በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መፍትሔ ማግኘት የምትችልባቸው መንገዶች

መፍትሔ ማግኘት የምትችልባቸው መንገዶች

መፍትሔ ማግኘት የምትችልባቸው መንገዶች

ብቸኝነት የሚያጠቃህ ከሆነ ራስህን የሚከተሉትን ጥያቄዎች መጠየቅ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል፦ ‘ሁኔታዬን ለማሻሻል ላደርጋቸው የምችላቸው ነገሮች ይኖራሉ? ምናልባት በሕይወቴ ውስጥ አንዳንድ ለውጦችን ማድረግ ያስፈልገኝ ይሆን? ከሆነስ ምን ለውጦችን ማድረግ ይኖርብኛል?’ የሚከተሉት ጥያቄዎች ራስህን እንድትገመግምና አጥጋቢ መፍትሔ እንድታገኝ ሊረዱህ ይችላሉ።

አመለካከቴን መለወጥ ያስፈልገኝ ይሆን?

ማንኛውም ሰው በብቸኝነት ሊጠቃ ይችላል። ይሁን እንጂ ይህ አሉታዊ ስሜት እንደ ከባድ ችግር የሚታየው ለረጅም ጊዜ ሲዘልቅ ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ ለሕይወት ያለህ አመለካከት መስተካከል እንደሚያስፈልገው የሚጠቁም ምልክት ሊሆን ይችላል። ችግሩ የሚመነጨው ከሌሎች ጋር ስትሆን ከሚኖርህ ባሕርይ ሊሆን ይችላል። አንዳንዶች ዙሪያቸውን በእሾሃማ ሽቦ ያጠሩ ያህል ሰዎች በጓደኝነት እንዳይቀርቧቸው የሚያግድ ነገር ሳይታወቃቸው ያደርጋሉ። አንዳንድ ጊዜ የሚያስፈልገው ነገር የአመለካከት ለውጥ ማድረግ ብቻ ሊሆን ይችላል።

ስደተኛ ሆና ወደ እንግሊዝ የሄደችው ሳቢኔ ያጋጠማትን ነገር እንመልከት። እንዲህ ብላለች፦ “አዳዲስ ጓደኛሞች በመካከላቸው መተማመን ተፈጥሮ አብረው ሲሆኑ ዘና ለማለትና አንዱ በሌላው ላይ እምነት ለመጣል እንዲችሉ ጊዜ ያስፈልጋል። ታዲያ ሌሎችን ስላስተዳደጋቸው ወይም ስለ ኋላ ታሪካቸው ለምን አትጠይቋቸውም? ‘በሁሉ ነገር ፍጹም ትክክል የሆነ ባሕል የለም፤ ከሁሉም ባሕሎች ጥሩውን ነገር ውሰጂ’ የሚል ምክር ተሰጥቶኝ ነበር።” አዎን፣ ለሳቢኔ ከተሰጣት ምክር መመልከት እንደሚቻለው አንተም ከሌሎች ባሕል ውስጥ ጠቃሚ የሆኑ ነገሮችን ለማግኘት ጥረት ብታደርግ ትጠቀማለህ።

ሰው አልቀርብም?

ራስህን እንዲህ ብለህ ልትጠይቅ ትችላለህ፦ ‘ሰዎችን የመቅረብ ችግር አለብኝ? እኔ የወዳጅነት ስሜት ባሳያቸው ሰዎች የበለጠ ይቀርቡኝ ይሆን?’ እንዲህ ዓይነት ችግር እንዳለብህ ከተሰማህ ይበልጥ ተግባቢ ለመሆን ጥረት አድርግ። ከጓዴሎፕ ወደ እንግሊዝ የሄደችው የ30 ዓመቷ ሮዘሊዝ “ብቸኝነት የሚሰማቸው ሰዎች ራሳቸውን የማግለል ዝንባሌ አላቸው” ብላለች። ስለዚህ እንዲህ በማለት መክራለች፦ “እንደ እናንተ ብቸኛ ለሆኑ ሰዎች ትኩረት ስጡ። ቅድሚያውን ወስዳችሁ አነጋግሯቸው። አንዳንድ ጊዜ ዘላቂ ወዳጅነት ለመመሥረት የሚያስፈልገው አንድ ጥያቄ መጠየቅ ብቻ ነው።”

ይሁንና የጠበቀ ወዳጅነት ለመመሥረት ጊዜና ጥረት ይጠይቃል። ጥሩ አዳማጭ መሆን እንዲህ ዓይነቱን ወዳጅነት ለመጀመር ጠቃሚ መንገድ ነው። በትኩረት ማዳመጥህ ሌላው ሰው ስለሚወዳቸው ነገሮች ለማወቅ ስለሚያስችልህ እሱ የሚያስደስተውን ነገር ለማውራት የተሻለ አጋጣሚ ይሰጥሃል። የሌላውን ሰው ስሜት መጋራት ወዳጅነት ለመመሥረት እንደሚረዳ አስታውስ!

