ብቸኝነት—መንስኤውን ለይቶ ማወቅ
ብቸኝነት—መንስኤውን ለይቶ ማወቅ
የብቸኝነት ስሜት ለብቻ ለመሆን ከመፈለግ የተለየ ነው። የብቸኝነት ስሜት ሲባል ጓደኛ ለማግኘት እየጓጉ ብቸኛ መሆንን ያመለክታል። በሌላ በኩል ግን ለብቻ ለመሆን መፈለግ ሲባል አንድ ሰው በራሱ ፍላጎት ከሌሎች ጋር ያለውን ግንኙነት መገደቡን ይጠቁማል።
ስለዚህ ለብቻ መሆን አንዳንድ ጊዜ የሚፈለግ ነገር ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳደረገው ብዙዎች ለብቻቸው መሆን የሚፈልጉት ለመጸለይ ወይም ለማሰላሰል ሲሉ ነው። (ማቴዎስ 14:13፤ ሉቃስ 4:42፤ 5:16፤ 6:12) በሌላ በኩል ግን ብቸኝነት የሚያሠቃይ ስሜት ነው። ለብቸኝነት ስሜት መንስኤ የሚሆኑ ነገሮች ምን ሊሆኑ ይችላሉ?
● በሕዝብ በተጨናነቀ ከተማ ብቸኛ መሆን
በትልልቅ ከተሞች በሺህ አልፎ ተርፎም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ቅርብ ለቅርብ ሆነው ይኖራሉ። የሚገርመው ግን ሰዎች እንደዚህ በሕዝብ ተከበው መኖራቸው በሰፊው ለተዛመተው ብቸኝነት ምክንያት ሆኗል። የከተማ ኑሮ ወከባ ብዙዎች ከጎረቤቶቻቸው ጋር እንዳይተዋወቁ ሊያግዳቸው ይችላል። በመሆኑም የከተማ ነዋሪዎች በባዕድ ሰዎች ተከበው ይኖራሉ። በማይተዋወቁ ሰዎች መካከል የሚታየው አለመተማመንና ሰዎች በግል ሕይወታቸው ሌሎች ጣልቃ እንዳይገቡባቸው መፈለጋቸው በትልልቅ ከተሞች ውስጥ ለብቸኝነት መስፋፋት ትልቅ ሚና ይጫወታሉ።
● ሠራተኞችን ደግነት በጎደለው መንገድ መያዝ
ብዙ ትልልቅ የንግድ ድርጅቶችና ኢንዱስትሪዎች የሚተዳደሩበት መንገድ በሁሉም ደረጃ ያሉ ሠራተኞቻቸው ብቸኝነት እንዲያድርባቸውና ብቃት እንደሌላቸው እንዲሰማቸው አድርጓል። ብዙውን ጊዜ ሠራተኞች ፋታ የሌለው ጫና ስለሚደርስባቸው ሁልጊዜ ውጥረት ይሰማቸዋል።
ከዚህም በላይ በትልልቅ ኩባንያዎች ውስጥ የሚታየው ሠራተኞችን በየጊዜው የማዘዋወር ሂደት በሠራተኞቹ ላይ የስጋት፣ የመገለልና የብቸኝነት ስሜት ይፈጥራል። ኢንተርናሽናል ሄራልድ ትሪቢዩን የተሰኘው ጋዜጣ በአንዳንድ የፈረንሳይ ኮርፖሬሽኖች ውስጥ ስለተዛመተው ራስን የመግደል አባዜ አስተያየት ሲሰጥ ብዙ የፈረንሳይ ሠራተኞች “ኢኮኖሚው በፍጥነት የሚለዋወጥ በመሆኑ የተነሳ ከአቅማቸው በላይ ጫና እንደሚደረግባቸው” እንደሚሰማቸው ገልጿል።
● ስሜት አልባ ግንኙነት
