በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከባታክ ሕዝቦች ጋር ተዋወቁ

ከባታክ ሕዝቦች ጋር ተዋወቁ

ከባታክ ሕዝቦች ጋር ተዋወቁ

በ13ኛው መቶ ዘመን ይኖር የነበረው ጣሊያናዊው አሳሽ፣ ማርኮ ፖሎ በኢንዶኔዥያ የምትገኘውን የሱማትራ ደሴት በጎበኘበት ወቅት “እንደ አውሬ ስለሚኖሩና የሰው ሥጋ ስለሚበሉ . . . የደጋ አገር ሰዎች” ገልጾ ነበር። ይህን የተናገረው ስለ ባታክ ሕዝቦች እንደሆነ ይገመታል። እኔና ባለቤቴ ግን ስለ እነዚህ ሕዝቦች ያለን አመለካከት ከዚህ በጣም የተለየ ነው። እኛ የተዋወቅናቸውንና የወደድናቸውን እነዚህን ሰዎች እናንተም ተዋወቋቸው።

“ሆራስ!” በሚስዮናዊነት እንድናገለግል ወደተመደብንበት በቶባ ሐይቅ አቅራቢያ ወደሚገኘውና በሰሜን ሱማትራ፣ ኢንዶኔዥያ ወዳለው ወደ አዲሱ ክልላችን ስንደርስ ከዚያ በፊት የማናውቃቸው ባታካውያን ወዳጆቻችን የተቀበሉን ይህን ሞቅ ያለ ሰላምታ በመስጠት ነበር። የቶባ ሐይቅ በሱማትራ ከሚገኙት እጹብ ድንቅ የሆኑ የተፈጥሮ ገጽታዎች አንዱ ነው። በዓለም ላይ በእሳተ ገሞራ ከተፈጠሩት ሐይቆች ሁሉ ትልቁ የሆነው ይህ ሐይቅ ከባታክ ሕዝቦች ሕይወት ጋር በእጅጉ የተሳሰረ ነው።—ከታች ያለውን  ሣጥን ተመልከት።

ባታካውያን በኢንዶኔዥያ ከሚገኙት የአካባቢው ተወላጅ የሆኑ ሕዝቦች መካከል በብዛት ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛሉ። ስምንት ሚሊዮን ገደማ ይሆናሉ ተብለው የሚገመቱት ባታካውያን ስድስት ከሚያክሉ ጎሳዎች የተውጣጡ ናቸው፤ እነዚህ ጎሳዎች ራሳቸውን የቻሉ ቢሆኑም የቅርብ ትስስር አላቸው። ጎሳዎቹም ቶባ፣ ሲመሉንጉን፣ ከሮ፣ ዳኢሪ፣ አንግኮላ እና መንዴሊንግ በመባል ይታወቃሉ። እያንዳንዱ ጎሳ በትልልቅ ቤተ ዘመዶች የተዋቀረ ነው። ባታካውያን በሚገናኙበት ጊዜ በአብዛኛው መጀመሪያ ላይ የሚጠይቁት ጥያቄ “አንተ ከየትኛው ቤተ ዘመድ ወገን ነህ?” የሚል ነው። ከዚያም ወዲያውኑ ዝምድናቸውን ለማወቅ የዘር ሐረጋቸውን ይቆጥራሉ።

የጋብቻ ደንቦች

ባሕላዊው የባታካውያን የጋብቻ ሥነ ሥርዓት ሁለት ሰዎችን ብቻ ሳይሆን ሁለት ቤተ ዘመዶችንም ያስተሳስራል። የእናትን ወንድም ወይም እህት ልጅ ማግባት እንደ ጥሩ የትዳር ጓደኛ ምርጫ የሚቆጠር ሲሆን የአባትን ወንድም ወይም እህት ልጅ አሊያም ደግሞ ከራስ ቤተ ዘመድ መካከል ማግባት እንደ ነውር ተደርጎ ይታያል። ከዚህ በተቀረ ግን ባሕላዊው የጋብቻ ደንብ እንደሚከተለው ነው፦ የቤተ ዘመድ ሀ ወንዶች፣ ሚስት የሚያገቡት ከቤተ ዘመድ ለ መካከል ነው፤ የቤተ ዘመድ ለ ወንዶች፣ ከቤተ ዘመድ ሐ ሚስት ያገባሉ፤ የቤተ ዘመድ ሐ ወንዶች ደግሞ ከቤተ ዘመድ ሀ ሚስት ያገባሉ። ይህ ዑደት የሚፈጥረው ትስስር የባታካውያንን ዝምድና የሚያጠናክር ከመሆኑም ሌላ አዲሶቹን ተጋቢዎች ብዙ ዘመዶች እንዲያፈሩ ያስችላቸዋል።