ችግሬ አሉታዊ አስተሳሰብ ነው?

ራስህን ዝቅ አድርገህ መመልከት ወዳጅነት ለመመሥረት እንቅፋት ሊሆንብህ ይችላል። ‘ራሴን ከሚገባው በላይ ዝቅ አድርጌ እመለከታለሁ?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። በጋና የምትኖረው የ15 ዓመቷ አቢጋኤል “አንዳንድ ጊዜ በውስጤ የሚፈጠርብኝ አሉታዊ አስተሳሰብ ብቸኝነት እንዲሰማኝ ያደርገኝ ነበር። የማልወደድና የማልረባ እንደሆንኩ ይሰማኝ ነበር” በማለት ተናግራለች። አንተ ቅድሚያውን ወስደህ ሌሎችን ከቀረብካቸውና በሆነ መንገድ ከረዳሃቸው የማትረባ እንደሆንክ አድርገው እንደማይመለከቱህ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። እነሱም ወዳጆችህ በመሆን አጸፋውን ሊመልሱልህ ይችላሉ። ታዲያ አንተ ለምን ቀዳሚ አትሆንም?

አዎንታዊ አስተሳሰብ የዕድሜ እኩዮችህ ካልሆኑ ሰዎች ጋር ወዳጅነት እንድትመሠርትም ይረዳሃል። በዕድሜ ከአንተ ከሚበልጥ ወይም ታናሽህ ከሆነ ሰው ጋር ወዳጅነት መመሥረት መልሶ የሚክስ ነው። አቢጋኤል የብቸኝነት ስሜቷን ለማሸነፍ የረዳት ዋናው ነገር በዕድሜ ከሚበልጧት መካከል ጓደኛ ለማግኘት ጥረት ማድረጓ ነው። “ከሕይወት ተሞክሯቸው ተጠቅሜያለሁ” በማለት ገልጻለች።

ራሴን አገልላለሁ?

ብቸኝነት የሚሰማቸው ብዙ ሰዎች ረዘም ላለ ጊዜ ቴሌቪዥን በመመልከት ወይም የቪዲዮ ጨዋታዎችን በመጫወት አሊያም ለሰዓታት በኮምፒውተራቸው ላይ በመሥራት ከብቸኝነታቸው መጠነኛ እፎይታ ያገኛሉ። ይሁን እንጂ ከእነዚህ ነገሮች ዘወር ሲሉ ያው እንደ ቀድሞው ብቸኝነት ይሰማቸዋል። በፓሪስ ያለችው የ21 ዓመቷ ኤልሳ “ቴሌቪዥንና የቪዲዮ ጨዋታዎች አንድን ሰው እንደ ዕፅ ሱስ ሊሆኑበትና ጓደኛ ማፍራት የማይፈልግበት ደረጃ ሊያደርሱት ይችላሉ” በማለት ተናግራለች።

ቴሌቪዥን መመልከት ካሉት አሉታዊ ገጽታዎች አንዱ ለመነጋገር፣ ሐሳብ ለመለዋወጥ ወይም ጓደኛ ለማፍራት አጋጣሚ የማይሰጥ መሆኑ ነው። የቪዲዮ ጨዋታዎችም ተመሳሳይ ተጽዕኖ አላቸው፦ ሰዎች መጫወታቸውን ሲያቆሙ እንደ ጉም በንኖ በሚጠፋ ምናባዊ ዓለም ውስጥ እንዲገቡ ያደርጓቸዋል። ያለ አንዳች ዓላማ ኢንተርኔትን ማሰስ ከገሐዱ ሕይወት ለመደበቅ ቢያስችልም ለብልግና ምስሎች ወይም ማንነታቸውን ለሚደብቁ ሰዎች ሊያጋልጥ ይችላል። ኢንተርኔት እውነተኛ ጓደኛ ለማግኘትም ሆነ ጓደኝነትን ለማጠናከር የሚቻልበት ቦታ አይደለም።

የትዳር ጓደኛ እየፈለግሁ ነው?

