በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ይኸው ዳግመኛ ተገናኘን!” ለማለት ጓጉቼአለሁ

“ይኸው ዳግመኛ ተገናኘን!” ለማለት ጓጉቼአለሁ

“ይኸው ዳግመኛ ተገናኘን!” ለማለት ጓጉቼአለሁ

አቢጌል ኦስተን እንደተናገረችው

በወቅቱ ዘጠኝ ዓመቴ ነበር። በሚያዝያ 1995 በአንድ ደስ የሚል ቀን በአካባቢያችን ያለው የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ አባላት የሆንን የተወሰንን ሰዎች ወደ እንግሊዝ ገጠራማ ቦታ ወጣ ብለን ለመዝናናት አሰብን። በቡድን በቡድን ተከፋፍለን በመኪና ጉዞ ጀመርን። ታላቅ እህቴ ሣራ፣ የቤተሰባችን ጓደኛ የሆነችው ዲቦራና እኔ ከአባቴና ከእናቴ ጋር ሆነን እየተጓዝን ነበር። በድንገት አንድ መኪና መስመሩን ለቆ በእኛ አቅጣጫ እየበረረ መጣና ገጨን። በሕይወት የተረፍኩት እኔ ብቻ ነበርኩ።

ሴን ስቼ በሆስፒታል ውስጥ ለሁለት ሳምንት ያህል ከቆየሁ በኋላ ነቃሁ። የራስ ቅሌ ተሰባብሮ ስለነበር ሐኪሞቹ አንድ ላይ ለማያያዝ በርከት ያሉ ሰው ሠራሽ ማያያዣዎች አስገብተውልኝ ነበር። ያም ሆኖ በፍጥነት አገገምኩ። በመጨረሻም ቤተሰቦቼ የሆነውን ነገር ሲነግሩኝ አላመንኳቸውም። ወላጆቼና እህቴ ተኝቼ እያለሁ ሊጠይቁኝ መጥተው እንደነበርና ሳላያቸው እንደሄዱ አድርጌ አስብ ነበር። በእርግጥ እንደሌሉ ያወቅሁት ከሆስፒታል ወጥቼ ቤት ከገባሁ በኋላ ነበር። በመሆኑም ልቤ በሐዘን ተሰበረ።

ይህን ከባድ ሐዘን እንድቋቋም የረዳኝ ምን ነበር?

ያገኘሁት መንፈሳዊ ውርስ

እኔ ከአምስት ልጆች መካከል የመጨረሻዋ ነኝ። አደጋው በደረሰበት ጊዜ ሣራ 22፣ ሼን 20፣ ጄሲካ 17፣ ሉክ ደግሞ 15 ዓመታቸው ነበር። እጅግ የሚያስቡልን ጥሩ ወላጆች ነበሩን። አባቴ ስቲቭ፣ ሺፕሌይ ውስጥ በሚገኘው በዌስት ዮርክሺር ጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ ያገለግል የነበረ ሲሆን ምንጊዜም ሌሎችን ለማዳመጥና ለመርዳት ጊዜውን መሥዋዕት የሚያደርግ ሰው በመሆኑ በሁሉም ዘንድ ተወዳጅ ነበር። እናቴ ካሮልም ተወዳጅ የነበረች ሲሆን በጉባኤው ውስጥ ያሉትን አረጋውያን እንደ ልጃቸው ሆና ትንከባከባቸው ነበር። ወጣቶች ለሆንነው ደግሞ አንድ ላይ ሆነን መጫወት የምንችልባቸውን ዝግጅቶች ታደርግልን የነበረ ከመሆኑም ሌላ ጥሩ ጓደኞች ማፍራት እንድንችል ትረዳን ነበር። ቤታችን ለሁሉም ክፍት ነበር። ወላጆቻችን ለጎረቤቶቻችንም ደግና አሳቢ እንድንሆን አስተምረውናል።

ሁልጊዜ ረቡዕ ምሽት ላይ በቤተሰብ አንድ ላይ ሆነን መጽሐፍ ቅዱስ እናጠና ነበር። አንዳንድ ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበረውን ዓይነት አለባበስ ለብሰን ድራማ እንሠራ ነበር። አባዬና እማዬ ከሕፃንነታችን ጀምሮ ለጉባኤ ስብሰባዎች እንዴት እንደምንዘጋጅና ከቤት ወደ ቤት እየሄድን ለሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት እንዴት እንደምንናገር አስተምረውናል። ወላጆቻችን አምስት ልጆች የማሳደግ ኃላፊነት ስላለባቸው ሥራ የሚበዛባቸው ቢሆንም ከእኛ ጋር ጊዜ ያሳልፉ የነበረ ሲሆን በመንፈሳዊም ጠንካሮች እንድንሆን ረድተውናል።

