚ” የሚል ትርጉም አለው። በመቶዎች የሚቆጠሩ ዓመታት ቆይቶ ከኖኅ የጥፋት ውኃ በፊት ሌሎች መላእክትም ሰብዓዊ አካል ለብሰው በምድር ላይ ለመኖር ሲሉ በሰማይ የነበራቸውን ቦታ ትተው ከሰይጣን ጋር ተባበሩ። (ዘፍጥረት 6:1-4፤ ያዕቆብ 1:13-15) የጥፋት ውኃ በመጣ ጊዜ ሥጋ ለብሰው የተገለጡት ‘ኃጢአት የሠሩ መላእክት’ ወደ መንፈሳዊው ዓለም የተመለሱ ይመስላል። (2 ጴጥሮስ 2:4፤ ዘፍጥረት 7:17-24) ከጊዜ በኋላ እነዚህ መላእክት አጋንንት ተብለው ተጠሩ።—ዘዳግም 32:17፤ ማርቆስ 1:34

ዓመፀኞቹ መላእክት አሁን የሚገኙበት ሁኔታ ከማመፃቸው በፊት ከነበሩበት በጣም የተለየ ነው። ይሁዳ 6 “መጀመሪያ የነበራቸውን ቦታ ያልጠበቁትንና ትክክለኛ መኖሪያቸውን የተዉትን መላእክት [አምላክ] በታላቁ ቀን ለሚፈጸምባቸው ፍርድ በዘላለም እስራት በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ አቆይቷቸዋል” በማለት ይናገራል። አዎን፣ አጋንንት ቀደም ሲል በሰማይ የነበራቸውን መብት እንዲያገኙ አምላክ አልፈቀደላቸውም፤ ከዚህ ይልቅ ከማንኛውም መንፈሳዊ የእውቀት ብርሃን ተገልለው በምሳሌያዊ “ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ” እንዲቆዩ አድርጓቸዋል።

“መላውን ዓለም እያሳሳተ” ነው

አጋንንት ዳግመኛ እንደ ሰው ሥጋ ለብሰው መገለጥ እንዳይችሉ ቢከለከሉም አሁንም ታላቅ ኃይል ያላቸው ከመሆኑም ሌላ በሰዎች አእምሮና ሕይወት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። እንዲያውም ሰይጣን ከአጋንንት ጭፍሮቹ ጋር በመሆን “መላውን ዓለም እያሳሳተ” ነው። (ራእይ 12:9፤ 16:14) እንዴት? በዋነኝነት ይህን የሚያደርገው ‘በአጋንንት ትምህርቶች’ አማካኝነት ነው። (1 ጢሞቴዎስ 4:1) ብዙውን ጊዜ ሃይማኖታዊ ይዘት ያላቸው እነዚህ የሐሰት ትምህርቶች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ስለ አምላክ እውነቱን እንዳያውቁ አእምሯቸውን አሳውረውታል። (2 ቆሮንቶስ 4:4) እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት።

ሙታን አሁንም ሕያው ናቸው የሚለው ትምህርት፦ አጋንንት፣ ሰዎች ምትሐታዊ ምስሎችን እንዲያዩና ድምፆችን እንዲሰሙ በማድረግ ወይም በሌሎች የማታለያ መንገዶች በመጠቀም ከሙታን ጋር መነጋገር እንደሚችሉ እንዲያምኑ ያደርጓቸዋል። ከዚህም በላይ ይህ በብልሃት የተሸረበ ማታለያ፣ ሰው ከሞተ በኋላ ከሥጋው ተለይታ መኖሯን የምትቀጥል ነገር እንዳለች የሚገልጸው የሐሰት ትምህርት ተቀባይነት እንዲያገኝ አድርጓል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ “ሙታን . . . ምንም አያውቁም” በማለት በግልጽ ይናገራል። (መክብብ 9:5, 6) ሙታን ‘ወደ ዝምታው ዓለም ስለወረዱ’ አምላክን ማመስገን እንኳ አይችሉም።—መዝሙር 115:17 *