ቴትሱሮ ሳይቶ የተባሉ በጃፓን የሚኖሩ ፕሮፌሰር እንዲህ ብለዋል፦ “አሁን አሁን ሞባይል ስልኮችና ሌሎች መሣሪያዎች ሰዎች ተቀራርበው ስሜታቸውን እንዳይገልጹ እንቅፋት በመሆናቸው የሐሳብ ልውውጥ የማድረግ ችሎታ እያሽቆለቆለ መሄዱ አይቀርም።” በአውስትራሊያ የሚታተመው ዘ ሰንዴይ ቴሌግራፍ እንዲህ ሲል ዘግቧል፦ “ቴክኖሎጂ . . . ሰዎችን ይበልጥ እያራራቃቸው ነው። ሰዎች . . . እርስ በርስ ከመነጋገር ይልቅ በኢሜይል ወይም በስልክ አማካኝነት መልእክት ይለዋወጣሉ።”
በፈረንሳይ የምትኖረው የ21 ዓመቷ ሪቼል ብቸኝነት እንዲሰማት ምክንያት የሆነውን ነገር ስትገልጽ እንዲህ ብላለች፦ “ሰዎች በስልክም ሆነ በኢንተርኔት የጽሑፍ መልእክት መለዋወጥ በቂ እንደሆነ ስለሚያምኑ በአካል ለመገናኘት እምብዛም ጥረት አያደርጉም። ይህ ግን ይበልጥ ብቸኝነት እንዲሰማኝ አድርጎኛል።”
● የመኖሪያ አካባቢ መቀየር
የኢኮኖሚ ቀውስ ሰዎች ከሥራ ገበታቸው ላለመፈናቀል ወይም ሥራ ለማግኘት ሲሉ ከቦታ ወደ ቦታ እንዲዘዋወሩ ስለሚያስገድዳቸው በየጊዜው መኖሪያቸውን ይቀያይራሉ። የመኖሪያ አካባቢ መቀየር ደግሞ ሰዎችን ሳይወዱ ከጎረቤቶቻቸው፣ ከጓደኞቻቸው፣ ከትምህርት ቤታቸውና አንዳንድ ጊዜም ከቤተሰባቸው እንዲርቁ ያደርጋቸዋል። በዚህ መንገድ አካባቢ የቀየሩ ሰዎች፣ ካለበት ቦታ ተነቅሎ ወደ ሌላ ቦታ ሲዛወር ሥሮቹ የቀድሞው ቦታ እንደቀሩ ተክል የሆኑ ያህል ይሰማቸዋል።
ፍራንሲስ ከጋና ወደ ፈረንሳይ የሄደበትን ቀን አይረሳውም። እንዲህ ይላል፦ “ቋንቋውን አለመቻሌ፣ ጓደኛ ማጣቴና ቀዝቃዛው የአየር ጠባይ አንድ ላይ ተዳምረው ከፍተኛ የብቸኝነት ስሜት እንዲያድርብኝ አደረጉ።”
ቤጃት፣ ስደተኛ ሆና እንግሊዝ የሄደችበትን ጊዜ በማስታወስ እንዲህ ብላለች፦ “ከአካባቢው ባሕል ጋር መላመድ አስቸጋሪ ሆኖብኝ ነበር። የማውቃቸው ሰዎች ቢኖሩም ሐሳቤን የማወያየውና ስሜቴን አውጥቼ የምነግረው እውነተኛ ጓደኛም ሆነ ቤተሰብ አልነበረኝም።”
● የሚወዱትን ሰው በሞት መነጠቅ
የትዳር ጓደኛ ሞት በሕይወት ባለው የትዳር ተጓዳኝ ሕይወት ውስጥ ትልቅ ክፍተት ይፈጥራል። በተለይም ደግሞ አንድ ሰው የትዳር ጓደኛውን ለረጅም ጊዜ ሲያስታምም ቆይቶ የትዳር አጋሩ በሞት ሲለየው የዚህ ዓይነት ሁኔታ መፈጠሩ አይቀርም። ብዙውን ጊዜ ግለሰቡ ከፍተኛ የባዶነት ስሜት ያድርበታል።