ሣራ፣ ሼንና ጄሲካ ትምህርታቸውን ሲጨርሱ ልክ እንደ ጓደኛችን እንደ ዲቦራ አቅኚዎች፣ ማለትም የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ሆነው ነበር። ሣራና እኔ ደግሞ በጣም እንቀራረብ ነበር። ሣራ ለእኔ እንደ ሁለተኛ እናቴ የነበረች ሲሆን ትምህርት ቤት ሲዘጋ ሌሎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያውቁ በመርዳት አብረን ጊዜ እናሳልፍ ነበር። እነዚያ ጊዜያት በጣም ያስደስቱኝ ነበር። አቅኚዎቹ በሙሉ ምን ያህል ደስተኞች እንደሆኑ ስለምመለከት ከእነሱ ጋር መሆን ያስደስተኝ ነበር። የእኔም ግብ ትምህርቴን ስጨርስ አቅኚ ሆኜ ከሣራ ጋር ማገልገል ነበር።

በእረፍት ቀኖች ቤተሰባችንና በጉባኤው ውስጥ ያሉ ሌሎች ወንድሞችና እህቶች አብረው ጊዜ ያሳልፉ ነበር። ወጣቶችም ሆኑ አረጋውያን ሁሉም በወዳጅነትና በፍቅር የተሳሰሩ ነበሩ። እነዚህ ጥሩ ጓደኞች በመጪዎቹ ቀናት ምን ያህል ሊረዱኝና ሊያጽናኑኝ እንደሚችሉ እምብዛም አልተገነዘብኩም ነበር!

ከአደጋው በኋላ

ከሆስፒታል ከወጣሁ በኋላ ወደ ወላጆቼ ቤት ተመለስኩ። ሼንና ጄሲካ የሚያስፈልገንን ለማቅረብና ሁላችንንም ለመንከባከብ በሳምንት ውስጥ ለተወሰኑ ሰዓታት ይሠሩ የነበሩ ሲሆን በሙሉ ጊዜ አገልግሎት በትጋት ይካፈሉ ነበር።

በጉባኤያችን ያሉ ብዙ የእምነት አጋሮቻችንም በችግራችን ጊዜ ደርሰውልናል። ብዙ ነገር አድርገውልናል! ራሳችንን እስክንችል ድረስ የምንበላውን ነገር በማቅረብ፣ ቤት በማጽዳት፣ ገበያ በመሄድና ልብሶቻችንን በማጠብ ይረዱን ነበር። ለዚህ ሁሉ በጣም አመስጋኞች ነን። በቅርብም ሆነ በሩቅ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር ስፍር የሌላቸው ስጦታዎችና የማጽናኛ ካርዶች ይልኩልን የነበረ ሲሆን ይህም በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ያለውን ጥልቅ ፍቅር እንድንገነዘብ አስችሎናል።

ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ ወንድሞቼና እህቴ እኔ በተረጋጋ ቤተሰብ ውስጥ ብኖር የተሻለ እንደሚሆን አሰቡ። በጉባኤው ውስጥ ያሉ አንዳንድ ደግ ቤተሰቦች ሊረዱን ራሳቸውን አቅርበው ስለነበር አባዬና እማዬ ለእኔና ለወደፊቱ መንፈሳዊ ደኅንነቴ ከሁሉ የተሻለ ነው ብለው ሊያስቡ የሚችሉትን ነገር ግምት ውስጥ በማስገባት ቤተሰቤ ቁጭ ብሎ ጉዳዩን መከረበት። ሊረዱን ፈቃደኛ ከሆኑት ቤተሰቦች መካከል ለየት ብሎ ያገኘነው አንድ ቤተሰብ ነበር። የጉባኤ ሽማግሌ የሆነው ቢሊና ሚስቱ ዶን የቤተሰባችን የቅርብ ወዳጆች የነበሩ ሲሆን ሎይስ የምትባል የአምስት ዓመት ልጅ ነበረቻቸው። እነሱም በደስታ ወደ ቤታቸው ወሰዱኝ፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ልክ እንደ ራሳቸው ልጅ አድርገው በፍቅር ተንከባክበው አሳደጉኝ። ምንም እንኳ ሎይስ የወላጆቿን ፍቅር ብጋራትም ቅናት አድሮባት አያውቅም፤ እስከ ዛሬም ድረስ ቅርርባችን ልክ እንደ እህትማማቾች ነው።

የደረሰብኝን ከባድ ሐዘን ልቋቋም የቻልኩት እንዴት ነው?

