በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የምዕራባዊው ንፍቀ ክበብ “የአራዊት ንጉሥ”

የምዕራባዊው ንፍቀ ክበብ “የአራዊት ንጉሥ”

የምዕራባዊው ንፍቀ ክበብ “የአራዊት ንጉሥ”

የትኛው አውሬ ይሆን? በሰሜን፣ በደቡብና በመካከለኛው አሜሪካ ከሚገኙት የድመት ዝርያ ያላቸው አራዊት በሙሉ ትልቁ የሆነው ጃጓር ነው። ጃጓር የሚኖረው የት ነው? በደቡብና በመካከለኛው አሜሪካ በሚገኙ ጫካዎች፣ ረግረጋማ ቦታዎች፣ ደኖች፣ በረሃዎችና ቁጥቋጦ የሚበዛባቸው አካባቢዎች ይኖራል። ይህ እንስሳ ከሌሎቹ የድመት ዝርያዎች በተለየ መሬት ላይ ወይም ዛፍ ላይ ብቻ ሳይሆን ውኃ ውስጥ መሆንም ያስደስተዋል።

እድገቱን ከጨረሰ አንድ ተባዕት ጃጓር አጠገብ እንደቆምክ አድርገህ አስብ። ጅራቱን ሳይጨምር ርዝመቱ እስከ ሁለት ሜትር ሊደርስ ክብደቱ ደግሞ ከ120 ኪሎ ግራም ሊበልጥ ይችላል። ጃጓር ለብቻው መኖርን የሚመርጥ እንስሳ በመሆኑ ከወገኖቹ ጋር የሚገናኘው የመራቢያው ወቅት ሲደርስ ብቻ ነው። አንድ ተባዕት ጃጓር ግንኙነት ለመፈጸም ዝግጁ የሚሆነው ሦስት ወይም አራት ዓመት ሲሞላው ሲሆን እንስቷ ግን ከሁለት ዓመቷ ጀምሮ መውለድ ትችላለች። ከሦስት እስከ አራት ወር ያህል ከሚቆየው የእርግዝና ወቅት በኋላ አብዛኛውን ጊዜ መንታ ግልገሎችን ትወልዳለች። አንዳንድ ጃጓሮች በአራዊት መጠበቂያ ስፍራዎች ውስጥ ከ20 ዓመት በላይ ሊኖሩ እንደሚችሉ ታውቋል።

የሥነ ሕይወት ተመራማሪ የሆኑ አንድ ግለሰብ እነዚህ ትልልቅ የድመት ዝርያዎች ስላላቸው የመሰወር ችሎታ ሲናገሩ “ጃጓሮችን ማግኘት በጣም አስቸጋሪ ነው! አጠገቡ ቆሜ እንኳን . . . ሳላየው ልቀር እችላለሁ” ብለዋል። ቆዳው ቀለበት የመሰሉ ጥቋቁር ጌጦች የተረጩበት ወርቃማና ዳለቻ ቀለም ያለው መሆኑ ጥላ ውስጥ ገብቶ በቀላሉ እንዲሰወር ያስችለዋል።

ድምፁን አጥፍቶ ብቻውን የሚያድን

የተዋጣለት አዳኝ የሆነው ጃጓር ታፒሮችን፣ አጋዘኖችንና ጦጣዎችን ጨምሮ 85 የእንስሳት ዝርያዎችን ይመገባል። ጃጓር ውኃ ላይ መሆን ስለሚያስደስተው ዓሦችንና የባሕር ኤሊዎችንም እያደነ ይበላል። በአንድ ወቅት ሰዎች አንድ ጃጓር ትልቅ ፈረስ ገድሎ 80 ሜትር ያህል መሬት ለመሬት እየጎተተ ከወሰደው በኋላ ወንዝ ጋር ሲደርስ አሁንም እየጎተተ ከወንዙ ማዶ ሲያሻግረው ተመልክተዋል።

ይህ ብልህ የድመት ዝርያ የሚያድነውን እንስሳ ዛፍ ላይ ሆኖ አድብቶ ይጠብቃል። ከአናቱ አድብቶ የሚጠብቅ እንስሳ እንዳለ ያላወቀው ፈጣን የከርከሮ ዝርያ የሆነው የፔካሪ መንጋ በዛፉ ሥር ሲያልፍ ጃጓሩ ዘሎ አንዱ ላይ ጉብ ይላል፤ በአንድ ኃይለኛ ንክሻ እንስሳውን ከገደለው በኋላ በፍጥነት ተመልሶ ዛፉ ላይ ይወጣል። ከዚያም የቀረው መንጋ አልፎ እስኪሄድ ድረስ ዛፉ ላይ ከቆየ በኋላ ወርዶ ግዳዩን ይወስዳል።

ይሁንና የድመት ዝርያ ካላቸው አራዊት ሁሉ ሰዎችን እምብዛም የማያጠቃው ጃጓር ነው፤ እንዲያውም ሰው በሊታ ከሆኑ አራዊት ተርታ ተመድቦ አያውቅም። እንደ እውነቱ ከሆነ ጃጓር በሰዎች ላይ ከሚፈጥረው ስጋት ይልቅ ሰዎች በጃጓር ላይ እያስከተሉ ያሉት አስጊ ሁኔታ ይበልጣል።

ቁጥራቸው አነስተኛ የሆነው ለምንድን ነው?

