በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

አንድ ጥናት እንዳመለከተው ከ15 እስከ 64 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ብራዚላውያን ወንዶች መካከል 10.3 በመቶ የሚሆኑት ባለፉት 12 ወራት ውስጥ በኢንተርኔት ከተዋወቁት ቢያንስ ከአንድ ሰው ጋር የፆታ ግንኙነት ፈጽመዋል።—የብራዚል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር

የአርክቲክ ውቅያኖስ እስከ 80 ሜትር የሚደርስ ጥልቀት ባለው ሰፊ የበረዶ ንጣፍ የተሸፈነ ነበር። አሁን ግን “ለበርካታ ዓመታት ሲነባበር የቆየው . . . [ይህ] የበረዶ ንጣፍ ሙሉ በሙሉ ጠፍቷል ለማለት ይቻላል፤ ይህ የበረዶ መቅለጥ ሰሜናዊውን ዋልታ በቀላሉ በመርከብ ለማቋረጥ እስከሚቻልበት ደረጃ የደረሰ መሆኑ በእጅጉ ያስደነግጣል።”—የሮይተርስ ዜና አገልግሎት፣ ካናዳ

ሞስኮና ቫቲካን ሙሉ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መመሥረታቸውን አስታውቀዋል።—ሪያ ኖቮስቲ፣ ሩሲያ

ከአፍሪካ በከፍታው አንደኛ የሆነው የኪሊማንጃሮ ተራራ “ከ2000 እስከ 2007 ባሉት ዓመታት ከነበረው የበረዶ ሽፋን 26 በመቶ የሚሆነውን አጥቷል።”—ዴይሊ ኔሽን፣ ኬንያ

የራሱን ሕይወት የሚመራ ማኅበረሰብ

ተመራማሪዎች እንደሚሉት የብሪታንያን ሕዝብ ያህል “በግል ሕይወት ላይ ያተኮረና ከማኅበረሰቡ ይልቅ ራሱን የሚያስቀድም ኅብረተሰብ በዓለም ላይ የለም” ሲል የለንደኑ ዴይሊ ቴሌግራፍ ዘግቧል። ሌላ ጥናት ደግሞ የብሪታንያ ሕዝብ በከባድ የመንፈስ ጭንቀት እንደሚሠቃይ ዘግቧል። አንዳንድ ባለሙያዎች፣ ሕዝቡ በግል ሕይወት ላይ ያተኮረ የአኗኗር ዘይቤ መከተሉ በመንፈስ ጭንቀት ከመጠቃቱ ጋር ተያያዥነት እንዳለው ያምናሉ። በምዕራቡ ዓለም የሚኖሩትን ማኅበረሰቦች እንደ ቻይናና ታይዋን ባሉ አገሮች ከሚገኙ ማኅበረሰቦች ጋር የሚያወዳድሩ ጥናቶች ተካሂደዋል። እንደ ቻይናና ታይዋን ባሉት አገሮች ከግል ሕይወት ይልቅ ለማኅበራዊ ሕይወት ትልቅ ቦታ መሰጠቱ ሰዎችን ከአእምሮ መታወክ የጠበቃቸው ይመስላል። በምዕራቡ ዓለም ያለው “ራስ ወዳድ የሆነ ማኅበረሰብ . . . በመንፈስ ጭንቀት እንድንዋጥ እያደረገን ነው” ብሏል ዴይሊ ቴሌግራፍ።

የስዊድን ቤተ ክርስቲያን ተመሳሳይ ፆታ ያላቸውን ሰዎች ጋብቻ ፈቀደች

በጥቅምት 2009 የስዊድን ሉተራን ቤተ ክርስቲያን ተመሳሳይ ፆታ ያላቸው ሰዎች ጋብቻ በቤተ ክርስቲያን እንዲከናወን ፈቅዳለች። ይህ ውሳኔ የተደረገው ከጥቂት ወራት በፊት የስዊድን ፓርላማ ያወጣውን ሕግ ተከትሎ ነው፤ ፓርላማው ተመሳሳይ ፆታ ባላቸው ሰዎች መካከል የሚደረግ ጋብቻን የሚፈቅድ ሕግ አጽድቆ ነበር። ዳገንዝ ኑዌሄተ የተባለው ጋዜጣ “የስዊድን ቤተ ክርስቲያን፣ ጋብቻ በወንድና በሴት መካከል የሚደረግ ጥምረት ነው ከሚለው የተለመደ አመለካከት ለማፈንገጥ የመጀመሪያ ከሆኑት ዋነኞቹ አብያተ ክርስቲያናት አንዷ ሆነች ማለት ነው” ብሏል።

ሕፃናት የሚያለቅሱት በምን ቋንቋ ነው?

ሕፃናት ከተወለዱ ከሁለተኛው ቀን አንስቶ ከአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ጋር በሚመሳሰል ቅላጼ እንደሚያለቅሱ የጀርመኑ ቩርስቡርግ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ገልጸዋል። ተመራማሪዎች የ30 ፈረንሳውያንና የ30 ጀርመናውያን ጨቅላ ሕፃናትን ለቅሶ ቀድተው የድምፁን ቃና እንዲሁም ቅጥነትና ውፍረቱን ብሎም ዜማውን መርምረዋል። የፈረንሳውያን ሕፃናት ለቅሶ ወፈር ብሎ ይጀምርና እየቀጠነ ሲሄድ የጀርመኖቹ ሕፃናት ደግሞ ቀጠን ብሎ ይጀምርና እየወፈረ ይሄዳል። የሁለቱም አገሮች ሕፃናት አለቃቀስ የወላጆቻቸውን ቋንቋ ቅላጼ የተከተለ ነው። ስለሆነም የሕፃናት የቋንቋ ችሎታ መዳበር የሚጀምረው በማህፀን ውስጥ እንደሆነ እንዲሁም አንድ ሕፃን መናገር የሚጀምረው ማልቀስ ሲጀምር እንደሆነ ይታመናል።