ልቅ ሥነ ምግባር፦ “መላው ዓለም . . . በክፉው ኃይል ሥር ነው” በማለት 1 ዮሐንስ 5:19 ይናገራል። ሰይጣንና አጋንንቱ በመገናኛ ብዙኃንና በሌሎች መንገዶች በመጠቀም ሰዎች ያላንዳች ገደብ ወራዳ ሥጋዊ ፍላጎታቸውን ሊያረኩ ይገባል የሚል ርኩስ አስተሳሰብ እንዲስፋፋ ጫና ያደርጋሉ። (ኤፌሶን 2:1-3) በመሆኑም በዛሬው ጊዜ ከተፈጥሮ ውጭ የሆነ የፆታ ግንኙነትን ጨምሮ ማንኛውም ዓይነት የሥነ ምግባር ብልግና ተስፋፍቷል። እንዲያውም እንዲህ ዓይነቱ ተግባር ምንም ችግር እንደሌለበት ተደርጎ ሲታይ የመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች ግን ብዙውን ጊዜ ዘመን እንዳለፈባቸው ወይም ጠባብ አስተሳሰብን እንደሚያንጸባርቁ ተደርገው ይታያሉ።

መናፍስታዊ ድርጊትን ማስፋፋት፦ ሐዋርያው ጳውሎስ “በጥንቆላ ሥራዋ ለጌቶቿ ከፍተኛ ገቢ ታስገኝላቸው” የነበረች “የጥንቆላ ጋኔን ያደረባት” አንዲት አገልጋይ አጋጥማው ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 16:16) ጳውሎስ ይህን ኃይል ያገኘችው ከየት እንደሆነ ስላወቀ ልጅቷ የምትናገረውን ለመስማት ፈቃደኛ አልነበረም። በተጨማሪም ኮከብ ቆጠራንና ምትሐታዊ ኃይልን ጨምሮ ማንኛውንም ዓይነት መናፍስታዊ ድርጊት አስጸያፊ እንደሆነ አድርጎ የሚመለከተውን አምላክ ለማሳዘን አልፈለገም።—ዘዳግም 18:10-12

ራስህን ከአጋንንት ጠብቅ

ራስህን ከክፉ መናፍስት መጠበቅ የምትችለው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “ራሳችሁን ለአምላክ አስገዙ፤ ዲያብሎስን ግን ተቃወሙት፤ እሱም ከእናንተ ይሸሻል” በማለት መልሱን ይሰጣል። (ያዕቆብ 4:7) ሰይጣንንና አጋንንቱን እንዲሁም የሚጠቀሙባቸውን “መሠሪ ዘዴዎች” በሚያጋልጠው ብቸኛ ቅዱስ መጽሐፍ ማለትም በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የምንመራ ከሆነ ከላይ ያለውን መመሪያ ተግባራዊ እንዳደረግን እናሳያለን። (ኤፌሶን 6:11፤ 2 ቆሮንቶስ 2:11) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ክፉ መናፍስትን ጨምሮ አምላክን የሚቃወሙ ሁሉ ለዘላለም እንደሚጠፉ ይነግረናል። (ሮም 16:20) ምሳሌ 2:21 “ቅኖች በምድሪቱ ይቀመጣሉና፤ ነቀፋ የሌለባቸውም በእርሷ ላይ ጸንተው ይኖራሉ” ይላል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.11 ሙታን ስለሚገኙበት ትክክለኛ ሁኔታና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስለተገለጸው የትንሣኤ ተስፋ ለማወቅ ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 6ን እና 7ን ተመልከት።

ይህን አስተውለኸዋል?

አጋንንትን የፈጠራቸው አምላክ ነው?—2 ጴጥሮስ 2:4

● ሙታንን ማነጋገር ትችላለህ?—መክብብ 9:5, 6

● ራስህን ከአጋንንት መጠበቅ የምትችለው እንዴት ነው?—ያዕቆብ 4:7

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አጋንንት በሰዎች ላይ በብዙ መንገዶች ተጽዕኖ ለማሳደር ይሞክራሉ