አንዳንድ ያላገቡ ሰዎች ለብቸኝነታቸው መፍትሔ ለማግኘት ሲሉ ብቻ ማግባት ይፈልጉ ይሆናል። እውነት ነው፣ ደግና አፍቃሪ የትዳር ጓደኛ በሕይወትህ ውስጥ ከፍተኛ ደስታ ሊያስገኝልህ ይችላል፤ ይሁን እንጂ ጋብቻን የመሰለ ትልቅ ውሳኔ ተቻኩለህ እንዳታደርግ ተጠንቀቅ።

ጋብቻ ከብቸኝነት የሚገላግል መፍትሔ ላይሆን ይችላል። የሐሳብ ልውውጥ የማድረግ ችግር ያለባቸው ያገቡ ሰዎች “በዓለም ላይ ብቸኝነት እጅግ ከሚያጠቃቸው መካከል” እንደሆኑ ይነገራል። የሚያሳዝነው ነገር፣ ከሚታሰበው በላይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች እንዲህ በመሰለው ሁኔታ ውስጥ ይኖራሉ። ስለዚህ ለማግባት የምትመኝ ከሆነ የፍቅር ግንኙነት ከመጀመርህ በፊት የብቸኝነት ችግርህን ለማሸነፍ ለምን አትጥርም? ከማግባትህ በፊት በአመለካከትህና በልማዶችህ ላይ ማስተካከያ በማድረግ እንዲሁም ጓደኛ ለማፍራት ቅድሚያውን በመውሰድ አስደሳች ጋብቻ ለመመሥረት የሚረዳህን ጠንካራ መሠረት ልትጥል ትችላለህ።

የብቸኝነትን ስሜት መቋቋም ትችላለህ

የብቸኝነት ስሜትህን በአንድ ጀንበር ለማሸነፍ የሚረዳህ መፍትሔ ላይኖር ይችላል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ የተናገረውን ወርቃማ ሕግ ከተከተልክ ይህን ስሜት በመቋቋም ረገድ ሊሳካልህ ይችላል። ኢየሱስ “ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር ሁሉ እናንተም እንደዚሁ ልታደርጉላቸው ይገባል” ብሏል። (ማቴዎስ 7:12) ስለዚህ ሌሎች ወዳጃዊ ስሜት እንዲያሳዩህ ከፈለግህ አንተም እንደዚህ አድርግ። ሌሎች ለአንተ ግልጽ እንዲሆኑልህ ከፈለግህ አንተም ግልጽ ሁንላቸው። ሁሉም ሰው አንተ እንዳደረግከው ባያደርግልህም ከጊዜ በኋላ አንዳንዶች ጥሩ ምላሽ መስጠታቸው አይቀርም። እንዲህ ባያደርጉም እንኳ ጥረት ስላደረግህ ደስተኛ ትሆናለህ።

ኢየሱስ ብቸኝነትን ለመቋቋም የሚረዳ ልብ ሊባል የሚገባው ሌላ ሐቅ ተናግሯል፤ “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል” ብሏል። (የሐዋርያት ሥራ 20:35) ጊዜህን ሌሎችን ለመርዳት ብታውል ለምሳሌ አንድን ትንሽ ልጅ የቤት ሥራውን ብታሠራው ወይም አንድን አረጋዊ ገበያ በመሄድ፣ ቤታቸውን በማጽዳት አሊያም አትክልታቸውን በመንከባከብ ብታግዛቸው ደስታ የምታገኝ ከመሆኑም በላይ ምናልባትም እውነተኛ ወዳጅነት ልትመሠርት ትችላለህ።

ከሁሉ የሚበልጡ ወዳጆች ማፍራት

ብቸኝነትን ለመቋቋም የሚረዱ ሌሎች መንገዶች አሉ። ቤት ውስጥ ከመቀመጥ ይልቅ ወጣ በል። የሚቻል ከሆነ በእግርህ ወደ መናፈሻ ቦታዎች ሂድ ወይም ከከተማ ወጣ በል። በቤት ውስጥ ብቻህን በምትሆንበት ጊዜ ልብስ መስፋትን፣ የቤት ውስጥ ሥራ መሥራትን፣ የተበላሹ ነገሮችን መጠገንን ወይም ማንበብን በመሳሰሉ አእምሮን የሚያሠሩ ነገሮች ጊዜህን አስይዘው። አንድ ፈረንሳዊ ደራሲ “ለአንድ ሰዓት ያህል ሳነብ ጭንቀቴ ያልተወገደበት ጊዜ የለም” በማለት ጽፏል። ብዙ ሰዎች በተለይ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን የመዝሙር መጽሐፍ በማንበብ መጽናኛ አግኝተዋል።

