በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

በካንሰር ላይ ምርምር የሚያደርገው ዓለም አቀፍ ድርጅት በአልትራቫዮሌት ብርሃን ቆዳን ለማጠየም መሞከር “በሰዎች ላይ የካንሰር በሽታ ሊያስከትሉ ይችላሉ” ተብለው ከሚገመቱ ነገሮች መካከል መቆጠሩ ቀርቶ በእርግጠኝነት “የካንሰር በሽታ ያስይዛሉ” ከሚባሉት ነገሮች መካከል እንዲመደብ አድርጓል። —ዘ ላንሴት ኦንኮሎጂ፣ ብሪታንያ

በአርጀንቲና ውስጥ ከ10 ነፍሰ ጡር ሴቶች መካከል ዘጠኙ ያረገዙት ፈልገውት አይደለም።—ክላሪን፣ አርጀንቲና

“የሥነ ሕይወት ተመራማሪዎች በየጊዜው አዳዲስ ዝርያዎችን እያገኙ ነው። የሥነ ሕይወት ተመራማሪዎች በቀን 50 የሚያህሉ ዝርያዎችን ያገኛሉ። በ2006 ብቻ ወደ 17,000 የሚጠጉ አዳዲስ የዕፅዋትና የእንስሳት ዝርያዎችን መለየት የቻሉ ሲሆን ይህም ስያሜ ከተሰጣቸው 1.8 ሚሊዮን የሚሆኑ ዝርያዎች መካከል 1 በመቶ ገደማ ይሆናል።”—ታይም፣ ዩናይትድ ስቴትስ

የጦር መሣሪያ ከአደጋ ሊታደግ ይችላል?

አንድ ሰው የጦር መሣሪያ መያዙ ራሱን ከጥቃት ለመከላከል ያስችለዋል? በዩናይትድ ስቴትስ፣ የፔንሲልቬንያ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ትምህርት ማዕከል ያደረገው ጥናት፣ በአማካይ ሲታይ የጦር መሣሪያ መያዝ ከጥቃት እንደማያስጥል አመልክቷል። ተመራማሪዎች ያደረጉት ጥናት እንዳመለከተው ከሆነ የጦር መሣሪያ የያዘ ሰው “በጥይት የመመታቱ ዕድል የጦር መሣሪያ ካልያዘ ሰው ጋር ሲነጻጸር 4.5 እጥፍ ይበልጣል፤” ይህ ስሌት ፖሊስ ጣልቃ የገባባቸውን ሁኔታዎች እንዲሁም በራስ ላይ በተተኮሰም ሆነ ሳይታሰብ በተተኮሰ ጥይት የተነሳ የደረሱ ጉዳቶችን አይጨምርም። ጥናቱ መሣሪያ የሚይዙ አንዳንድ ሰዎች የሚሰነዘርባቸውን ጥቃት በተሳካ ሁኔታ መከላከል እንደሚችሉ ያሳየ ቢሆንም ይህን ለማድረግ የሚችሉበት አጋጣሚ እጅግ አነስተኛ መሆኑን አመልክቷል። ሪፖርቱ መሣሪያ መያዝ “ራስን ከአደገኛ ሁኔታ ለመከላከል ያስችላል” የሚለው አመለካከት “እንደገና ሊታሰብበትና በሚገባ ሊጤን ይገባዋል” ሲል ገልጿል።

ሊፕስቲክ የሚቀቡ ወንድ መነኮሳት

በባንኮክ የወጣ አንድ የዜና ዘገባ እንደገለጸው በታይላንድ የሚገኙ አዳዲስ መነኮሳት ሊፕስቲክ በመቀባት፣ ቀሚሶቻቸውን አጥብቀው በማሰር እንዲሁም “ዳሌያቸውን ቅጥ በሌለው ሁኔታ እያወዛወዙ በመሄድና የሴት ቦርሳ በመያዝ ወግ አጥባቂ የሆነውን የቡድሂስት እምነት ስም እያጎደፉ ነው።” ግብረ ሰዶማውያን የሆኑት አዳዲስ መነኮሳት ጠባይ ያሳሰባቸው የሃይማኖት ባለሥልጣናት መነኮሳቱ ከሥነ ምግባር ጋር የተያያዘ ሥልጠና እንዲሰጣቸው ሐሳብ አቅርበዋል። አንድ ታዋቂ የቡድሂስት እምነት ሰባኪ፣ መነኮሳቱ ግብረ ሰዶም እንዳይፈጽሙ የሚያግድ ሕግ እንደሌለ ከገለጹ በኋላ እንዲህ ዓይነት ሕግ “ቢኖር ኖሮ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ከምንኩስናቸው እንዲገለሉ ይደረግ ነበር” ብለዋል።

ሴቶች ብቻ የሚሳፈሩባቸው ባቡሮች

በሰው በተጨናነቁ የሕዝብ ማመላለሻ ባቡሮች የሚጓዙ ሴት ተሳፋሪዎች ለበርካታ ዓመታት ስድብ ሲሰነዘርባቸው እንዲሁም ወንዶች ሲዳብሷቸው፣ አፍጥጠው ሲመለከቷቸውና በአጠቃላይ የፆታ ትንኮሳ ሲፈጽሙባቸው ቆይተዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚቀርበው ስሞታ ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ በመሄዱ መንግሥት በአንዳንድ ሁኔታዎች ወንዶች ጨርሶ አብረዋቸው እንዳይሳፈሩ ለማድረግ መወሰኑን በካልካታ የሚታተመው ዘ ቴሌግራፍ የተሰኘው ጋዜጣ ዘግቧል። በመሆኑም በሕንድ አራት ትልልቅ ከተሞች ይኸውም በኒው ዴልሂ፣ በሙምባይ፣ በቼናይና በካልካታ “ለሴቶች ብቻ” አገልግሎት የሚሰጡ የተወሰኑ ባቡሮች እንዲመደቡ ተደርጓል። በዚህም ተሳፋሪዎች እንደተደሰቱ ተገልጿል።