መጀመሪያ ላይ ‘ወላጆቼ፣ እንዲሁም ሣራና ዲቦራ ለይሖዋና ለሰዎች ጥልቅ ፍቅር እያላቸው፣ በቤተሰባችን ላይ እንዲህ ያለ አሳዛኝ ሁኔታ የደረሰው ለምንድን ነው?’ እያልኩ አስብ ነበር። ይሁን እንጂ ኢዮብ ልጆቹን ሁሉ በሞት ቢያጣም በአምላክ ላይ ያለውን እምነት እንደጠበቀ የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ አስታወስኩ። (ኢዮብ 1:19, 22) ‘አዎ፣ መጀመሪያውኑም ቢሆን መከራንና ሞትን ወደዚህ ዓለም ያመጣው ሰይጣን ነው፤ ስለሆነም ይህ አደጋ አምላክን ማገልገላችንን እንድናቆም ቢያደርገን በጣም ይደሰታል’ ብዬ አሰብኩ። (ዘፍጥረት 3:1-6፤ ራእይ 12:9) በተጨማሪም ይሖዋ በፍቅር ተገፋፍቶ አስደናቂውን የትንሣኤ ተስፋ እንደሰጠን አስታወስኩ። (ዮሐንስ 5:28, 29) ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ቤተሰባችንንና ዲቦራን እንደገና እናገኛቸዋለን! እንዲያውም ለይሖዋ ያለኝ ፍቅር ይበልጥ ተጠናከረ።

መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተገለጸውን ውድ የትንሣኤ ተስፋ ያልሰሙ እንደኔው ከባድ ሐዘን የደረሰባቸው ሰዎች ሳገኝ በጣም አዝንላቸዋለሁ። ይህም እኛ ያገኘነውን ተስፋ ለእነሱም ለማካፈል እንድነሳሳ ያደርገኛል፤ ምክንያቱም ይዋል ይደር እንጂ የተስፋ ጎህ መቅደዱ እንደማይቀር በመገንዘብ ያጋጠመንን የጨለማ ወቅት ልናልፍ የቻልነው በይሖዋና በድርጅቱ ድጋፍ ብቻ ነው።

ምናልባትም በእኛ ላይ የደረሰው ሁኔታ አንዳንድ ወላጆች ‘እኛ አንድ ነገር ብንሆን ልጆቻችን ብቻቸውን ይሖዋን ማገልገላቸውን እንዲቀጥሉ የሚያስችል በቂ የሆነ ጠንካራ መንፈሳዊ መሠረት ጥለንላቸዋል?’ ብለው ራሳቸውን እንዲጠይቁ ሳያደርጋቸው እንዳልቀረ እገምታለሁ።

አባዬና እማዬ አሁንም በሕይወት እንዳሉ አድርጌ በማሰብ ሕይወቴን ለመምራት ጥረት አድርጌያለሁ። እነሱ ያደርጉት እንደነበረው ሁሉ ሌሎችን ለመርዳት ተግቼ እንድሠራ እንደሚፈልጉ አውቃለሁ። ትምህርቴን ከጨረስኩ ጀምሮ አቅኚ ሆኜ እያገለገልኩ ሲሆን አሁን ደግሞ ሎይስም አቅኚ ሆና አብራኝ እያገለገለች ነው። ወንድሞቼና እህቴ ትዳር መሥርተው በየጉባኤዎቻቸው ይሖዋን በደስታ እያገለገሉ ነው።

አምላክ የሚያመጣውን አዲስ ዓለምና የትንሣኤ ተስፋ የሚፈጸምበትን ጊዜ በጉጉት እጠባበቃለሁ! ከዚያ በኋላ ሥቃይም ሆነ ሞት አይኖርም። (ራእይ 21:3, 4) ሁላችንም እንደገና እንደምንገናኝ ማወቄ የሚያጋጥሙኝን ችግሮች ተቋቁሜ ወደ ፊት እንድገፋ ረድቶኛል። አባዬን፣ እማዬን፣ ሣራንና ዲቦራን እቅፍ አድርጌ ለመሳምና “ይኸው ዳግመኛ ተገናኘን!” ለማለት ጓጉቼአለሁ።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአሁኑ ጊዜ፣ አቢጌል (በስተ ግራ በኩል ሁለተኛዋ) ካሳደጋት ቤተሰብ ጋር