በአንድ ወቅት ጃጓሮች ከደቡባዊ ዩናይትድ ስቴትስ እስከ ደቡብ አሜሪካ የታችኛው ጫፍ አቅራቢያ ድረስ ባሉ አካባቢዎች በብዛት ይኖሩ ነበር። በአሁኑ ጊዜ ግን ጃጓሮች ከዛሬ መቶ ዓመት በፊት ይኖሩባቸው ከነበሩት አካባቢዎች ግማሽ የሚያህሉት ጠፍተዋል። እስከ 1970ዎቹ አጋማሽ ድረስ አዳኞች በየዓመቱ በሺህ የሚቆጠሩ ጃጓሮችን ለቆዳቸው ሲሉ ይገድሉ ነበር። በ1968 ብቻ ከ13,500 የሚበልጥ የጃጓር ቆዳ ከሰሜን፣ ከደቡብና ከመካከለኛው አሜሪካ አገሮች ወደ ሌሎች አገሮች ተልኳል። በ2002 የጃጓሮች ብዛት ከ50,000 እንደማይበልጥ ተገምቶ ነበር። በዛሬው ጊዜ ከእንስሳት መጠበቂያ ስፍራዎች ውጭ የሚኖሩ ጃጓሮች ብዛት ከ15,000 እንደማይበልጥ ይገመታል።

አንድ የዱር አራዊት ጥበቃ ማኅበር ያደረገው ጥናት እንደሚያመለክተው የጃጓር መኖሪያ ከነበሩት አካባቢዎች መካከል 40 በመቶ ገደማ የሚሆኑት በደን ጭፍጨፋ ምክንያት ወድመዋል። በሜክሲኮ ብቻ በየደቂቃው አንድ የእግር ኳስ ሜዳ የሚያክል የእንስሳት መኖሪያ ይወድማል። በዚህ ምክንያት ጃጓሮች ሕይወታቸውን ለማቆየት ሲሉ ከብቶችን አድነው ለመብላት ይገደዳሉ።

ጠብቆ ለማቆየት የሚደረግ ጥረት

ለመጥፋት የተቃረቡ ዝርያዎችን ለመጠበቅ በወጣው ዓለም አቀፋዊ ድንጋጌ መሠረት ወደ 200 የሚጠጉ አገሮች ጃጓሮችን አድኖ ለንግድ ማዋልን እንደ ሕገ ወጥ ድርጊት አድርገው ተቀብለውታል። ተፈጥሯዊ የአራዊት መኖሪያዎችን ጠብቆ ለማቆየትም ብሔራዊ ፓርኮች ተቋቁመዋል። በ1986 በቤሊዝ የተቋቋመው የኮክስኮምብ ቤዝን የዱር አራዊት መጠበቂያ ስፍራ ጃጓርን ከጥፋት ለመታደግ በዓለም ላይ ከተቋቋሙት ስፍራዎች የመጀመሪያው ለመሆን በቅቷል። በተጨማሪም ሜክሲኮ ጃጓርን ለመጠበቅ በሚል በዩካታን ባሕረ ገብ መሬት ካላክሙል ባዮስፊር ሪዘርቭ በተባለው ክልል ውስጥ የሚገኝ 150,000 ሄክታር ስፋት ያለው የሐሩር ክልል ደን እንዲከለል አድርጋለች።

ይህን “የአራዊት ንጉሥ” ከጥፋት ለማዳን የሚደረገው እንዲህ ያለው ሰብዓዊ ጥረት ምን ያህል እንደሚሳካ ገና ወደፊት የምናየው ነገር ይሆናል። ሆኖም አፍቃሪው ፈጣሪያችን “ምድርን እያጠፉ ያሉትን” በቅርቡ ‘እንደሚያጠፋና’ አስቀድሞ ባሰበው መሠረት በዚያን ጊዜ በሰው ልጆችና በአራዊት መካከል ፍጹም ሰላም እንደሚሰፍን ማወቃችን ሊያጽናናን ይችላል።—ራእይ 11:18፤ ኢሳይያስ 11:6-9

[በገጽ 24 እና 25 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ጃጓር የሚኖርበት ክልል

የቀድሞው ክልል

የአሁኑ ክልል

ሰሜን አሜሪካ

መካከለኛው አሜሪካ

ደቡብ አሜሪካ