ባታካውያን የትዳር ጥንዶች በሕግ የተጋቡና ልጆች የወለዱ ቢሆንም እንኳ በቤተ ዘመድ ባሕላዊ የሠርግ ሥነ ሥርዓት እስካልተጋቡ ድረስ ትዳራቸው በቤተ ዘመዶቻቸው ዘንድ ተቀባይነት አያገኝም። ሰፊ የሆነው ባሕላዊው የሠርግ ሥነ ሥርዓት በመቶዎች የሚቆጠሩ ዘመዶች የሚገኙበትና ለብዙ ሰዓታት የሚቆይ ሊሆን ይችላል።

ለምሳሌ ያህል፣ በከሮ ጎሳ የሠርግ ሥነ ሥርዓት መሠረት የሙሽራው ቤተሰቦች ለሙሽሪት ቤተሰቦች ጥሎሽ ይሰጣሉ፤ የሙሽሪትም ቤተሰቦች ገንዘቡን አንድ በአንድ ይቆጥራሉ። የጋብቻ ሥነ ሥርዓቱ የሚከናወነው ይህ ከተሟላ ብቻ ነው። የቤተ ዘመድ አባላት ትዳርን በተመለከተ ረጅም ሰዓት የሚወስዱ ንግግሮች ይሰጣሉ። ሙሽራውና ሙሽሪትም ንግግሮቹን በአክብሮት ያዳምጣሉ። የሠርግ ሥነ ሥርዓቱ በግብዣና በጭፈራ ይደመደማል።

የገበሬዎች ገነት

በቀድሞዎቹ ዘመናት አብዛኞቹ የባታካውያን ቤተሰቦች፣ የጎሽ ቀንድ የሚመስሉ ወደ ላይ የሾሉ ሁለት ጫፎች ባሏቸው ለየት ያሉ ጣሪያዎች በተሸፈኑ ትላልቅና ረጃጅም ቤቶች ውስጥ በኅብረት ይኖሩ ነበር። በጌጥ ከተንቆጠቆጡት ከእነዚህ ቤቶች መካከል አንዳንዶቹ በእንጨት፣ በቀርከሃና ከዘንባባ በሚገኝ ቃጫ የተሠሩና ከመሬት ከፍ ብለው የተገነቡ ናቸው፤ አንዳንዶቹ በጣም ትልልቆች ከመሆናቸው የተነሳ እስከ 12 ቤተሰብ ድረስ መያዝ ይችላሉ። እነዚህ ቤቶች በምስማር የተያያዙ አይደሉም። ከ300 ዓመታት በፊት የተሠሩ አንዳንድ ቤቶች አሁንም ድረስ ለመኖሪያነት ያገለግላሉ። ከፍ ብሎ ከተሠራው የቤቶቹ ወለል በታች እንደ ከብቶች፣ ዶሮዎች፣ ውሾች፣ አሳማዎችና ለማዳ ጎሾች ያሉ የቤት እንስሳት ይኖራሉ።

የአካባቢው ኢኮኖሚ በዋነኝነት የተመሠረተው በግብርና፣ ዓሣ በማስገር፣ ከብቶች በማርባትና በቱሪዝም ነው። እንዲያውም በቶባ ሐይቅ ዙሪያ የሚገኘው የአምፊቲያትር ዓይነት ቅርጽ ያለው በጣም ሰፊ አካባቢ የገበሬዎች ገነት ነው። ከሐይቁ በላይ ባሉት ረግረጋማ ቦታዎች ላይ የሚታዩት ለምለም የሆኑ የሩዝ ማሳዎች እርከኖች ተሠርቶላቸዋል። ባማሩት የአትክልት ቦታዎች አጠገብ በእሳተ ገሞራው አማካኝነት በተፈጠረው ጥቁር ለም አፈር ላይ ቡና፣ ፍራፍሬና የቅመማ ቅመም ተክሎች በብዛት ይበቅላሉ። ዓሣ አስጋሪዎች ከእንጨት በተሠሩት ታንኳዎቻቸው ላይ ሆነው ቀዝቃዛ ከሆነውና ኩልል ካለው ሐይቅ ውስጥ ዓሦችን በብዛት ያጠምዳሉ።

