በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በጭንቀት ከመዋጥ መገላገል የምችለው እንዴት ነው?

በጭንቀት ከመዋጥ መገላገል የምችለው እንዴት ነው?

የወጣቶች ጥያቄ

በጭንቀት ከመዋጥ መገላገል የምችለው እንዴት ነው?

“ጓደኞቼ ችግር ሲያጋጥማቸው ፈጥኜ በመድረስ መፍትሔ እንዲያገኙና እንዲረጋጉ እረዳቸዋለሁ። ወደ ቤቴ ከተመለስኩ በኋላ ግን መኝታ ክፍሌ ገብቼ አለቅሳለሁ፤ ይህን የሚያውቁት ጥቂት ሰዎች ብቻ ናቸው።”—ኬሊ*

በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንድ ስሞች ተቀይረዋል።

“በጭንቀት በምዋጥበት ጊዜ ራሴን ከሰዎች አገላለሁ። የተጋበዝኩበት ቦታ ካለ ላለመሄድ ሰበብ እፈጥራለሁ። ቤተሰቦቼ እንዳይነቁብኝ ለማድረግ ብዙ ስለምጥር ችግር እንዳለብኝ አይሰማቸውም።”—ሪክ

ሊ ወይም ሪክ የተሰማቸው ዓይነት ስሜት ተሰምቶህ ያውቃል? ከሆነ፣ ችግር አለብኝ ብለህ ለመደምደም አትቸኩል። እውነቱን ለመናገር፣ ሁሉም ሰው አልፎ አልፎ መጨነቁ አይቀርም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ታማኝ ወንዶችና ሴቶችም እንኳ እንዲህ ያለ ስሜት ተሰምቷቸው ያውቃል።

በጭንቀት የተዋጥክበትን ምክንያት የምታውቅበት ጊዜ ሊኖር ቢችልም አንዳንድ ጊዜ ግን ግራ ሊገባህ ይችላል። “በጭንቀት የምትዋጠው የግድ አስከፊ ሁኔታ ሲደርስብህ ብቻ አይደለም” በማለት የ19 ዓመቷ አና ትናገራለች። “በማንኛውም ጊዜ ሌላው ቀርቶ ምንም ችግር ሳይኖርብህም ጭምር በጭንቀት ልትዋጥ ትችላለህ። የማይመስል ሊሆን ይችላል፤ ግን የሚያጋጥም ነገር ነው!”

ያስጨነቀህ ነገር ምንም ይሁን ምን ሌላው ቀርቶ የተጨነቅከው አለምንም ምክንያት እንደሆነ ቢሰማህም እንኳ እንዲህ ዓይነቱን ሁኔታ ለማሸነፍ ምን ማድረግ ትችላለህ?

ጠቃሚ ምክር 1፦ ስሜትህን አውጥተህ ተናገር። መጽሐፍ ቅዱስ “ወዳጅ ምንጊዜም ወዳጅ ነው፤ ወንድምም ለክፉ ቀን ይወለዳል” ይላል።—ምሳሌ 17:17

ኬሊ፦ “ለሆነ ሰው ስሜቴን አውጥቼ ከተናገርኩ ትልቅ እፎይታ አገኛለሁ። ቢያንስ አሁን፣ ስላለሁበት ሁኔታ የሚያውቁ ሰዎች አሉ። አስፈላጊውን እርዳታ በመስጠት ከወደቅሁበት አዘቅት ጎትተው ሊያወጡኝ ስለሚችሉ በቃ ዳንኩኝ ማለት ነው!”

የመፍትሔ ሐሳብ፦ በጭንቀት በምትዋጥበት ጊዜ ልታዋየው የምትችለውን የአንድ ‘ወዳጅህን’ ስም በክፍት ቦታው ላይ ጻፍ።

․․․․․

ጠቃሚ ምክር 2፦ ስሜትህን በጽሑፍ አስፍረው። የተሰማህ ጭንቀት ለሕይወት ባለህ አመለካከት ላይ መጥፎ ተጽዕኖ በሚያሳድርበት ጊዜ ስሜትህን በጽሑፍ ማስፈርህ ሊረዳህ ይችላል። ዳዊት በመንፈስ አነሳሽነት በጻፋቸው መዝሙሮች ላይ የተሰማውን ከፍተኛ ጭንቀት የገለጸባቸው ጊዜያት ነበሩ። (መዝሙር 6:6) ስሜትህን በጽሑፍ ማስፈርህ “ትክክለኛ ፍርድንና አስተውሎ መለየትን” እንድትጠብቅ ሊረዳህ ይችላል።—ምሳሌ 3:21

ሄዘር፦ “ስሜቴን በጽሑፍ ማስፈሬ ጭንቀቱ የፈጠረብኝን በአእምሮዬ የሚጉላሉ የተዘበራረቁ ሐሳቦችን መስመር ለማስያዝ ይረዳኛል። ስሜትህን አውጥተህ መግለጽና በጭንቀት እንድትዋጥ ያደረገህን ምክንያት መረዳት ከቻልክ ጭንቀትህ ይቀንስልሃል።”