ከእምነት አጋሮች ጋር መሰብሰብ ብቸኝነትን ለማሸነፍ ሊረዳና ለጤንነትም ቢሆን ጠቃሚ ሊሆን እንደሚችል ባለሙያዎች ተናግረዋል። ታዲያ ወርቃማውን ሕግ በተግባር ለማዋል ጥረት የሚያደርጉ ሰዎችን የት ልታገኝ ትችላለህ? ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴዎችን አስመልክቶ በተጻፈ አንድ መጽሐፍ ላይ አንድ ገለልተኛ ታዛቢ “[የይሖዋ] ምሥክሮች በራሳቸው ጉባኤ ውስጥ መተማመን የሰፈነበትና ማንም እንደተገለለ እንዲሰማው የማያደርግ እውነተኛ ማኅበረሰብ መሥርተዋል” ብለዋል።

ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ “በመካከላችሁ ፍቅር ካለ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ” ብሎ ሲናገር እውነተኛ ክርስቲያኖችን ለይቶ የሚያሳውቃቸውን ምልክት ገልጿል። (ዮሐንስ 13:35) በመጀመሪያ ለአምላክ፣ ቀጥሎም ለእምነት አጋሮች የሚገለጸው ይህ ፍቅር እውነተኛውን ሃይማኖት የያዙት ሰዎች ዋነኛ መለያ ነው።—ማቴዎስ 22:37-39

ከአምላክ ጋር ወዳጅነት መመሥረት ብቸኝነትን ለመቋቋም የሚረዳ ከሁሉ የተሻለ መንገድ ነው። አምላክ ጓደኛህ ከሆነ ፈጽሞ ብቸኝነት ሊሰማህ አይገባም!—ሮም 8:38, 39፤ ዕብራውያን 13:5, 6

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ብቸኝነትን ለመቋቋም የረዱኝ ነገሮች

አኒ፣ መበለት፦ “አስተሳሰቤን ለመቆጣጠርና ያለሁበት ሁኔታ የሚያስገኛቸውን መልካም ጎኖች ለማሰብ እጥራለሁ።”

ካርመን፣ ያላገባች፦ “ባለፈው ሕይወቴ ላይ ከማተኮር ይልቅ አዲስ ወዳጅነት በመመሥረት ወደፊት መጓዝን ተምሬያለሁ።”

ፈርናንድ፣ መበለት፦ “ሌሎችን ለመርዳት ጥረት የምታደርጉ ከሆነ የራሳችሁን ችግር ትረሳላችሁ።”

ዣን ፒየር፣ ያላገባ፦ “አዘውትሬ ረጅም የእግር ጉዞ የማደርግ ሲሆን በዚህ ወቅት ለአምላክ የልቤን ግልጥልጥ አድርጌ በጸሎት እነግረዋለሁ።”

በርናርድ፣ ሚስቱ የሞተችበት፦ “ከጓደኞቼ ጋር አዘውትሬ በስልክ አወራለሁ፤ ይህን የማደርገው አሳዛኝ ትዝታዎችን ለማስታወስ ሳይሆን ከእነሱ ጋር መጫወት ደስ ስለሚለኝ ነው።”

ዴቪድ፣ ያላገባ፦ “በተፈጥሮዬ ለብቻዬ መሆን ደስ የሚለኝ ቢሆንም ከሌሎች ጋር ለማውራት ልዩ ጥረት አደርጋለሁ።”

ሎሬና፣ ያላገባች፦ “ቅድሚያውን ወስጄ ሰዎችን ለመቅረብና ጓደኝነት ለመመሥረት እጥራለሁ።”

አቢጋኤል፣ ዕድሜ 15፦ “በዕድሜ ከሚበልጡኝ ጓደኞቼ ጋር ጊዜ በማሳለፍ ከተሞክሯቸው እጠቀማለሁ።”

ቼሪ፣ ያላገባች፦ “ለሰዎች ብቸኝነት እንደሚሰማችሁ ከነገራችኋቸው ለእናንተ ወዳጃዊ ስሜት ለማሳየት ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርጉ ተገንዝቤያለሁ።”

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ብቸኝነትን ለመቋቋም የሚረዱ እርምጃዎች

አዎንታዊ አመለካከት አዳብር

ብቻህን እንድትሆን ሊያደርጉ በሚችሉ እንደ ቴሌቪዥን ባሉ መዝናኛዎች ላይ ገደብ አብጅ

ትልቅ ቦታ የምትሰጣቸውን ነገሮች የሚያደንቁ ወዳጆች (እኩዮችህ ባይሆኑም እንኳ) ለማግኘት ጥረት አድርግ

ከሁሉ በላይ ከአምላክ ጋር ወዳጅነት ለመመሥረት ጥረት አድርግ

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የዕድሜ እኩዮችህ ካልሆኑ ሰዎች ጋር ወዳጅነት መሥርት