በቀኑ መገባደጃ ላይ ልጆች በደስታ ተሞልተው በሐይቁ ውስጥ ሲንቦራጨቁና ሲዋኙ ማየት የተለመደ ነው፤ አዋቂዎች ደግሞ በየካፊቴሪያዎቹ ቁጭ ብለው ይጫወታሉ፤ ሙዚቃው ቀዝቃዛ በሆነው የምሽቱ አየር ውስጥ ያስተጋባል። እንዲያውም ባታካውያን ስሜት በሚማርኩትና ቀልብን በሚገዙት ዘፈኖቻቸው በአካባቢው የታወቁ ናቸው። በተጨማሪም ጭፈራ የሚወዱ ሲሆን ወንዶችና ሴቶች ለየብቻ ሆነው ማራኪ በሆነ መንገድ ክንዳቸውንና እጃቸውን እያንቀሳቀሱ ይጨፍራሉ።

ክፉና ደጉ የተፈራረቀበት ታሪክ

ማርኮ ፖሎ ከኖረበት ዘመን አንስቶ እስከ 19ኛው መቶ ዘመን ድረስ ባታካውያን ሰው የሚበሉ ጨካኝ ሕዝቦች እንደሆኑና በአምልኮ ሥርዓቶቻቸው ላይ የጠላት ተዋጊዎችንና የወንጀለኞችን ሥጋ ይበሉ እንደነበር ዘገባዎች ያመለክታሉ። ይሁን እንጂ የታሪክ ፕሮፌሰር የሆኑት ሊዮናርድ አንዳያ እንደተናገሩት “የሰውን ሥጋ ስለ መብላት በዝርዝር የሚገልጹ [አንዳንድ] ዘግናኝ ታሪኮች ባታካውያን ራሳቸው የባዕድ አገር ሰዎች ወደ አካባቢያቸው እንዳይገቡ ለመከላከል ሲሉ ያስነገሯቸው ሊሆኑ ይችላሉ።” ያም ሆነ ይህ ዘ ባታክ—ፒፕልስ ኦቭ ዘ አይላንድ ኦቭ ሱማትራ የተባለው መጽሐፍ “በ19ኛው መቶ ዘመን የደች ቅኝ ገዢ መንግሥት በቁጥጥሩ ሥር ባሉት ግዛቶች ውስጥ የሰውን ሥጋ የመብላት ልማድ በሕግ እንዲታገድ አደረገ” በማለት ይገልጻል።

ባታካውያን የመናፍስት አምልኮን ያራምዱ የነበረ ሲሆን ብዛት ባላቸው ጣዖታትና መናፍስት ያምኑ ነበር። በተጨማሪም መሥዋዕት የሚያቀርቡባቸው ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች የነበሯቸው ከመሆኑም ሌላ መናፍስታዊ ድርጊቶችን፣ ሟርትንና አስማታዊ ድርጊቶችን ይፈጽሙ ነበር። ድግምትን፣ የጥንቆላ ጽሑፍንና የመድኃኒት መቀመሚያ ቀመሮችን 15 ሜትር የሚያህል ርዝማኔ ባላቸውና እንደ አኮርዲዮን በተጣጠፉ የዛፍ ልጦች ላይ በመጻፍ መጽሐፍ ቢጤ ያዘጋጁ ነበር። ደግሞም ክፉ መንፈስን ለማባረርና ስለ ወደፊቱ ጊዜ ለመተንበይ ይረዳሉ ተብለው የሚታሰቡ በጌጥ ያሸበረቁ ቅዱስ ልብሶች ይሸምኑ ነበር።

በ1824 ወደ ባታክ የገቡት የመጀመሪያዎቹ ምዕራባውያን ሚስዮናውያን የባብቲስት እምነት ተከታዮች የሆኑት ሪቻርድ በርተን እና ናትናኤል ዋርድ እንደሆኑ ዘገባዎች ያሳያሉ። ከአሥር ዓመት በኋላ፣ የደች ጦር ሠራዊት በአካባቢው ያሉትን አንዳንድ ቦታዎች ለመያዝ ጥረት ባደረገበት ጊዜ ሄንሪ ላይመን እና ሳሙኤል መንሰን የተባሉ ሌሎች ሁለት አሜሪካውያን ሚስዮናውያን ወደ ባታክ ክልል ዘልቀው ገቡ፤ ሆኖም ብዙም ሳይቆይ ተገደሉ። አደገኛ ወደሆኑ አካባቢዎች እንዳይሄዱ የተሰጣቸውን ማስጠንቀቂያ ችላ ያሉ ሌሎች ሁለት የካቶሊክ ሚስዮናውያንም ተመሳሳይ ዕጣ ሳይገጥማቸው አልቀረም።