የመፍትሔ ሐሳብ፦ አንዳንዶች የዕለት ውሏቸውን በማስታወሻ ላይ መመዝገብ ይመርጣሉ። አንተም እንዲህ ለማድረግ ካሰብክ ስለ ምን ነገር ልትጽፍ ትችላለህ? በጭንቀት በምትዋጥበት ጊዜ፣ በውስጥህ የሚሰማህን ስሜትና ለጭንቀትህ መንስኤ ሊሆን ይችላል ብለህ ያሰብከውን ነገር ጻፍ። ከአንድ ወር በኋላ የጻፍከውን ነገር አንብበው። ለጉዳዩ የነበርህ ስሜት ተለውጧል? ከሆነ የረዳህ ነገር ምን እንደሆነ ጻፍ።

ጠቃሚ ምክር 3፦ ስለ ጉዳዩ ጸልይ። ስለሚያሳስብህ ነገር የምትጸልይ ከሆነ ‘ከማሰብ ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም ልብህንና አእምሮህን እንደሚጠብቅ’ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።—ፊልጵስዩስ 4:7

ኤስተር፦ “በትካዜ የምዋጥበትን ምክንያት ለመረዳት ብሞክርም ላውቀው አልቻልኩም ነበር። ደስተኛ እንድሆን እንዲረዳኝ ይሖዋን ለመንኩት። አለምንም ምክንያት ዝም ብዬ መጨነቄ ያበሳጨኝ ነበር። በመጨረሻ ግን ከመጨነቅ አባዜ ተገላገልኩ። የጸሎትን ኃይል አቅልላችሁ አትመልከቱ!”

የመፍትሔ ሐሳብ፦ ወደ ይሖዋ በምትጸልይበት ጊዜ መዝሙር 139:23, 24ን እንደ ናሙና ተጠቀምበት። ለይሖዋ የውስጥህን አውጥተህ ንገረው፤ እንዲሁም የጭንቀትህን መንስኤ ለይተህ ለማወቅ እንዲረዳህ ጠይቀው።

ከላይ ከተጠቀሱት የመፍትሔ ሐሳቦች በተጨማሪ የአምላክ ቃል ከፍተኛ እርዳታ ሊያበረክትልህ ይችላል። (መዝሙር 119:105) መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ አእምሮህን በሚያንጹ ሐሳቦች መሙላትህ በአስተሳሰብህ፣ በስሜትህና በድርጊትህ ላይ አዎንታዊ ውጤት ሊኖረው ይችላል። (መዝሙር 1:1-3) የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ስሜት ቀስቃሽና አስደሳች ዘገባዎችን ይዟል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚያበረታቱ ታሪኮች የሚገኙባቸውን ሌሎች ቦታዎች ለማወቅ፣ በይሖዋ ምሥክሮች ከተዘጋጀው ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 2 ከተሰኘው መጽሐፍ ላይ “አርዓያ የሚሆኑ ሰዎች” የተጠቀሱባቸውን ዘጠኝ ገጾች መመልከት ትችላለህ። በእነዚህ ገጾች ላይ ታሪካቸው ከቀረበው ሰዎች መካከል ዮሴፍ፣ ሕዝቅያስ፣ ሊዲያና ዳዊት ይገኙበታል። በገጽ 227 ላይ ደግሞ ሐዋርያው ጳውሎስም እንኳ ፍጹም ባለመሆኑ ምክንያት አንዳንድ ጊዜ ያስቸግረው የነበረውን አፍራሽ ስሜት እንዴት እንዳሸነፈ ማንበብ ትችላለህ።

ብዙ ጥረት ብታደርግም ከጭንቀት መላቀቅ ቢያቅትህስ?

ከጭንቀት መላቀቅ ሲያቅትህ

“አንዳንድ ጊዜ ጠዋት ስነሳ ቀኑን ያለምንም ዓላማ ከማሳልፍ ተኝቼ ብውል እንደሚሻለኝ ይሰማኛል” በማለት ራያን ይናገራል። ራያን ከባድ የመንፈስ ጭንቀት ያለበት ሲሆን የዚህ በሽታ ተጠቂ እሱ ብቻ አይደለም። ከ4 ወጣቶች መካከል 1ዱ ለአካለ መጠን ከመድረሱ በፊት የመንፈስ ጭንቀት እንደሚይዘው ጥናቶች ያመለክታሉ።

