በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ገራገር ሆኖም ጠንካራ የሆነው የሼትላንድ ድንክ ፈረስ

ገራገር ሆኖም ጠንካራ የሆነው የሼትላንድ ድንክ ፈረስ

ገራገር ሆኖም ጠንካራ የሆነው የሼትላንድ ድንክ ፈረስ

ከዚህ ቀደም የሼትላንድ ድንክ ፈረስ አይተህ ምናልባትም ጋልበህ ታውቅ ይሆናል። ስማቸው እንደሚጠቁመው የሼትላንድ ድንክ ፈረሶች ዋነኛ መገኛ የሆኑት በሰሜናዊ ምሥራቅ ስኮትላንድ የሚገኙት የሼትላንድ ደሴቶች ናቸው። እንዲያውም አርኪኦሎጂስቶች በአካባቢው ባደረጉት ቁፋሮ በሺህ የሚቆጠሩ ዓመታትን ያስቆጠሩ የትንንሽ ድንክ ፈረሶችን አፅም አግኝተዋል።

የሼትላንድ ድንክ ፈረሶች በአጫጭር እግሮቻቸው፣ በረጅም ጋማቸውና ጭራቸው እንዲሁም በሼትላንድ ደሴቶች ያለውን አስቸጋሪ የአየር ጠባይ ለመቋቋም በሚያስችላቸው ጥቅጥቅ ያለ ፀጉራቸው በቀላሉ ተለይተው ይታወቃሉ። እነዚህ ድንክ እንስሳት ቁመታቸው ከ70 እስከ 107 ሴንቲ ሜትር የሚደርስ ሲሆን በአብዛኛው ጥቁር ወይም ጠቆር ያለ ቡናማ ቀለም ያላቸው ናቸው፤ እስከ 117 ሴንቲ ሜትር የሚደርስ ቁመት ያላቸውን የአሜሪካዎቹን የሼትላንድ ፈረሶች ሳይጨምር የእነዚህ ድንክ ፈረሶች የመጨረሻ ርዝማኔ 107 ሴንቲ ሜትር ነው።

የሼትላንድ ፈረሶች ቁመታቸው አጭር ቢሆንም ጠንካሮች ናቸው። እንዲያውም ከቁመታቸው አንጻር ሲታዩ ከሁሉም የፈረስ ዝርያዎች ይበልጥ ጠንካሮች ናቸው። በዚህም ምክንያት ሰዎች እነዚህን ድንክ ፈረሶች ለማዳበሪያ የሚሆን ከፍተኛ ክብደት ያለው ብስባሽ ለማጓጓዝ፣ የእርሻ መሬት ለማረስና ትናንሽ እንስሳት ብቻ ሊሾልኩባቸው የሚችሉ ዋሻዎች ባሉባቸው የከሰል ድንጋይ ማውጫዎች ውስጥ ለመሥራት ይጠቀሙባቸው እንደነበር ይነገራል። እንዲያውም ብዙዎቹ ድንክ ፈረሶች መላ ሕይወታቸውን የሚያሳልፉት የቀኑን ብርሃን ማየት በማይችሉባቸው የማዕድን ማውጫዎች ውስጥ ነበር።

የሼትላንድ ድንክ ፈረሶች በአግባቡ ከሠለጠኑ ገራገርና ታዛዦች በመሆናቸው ለልጆች ተስማሚ ናቸው። ገራገር ጠባያቸው የአካል ጉዳተኛ የሆኑ ሰዎች በሚረዱበት የሕክምና ፕሮግራም ውስጥ እነዚህን ፈረሶች በማሠራት ለተገኘው ጥሩ ውጤት አስተዋጽኦ አበርክቷል።

የሼትላንድ ድንክ ፈረሶች ማራኪ ጠባይና የተለያዩ አካባቢዎችን ቶሎ የመላመድ ችሎታ ያላቸው በመሆኑ ወደ ተለያዩ የዓለም ክፍሎች ተልከዋል፤ በተጨማሪም በእነሱ ምክንያት በርካታ ክለቦችና የእንስሳት ዝርያዎችን የሚመዘግቡ ተቋማት ተመሥርተዋል። ይሁን እንጂ የዚህ እንስሳ ስም አሁንም ቢሆን ዋና መገኛው ከሆኑት ደሴቶች ስም ጋር የተያያዘ ነው፤ በዚያ የሚገኘው የሼትላንድ ዝርያ አሁንም ድረስ በአስደናቂ ሁኔታ ጤናማ ከመሆኑም በተጨማሪ ከሌሎች ዝርያዎች ጋር ሳይዳቀል መቆየት ችሏል።

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሼትላንድ ድንክ ፈረሶች ከቁመታቸው አንጻር ሲታዩ ከሁሉም የፈረስ ዝርያዎች ይበልጥ ጠንካሮች ናቸው

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

© S Sailer/A Sailer/age fotostock