ይሁንና በ1862 በባታካውያን መካከል ማገልገል የጀመረው ሉትቪክ ኖሜንዘን የተባለ ጀርመናዊ ሚስዮናዊ በሕይወት መቆየትና በቀላሉ የማይገመት ስኬት ማግኘት ችሎ ነበር። እንዲያውም ብዙዎቹ የአካባቢው ነዋሪዎች አሁንም ድረስ ለእሱ ትልቅ አክብሮት አላቸው። በዛሬው ጊዜ አብዛኞቹ ባታካውያን የክርስትና እምነት ተከታዮች እንደሆኑ የሚናገሩ ሲሆን የተቀሩት ደግሞ በአብዛኛው ሙስሊሞች ወይም የመናፍስት አምልኮ ተከታዮች ናቸው። ያም ሆኖ ብዙዎቹ አሁንም ድረስ ከአንዳንድ ባሕላዊ እምነቶቻቸው አልተላቀቁም።

እውነተኛው ምሥራች ደረሳቸው

በ1936 አካባቢ የይሖዋ ምሥክሮች ባታካውያን ወደሚኖሩባቸው ክልሎች በመግባት ኢየሱስ “በመላው ምድር ይሰበካል” በማለት አስቀድሞ የተናገረለትን የአምላክ መንግሥት ምሥራች አብስረዋል። (ማቴዎስ 24:14) በርካታ ባታካውያን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ለተመሠረተው መልእክት አዎንታዊ ምላሽ በመስጠት አጉል እምነቶቻቸውን እርግፍ አድርገው ትተዋል። በመሆኑም በአሁኑ ጊዜ በአካባቢው 30 የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ይገኛሉ።—በስተ ቀኝ ያለውን  ሣጥን ተመልከት።

እኔና ባለቤቴ በአካባቢው ለሚኖሩ ሰዎች ምሥራቹን ስንናገር አብዛኛውን ጊዜ እጹብ ድንቅ የሆነውን የቶባ ሐይቅ ገጽታና ተስማሚ የአየር ንብረት የሚያደንቁ ጎብኚዎች ያጋጥሙናል። እኛም ይህን ስሜታቸውን እንጋራለን። ይሁንና በዚህ ስፍራ ካሉት ነገሮች ሁሉ ይበልጥ ውብ የሆኑት ሞቅ ያለ ወዳጃዊ መንፈስ ያላቸው የባታክ ሕዝቦች እንደሆኑ ይሰማናል።

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

 እሳተ ገሞራ የወለደው ቀዝቃዛ ሐይቅ

ቶባ ሐይቅ 87 ኪሎ ሜትር ርዝመትና 27 ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን በዓለም ላይ ካሉት በእሳተ ገሞራ የተፈጠሩ ሐይቆች ሁሉ በትልቅነቱ የሚተካከለው የለም። ሐይቁ የያዘው ጨዋማ ያልሆነ ውኃ መላውን የዩናይትድ ኪንግደም ግዛት በዘጠና ሴንቲ ሜትር ገደማ ከፍታ ሊሸፍን ይችላል። የባሪሴን ተራሮች ክፍል በሆኑትና በእሳተ ገሞራ በተፈጠሩት አረንጓዴ ምንጣፍ የለበሱ ከፍታ ቦታዎች መካከል የሚገኘው ይህ እጹብ ድንቅ የሆነ ሐይቅ ከየትኛውም አቅጣጫ ሲታይ ማንኛውንም ፎቶግራፍ አንሺ የሚያማልል ውበት አለው።

ይህ ሐይቅ አንዴ ወይም በተደጋጋሚ ጊዜያት በተከሰቱ ኃይለኛ የእሳት ገሞራ ፍንዳታዎች ምክንያት የተፈጠረ ሲሆን ሳይንቲስቶች በዚህ ስፍራ የተከሰተው ፍንዳታ በምድር ታሪክ ከተከሰቱት እጅግ ኃይለኛ የሆኑ ፍንዳታዎች አንዱ እንደሆነ ያምናሉ። በእሳተ ገሞራው ፍንዳታ ምክንያት የተፈጠረው በጣም ትልቅ የሆነ ጉድጓድ ከጊዜ በኋላ በውኃ ተሞልቶ በአሁኑ ጊዜ ቶባ በመባል የሚታወቀው ሐይቅ ተፈጥሯል። ከዚያ በኋላ ከሐይቁ በታች በተከሰቱት የሥነ ምድር ለውጦች የተነሳ 250 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ያላት ውብ የሆነችው የሳሞሲር ደሴት ልትፈጠር ችላለች፤ የደሴቲቱ ስፋት የሲንጋፖር ሪፑብሊክን የቆዳ ስፋት ያክላል።