ታዲያ የመንፈስ ጭንቀት ይዞህ እንደሆነ እንዴት ማወቅ ትችላለህ? ከመንፈስ ጭንቀት ምልክቶች መካከል በግልጽ የሚታይ የስሜትና የጠባይ መለዋወጥ፣ ራስን ማግለል፣ በየትኛውም ዓይነት የሕይወት እንቅስቃሴ ማለት ይቻላል የሥራ ፍላጎት ማጣት፣ በጉልህ የሚታይ የአመጋገብና የእንቅልፍ መዛባት እንዲሁም ሥር የሰደደ የዋጋ ቢስነት ስሜት ወይም መሠረተ ቢስ የጥፋተኝነት ስሜት ይገኙበታል።

ከላይ ከተጠቀሱት መካከል አንዱ ወይም ከዚያ በላይ የሆኑት ምልክቶች በማንኛውም ሰው ላይ ሊታዩ የሚችሉባቸው ጊዜያት እንዳሉ ምንም ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ ምልክቶቹ ከሁለት ሳምንት በላይ ከቀጠሉ ወላጆችህ እንዲያስመረምሩህ ለምን አትነግራቸውም? የሚመረምርህ ሐኪም፣ የያዘህ ጭንቀት ሕክምና የሚያስፈልገው መሆን አለመሆኑን ለይተህ እንድታውቅ ሊረዳህ ይችል ይሆናል። *

የመንፈስ ጭንቀት ይዞህ ከሆነ ልትሸማቀቅ አይገባም። በዚህ በሽታ የተያዙ ብዙ ሰዎች ባገኙት የሕክምና እርዳታ ጤንነታቸው የተሻሻለ ሲሆን ምናልባትም ለብዙ ጊዜ ተሰምቷቸው የማያውቅ ጥሩ ስሜት ሳይሰማቸው አልቀረም! ለጭንቀትህ መንስኤ የሆነው ነገር የመንፈስ ጭንቀት ሆነም አልሆነ፣ በመዝሙር 34:18 ላይ የሚገኙትን ይሖዋ “ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፤ መንፈሳቸው የተሰበረውንም ያድናቸዋል” የሚሉትን አጽናኝ ቃላት አስታውስ።

www.watchtower.org/ype በሚለው ድረ ገጽ ላይ “Young People Ask” በሚለው አምድ ሥር ተጨማሪ ርዕሶችን ማግኘት ይቻላል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.24 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንድ ስሞች ተቀይረዋል።

አንዳንድ ወጣቶች የሚሰማቸው ጭንቀት ለረጅም ጊዜ ሲቆይባቸው ሕይወታቸውን ስለማጥፋት ያስባሉ። አንተም ተመሳሳይ ሐሳብ ከመጣብህ ለምትተማመንበት አንድ ትልቅ ሰው ሳትዘገይ ተናገር።—የግንቦት 2008 ንቁ! ከገጽ 26-28ን ተመልከት።

ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች

ማልቀስ ጥቅም ይኖረዋል?

“በቀላሉ የማለቅስ ሰው አልነበርኩም፤ አሁን ግን በጭንቀት በተዋጥኩ ቁጥር የግድ ማልቀስ አለብኝ። እስኪወጣልኝ ድረስ ካለቀስኩ ስሜቴ ይረጋጋል። ከዚያ በኋላ በምክንያታዊነት ማሰብ ብሎም ስለ ወደፊቱ ጊዜ ብሩሕ አመለካከት መያዝ እችላለሁ።”—ሊያን

ጭንቀትህን እንድትቋቋም ሌሎች ሊረዱህ የሚችሉት እንዴት ነው?

“በጭንቀት በምዋጥበት ጊዜ ራሴን ከማግለል መቆጠብ አለብኝ። ውስጤን ለማዳመጥ ምናልባትም እስኪወጣልኝ ለማልቀስ ብቻዬን መሆን ሊያስፈልገኝ ይችላል። ከዚያ በኋላ ግን ጭንቀቴን እንድረሳው ከሰዎች ጋር መሆን እንደሚያስፈልገኝ አውቃለሁ።”—ክሪስቲን

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

እኩዮችህ ምን ይላሉ?

አብዛኛውን ጊዜ በጭንቀት የምዋጠው ስለ ራሴ ብዙ ሳስብ ነው። በመሆኑም ሌሎችን በመርዳት የትኩረቴን አቅጣጫ እቀይራለሁ፤ ይህ ደግሞ ደስታዬን መልሼ እንዳገኝ ያስችለኛል።

አዘውትሬ ስፖርት መሥራቴ ለራሴ ጥሩ ስሜት እንዲኖረኝ ስለሚያስችለኝ አፍራሽ የሆኑ ስሜቶች ይቀንሱልኛል። ከዚህም በላይ ስፖርት በምሠራበት ጊዜ በጣም ስለሚደክመኝ መጥፎ ሐሳቦችን ለማስተናገድ አቅሙ አይኖረኝም!

[ሥዕሎች]

ድሬኔል

ሬቤካ

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጥረት ካደረግህ ብሎም የሌሎችን እርዳታ የምትቀበል ከሆነ ከገባህበት የጭንቀት አዘቅት መውጣት ትችላለህ