በፓሪስ የምትኖረው ፈርናንድ የተባለች ባሏ የሞተባት ሴት “ከምንም በላይ የከበደኝ ነገር በጣም ለምቀርበው ጓደኛዬ ማለትም ለባለቤቴ ከእንግዲህ ሚስጥሬን ማካፈል የማልችል መሆኑ ነው” በማለት ተናግራለች። አኒ ደግሞ “በተለይ የጤና ችግሮችን ወይም ሌሎች ጉዳዮችን በሚመለከት
አስፈላጊ የሆነ ውሳኔ ማድረግ” በሚኖርባት ጊዜ ባለቤቷ ከጎኗ ባለመሆኑ ይበልጥ እንደሚሰማት ገልጻለች።● ፍቺ፣ መለያየት፣ ነጠላነት
መፋታት ወይም መለያየት ብዙውን ጊዜ የብቸኝነትና የእርባና ቢስነት ስሜትን ትቶ ያልፋል። ባለሙያዎች ቀደም ሲል ያስቡት ከነበረው ይበልጥ አብዛኛውን ጊዜ በዚህ ሁኔታ በጣም የሚጎዱት ልጆች ናቸው። አንዳንድ ባለሙያዎች፣ ወላጆቻቸው የተፋቱባቸው ልጆች አዋቂዎች ሲሆኑ በብቸኝነት የመጠቃት አጋጣሚያቸው ከፍ ያለ እንደሆነ ያምናሉ።
ተስማሚ የትዳር ጓደኛ ሊያገኙ ባለመቻላቸው ምክንያት ያላገቡ ሰዎችም አልፎ አልፎ ብቸኝነት የሚሰማቸው መሆኑ የተለመደ ነው። በተለይ ደግሞ ሌሎች “ለምን አታገባም?” እንደሚለው ያሉ አሳቢነት የጎደላቸው አስተያየቶችን ሲሰነዝሩ የብቸኝነት ስሜቱ ሊባባስባቸው ይችላል።
ነጠላ ወላጆችም ብቸኝነት ይሰማቸዋል። ወላጅ መሆን አስደሳች ቢሆንም ችግሮችም አሉት፤ ነጠላ ወላጆች የሚያማክሩት የትዳር ጓደኛ ስለሌላቸው እነዚህን ችግሮች ብቻቸውን መፍታት ይኖርባቸዋል።
● እርጅናና የወጣትነት ጊዜ
አረጋውያን፣ በቤተሰባቸው አባላት ችላ ባይባሉም እንኳ ብዙውን ጊዜ ብቸኝነት ሊሰማቸው ይችላል። ዘመዶቻቸውና ጓደኞቻቸው አልፎ አልፎ ሊጠይቋቸው ቢችሉም ማንም ሰው ሳይጠይቃቸው የሚያልፉ ቀናት ምናልባትም ሳምንታት ሊኖሩ ይችላሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ ወጣቶችም ብዙውን ጊዜ ብቸኝነት ያጠቃቸዋል። ብዙዎች ቴሌቪዥን መመልከት፣ የቪዲዮ ጨዋታዎችን መጫወት፣ በኮምፒውተራቸው ላይ ብዙ ሰዓት ማሳለፍና እነዚህን የመሳሰሉት ብቻቸውን እንዲሆኑ የሚያደርጓቸው መዝናኛዎች ሱስ ሆነውባቸዋል።
ታዲያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰ ለሚሄደው ለዚህ ችግር መፍትሔ ማግኘት ይቻላል? ብቸኝነትን መቋቋም የሚቻለው እንዴት ነው?
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ ]
“ቋንቋውን አለመቻሌ፣ ጓደኛ ማጣቴና ቀዝቃዛው የአየር ጠባይ አንድ ላይ ተዳምረው ከፍተኛ የብቸኝነት ስሜት እንዲያድርብኝ አደረጉኝ”