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ወይና ደጋ የአየር ንብረት ያላት ገነት

ቶባ ሐይቅ ከምድር ወገብ 300 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቆ የሚገኝ ቢሆንም በዚያ ያለው የአየር ንብረት ቀዝቀዝ ያለ መሆኑ ያስገርማል። ይህ የሆነው ሐይቁ ከባሕር ወለል በላይ 900 ሜትር ከፍታ ላይ ስለሚገኝ ነው። ወይና ደጋ የአየር ንብረት ባለው በዚህ ገነት የዘንባባ ዛፎችና የፈረንጅ ጥዶች በብዛት ይበቅላሉ።

ሐይቁ በርካታ እንስሳት የሚኖሩበትን ክልል የሚለይ ሥነ ምህዳራዊ ድንበር ሆኖ ያገለግላል። ለምሳሌ ያህል፣ ኦራንጉተንና ባለ ነጭ እጅ ጊበን ተብለው የሚጠሩት የዝንጀሮ ዝርያዎች እንዲሁም ቶማስስ ሊፍ የሚባሉት ጦጣዎች ከሐይቁ በስተ ሰሜን የሚኖሩ ሲሆን ቴፐርና ታርሲር ተብለው የሚጠሩት እንስሶችና ባንድድ ሊፍ በመባል የሚታወቁት ጦጣዎች በስተ ደቡብ በኩል ይኖራሉ።

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

 ከመናፍስት ጠሪነት ወደ እውነተኛ ክርስቲያንነት መለወጥ

ኑርሲ የባታክ ዱኩን ወይም ጠንቋይ ነበረች። በሽታን ለመፈወስ፣ ክፉ መናፍስትን ለማስወጣትና “ከሙታን” ጋር ለመገናኘት አስማታዊ ኃይል ትጠቀም ነበር። * ይህ ሥራዋ ብዙ ገንዘብ ያስገኝላት ነበር፤ እንዲህ ያሉ መናፍስታዊ ድርጊቶችን ትፈጽም የነበረ ቢሆንም በአካባቢዋ ያለው የፕሮቴስታንት ቤተ ክርስቲያን የተከበረች አባል ነበረች።

ኑርሲ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር በተገናኘች ጊዜ የአምላክ ስም ይሖዋ መሆኑን ስታውቅ በጣም ተገረመች። (መዝሙር 83:18 NW) በኋላም መጽሐፍ ቅዱስን ስታነብ፣ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖሩ የነበሩ ወደ ክርስትና የተለወጡ ብዙ ሰዎች አምላክን እሱ በሚፈልገው መንገድ ለማምለክ ሲሉ አስማታዊ ድርጊቶቻቸውን እርግፍ አድርገው እንደተዉና ለመናፍስታዊ ድርጊቶች ይጠቀሙባቸው የነበሩትን መጻሕፍት እንዳቃጠሉ ተገነዘበች። (የሐዋርያት ሥራ 19:18, 19) ኑርሲ ከፍተኛ ተቃውሞ ቢደርስባትም “እውነትም ነፃ ያወጣችኋል” በሚሉት የኢየሱስ ቃላት ሙሉ በሙሉ በመተማመን እሷም ተመሳሳይ እርምጃ ለመውሰድ ወሰነች።—ዮሐንስ 8:32

በአሁኑ ጊዜ ኑርሲና ልጇ ቤስሊ የተጠመቁ የይሖዋ ምሥክሮች ሲሆኑ ባለቤቷ ኔንግኩስ ደግሞ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትሮ ይገኛል። “አሁን ይሖዋን እያገለገልኩ ነው፤ ሕይወቴ ከቀድሞው እጅግ የተሻለ ነው! ዱኩን በነበርኩበት ጊዜ እውነትን ለማወቅ እጓጓ ነበር፤ አሁን በጣም ረክቻለሁ” ስትል ተናግራለች።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.31 በገጽ 20 ላይ የሚገኘውን “መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? አጋንንት እነማን ናቸው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

[ሥዕል]

ኑርሲ ከባለቤቷና ከልጇ ጋር

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ሱማትራ

ቶባ ሐይቅ

[ምንጭ]

Based on NASA/Visible Earth imagery

[በገጽ 16 እና 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቶባ ሐይቅ ከፑሱክ ቡሂት ተራራ ሲታይ

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በቶባ ሐይቅ በስተ ሰሜን ጫፍ ላይ የሚገኘው የሲፒሶፒሶ ፏፏቴ 110 ሜትር ወደ ታች ይወረወራል